Monday, December 23, 2013

የተመስገን ደሳለኝ ተረቶችና አፄ ምንሊክ

ተመስገን ደሳለኝ የኮሜርስ ውጤት ቢሆንም በተማረው መስክ ነግዶ ማትረፍ አልሆንለት ሲለው የፈጠራ ወሬ ነጋዴ ለመሆን ተገደደ፡፡ መፃፍ ይችላል፤ ምንጮቼ እንደነገሩኝ፣ከታማኝ ምንጮች በሰማሁት መሰረት ወዘተ እያለ ወሬ ይቸረችራል፡፡ምክንያቱም ደግሞ የጋዜጠኝነት ሀ… ሁ ሰለሌለው ነው፡፡
እናም ተመስገን ደሳለኝዳግማዊ ምኒሊክን ‹‹ታሪክ የጨከነችበት ጀግና ›› በማለት ሃዘኑን ገልፆላቿል፡፡ለመሆኑ ኢትዮጵያ ታሪክ የምኒሊክን ያህል የራራችለት ሰው አለ? ማን ነው ሃገር ሽጦ ጀገና የተባለው? ማን የዘር ማጥፋት ዘመቻ አካሂዶ ‹‹ቅዱስ ቅዱስ›› እየተባለ የተዘመረለት?ምኒሊክ ብቻ፡፡ ይሳካለት ይሆን? በአሽዋ ላይ የተገነበው ታሪክ እስከ መቸ ነው ሊዘልቅ የሚችለው?እስኪ አንኳር አንኳሮቹን የተመስገን ተረቶች አለፍ አለፍ እያልን እንያቸው፡፡

 ‹‹‹ዳግማዊ ምኒሊክበሚል ስያሜ ዘውድ የደፋው ንጉሥ፣ የረቀቀውን የጣሊያንን ፖለቲካዊ ሴራ ከመበጣጠስም አልፎ በወርሃ የካቲት 23 ቀን 1888 .. ‹አድዋበተባለ የሀገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል የተደራጀውንና ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የታጠቀውን ሠራዊቷን ድል በመንሳት አለምን ጉድ አሰኝቷል፡፡›› ዳግማዊ ምኒሊክ አገር በጣጠሱ እንጂ የጣልያን ሴራ አልበጣጠሱም፡፡የቤተ ምንግስት ዜና መዋእል ዘጋቢዎች ንጉሰ ነገስቱን ለማስደሰት የፃፉት የፈጠራ ወሬ ታሪክ ሳይሆን ተረት ተረት ነው፡፡የአድዋው ጦርነት እንዲካሄድም የእተጌ ጣይቱ ሚና ከዳግማዊ ምኒሊክ በላይ እንደነበር ነው የታሪክ ድርሳናት የሚያወሱት፡፡አቶ ተመስገን ይንህን እውነታ ለምን ዘልለከው?

‹‹በአስተዳደር ዘይቤውም ቢሆን እንደ አባቶቹፍለጠው፣ ቁረጠውአለመሆኑን የሚያሳየው በፍቃደኝነት የውህደቱ ተባባሪ የሆኑ ክፍለ ሀገሮች፣ ያለብዙ ጣልቃ ገብነት፣ ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ማመቻቸቱ ነው፡፡›› የምኒሊክ አስተዳደር የ‹‹ቁረጠው፣ ፍለጠው›› አስተዳደር ካልሆነ በአዳማ የቆመው የኦሮሞ ህዝብ የመታሰባያ ሃወልትን ሄደህ እይና እውነታውን እወቅ፡፡የኦሮሞ ህዝብም ጠይቅ ያ እጅና እግሮቹን የተቆረጠ የሰው ምስል ያለው ሃወልት ዓይነት ምስል በእያንዳንዱ የኦሮሞ ተወላጅ ልብ ተተክሎ ታገኘዋለህ፡፡

