Sunday, November 29, 2015

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በድርቁ የተጠቃው የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት ‹‹20 ሚሊዮን ሊሆን ይችላል›› አሉ


Ø  ‹‹በኢትዮጵያ ውስጥ በእንዲህ ዓይነት ስፋት ድርቅ ተከስቶ አያውቅም››

Ø  ‹‹ከአየር ንብረቱ መዛባት ጋር ተያይዞ ብዙ ቦታዎች ላይ ያሉ ግድቦቻችን በከፍተኛ ደረጃ ቀንሰዋል፡፡››

  Ø‹‹ስለዚህ ድርቁ ራሱ በፈጠረው የውኃ ችግር የኤሌክትሪክ እጥረት አጋጥሟል፡፡››

Ø‹‹በድርቁ የተጠቃው የህዝብ ብዛት እየተጠና ነው፤ ‹‹አሥራ አምስት ሚሊዮንም ሊሆን ይችላል፤ ሃያ ሚሊዮን ሊሆን ይችላል፡፡››

Ø  ‹‹መጀመሪያዎቹ አካባቢ ከውጭ ያስገባነው ወደ 250 ሺሕ ሜትሪክ ቶን እህል ነበር፡፡ አሁን ግን ተጨማሪ 650 ሺሕ ሜትሪክ ቶን እህል እንደገና አዘናል፡፡››

Ø  ‹‹የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ገና ተግባራዊ አልሆነም፡፡ አዲስ አበባ የራሷ ድንበር አላት፡፡ ከድንበሩ አንድ ኢንች ወደ ኦሮሚያ አትገባም፡፡››

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ


ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከሪፖርተር ጋርባደረጉት ረዘም ያለ ቃለ መጠይቅ ድርቁ ያስከተላቸው መጠነ ሰፊ ችግሮችን ይፋ አድርጓል፡፡ጠቅላይ ሚኒትሩ ባሃገራችን ከሚገኙ የግል መገናኛ ብዙሐን ቃለ መጠይቅ ሲያደርጉ የመጀመርያቸው ሲሆን በኢትዮጵያ የተከሰተው እጅግ አደገኛ ድርቅ የሃገሪቱ አንድ አራተኛ የሚሆነውን ህዝብ ለተረጅነት ሊዳርግ እንደሚችልና የግድቦች የውሃ መጠን በጣም በመቀነሱ ምክንያት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ዕጥረት ማስከተሉን ተናግሯል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘንድሮ የተከሰተው ድርቅ ‹‹በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከተከሰተው ድርቅ ሰፋ ያለና›› አብዛኛው የሃገሪቱ ክፍል ያካለለ በመሆኑ የተረጂዎች ቁጥር ሊያሻቅብ እንደሚችል ገልፀዋል፡፡‹‹ማንም የማይቆጣጠረው ሰፊ አካባቢ በድርቁ ተጠቅቷል፡፡›› ያሉት ሚኒስትሩ ‹‹ቁጥሩ ምን ይሁን ምን በሒደት የሚወሰን ነው፡፡ አሥራ አምስት ሚሊዮንም ሊሆን ይችላል፤ ሃያ ሚሊዮን ሊሆን ይችላል፡፡ እኛ ብዙ ትኩረት የምንሰጠው ቁጥሩ ላይ አይደለም፡፡ ዋናው ግን እኛ እያደረግን ያለነው እያንዳንዱ ቤተሰብ ምን ደረጃ ላይ ነው? የሚለው ነው›› ሲሉም አስተያየታቸውን አክሏል፡፡


በመቀጠለም የተረጅዎች ቁጥር ‹‹…እስካሁን ድረስ በተሠራው ጥናት መሠረት 8.2 ሚሊዮን ነው፡፡ እንደሚታወቀው በቅርቡ ደግሞ የመኸር ግምገማ ተካሂዷል፡፡ ውጤቱ ሲመጣ 12 ሚሊዮን ወይም 10 ሚሊዮን ወይም 15 ሚሊዮን ሊሆን ይችላል፡፡›› በማለት ግምታቸውን ሰጥቷል፡፡

