Wednesday, March 18, 2015

መጪው ጊዜ ከኢህአዴግ ጋራ እንደ ድሮው ነው
Share/Bookmark
በ1980ዎቹ ገደማ አንድ ሴትዮ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስተር አቶ መለስ ዜናዊን የኢትዮጵያ ህዝብ ከአስር ዓመታት በኋላ ምን ዓይነት ኑሮ እንዲኖር እንደሚመኙለት ጠይቀዋቸው ነበር፡፡ሰውየው ሲመለሱ ‹‹የዛሬዓስር ዓመት ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ በቀን ሶስት ጊዜ ምግብ ያገኛል›አሉ፡፡ያ ምኞት የቀን ቅዠት ነበር መሰለኝ ከአስር ዓመታት በኋላ ቀርቶ ከ24 ዓመታት በኋላም እውን አልሆነም፡፡በእርግጥ በኢቢሲ የምንመለከታት ኢትዮጵያ የቅር በአፍሪካ በአውሮፓም ተወዳዳሪ የሚገኝላት አትመስልም፡፡
የኢቢሲዋን ኢትዮጵያ ለኢቢሲዎች እንተዋትና እኛ ስለምንኖርባት ኢትዮጵያን እንጨዋወት፡፡


ከሶስት ዓመታት በፊት የአዲስ አበባ ህዝብን ስለሚፈታተኑ አምስት አንኳር ችግሮችን አስመልክቸ ትንሽየ መጣጠፍ ፅፌ ነበር፡፡እነዝያ ችግሮች ለብዙ ዓመታት አብሯችን ከመኖራቸው የተነሳ ነው መሰለኝ በምሬት ስንነጋገርባቸው አይስተዋልም፡፡ውሃ ለሳምንታት ይጠፋል፤መብራት በየጊዜው ይሄዳል ይመጣል፤የኑሮ ውድነቱ…የሱኳር፣የዘይትና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች መጥፋት፣የትራንስፖርት እጥረት፣የቤት ክራይ ዋጋ ጣራ መንካት ወዘተ ዛሬም ህዝቡን ከመጠን በላይ እየተፈታተኑት ይገኛሉ፡፡ ህዝቡ ግን ምሬቱን ሲገልፅ አይታይም፡፡ የመገናኛ ብዙሓን ስለእነዚህ ችግሮች መዘገብ አቁሟል…በጣም ከመደጋገማቸው የተነሳ ሳይሰለቻቸው አልቀረም፡፡


በአሁኑ ጊዜ ውሃና መብራት የሚጠፋው እንደ ድሮው ሳት እያለ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ እንደሚናፈቅ አድርጎ ነው፡፡ለሳምንታት እልም ብሎ ይጠፋል፡፡መብራት ሲጠፋ ስልክ ይጠፋል…ኔትወርክ ይጠፋል…ባንኮች አገልግሎት መስጠት ያቆማሉ…ከተማው የለመደው እንዳጣ ሱሰኛ አፉን ከፍቶ ያዛጋል፡፡ማንም አይናገርም…አይጋገረም፡፡ሁሉም ዝም…ጭጭ፡፡ያው አምርሮ የሚናገር እጣው ምን እንደሚሆን ያውቃታል…እስር ቤት ወይም ስደት ነው፡፡ስለዚህ፣ የባሰ አታምጣ እያለ እንዳላየና እንዳልሰማ መስሎ ዝም ነው፡፡ህዝቡ ቢርበው ጉልበቱን አጥፎ ዝም ነው፤ቢጠማው ዝም…ኑሮው ቢከፋው ዝም…ዝም ከማለት ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌለው ከልምድ ተምሯልና፡፡


