Thursday, February 26, 2015

አምልኮተ መለስ



ህወሓት የተመሰረተበት 40ኛው ዓመት የተከበረበት ቀንን ተንተርሰው የብአዴኑ አመራር አቶ በረከት ስምኦንና የህወሓቱ ከፍተኛ አመራር አቦይ ስብሓት ነጋ ስለመለስ የሰጧቸው አስተያየቶች አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ፌስቡክን ጨምሮ የማሕበራዊ ድረገፆች ተጠቃሚዎች ሲቀባበሏቸው ሰንብቷለ፤ የየራሳቸው አስተያየቶችም ሰጥተውባቸዋል፡፡ከፊሎቹ በረከት ነው ትክክል ሲሉ፣ ከፊሎቹ ደሞ አይ አቦይ ስብሓት ናቸው ትክክል ሲሉም ተስተውሏል፡፡ለማስታወስ ያህል ሁለቱም የኢህአዴግ አመራሮች የሰጥዋቸው አስተያየቶች እንሆ፡
አቶ በረከት ስምኦን‹‹ መለስ በክፍለ ዘመን አንዴ ከሚፈጠሩ ሰዎች የሚመደብ ነው›› ሲሉ፣ አቶ ስብሐት ነጋ በበኩላቸው ‹‹የለም፣ አሁኑኑ ብዙ መለሶች መፈጠር ይችላሉ›› በማለት የአቶ በረከት አስተያየት እንደተቃወሙት ሪፖርተር ጋዜጣ ሳይቀር ዘግቦታል፡፡ለመሆኑ እነዚህ አስተያየቶች ዩነት አላቸው? ካላቸው፣ ልዩነቱ ምንድን ነው? አንድነታቸውስ ምን ድን ነው? እስኪ  የቻልነውን ያህል በጥልቀት እንመርምራቸውና ከአምልኮተ መለስ ጋራ ያላቸው ዝምድና ለማየት እንሞክር፡፡

ሁለቱም አስተያየቶች በጥንቃቄ ስንመረምራቸው ያን ያህል የጎላ ልዩነት የላቸውም፡፡አቶ በረከት ያሉት መለስን የመሰለ መሪ ለማፍራት ብያንስ አንድ ክፍለ ዘመን ይወስዳል ሲሆን አቦይ ስብሓት ግን አሁኑኑ ብዙ መለሶች መፍጠር ይቻላል ነው ያሉት፡፡በመሆኑም በሁለቱም አስተያየቶች ያለው ልዩነት የጊዜው ማጠርና መርዘም ብቻ ነው፡፡
በተረፈ ግን፣ ሁለቱም መለስን ከማድነቅ አልፈው አምላኪዎች መሆናቸውን አሌ የሚባል አይደለም፡፡የሁለቱም ፍላጎትና ፀሎት መለስን የመሰለ ‹‹መሪ›› በማፍራት ላይ ያጠነጥናል፡፡ሁለቱም በመለስ ፍፁምነት ያምናሉ፤ እንደ ጣኦት ያመልካሉ፡፡መለስን በሌላ ‹‹መሪ›› መለወጥ ማለት ሃይማኖት የመለወጥ ያህል ይቆጥሩታል፡፡በመለስ ላይ ያላቸው እይታ ምክንያታዊ ሳይሆን በጭፍን ስሜታዊነት የታወረ ነው፡፡ለዛም ነው መለስ የማይካዱ ጠንካራ ጎኖች እንደነበሩት ሁሉ፣ ማንም በቀላሉ የማይረሳቸው የዘቀጡ ስራዎች ማከናወኑም ግልፅ ሆኖ ሳለ እነሱ ግን ማስተዋል የተሳናቸው፡፡

Wednesday, February 18, 2015

ጦርነት ለታወጀበት ቀን ‹‹እንኳን አደረሳችሁ›› ይባላል?

‹‹ጦርነት የተደራጀ ግድያ እንጂ ሌላ አይደለም››


‹‹የዕብደት ውድመቱ የተጠነሰሰው በስመ አምባገነናዊ ስርዓትም ሆነ በስመ ቅዱሱ ነፃነት ወይም ዴሞክራሲ በጦርነቱ ለሞተው፣ ወላጅ አልባ ለሆነውና ቤቱን ላጣው(ቤት አልባ ለሆነው) ምን ለውጥ ይኖሯል›› ማህተመ ጋንዲ

ህወሓት ደርግን ለማሸነፍ ጦርነት የጀመረበት 40ኛው ዓመት ከመቼውም ጊዜ በላይ በጣጣጣጣ...ጣጣጣም ጮክ ብሎ እያከበረ ይገኛል፡፡በህይወቴ ጦርነት የተጀመረበት ቀን ይህን ያህል ከመጠን በላይ ተጋንኖ ሲከበር አይቼ አላውቅም፤ ለወደፊቱም ቢሆን ባላይ እመርጣለሁ፡፡ይህ ቀን በሃገራችን፣ ብሎም በዓለማችን ጦርነት የቆመበት(ታሪክ የሆነበት) ቀን ቢሆን ኖሮ ‹‹እንኳን አደረሳችሁ›› ለማለት ማንም አይቀድመኝም ነበር፡፡ምን ዋጋለው! ቀኑ ጦርነት የተጀመረበት ነውና በጣም ለምወደው ህዝቤና ወገኔ የውድመት ቀን ለታወጀበት ቀን ‹‹እንኳን አደረሰህ›› ለማለት ይከብደኛል፡፡