በተጨማሪም፣ ጠቅላይ ሚኒስተር ሃይለማርያም ፕረዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከሳዑዲ ዓረቢያናዩናይትድ ዓረብ ኤምሬትስ እየፈፀሟቸው ስላሉ ስምምነቶች ተጠይቀው ሲመልሱ ‹‹ሁለቱ አገሮች በተለይ ደግሞ ዩናይትድ ዓረብ ኤምሬትስ አሰብን ተጠቅማ የመን ላይ ያላቸውን ስትራትጂያዊ ጉዳይ ለማስታገስ አውሮፕላናቸው የመን ላይ የኦፕሬሽን ሥራ እንደሚሠራ ይታወቃል፡….የተፈራረምነውም ግልጽ የሆነ 30 ዓመት፣ 40 ዓመት የለንም ነው ያሉት፡፡›› በሏል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት የቁጥጥር ቡድን ያወጣቸው መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ፣ ሳዑዲ ዓረቢያና ዩናይትድ ዓረብ ኤምሬትስ በየመን ላይ እያደረጉት ላለው ጦርነት የአሰብ ወደብ 30 ዓመታት እንደተከራዩት፣ የኤርትራ ወታደሮች በየመኑ ውግያ ላይ እየተሳተፉ መሆናቸውንና የጦር መሣሪያም ወደ ኤርትራ እየገባ መሆኑን ይፋ አድርጓል፡፡ 

ድርቁ ያስከተለው የመብራት እጥረትና መዘዙ

የኢትዮጵያ መብራት ሃይል መብራት የሚቋረጠው በሀይል እጥረት አይደለም” ሲል እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡መንግስትም በሃገሪቱ የሃይል እጥረት እንደሌለ በድፍረት ይናገር ነበር፡፡ አሁን ግን፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካኝነት ከፍተኛ የሆን የኤሌክትሪክ እጥረት ማጋጠሙን ይፋ አድርጓል፡፡የአስረኛው ዙር የኮንድሚኔም ዕጣ ከወጣ አንድ አማት የሞላው ሲሆን የዕጣው እድለኞች እስሁን ድረስ የቤት ቁልፍ አለመረከባቸው ግን የሚታወቅ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምክንያቱን ከሃይል ዕጥሩቱ ጋር በማያያዝ ሲያብራሩ ‹‹ሰው ባልገባበት ኃይል ከምንሰጥ ሰው ባለበት ራሱ እየተቆራረጠ ስለሆነ፣ ሰው ያልገባበት ቢቆይ ይሻላል የሚል ውሳኔ ወስደናል፡፡ የአየር መዛባቱ እስኪስተካከልና ግድቦቻችንም ውኃ እስከሚይዙ ድረስ ያንን ነገር መታገስ ነበረብን፡፡›› ያሉ ሲሆን፣ በመቀጠልም‹‹ይሄን ደግሞ በሚዲያም ገልጸናል፡፡ምክንያቱም ይሄ እኛ የፈጠርነው ችግር አይደለም፡፡ የድርቅ ችግር ነው፡፡›› በማለት የሃገሪቱ የኤሌክትሪክ ሃይልም ልክ እንደግብርናው በዝናብ ላይ የተንጠለጠለ መሆኑን አመላክቷል፡፡

‹‹ብዙዎቹ ግድቦቻችን ለምሳሌ አዋሽ ወንዝ ላይ ያለው የቆቃ ግድብ በጣም ብዙ ችግር ውስጥ ገብቷል፡፡›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹ ሌላው ቀርቶ የአዋሽ ወንዝ ፍሰቱ ጭምር ሊጠፋ የደረሰበት ደረጃ ላይ ነው ያለው፡፡በተመሳሳይ መልካ ዋከና ቆሟል ማለት ይቻላል፡፡ ተከዜም 10 ሜጋ ዋት ብቻ ነው የሚያመነጨው፤ እየደረቀ ነው፡፡›› ከዚህ የተነሳም ‹‹ድርቁ ራሱ በፈጠረው የውኃ ችግር የኤሌክትሪክ እጥረት አጋጥሟል፡፡›› በለዋል፡፡