ኢህአዴግ በበኩሉ፣ እንደተለመደው ‹‹አበበ በሶ በላ›› እያለ ይለፍፋል፤ ‹‹መጭው ጊዜ ከኢህአዴግ ጋር ብሩህ ነው›› ይላል፡፡እንደዚህ ዓይነቱ ‹‹ካፈርኩ አይመልሰኝ›› ዓይነ ደረቅነት ይኖር ይሆን?ኢህአዴግ ከሚያቀርባቸው ለኑሮ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች መቼም ቢሆን እንደልብ እንደማይገኙ ይታወቃል፡፡ህዝቡ ውሃ ፍለጋ ይሰለፋል…ታክሲ ፍለጋ ይሰለፋል…የኮንደምኔም እጣ ፍለጋ ይሰለፋል…ምሬቱን ለመግለፅ ብቻ ነው እንዲሰለፍ የማይፈቀድለት፡፡ምሬቱን ለመግለፅ እንዳይሰለፍ ምን የሚያካክሉ ወጠምሾች ዱላ ይዘው ይጠባበቃሉ፡፡ሰልፍ ለመውጣት የሞከሩ እስኪያስመልሳቸው ድረስ ተጠብጥቧል፡፡መብቴ ተደፍሯል ብትል ሰሚ የለም፤ ውሃ ጠፋ ብትል ሰሚ የለም፤ፍትሕ አጣሁ ብትል ሰሚ የለም፡፡ የኢህአዴጎች የተለመደው መልስ ‹‹ እንድ አንድ ትምክህተኞች…አንድ አንድ ፀረ ሰላም ሃይሎች…አንድ አንድ ጨለምተኞች የሚያወሩት ውሸት ነው››ይላል፡፡


ቢሆንም ግን ‹‹ምርጫ›› በደረሰ ቁጥር ‹‹መጭው ጊዜ ከኤህአዴግ ጋራ ብሩህ ነው›› ይለናል፡፡ብሩህ የሆነው ምኑን ነው? መቼስ ፀሐይ የምትወጣው ኢህአዴግ ስላዘዛት ነው ማለት አይቻልም፡፡የዓይኖቻችን ብርሃን ያልጠፉት ኢህአዴግ በስልጣን ስላለ ነው ማለትም አንችልም፡፡ህዝቡ ኦክስጅን የሚተነፍሰው ኢህአዴግ እየቆነጠረለት አይደለም፡፡አንድ አንድ የአዲስ አበባ ኗሪዎች በኢቢሲ አለፋላፊነት ደስታቸው ስለገለፁ ብቻ ህዝቡ ደስተኛ ነው፤ ደልቶታል…ቁጭ ቢል ሶፋ ላይ…ቢተኛ ስፕንጅ ፍራሽ ላይ…ቢራመድ በቀይ ምንጣፍ ላይ አይደለም፡፡በእግሩ ቢራመድ ቀይ ሽብር ይገጨዋል(ሲኖትራክም ይሉታል፤ ቻይና በኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት ተማርራ የላከችብን መዓት?)…ቢሰለፍ ሰልፉ ማለቅያ የለውም፡፡ሰልፉን እንደምንም አልቆ ታክሲ ተሳፍሮ ሲጓዝ የትራፊክ መጨናነቁ አይጣል ነው፡፡ብሩህ የሆነው የቱ ጋር ነው?


‹‹በምርጫ›› 2002 ዓ.ም ወቅት አንገብጋቢ የነበሩ ህዝቡ እረሮዎች ዛሬም እንዳሉ ናቸው፡፡ውሃ…መብራት…ስልክ…የኑሮ ውድነት…የቤት ክራይ መናር…ሱኳር…ዘይት… እያሉ ችግሮችን መዘርዘር ይቻላል፡፡አምስት ዓመት ቀላል አይደለም…በአምስት ዓመታት ውስጥ ግን አንዳቸውም አልተፈቱም፡፡የፕረስ መፃነት ታሪክ እየሆነ ነው…መታሰር፣ መንገላታት…ነበሩ አሉ፡፡ሞባሌ ተዘረፍኩ ማለት ተራ ወሬ ሆኗል፤ላፕቶፕ…መኪና…ሌሎች ትላልቅ ንብረቶች መዘረፍ እየተዘወተሩ ነውና፡፡ዘራፌዎች…ማጅራት መቼዎች…ታሰሩ ቢባል ስድስት ወር…እስከ ሶስት ዓመት ነው፡፡መብቱ ጠይቆ የሚታሰረው ግን ፍርድ ሳያገኝም ለዓመታት ይታሰራል፡፡ፀሐይ በጠለቀች ቁጥር ህዝቡ የሚሸማቀቅ ከሆነ ብርሃኑ የቱ ጋር ነው? እንደ ልብ ገብቶ መውጣት ካልተቻለ ፖሊሶቹ እንደአሸን ቢፈሱ ምን ይፈይዳሉ?


