ምክኒያታዊነትና ሰብአዊነት
‹‹ከአሜን ባሻገር›› በ246 ገፆች የተሰደሩ
20 መጣጥፎች ይዛለች፡፡የመፅሐፏ ሽፋን ልዩ ምልክት ብስኪሌት(ባይሲክል) ስትሆን የሳይክሏ የፊትጎማ የዳግማዊ ምኒልክ ምስል ያለው
ሳንቲም፣ እንዲሁም የኋለኛው ጎማ በ2002 ዓ.ም ታትሞ በማገልገል ላይ ያለው ብረቱ የአንድ ብር ኖት ነው፡፡
የሳይክሏ በዚህ መልኩ መቅረብ የሚጠቁመው ድሮና
ዘንድሮ የኢትዮጵያ የማይነጣጠሉ ሁለት ገፅታዎች መሆናቸውን ለመጠቆም ይመስላል፤ ‹‹የኋላው ከሌለ አይኖሩም የፊቱ›› እንዲሉ፡፡ወይም
ድሮ ያለዘንድሮ መንቀሳቀስ አይችልም የሚል እሳቤ ለማስረገጥ ነው፡፡አንድ የርቀት ዝላይ ስፖርተኛ ወደፊት መዝለል የሚችለው ርቀት
ወደ ኋላ ተንደርድሮ የሮጦው ፍጥነት ወሳኝ የሆነውን ያህል፣ የዛሬው የሃገራችን እርምጃም ትናንት ስትራመደው በነበረው ፍጥነት ይወሰናል፤
አሳማኝ ነው፡፡
ደራሲው ድሮና ዘንድሮ ምንኛ እንደተዋኸዱ ሲገልፅ፣‹‹የዛሬው
ዘመን ምን ቢታገል ካለፈው ዘመን ተለይቶ ጎጆ መውጣት አይችልም፡፡ያለፈው ዘመንና የዛሬው ዘመን እንዳይፋቱ ሆነው ተቆራኝተዋል፡፡አንዳንዴ
ሳስበው፤ ‹‹ዘንድሮ›› በሚለው ቃል ውስጥ ‹‹ድሮ›› የሚለው ቃል መገኘቱ ባጋጣሚ አይመስለኝም፡፡›› ብሏል በገፅ 9 ላይ፡፡እዚ
ጋ፣ አንድ ጥያቄ መነሳት አለበት፤ እሱም፣ ድሮና ዘንድሮ ይህን ያህል የተቆራኙ ከሆኑ ዘንድሮን ከድሮ ነጥለን መተቸት እንችላለን
ወይ? የትናንቱ ታሪካችን ያተነፈሰው ጎማ፣ ዛሬ በፈለግነው ፍጥነት ሊያንቀሳቅሰን ካልቻለ ዘንድሮን ነው መኮነን ያለብን? ደራሲው፣
እስከ መቼ ድረስ የነበረውን ታሪካችን ነው ‹‹ድሮ›› እያለ የሚጠራው? ‹‹ዘንድሮ›› የሚለውንስ?
ደራሲው ‹‹ድሮ›› የሚለው የአጼ ምኒልክ አገዛዝ
ሲሆን ‹‹ዘንድሮ›› ደግሞ ‹‹የኢህአዴግ›› አገዛዝ ይመስላል፡፡ምክንያቱም፣ በውቀቱ ‹‹የጦርነት ፍሬ ናት›› የሚላት ሐረር በአሚሮችና
በግብጾች በወረፋ ስትገዛ እንደኖረች፣ በምኒልክ የሰላምና የአብሮ መኖር ተምሳሌት እንደሆነች ካተተ በኋላ በገፅ 168 ደሞ ‹‹ከድሮ
ወደ ዘንድሮ ልሸጋገር፡፡ኡሁን ከጁገል በር ላይ ቆሜ ሳያት፣ ሐረር ተስፋና ሥጋት አርግዛ
ታየችኝ›› በማለቱ ነው፡፡የጣልያን አስቶርጓሚና ባንዳ ነበር የተባለው ገብረእግዚአብሔር ጊላማርያም ባአጼ ምኒልክ
ዘመንና ከዛበፊት ስለነበረው ጊዜ፤
‹‹በአገራችን ድኽነት መብዛቱና
መበርታቱ ጌቶች በዝተው እውነተኛ ዳኛና ጠባቂ ስለታጣ ነው፡፡›› ብሎ በመፃፉ በውቀቱን አስከፍቶታል፡፡