‹‹በኢትዮጵያ 3 ዘመን ታሪክ በጀግንነትም ሆነ ዳር ድንበር በማስከበር አቻ የማይገኝለት… በዓላማችን ለመጀመሪያ ጊዜ የዘመናዊውን አውሮፓ ሀገር በጦር መሳሪያ ማሸነፉ የተሳካለት መሪ ሀገሩና ታሪክ የሚገባውን ቦታ በመንፈግ የጨከኑበት ይመስለኛል፡፡›› ዳግማዊ ምኒሊክ የኢትዮጵያ ዳር ደንበር ብያስከበሩ ንሮ ኤርትራን ለጣልያን ይሸጧት ነበር? የኢትዮጵያ ዳር ድንበር ከይት እስከ የት ነበር? ምኒሊክ ባይነግሱ ጁቡቲም ለፈረንሳይ አትሸጥም ነበር፡፡የትኛው ዳር ድንበር ነው ያስከበሩት? ‹‹ለመጀመሪያ ጊዜ  የዘመናዊውን አውሮፓ ሀገር በጦር መሳሪያ ማሸነፉ የተሳካለት መሪ›› ምኒሊክ ሳይሆን ራስ አሉላ አባ ነጋ ነው፡፡የሰሓጢና የዶግዓሊ ጦርነቶች ከዓድዋው በፊት የተካሄዱና በአሉላ አባ ነጋ አሸናፊነት መቋጨታቸው የኮሜርስ አስተማሪዎችህ አልነገሩህም?

‹‹በግልባጩ ከአፍሪካ መጨረሻ ልጆች ተርታ የምትመደበው ደቡብ አፍሪካን ከአፓርታይድ አገዛዝ ነፃ ለማውጣት (ምንም እንኳ ባይሳካለትም) የታገለው ኒልሰን ማንዴላ ማለፉን ተከትሎየአፍሪካ የነፃነት አባትበመባል ያልዘራውን ሲያጭድ፣ ያልዋለበትን ሲሰበስብ ቁጭት ባረበበት አርምሞ አስተውያለሁ፡፡›› አዬ ተመስገን ታድያ አንተ የዘራሀው ነበር ኔልሰን ማንዴላ ያጨዱት? ላንተና መሰሎችህ ምኒሊክ ‹‹አቻ የማይገኝለት›› ንጉስ ሊመስላቹ ይችላል፡፡ እውነታው ብታውቀው ንሮ ግን እንዲህ ብለህ በመደምደምህ ታፍርበት ነበር፤ ህሊና ካለህ፡፡

‹‹ይሁንና አስቀድሞ ሀገሩን ከቅኝ አገዛዝ መታደግ የቻለ መሪ ከዳግማዊ ምኒሊክ በቀር አንድም ማግኘት አይቻልም፤ የዘመናዊ አስተዳደር መሰረትን ከየትኛውም አፍሪካ ሀገር ቀድሞ በራሱ ሰዎች ያዋቀረ ንጉስም እርሱ ብቻ ነበር፡፡›› ተው እንጂ አቶ ተመስገን! ማን ነው እንዲህ ብሎ የሰበከህ? ኢትዮጵያ የባህር በር አልባ ያደረጋት ማን ሆነና ነው ከህፃንነትህ ጀምሮ የተሰበከከውን እኛን ለመስበክ የምትፍጨረጨረው?የትግራይ ሊሂቃን በሁለቱ መረቦች ተከፋፍለው እንዲቀሩ ያደረገው እኮ ያንተው አምላክ ምኒሊክ ነው፡፡ወገኖችህ ለባርነት በመሸጥ መተዳደር የዘመናዊነት ተምሳሌት ያስብላል? ያዘመናዊ አስተዳደር ታድያ ዛሬ የት ገባ?

‹‹በነገራችን ላይ የማዲባ ህልፈት በሳዑዲ ዓረቢያ በስቃይ ላይ የሚገኙ ወገኖቻችንን ጩኸት እንዲደበዝዝ /ጨርሶ እንዳይሰማ/ እስከ ማድረግ የደረሰ ይመስለኛል፡፡ በርግጥ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ሀገራዊ ሀላፊነታቸውን በመወጣታቸው በግሌ ማመስገን የምፈልጋቸው አካላት አሉ፤ የመጀመሪያው የኢሳት ቴሌቪዥን ጣቢያ ነው፤ ቪቫ ኢሳት!›› ኢሳትን ለማመስገን ይህን ሁሉ ዙርያ ጥምጥም መሽከረከር አያስፈልግም፡፡ኢሳት ያለው ቨርጂንያ አሜሪካ፣ የወገኖቻችን ስቃይ የደረሰው በሳዑዲ ዓረብያ… አልተገናኝቶም ነው ነገሩ፡፡ በወሬ ብቻ የወገን ስቃይ የሚፈታ ከሆነ አንተና መሰሎችህ የመንደር ወሬ ስትሰልቁ መኖራችሁ ይታወቃል፡፡ ታድያ ችግሮቹ መቼ ተፈቱ?