የህግ ስርዓቱ ግለ ሰዎች ለፈልጉት ጥቅም የሚያውሉት ከሆነ ህግነቱ ምኑ ላይ ነው?ዘራፊዎች፣ ማጅራት መቺዎች፣ሙሰኞች በኩራት ተንቀባርረው የሚኖሩባት ሃገር ይዘን፤ ድህነት በቁማችን ሊቀብረን የተቃረበባት ሃገር እየመሩ ስለጭው ጊዜ ብሩህነት መለፈፍ ‹‹ከሞትክ በኋላ ገነት ትገባለህ›› ከሚሉት ስብከት በምን ይለያል?ከአምስት ዓመታት በፊት የነበሩ ችግሮች ዛሬም ብሶባቸው ኑሯችን ከድጡ ወደ ማጡ የሚያደርጉት ከሆነ መጪው ጊዜም ከኢህአዴግ ጋራ ያው እንደ ድሮው ነው፡፡Thursday, February 26, 2015

አምልኮተ መለስ
Share/Bookmark


ህወሓት የተመሰረተበት 40ኛው ዓመት የተከበረበት ቀንን ተንተርሰው የብአዴኑ አመራር አቶ በረከት ስምኦንና የህወሓቱ ከፍተኛ አመራር አቦይ ስብሓት ነጋ ስለመለስ የሰጧቸው አስተያየቶች አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ፌስቡክን ጨምሮ የማሕበራዊ ድረገፆች ተጠቃሚዎች ሲቀባበሏቸው ሰንብቷለ፤ የየራሳቸው አስተያየቶችም ሰጥተውባቸዋል፡፡ከፊሎቹ በረከት ነው ትክክል ሲሉ፣ ከፊሎቹ ደሞ አይ አቦይ ስብሓት ናቸው ትክክል ሲሉም ተስተውሏል፡፡ለማስታወስ ያህል ሁለቱም የኢህአዴግ አመራሮች የሰጥዋቸው አስተያየቶች እንሆ፡
አቶ በረከት ስምኦን‹‹ መለስ በክፍለ ዘመን አንዴ ከሚፈጠሩ ሰዎች የሚመደብ ነው›› ሲሉ፣ አቶ ስብሐት ነጋ በበኩላቸው ‹‹የለም፣ አሁኑኑ ብዙ መለሶች መፈጠር ይችላሉ›› በማለት የአቶ በረከት አስተያየት እንደተቃወሙት ሪፖርተር ጋዜጣ ሳይቀር ዘግቦታል፡፡ለመሆኑ እነዚህ አስተያየቶች ዩነት አላቸው? ካላቸው፣ ልዩነቱ ምንድን ነው? አንድነታቸውስ ምን ድን ነው? እስኪ  የቻልነውን ያህል በጥልቀት እንመርምራቸውና ከአምልኮተ መለስ ጋራ ያላቸው ዝምድና ለማየት እንሞክር፡፡