በመሆኑም፣ በውቀቱ የሚከተለው
የተቃውሞ ፅሑፍ አስፍሯል፤ ‹‹አንድ የፈረንጅ ጸሐፊ፣ ‹ዘንድሮ ተስፋ የቆረጠ ወደ ድሮ ይሰደዳል› ይላል፡፡ባለቀቢጸ-ተስፋዎች ወደ
ድሮ ከመሰደዳቸው በፊት ድሮው እንዲመቻቸው እርገው ያሳምሩታል፡፡ከምናባቸው በሚመነጭ ውበት ያስጌጡታል፡፡›› በውቀቱ ይህን ይበል
እንጂ ከርሱ በላይ በዘንድሮ ተስፋ ቆርጦ ድሮን በማሽሞንሞን የተጠመደ ሰው የለም፡፡ ባይሆን ኖሮ ‹‹ደስታና ቀቢፀ ተስፋ›› የሚለው
መጣጥፉን ባልፃፈ፡፡
የሚገርመው ታድያ፣ የዘመኑ
ስርዓት ለመውቀስ ሲፈልግ ዘንድሮን ተስፈየለሽ የጨለማ ዘመን ይለዋል፤ የአጼ ምኒልክ አገዛዝ ላይ ያነጣጠረ ወቀሳ ሲቀርብ ግን 180
ድግሪ ታጥፎ ‹‹ዘንድሮ ተስፋ የቆረጠ ወደ ድሮ ይሰደዳል›› በማለት ሊያጣጥለው ይሞክራል፡፡የትግራይ ሰው እንዲህ ያለ የአቋም
አክሮባቲስት ሲያጋጥመው ‹‹ክትኩሰካ ብማንካ፣ ክዝሕለካ ብኢድኻ›› ብሎ ይተርትበታል፡፡ለካ ልጅ በውቀቱም እስከዚህም በአቋማ መዋዠቅ
የሚሰቃይ ደራሲ ኖሯል?
‹‹በርግጥ›› ይላል በውቀቱ፣ ‹‹ተናግሮ ማሳመን፣
ታግሎ መጣል ሁልጊዜ አይሳካም፡፡ያም ሆኖ፣ እስክረታ ድረስ ካልታገልሁ፤ እስክታፈን ድረስ ካልተናገርሁ፤ የረባ ኑሮ ኖርሁ ማለት
ይከብደኛል፡፡›› እናም፣ መታገሉም ሆነ መናገሩ እስከ መጨረሻ እቀጥልበታለሁ ይላል፡፡በውቀቱ፣ እንደህ በማለቱ አበጀህ! ደግ አደረግክ
ብየዋለሁ፡፡ለራሱ ይህን ያክል የዓላማ ሰው አድርጎ ሲያበቃ ‹‹የዘመኔ ጀግና›› በቀቢፀ ተስፋ የሚነዳ ተስፋ ቢስ ማድረጉን ግን
ተገቢ አይመስለኝም፡፡የበውቀቱን ይህል ጠንካራ ሊሆንም ላይሆንም ይችላል፤ሙሉ በሙሉ ተስፋቢስና ዓላማ የለሽ ነው ብሎ በጭፍን መፈረጅ
ግን ተገቢ አይደለም፡፡
የበውቀቱ የሐሳብ አርአያዎቼ ‹‹የጥንት አንጎራጎሪ
ሴቶች እንጂ ፕሮፌሽናል ፖለቲከኞች አይደሉም፡፡›› ይላል፡፡(ገፅ 8) ፖለቲካ ቀመስ መጣጥፎቹ የከተባቸውም እነርሱ ከባድ በደል
ሲደርስባቸው ስሜታቸው ገንፍሎ ‹‹ንጉስና ካህን ከፈቀዱላቸው ወሰን አልፈው›› እንደሚናገሩትና እንደሚገጥሙት አይነት ነው፡፡
ስለዚህ፣እነዚህን መጣጥፎች የፃፋቸው ሰከን ብሎ፣አሰላስሎ፣ግራና
ቀኝ መዝኖ ሳይሆን እንዲሁ እንደ ድስት ገንፍሎና በስሜት ተገፋፍቶ ነው ማለት ይቻላል፡፡ምን ዓይነት ውጤት እንደሚያስከትሉም አላጤነም፡፡የሚገርመው
ድግሞ የራሱ ስሜታዊነት ሰይቆጣጠር ታሪክ ለማቃናት መነሳቱን ነው፡፡ በደም ፍላት የተጣመመው
ታሪካችን በደም ፍላት ሊስተካከል ይችላል?