‹‹የህወሓት መስራቾች ለትግል በረሃ ከወጡበት ዘመን ጀምሮ፣ ቂም ቋጥረው ደም የተቃቡት ከደርግ አገዛዝ ጋር ብቻ ሳይሆን ከሀገሪቱ ታሪክም ጋር እስኪመስል ድረስ በአፍራሽ ፕሮፓጋንዳ ላይ ተጠምደው እንደነበር ይታወሳል፤ በተለይም ለአፄ ምኒሊክ ስምና ስራ ያላቸው ጥላቻ ወሰን አልባ ነው፡፡›› የህወሓት መስራቾች   ቂም የቋጠሩ ለምን ይመስልሃል? ጥጋብ ነው? በምኒሊክ ‹‹ዘመናዊ›› አስተዳደር ከመጠን በላይ ከመርካታቸው የተነሳ?በደል በሌለበት ቂም መቋጠር ከቶ ሊኖር አይችልም፡፡እናም ምኒሊክ በፈፀማቻው በደሎች ቂም ቢቋጥሩ ችግሩ ምኑ ላይ ነው? በዳዩ ጋ ወይስ ተበዳዩ ጋ?

‹‹ርግጥ ነው አማርኛ ቋንቋ አፍ መፍቻቸው ካልሆኑ የጦር አበጋዞቹ ጭምር ወደ ደቡባዊቷ ኢትዮጵያ ሲዘምት፣ የተከሰተው ዕልቂት ዘግናኝ እንደነበረ፣ የተናዱትወጥ ማንነቶችብዙ እንደነበሩ ባይካድም፣ በተጨማሪም እርሱን የምንወቅስባቸው ተጨባጭ በደም የተፃፉ ሁነቶች ቢኖሩም…›› ወይ መገለባበጥ! የቃላት አኩሮባት ምን ያደርጋል? ‹‹አቻ የማይገኝለት›› የምኒሊክ ‹‹ዘመናዊ›› አስተዳደርም ዘግናኝ ዕልቂት ማስከተሉን አመንክ፡፡አቶ ተመስገን ለንተ ዘመናዊነት ምንድ ነው?በሃይል ለማስገበር ዘግናኝ ዕልቂት መፈፀም ወይስ በስምምነት ላይ የተመሰረት ፌደራሊዝም? ከዘግናኝ እልቂቱ የተረፉም ቢሆን ምኒሊክ የአንዱን ህዝብ ትዕቢት ለመጠበቅ ሲል የሌሎች ‹‹ወጥ ማንነቶች›› በሃይል እንዲጠፋ አድርጓል፡፡ህይወትንና ማንነትን ከማጣት የከፋ ነገር ምን አለ?

‹‹ይሁንና የታሪክ መሰረቶች ላይ የሚቆሙ መተናነቆችን መሻገሪያው ብቸኛው መፍትሄ ጉዳዩን ለታሪክ ባለሙያዎች መተው ብቻ ይመስለኛል፡፡ ከዚያም የአፄውን በጎ ምግባሮች በጋራ እያወደሱ፣ የተሻለች ሀገር ትኖረን ዘንድ በህብረት መትጋት ቢያንስ ከቀጣይ ትውልዶች ከሳሽነት ነፃ ያደርጋል፡፡›› ታሪኩን በፈለግከው መልኩ ፅፈህ ከጨረስክ በኋላ ለታሪክ ባለሙያዎች መተው ይቻላል?ጀምረህ ጨረስከው እኮ ምን ቀረ? ደግሞ ‹‹የአፄውን በጎ ምግባሮች በጋራ እያወደሱ›› ሳይሆን የተሻለች ሃገር መገንባት የሚቻለው በጎ ምግባሮቹን በማወደስና እንደ መልካም አርአያ በመውሰድ፣ መጥፎ ምግባሮቹን በመውቀስና እንዳይደገሙ በማስተማር ነው፡፡

