ስሜት
በውቀቱ ስዩም ዘመኑ ካፈራቸው ደንቅ የስነ ፅሑፍ ሰዎች አንደኛው ነው፡፡ በቅርቡ ‹‹ከአሜን
ባሻገር›› የተሰኘው መፅሐፉን ለሕትመት ማብቃቱን ስሰማ ደስታየ ወደር አልነበረውም፡፡ የእርሱ መፅሐፍ ለማንበብ የነበረኝ ጉጉት
የላቀ ስለነበረም የመጀመርያው እትም ገዝቼ ማንበብ ችያለሁ፡፡
የበውቀቱ ሽሙጦች ባነበቡኩኝ ቁጥር እንባየን መቆጣጠር እስኪያቅተኝ ድረስ በሳቅ እንፈረፈራለሁ፡፡በመሆኑም
የሆነ ደባሪ፣ረዥምምምና ጨፍጋጋ ጊዜ መግደል ሲያስፈልገኝ ‹‹መውጣትና መግባት››ና ‹‹እንቅልፍና እድሜ›› የተሰኙ መፃሐፎቹን ደጋግሜ
አነባለሁ፡፡ከ‹‹አሜን ባሻገር››ን ሳነበም ሁለት ነገሮች እንደ እብድ ብቻየን እንድስቅ አስገድደውኛል፡፡አንደኛው የበረራ አስተናጋጆች(ወይም
በወንበሩ በተገጠሙት ስክሪኖች አማካኝነት የሚታየው መመርያ) በአደጋ ጊዜ እንደህ አድርጉ እንድያ በሉ እያሉ ተጓዦችን የሚያስቡኩበት
ክፍለ ጊዜ የገለፀበት ፅሑፍ ላይ፣
‹‹ለመሆኑ በአደጋ ሰዓት ከወንበሬ ስር መንሳፈፍያ ከረጢት መኖር አለመኖሩን ይቅርና፣ ወንበር
ላይ ልቀመጥ ጉቶ ላይ እንዴት ትዝ ሊለኝ ይችላል? ሰው አለቅጥ ሲደነግጥ እንዲህ ያለውን የጥንቃቄ ዝርዝር ይቅርና በሽንት ቤት
እና በሱሪው መካከል ያለውን ልዩነት እንኳን ይረሳዋል፡፡ለዚህ ነው ብዙ ደንጉጦች በአደጋ ሰዓት ሽንታቸውን ለሱሪያቸው የሚያስረክቡት፡፡››
የሚለውን ሳነብ በጣም ስቄያለሁ፡፡ አሁንም እየሳቅኩኝ ነው የምፅፈው፡፡(ገፅ 41)
ሌላው በጣም ያሳቀኝ ደሞ፣ በቢላደን ምክንያት ፂማም ሰዎች ሁሉ አሸባሪዎች እንደሚመስሉት ይገልጥና፣
ካጠገቡ የተቀመጠው ፂማም ተሳፋሪም አሸባሪ እንዳይሆን ስለጠረጠረ ሰውየው ‹‹ጠብደል ከመሆኑ የተነሳ›› አውሮፕላንዋን
አንዳይጠልፋት መስጋቱን ይተርካል፡፡ከዛም፣ ያ አሸባሪ ሊሆን ይችላል ብሎ የገመተው ሰውዬ አውሮፕላንዋን ሳይሆን ሽንት ቤቱን መጥለፉ(
ሽንት ቤት ውስጥ በጣም መቆየቱን) ይታዘባል፡፡ያኔ፣ ‹‹ሰውዬው ኑሮውን ነው እንዴ የሚፀዳዳው?›› የሚለውን መስመር ሳነብ በሳቅ
ፍርስ ብያለሁ፡፡(ገፅ 43)
የስነ ግጥም ጥበብ መግጠሙ ላይ ብቻ ሳይሆን አነባበቡም የተለየ ተሰጥኦና ክህሎት የሚጠይቅ
ይመስለኛል፡፡ለዛም ሳይሆን አይቀርም በሃገራችን በገጣሚነታቸው ወደር የለሽና አንቱ የተባሉ ገጣሚዎች የገጠሙት ግጥም ራሴ ሳነበው
ያን ያህል ስሜት አይሰጠኝም፡፡በተለይ ግጥሙ በጣም ረዥም ከሆነ፣ያለወትሮየ እንቅልፍ እንቅልፍ ይለኛል፤ አሁንም አሁንም ያፋሽገኛል፡፡እናም
ሳልጨርሰው በጅምር ይቀራል፡፡ገጣሚዎቹ ሲያንቆረቁሩት ማዳመጥ ግን የሆነ ለመግለፁ የሚከብደኝ የመንፈስ ልዕልና ይሰማኛል፡፡
የበውቀቱ አጫጭር ግጥሞች ግን ከዚህ የተለዩ ሆኖው አግቻቸዋለሁ፡፡ገጣሚው ሲያነባቸውም ሆነ
ራሴ ሳነባቸው፣ ህሊናየን እንደ ምግብ ያጠግቧታል፣ ለነብሴም መድሓኒት ሆኖው ይፈውሷታል፡፡ራሱ የገጠማቸው ግጥሞች ብቻም ሳይሆን
የሚፅፋቸው መጣጥፎች ጥልቅ የሆነ መልእክት እንዲያስተላልፉለት የሚመርጣቸው ግጥሞችም አስደናቂ ናቸው፡፡