የታሪክ ቀመስ መጣጥፎቹ መግብያ ላይ ደግሞ፣
‹‹ታሪክ ቀመስ መጣጥፎቼ፤አላግባብ የተወቀሱትን ከማወደስ፤ አላግባብ የተረሱትን ከማስታወስ ያለፈ ዓላማ አላቸው፡፡›› የሚል ሐሳብ
በገፅ 9 ላይ አስፍሯል፡፡አላግባብ የተወቀሱትና በደራሲው ሊወደሱ የተመረጡት እነማን ናቸው?አላግባብ የተረሱትና በደራሲው አማካኝነት
የሚታወሱትስ እነማነ ይሆኑ? መስፈርቱስ ምንድ ነው? የመጣጥፎቹ ዓላማ
ከማወደስና ከማስታወስ ያለፈ ከሆነ ያ ዓላማ ምንድ ነው? የእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ከመፅሐፉ መፈለግ ግድ ሰለሚለን እንዲሁ መጠየቁ
አይከፋም፡፡
በደራሲው እምነት፣‹‹አላግባብ የተወቀሱት››
አጼ ምኒልክ ናቸው፡፡አጼውን አላግባብ የወቀሱም የጨለንቆ ጦርነት የሐረሪዎች ቁጥር አመናምኗል፤ አርሲም ‹‹ ‹የምኒልክ አስከፊ በደል›
ማሳያ አድርገዋል፤ ወላይታዎችም በምኒልክ አገዛዝ ወላሞ (ዋ! ላሞ) ተብለዋል ብለው ፅፈዋል፤ሐወልት አቁመዋል እያለ የሚማረርባቸው
‹‹የዘመኑ ብሔርተኞች›› ናቸው፡፡እነዚህ ‹‹ደረቅ ብሔርተኞች›› አጼ ምኒልክን አላግባብ መውቀሳቸው ለበውቀቱ ‹‹መሰሪ ራስ ወዳድነት››
ነው፡፡እናም፣ በውቀቱ ሥዩም-በዳዳ-ደስታ-ወይሳ እኝህ ‹‹አላግባብ የተወቀሱት›› አጼ ምንሊክን ከማወደስ ያለፈ ዓለማ
ሰንቆ ተነሳ፡፡ይህ ከማወደስ ያለፈ ዓለማ ምንሊክን አምልኩ እያሉ መስበክ ካልሆነ በስተቀር ምን ሊሆን እንደሚችል ለጊዜው ግልፅ
አይደለም፡፡
አጼ
ምኒልክ ‹‹የአርሲዎችን
አይበገሬነት ለመስበር ባንድ ቀን ብቻ የአራት መቶ አንጋፋዎችን ክንድ አስቆርጧል፡፡›› ይላል በገፅ 178 ላይ፡፡ይህን የመሰለ
ጭካኔ መፈፀማቸው ግን ለበውቀቱ ቅንጣት ታህል አይፀፅተውም፡፡እኔ እንጃ፣ ይህ ነገር ካልሰቀጠጠው እንግዲህ ምን ማለት እንደሚቻል
አላውቅም፡፡እስኪ አስቡት፣ የሰው ልጅ ከፊት ለፊታችሁ ተጋድሟል፤ ከዛም ያኔ በነበረው ድልዱም ስለት ክንዱን ለመቁረጥ ስትታገሉ፣
ሰውዬው በሞትና በመኖር መካከል ሆኖ ሲያጣጥር…ወንድ ልጅ የሞት ክብር ተነፍጎ ከፊት ለፊታችሁ ወድቆ ከሞት ሺ ጊዜ በከፋ ቅጣት
ሲቀጣ…ከዛም በደም ጎርፍ ሲታጠብ…ከኋላ ተሰልፎ ይህን የሚመለከት ሌላ ሰውዬም በደም በጨቀየው ስለት ክንዱን ሊቆረጥ ታስሮ ወደፊት
እየተገፈተረ ሲቀርብ ከዛም…ውይ! እኔ እጃ! ብቻ ይህን ያደረገ ሰው ምንጊዜም ቢወቀስ ‹‹አላግባብ›› ተወቀሰ ብየ የማስተባብልበት
ወኔ አይኖረኝም፡፡
በውቀቱ ግን ይቀር ሊሰቀጥጠው