ለእኔ የካቲት 11 ቀን 1967 ዓ.ም ለትግራይ ህዝብ የምፅአት ቀን የታወጀበት ቀን ነው፡፡በእርግጥ፣ ለትግራይ ህዝብ ብቻ አልነበረም፤ ለመላው ኢትዮጵያዊ እንጂ፡፡ጦርነቱን ማስቀረት ይቻል ነበር ወይ? ሌላ ጥያቄ ነው፡፡ያ ሃገር እንደ ሃገር የወደመችበት ጦርነት የታወጀበት ቀንን ለማክበር ይህን ያህል ጨርቅን ጥሎ ማበድ ግን እንደ ቅጠል ለረገፋው የሰው ህይወትና ወደ አመድነት ለተቀየረው የሃገር ንብረት ቅንጣትም አለመቆርቆር ነው፡፡በጣም የሚገርመው ደሞ፣ ‹‹የያኔው ጦርነት በሃገራችን እንዳይደገም ምን እናድርግ?›› አይደለም እየተባለ ያለው፡፡ይልቅስ፣ ‹‹ጦርነቱ አሁን ላለንበት ደረጃ አድርሶናልና እንኳን ደስ ያላችሁ›› ነው እየተባለ ያለው፡፡‹‹የት ደረስን?›› ብሎ ለሚጠይቅ ዜጋ የሚሰጠው መልስ ግን ‹‹ፀረ ልማት፣ የድሮ ስርዓት ናፋቂ፣ ምንትስ ምንትስ…›› ነው የሚባለው፡፡ከዚሁ የምንረዳው ቢኖር የትም አለመድረሳችን ነው፡፡

ጦርነቱ ያመጣው ድህነት፣ኋላ ቀርነትና ውርዴት ምን ያህል ነው? አይታወቅም! የማን ደፋርስ ነው እንዲህ ብሎ የሚጠይቀው? ብቻ ግን ከ60 ሺ በላይ ወገኖች ህይወታቸውን እንዳጡና ከ100 ሺ የሚልቁ ደሞ አካላቸውን እንዳጡ ይነገራል፡፡እንግዲህ፣ ‹‹60 ሺ ወገኖች እንደ ቅጠል ረገፉ፤ 100 ሺ አካላቸው ጎደሉ›› ሲባል ከቁጥር በስተቀር ምንም ነገር ትዝ የማያላቸው ‹‹ሰዎች›› መኖራቸውን አንርሳ፡፡ለአንድ በቢልዮኖች የሚቆጠር ብር ተቀብሎ በባንክ አካውንት የሚያስቀምጥ የሒሳብ ሰራተኛ ያብር ምኑም አያደለም፤ ቁጥር ብቻ ነው፡፡ለእነዚህ ወገኖችም 60 ሺ ሙትና 100 ሺ አካል ጉዳተኛ ሲባል ከቁጥር ውጪ ሌላ አይታያቸውም፡፡ምን ያህል ቤተ ሰብ ልቡ በሃዘን ተሰበረ? ምን ያህል የዕድሜ ባለፀጎች ያለ ጧሪና ቀባሪ ቀሩ? ምን ያህል እናቶች አባት የሌላቸው ልጆች ብቻቸውን ለማሳደግ ተገደዱ? ምን ያህል ልጆች ያለ አባት ወይም ያለ እናት ወይም ያለ አባትና እናት ቀሩ? ወዘተ የመሳሰሉ ጥያቄዎች ማንም አይጠይቅም፡፡

እንደ ኢትዮጵያዊና እንደ ማንኛውም ሰብአዊ ፍጡር እናስብ ቢባል ደሞ ያ ጦርነት የታወጀበት ቀን በጭፈራና በሆታ ማክበራችን ‹‹ለመሆኑ ሰዎች ነን?›› የሚያስብሉ እውነታዎች መኖራቸውን እናስተውላለን፡፡ህወሓቶች ‹‹በትጥቅ ትግሉ ወቅት 60 ሺ ተሰውተዋል፣ 100 ሺ ደሞ አካል ጉዳተኛ ሆኗል›› ሲሉ የህወሓት ታጋዮችን ብቻ ስለሚቆጥሩ ነው፡፡በየቤቱ የተገደለውስ ማን ነው የሚቆጥረው? በ1977ቱ ድርቅ እንደ ቅጠል የረገፈው የትግራይ ህዝብስ? ጦርነቱ ባይኖር ኖሮ ያን ያህል ህዝብ ያልቅ ነበር? እያሉ መጠየቅ ስሜት አይሰጣቸውም፡፡