‹‹…ሃገሬ…ለመላው አፍሪካውያን የነፃነት መገለጫ የመሆኗን ጉዳይ ለጊዜው ማደብዘዙ የተሳካ ቢመስልም፣ ከታሪክ መዝገብ የሚፋቅ ባለመሆኑቪቫ ምኒልክእያልኩ ባርኔጣዬን ከፍ አደርግለታለሁ፡፡›› ስግደቱ ማንም አይከለክልህም፤ ባርኔጣህን ቀርቶ ራስህን ብትሰቅልለትም አያገባንም፡፡ በውሸት ላይ ስለተገነባው ታሪክ ግን ያን ያህል ባትኩራራ ይሻልሃል፡፡ያንተ አማልክት ኢትዮጵያ በርሃብ እንድትታወቅ አደረጉ እንጂ ሌላ የፈየዱት ነገር የለም፡፡


በአጠቃላይ


አፄ ምኒሊክ የሚወራላቸውን ያህል መልአክ አልነበሩም፡፡ብዙ እጅግ በጣም ብዙ ክህደቶች ፈፅሟል፤ ኤርትራን ለጣልያን አሳልፈው ሸጧል፡፡ ጅቡቲን ለፈረንሳይ በአሮጌ ቆርቆሮ ለውጧታል፡፡በሰፊው የአሮም ህዝብ ላይ፣ በደቡብ ህዝቦች፣ በትግራይና ኤርትራውያን ላይ ታሪካዊ ክህደት መፈፀማቸው የማይካድ ነው፡፡ይሁን እንጂ ሙሉ በሙሉ አፍራሽ ስራ ሰርቷል ማለት አይቻልም፡፡ ስለዚህ እኝህ አጤ ስናስታውስ ጠንካራና ደካማ ጎኖቻቸውን እኩል ማጤን አለብን፡፡

ለምሳሌ ያህል ከአንድ ዓመት በፊት በሞት የተለዩን ጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ያበረከቷቸው ታሪካዊ ዳራዎችን ስናስታውስ ያጠፏቸው ጥፋቶችም በጋራ ማንሳት የግድ ይለናል፡፡ካበረከቷቸው ታሪካዊና ሃገራዊ ጥቅሞች የህዳሴ ግድብ፣ (ከጓዶቻቸው ጋር) የደርግ አገዛዝ መገርሰስ፣ የኢትዮጵያ ህዳሴ ፅንሰ ሃሳቦች ማመንጨትና ለተግባራዊነታቸው ጠንክሮ መስራት፣ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ ከአዲስ አበባ እንደይነሳ መታግል፣ ኢትዮጵያ ብሎም አፍሪካ በዲፕሎማሲው መስክ በዓለም ደረጃ ተሰሚነታቸው እንዲጨምር ማድረግ … እያን ዘርዝረን ስናበቃ ድክመቶቻቸውም ማንሳት ይኖርብናል፡፡

ጥቂቶቹ ለማውሳት ይህል፡- ኤርትራ ከኢትዮጵያ ስትፈነጨል የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ማጣት አልነበረባትም፡፡በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ላይ አሸናፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ሁኖ ሳለ በድሜን ለኤርትራ አሳልፎ ለመስጠት ‹‹የአልጄርስ ስምምነት›› መፈረም አልነበረባቸውም፡፡ መፈረም ቢኖርብንም  ያ በኤርትራ ሪፈረንደም ያጣነውን የባህር በር ለማስመለስ ጥረት ማድረግ ነበረባቸው … እያልን ለመዘርዘር ድፍረት ሊኖረን ይገባል፡፡

ይህ ካልሆነስ? እንዲህ ካላደረግን እማ በሁሉም ሃገራዊ ጉዳዮቻችን ላይ ሳንግባባ እንቀራለን ማለት ነው፡፡አንድነታችን በአደጋ ላይ ይወድቃል፡፡ አንድነታችን ከተሸረሸረ የውጭ ወራሪ ሃይሎች መጫወቻ ሁነን መቅረታችን ይሆናል፡፡ይኸው ደግሞ ለድህነትና ኋላ ቀርነት ይዳርገናል ማለት ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች የዛሬቱ ኢትዮጵያ ለምን የድህነት ተምሳሌት እንደሆነች የሚያብራሩ ናቸው፡፡