አጼ ምኒልክን ‹‹አባ ዳኘው›› (ገፅ
164)ና ‹‹ኢትዮጵያዊው ቢስማርክ››(ገፅ 178) እያለ ያሞካሻቸዋል፡፡እርሳቸው የመፀሟቸውና ያስፈፀሟቸው አረመኒያዊ ግፎችም በተፋለሱና
ከእውነት በራቁ ሽንገላዎች አመካኝነት ለማስተባበል ይሞክራል፡፡የበውቀቱ ህፀፆች ይኸውና፤
አንደኛው፣አጼ
ምኒልክ ሌሎች ያልፈፀሟቸው ግፎች አልፈፀሙም የሚል አጉል ሙግት ነው፡፡ለምሳሌ ያሄል የሚከተለውን ከመፅሐፉ
ልጥቀስ፤ ‹‹እርግጥ ነው፤ አርሲ በስጦታ
ወይም በስምምነት የተደባለቀ ሀገር አይደለም፡፡የተገኘው በብዙ አገሮች እንደተደረገው፤ በጉልበትና በነውጥ ነው፡፡›› ይልና፣‹‹በሌላ
በኩል›› ብሎ ይቀጥላል ፤‹‹በጉልበት ሌላውን ማስገበር አያሌ ህዝቦች በፈረቃ ያደረጉት ሆኖ ሳለ አንድ ንጉሥና እንድ ብሔረሰብ
ብቻ ጠቅልሎ የያዘው አድርገው ለማሳየት የሚሞክሩ አሉ፡፡ የዚህ ምእራፍ ዓላማ ከላይ የተጠቀሱትን የተሳሳቱና ጠንቀኛ አስተሳሰቦች
ማቃናት ነው፡፡›› ይላል፡፡
ይህ
አይነት አባባል አቅጣጫ ለማሳትና ለማጃጃል የሚቀርብ የአስተሳሰብ ህፀፅ ወይም ‹‹ፋላሲ›› ነው፡፡ ‹‹Appeal to
Popularity›› ወይም ‹‹Bandwagon approach››
ይባላል፡፡ አንድ ነገር፣ ብዙ
ሰዎች የሚያዘወትሩት ከሆነ ትክክል ነው፤ ከሚል እሳቤ ይነሳል፡፡ይህ ማለት፣ ቀይሽብር ከደርግ በፊት ጆሴፍ ስታሊን ተግባራዊ አድርጎታል
እና የመንግስቱ አገዛዝ ተወቃሽ ሊሆን አይችልም እንደማለት ነው፡፡በሌላ አባባል፣ ሰው ገድሎ ‹‹መግደል በእኔ አልተጀመረም››፤
ስርቆ፣ ‹‹ስርቆት በእኔ አልተጀመረም››፤ በአጠቃላይ ወንጀል
ስርቶ ‹‹ወንጀል መስራት በእኔ አልተጀመረም›› እያሉ እንደማሳበብ ነው፡፡
ሁለተኛው የበውቀቱ ሙግት፣ አጼ ምኒልክ የወላይታ፣የከፋ፣
የአርሲና የሐረር ህዝቦችን በሐይል ለማስገበር የተገደዱት እነዚህ ህዝቦች የአጼ ምኒልክ አገዛዝ አሜን ብለው ስላልተቀበሉ ነው የሚል
ሰንካላ ክርክር ነው፡፡አሁንም አንዳንድ ምሳሌዎችን ከመፅሐፉ ቀንጭበን እናቅርብ፤‹‹ቅድመ ምኒልክ አርሲ›› በሚለው አርእስት ስር
‹‹የአርሲ ማሕበረሰብ የአኗኗር ዘይቤ›› ዊልያም ሐሪስ የተባለ ፈረንጅን ጠቅሶ ‹‹ ‹በተራራ እቅፍ ውስጥ የሚኖሩትን፣ ከላይ እስከታች
ሰውነታቸውን በስብ ተለቅልቀው ራቁታቸውን የመዋጋት ልምድ ያላቸውን የጦር-ጭልፊቶች (ሣኅለሥላሴ) ጦር ሊየዘምትባቸው አልደፈረም፡፡
ምህረት የለሽና ሌላውን የማጥቃት ልማድ ያላቸው ሲሆኑ … በዙርያቸው ያሉትን ጎሳዎች የሚያሸብሩ እንደሆኑ ይነገርላቸዋል› ይላል››