በሃገራችን ያጋጠመው የዶላር እጥረት

ሁለት ሌቦች የሰው ንብረት ለመዝረፍ ይስማሙና ወደ አንድ ቤት ዘው ብለው ይገባሉ፡፡እንደ አጋጣሚ ሆኖ የቤቱ ባለቤት ወድያው ወደ ቤቱ ይገባና አንደኛውን ሌባ እቃውን ዘርፎ ሊወጣ ሲል እጅ ከፈንጅ ይይዘዋልና በዱላ እየዠለጠ ‹‹የማን እቃ ነው የምትዘርፈው አንተ ሌባ›› እያለ ያለፋልፈው ገባ፡፡ዱላውን መቋቋም ያቃተው ሌባ ‹‹እኔ ብቻ ነኝ እንዴ ሌባው? እኔ ብቻ ነኝ እንዴ?›› እያለ ይቀባጥር ጀመር፡፡ትንፋሹን አጥፍቶ ተደብቆ የነበረው ሌላኛው ሌባ ምን ቢመልስ ጥሩ ነው ‹‹ታድያ ማን አባህ አለ ሌላ?›› አለ ይባላል፡፡  

የኢህአዴግ ባለስልጣናትም ግዴታቸውን መዋጣት ሲያቅታቸው ‹‹እኛ ብቻ ነን እንዴ?›› በማለት የአምሳያዎቻቸውን ዝርዝር ያቀርባሉ፡፡አሁንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሃገራችን ስላጋጠመው የውጪ ምንዛሪ እጥረት ‹‹የዶላር እጥረት በታዳጊ ኢኮኖሚ ውስጥ ሁሉም አገር አልፈውበታል፡፡ቻይና በዚህ ዓይነት አልፋለች፤ ኮርያ በዚህ ዓይነት አልፋለች፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተ አዲስ ነገር አይደለም፡፡›› በማለት አስተባብሏል፡፡

የአዲስ አበባ ‹‹ማስተር ፕላን››ና ያስነሳው አቧራ

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን በኦሮምያ ተወላጆች ስላጋጠመው ከፍተኛ ተቃውሞ ተጠይቀው ሲያብራሩ ‹‹ማስተር ፕላኑ እኮ ገና አልፀደቀም፤ኅብረተሰቡ ቅሬታ እያቀረበ ነው የሚባለው፣ ማስተር ፕላኑ ተግባራዊ ሳይደረግ ምንድን ነው ቅሬታው? ተግባራዊ ሲሆን የሚነካ ሰው፣ ቅሬታውን ሊያቀርብ ይችላል፡፡›› ብለዋል፡፡በተጨማሪም ማስተር ፕላን በባህሪው ከሕዝብ ጋር መወያየት ስለሚያስገድድ በሙያተኞች እንደተጠናና ሕዝቡም እንደተወያየበት ገልፀዋል፡፡


 ነገር ግን አሉ ጠቅላይ ሚኒስተሩ ‹‹አንደኛው ወገን በስህተት ሕዝብ ለማነሳሳት ሲፈልግ፣ አዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ የኦሮሚያ ከተሞች ወደ አዲስ አበባ ሊገቡ ነው ብሎ ይቀሰቅሳል፡፡›› ይሁን እንጂ ‹‹ይህ በጭራሽ ያልታሰበና ሊሆንም የማይችል ነው፡፡ አዲስ አበባ የራሷ ድንበር አላት፡፡ ከድንበሩ አንድ ኢንች ወደ ኦሮሚያ አትገባም፡፡›› በማለት ተቃውሞው በአወናባጆች የተጠነሰሰ መሆኑን ግልፅ አድርጓል፡፡ ይልቁንስ ‹‹አሁን የታሰበው ማስተር ፕላኑ በጋራ ቢሠራና የጋራ ተጠቃሚነት ይኖራል በሚል›› እሳቤ የታቀደ መሆኑን አውስቷል፡፡

No comments:

Post a Comment