ሁለቱም አስተያየቶች በጥንቃቄ ስንመረምራቸው ያን ያህል የጎላ ልዩነት የላቸውም፡፡አቶ በረከት ያሉት መለስን የመሰለ መሪ ለማፍራት ብያንስ አንድ ክፍለ ዘመን ይወስዳል ሲሆን አቦይ ስብሓት ግን አሁኑኑ ብዙ መለሶች መፍጠር ይቻላል ነው ያሉት፡፡በመሆኑም በሁለቱም አስተያየቶች ያለው ልዩነት የጊዜው ማጠርና መርዘም ብቻ ነው፡፡
በተረፈ ግን፣ ሁለቱም መለስን ከማድነቅ አልፈው አምላኪዎች መሆናቸውን አሌ የሚባል አይደለም፡፡የሁለቱም ፍላጎትና ፀሎት መለስን የመሰለ ‹‹መሪ›› በማፍራት ላይ ያጠነጥናል፡፡ሁለቱም በመለስ ፍፁምነት ያምናሉ፤ እንደ ጣኦት ያመልካሉ፡፡መለስን በሌላ ‹‹መሪ›› መለወጥ ማለት ሃይማኖት የመለወጥ ያህል ይቆጥሩታል፡፡በመለስ ላይ ያላቸው እይታ ምክንያታዊ ሳይሆን በጭፍን ስሜታዊነት የታወረ ነው፡፡ለዛም ነው መለስ የማይካዱ ጠንካራ ጎኖች እንደነበሩት ሁሉ፣ ማንም በቀላሉ የማይረሳቸው የዘቀጡ ስራዎች ማከናወኑም ግልፅ ሆኖ ሳለ እነሱ ግን ማስተዋል የተሳናቸው፡፡

Wednesday, February 18, 2015

ጦርነት ለታወጀበት ቀን ‹‹እንኳን አደረሳችሁ›› ይባላል?
Share/Bookmark
‹‹ጦርነት የተደራጀ ግድያ እንጂ ሌላ አይደለም››


‹‹የዕብደት ውድመቱ የተጠነሰሰው በስመ አምባገነናዊ ስርዓትም ሆነ በስመ ቅዱሱ ነፃነት ወይም ዴሞክራሲ በጦርነቱ ለሞተው፣ ወላጅ አልባ ለሆነውና ቤቱን ላጣው(ቤት አልባ ለሆነው) ምን ለውጥ ይኖሯል›› ማህተመ ጋንዲ

ህወሓት ደርግን ለማሸነፍ ጦርነት የጀመረበት 40ኛው ዓመት ከመቼውም ጊዜ በላይ በጣጣጣጣ...ጣጣጣም ጮክ ብሎ እያከበረ ይገኛል፡፡በህይወቴ ጦርነት የተጀመረበት ቀን ይህን ያህል ከመጠን በላይ ተጋንኖ ሲከበር አይቼ አላውቅም፤ ለወደፊቱም ቢሆን ባላይ እመርጣለሁ፡፡ይህ ቀን በሃገራችን፣ ብሎም በዓለማችን ጦርነት የቆመበት(ታሪክ የሆነበት) ቀን ቢሆን ኖሮ ‹‹እንኳን አደረሳችሁ›› ለማለት ማንም አይቀድመኝም ነበር፡፡ምን ዋጋለው! ቀኑ ጦርነት የተጀመረበት ነውና በጣም ለምወደው ህዝቤና ወገኔ የውድመት ቀን ለታወጀበት ቀን ‹‹እንኳን አደረሰህ›› ለማለት ይከብደኛል፡፡

