Sunday, November 29, 2015

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በድርቁ የተጠቃው የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት ‹‹20 ሚሊዮን ሊሆን ይችላል›› አሉ


Ø  ‹‹በኢትዮጵያ ውስጥ በእንዲህ ዓይነት ስፋት ድርቅ ተከስቶ አያውቅም››

Ø  ‹‹ከአየር ንብረቱ መዛባት ጋር ተያይዞ ብዙ ቦታዎች ላይ ያሉ ግድቦቻችን በከፍተኛ ደረጃ ቀንሰዋል፡፡››

  Ø‹‹ስለዚህ ድርቁ ራሱ በፈጠረው የውኃ ችግር የኤሌክትሪክ እጥረት አጋጥሟል፡፡››

Ø‹‹በድርቁ የተጠቃው የህዝብ ብዛት እየተጠና ነው፤ ‹‹አሥራ አምስት ሚሊዮንም ሊሆን ይችላል፤ ሃያ ሚሊዮን ሊሆን ይችላል፡፡››

Ø  ‹‹መጀመሪያዎቹ አካባቢ ከውጭ ያስገባነው ወደ 250 ሺሕ ሜትሪክ ቶን እህል ነበር፡፡ አሁን ግን ተጨማሪ 650 ሺሕ ሜትሪክ ቶን እህል እንደገና አዘናል፡፡››

Ø  ‹‹የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ገና ተግባራዊ አልሆነም፡፡ አዲስ አበባ የራሷ ድንበር አላት፡፡ ከድንበሩ አንድ ኢንች ወደ ኦሮሚያ አትገባም፡፡››

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ


ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከሪፖርተር ጋርባደረጉት ረዘም ያለ ቃለ መጠይቅ ድርቁ ያስከተላቸው መጠነ ሰፊ ችግሮችን ይፋ አድርጓል፡፡ጠቅላይ ሚኒትሩ ባሃገራችን ከሚገኙ የግል መገናኛ ብዙሐን ቃለ መጠይቅ ሲያደርጉ የመጀመርያቸው ሲሆን በኢትዮጵያ የተከሰተው እጅግ አደገኛ ድርቅ የሃገሪቱ አንድ አራተኛ የሚሆነውን ህዝብ ለተረጅነት ሊዳርግ እንደሚችልና የግድቦች የውሃ መጠን በጣም በመቀነሱ ምክንያት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ዕጥረት ማስከተሉን ተናግሯል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘንድሮ የተከሰተው ድርቅ ‹‹በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከተከሰተው ድርቅ ሰፋ ያለና›› አብዛኛው የሃገሪቱ ክፍል ያካለለ በመሆኑ የተረጂዎች ቁጥር ሊያሻቅብ እንደሚችል ገልፀዋል፡፡‹‹ማንም የማይቆጣጠረው ሰፊ አካባቢ በድርቁ ተጠቅቷል፡፡›› ያሉት ሚኒስትሩ ‹‹ቁጥሩ ምን ይሁን ምን በሒደት የሚወሰን ነው፡፡ አሥራ አምስት ሚሊዮንም ሊሆን ይችላል፤ ሃያ ሚሊዮን ሊሆን ይችላል፡፡ እኛ ብዙ ትኩረት የምንሰጠው ቁጥሩ ላይ አይደለም፡፡ ዋናው ግን እኛ እያደረግን ያለነው እያንዳንዱ ቤተሰብ ምን ደረጃ ላይ ነው? የሚለው ነው›› ሲሉም አስተያየታቸውን አክሏል፡፡

‹‹ሌብነት የለመደ በአንድ ሳምንት ውስጥ ቴሌቪዥን ላይ ወጥተን ስለጮህን እጁን ይሰበስባል ማለት አይደለም›› ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ


ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲህ ዓይነት ቆይታ ከግል የኅትመት ሚዲያ ጋር ሲያደርጉ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቆይታቸውም ወቅታዊ በሆኑ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በቅርቡ ከተከሰተው ድርቅ አንስቶ ስለመልካም አስተዳደር ችግሮች፣ እንዲሁም በኤርትራ ጉዳይ ላይ ያደረጉት ልዩ ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡  
ሪፖርተር፡- ከኤልኒኖ ጋር በተያያዘ በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች ድርቅ መከሰቱ ይታወቃል፡፡ እስካሁን ድረስ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ቁጥር 8.2 ሚሊዮን መድረሱን መንግሥት አስታውቆ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ዓለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅቶች የተረጂዎቹ ቁጥር 15 ሚሊዮን እንደሚደርስ እየተናገሩ ነው፡፡ በተጓዳኝ ደግሞ ከለጋሾች የሚጠበቀው ዕርዳታ በተጠበቀው መጠን እየተገኘ አይደለም፡፡ ስለዚህ ነገሮች በዚሁ ከቀጠሉ መንግሥት ጉዳዩን እንዴት ለመወጣት አስቧል? የሚታጠፉ የመንግሥት ፕሮጀክቶች አሉ ብለዋል፡፡ የትኞቹ ናቸው? የአገሪቱ የአደጋ መከላከል ዝግጁነት ምን ይመስላል? በተለይ ከዚህ ድርቅ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ጥያቄ ተጎጂዎች ዕርዳታው በአግባቡ እየደረሳቸው አለመሆኑን ነው፡፡ እኛም በቦታ ላይ ተገኝተን ይህን መታዘብ ችለናል፡፡ ስለዚህ በድርቁ የተጎዱ ወገኖችን የመርዳቱ ሒደት ቅንጅት የጎደለው ነው ይባላል? እዚህ ላይ ምን ይላሉ?