ለእኔ የካቲት 11 ቀን 1967 ዓ.ም ለትግራይ ህዝብ የምፅአት ቀን የታወጀበት ቀን ነው፡፡በእርግጥ፣ ለትግራይ ህዝብ ብቻ አልነበረም፤ ለመላው ኢትዮጵያዊ እንጂ፡፡ጦርነቱን ማስቀረት ይቻል ነበር ወይ? ሌላ ጥያቄ ነው፡፡ያ ሃገር እንደ ሃገር የወደመችበት ጦርነት የታወጀበት ቀንን ለማክበር ይህን ያህል ጨርቅን ጥሎ ማበድ ግን እንደ ቅጠል ለረገፋው የሰው ህይወትና ወደ አመድነት ለተቀየረው የሃገር ንብረት ቅንጣትም አለመቆርቆር ነው፡፡በጣም የሚገርመው ደሞ፣ ‹‹የያኔው ጦርነት በሃገራችን እንዳይደገም ምን እናድርግ?›› አይደለም እየተባለ ያለው፡፡ይልቅስ፣ ‹‹ጦርነቱ አሁን ላለንበት ደረጃ አድርሶናልና እንኳን ደስ ያላችሁ›› ነው እየተባለ ያለው፡፡‹‹የት ደረስን?›› ብሎ ለሚጠይቅ ዜጋ የሚሰጠው መልስ ግን ‹‹ፀረ ልማት፣ የድሮ ስርዓት ናፋቂ፣ ምንትስ ምንትስ…›› ነው የሚባለው፡፡ከዚሁ የምንረዳው ቢኖር የትም አለመድረሳችን ነው፡፡

ጦርነቱ ያመጣው ድህነት፣ኋላ ቀርነትና ውርዴት ምን ያህል ነው? አይታወቅም! የማን ደፋርስ ነው እንዲህ ብሎ የሚጠይቀው? ብቻ ግን ከ60 ሺ በላይ ወገኖች ህይወታቸውን እንዳጡና ከ100 ሺ የሚልቁ ደሞ አካላቸውን እንዳጡ ይነገራል፡፡እንግዲህ፣ ‹‹60 ሺ ወገኖች እንደ ቅጠል ረገፉ፤ 100 ሺ አካላቸው ጎደሉ›› ሲባል ከቁጥር በስተቀር ምንም ነገር ትዝ የማያላቸው ‹‹ሰዎች›› መኖራቸውን አንርሳ፡፡ለአንድ በቢልዮኖች የሚቆጠር ብር ተቀብሎ በባንክ አካውንት የሚያስቀምጥ የሒሳብ ሰራተኛ ያብር ምኑም አያደለም፤ ቁጥር ብቻ ነው፡፡ለእነዚህ ወገኖችም 60 ሺ ሙትና 100 ሺ አካል ጉዳተኛ ሲባል ከቁጥር ውጪ ሌላ አይታያቸውም፡፡ምን ያህል ቤተ ሰብ ልቡ በሃዘን ተሰበረ? ምን ያህል የዕድሜ ባለፀጎች ያለ ጧሪና ቀባሪ ቀሩ? ምን ያህል እናቶች አባት የሌላቸው ልጆች ብቻቸውን ለማሳደግ ተገደዱ? ምን ያህል ልጆች ያለ አባት ወይም ያለ እናት ወይም ያለ አባትና እናት ቀሩ? ወዘተ የመሳሰሉ ጥያቄዎች ማንም አይጠይቅም፡፡

እንደ ኢትዮጵያዊና እንደ ማንኛውም ሰብአዊ ፍጡር እናስብ ቢባል ደሞ ያ ጦርነት የታወጀበት ቀን በጭፈራና በሆታ ማክበራችን ‹‹ለመሆኑ ሰዎች ነን?›› የሚያስብሉ እውነታዎች መኖራቸውን እናስተውላለን፡፡ህወሓቶች ‹‹በትጥቅ ትግሉ ወቅት 60 ሺ ተሰውተዋል፣ 100 ሺ ደሞ አካል ጉዳተኛ ሆኗል›› ሲሉ የህወሓት ታጋዮችን ብቻ ስለሚቆጥሩ ነው፡፡በየቤቱ የተገደለውስ ማን ነው የሚቆጥረው? በ1977ቱ ድርቅ እንደ ቅጠል የረገፈው የትግራይ ህዝብስ? ጦርነቱ ባይኖር ኖሮ ያን ያህል ህዝብ ያልቅ ነበር? እያሉ መጠየቅ ስሜት አይሰጣቸውም፡፡