ይላል፡፡
በተጨማሪም
ሀንቲግተፎርድ የተባለ ሌላ ፈረጅን ጠቅሶ ‹‹ስለጥንታዊው የአርሲ የአኗኗር ዘይቤ የሚከተለውን ጽፏል፡፡›› ይልና ‹‹ ‹ሌሎች የኦሮሞ
ጎሳዎች ሳይቀር አርሲዎች ነውጠኛ አድርገው ይመለከቷቸው ነበር፡፡ለነሱ እያንዳንዱ ክብረ-በአል መጨረሻ ላይ ሰው መግደል የክብር
ምልክት እና ማኅበራዊ ግዴታ ተደርጎ ይወሰድ ነበር፡፡ አንድ አርሲ ሌላውን አርሲ ከገደለ ለቁምጥና ይዳረጋል የሚል እምነት ነበር፡፡
ይሁን እንጂ የሌላውን ጎሳ አባል እንዲገድል ተፈቅዶለታል፡፡ አንድ አርሲ ለግድያ ከመሰማራቱ በፊት ለወኔው ማነሳሻ ብዙ (የከብት)
ደም ይጠጣል፡፡ከዚያም ሀገር አማን ብሎ የሚሄደውን መንገደኛ አድብቶ ይገድልና ብልቱን ቆርጦ ወደጎጆው ይመለሳል፡፡ ሲመለስ ፉከራ
ያሰማል፡፡ እንዲሁም የተገደለው ሰው ያስማውን የጣር ድምጽ አስመስሎ በመጮህ ያፌዛል፡፡አንድ ወንድ ይህንን ማድረግ ከቻለ ብቻ ነው
በጆሮው ላይ የብር ሎቲ ማንጠልጠል የሚፈቀድለት፡፡ … ከክብረበአሉ በፊት ሰው ገድሎ መመለስ ያልቻለ ሰው ወርደት ይከናነባል፡፡አንድ
ሰው ትልቅ አውሬ ወይም ሰው ካልገደለ በቀር ሥርዓት ውስጥ ቦታ አይኖረውም፡፡› ›› የሚለው የድሮ አርሲዎች ስእል ያቀርብልናል፡፡(ገፅ
180-182)
ከእነዚህ ጥቅሶች ብያንስ ሁለት ወሳኝ ቁም ነገሮች
ማንሳት እንችላለን፡፡የመጀመርያው፣ የመረጃው ተአማኒነት ምን ያህል ነው የሚል ነው፡፡ብዙ የውጭ ሀገር ፀሐፊዎች ለአፍሪካውያን የነበራቸው
አመለካከት በጣም የተዛባ እንደነበረ የሚታወቅ ነው፡፡ዛሬ አንጋፋ የሚባሉት ፈላስፎች ሳይቀር ብዙ አሳፋሪ መላምቶችን ቀባጥሯል፡፡እነ
ቮልቴር፣ ኢማኑኤል ካንት፣ ግዮርገስ ኩውየር ወዘተ. የመሳሰሉ አሰላሳዮች ለጥቁሮች የነበራቸው አመለካከት በጣም አፀያፊ ነበር፡፡ይህም፣ሳይንትፊክ
ሬሲዝም (ሳይንሳዊ ዘረኝት) በሚባለው ኋላ ቀር ዘርፍ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡በተለይ ደግሞ እ.አ.አ ከ1880-1914 የነበረው የነጮች
ኢምፔርያሊዝም ለማስረገጥ በሳይንስ ስም ጥቁሮችን ማንቋሸሽና ከሰው በታች አድርጎ መሳል የተለመደ ነበር፡፡እናም፣ በውቀቱ በአስረጂነት
የሚጠቅሳቸው ፈሮንጆችም ከንዲህ ዓይነቱ ኋላ ቀር አመለካከት የፀዱ ነበሩ ብሎ መደምደም ይከብዳል፡፡
ሁለተኛው ግን፣ አውሮፓውያን ሌላውን ዓለም ለመቀራመት
እንደ ምክኒያት የሚጠቅሱት ‹‹ሌላውን ዓለም የማዘመን ሰብአዊ ግዴታ›› ነው፡፡ ‹‹የዘመኑ›› የሚባሉት ሀገሮች አፍሪካንና ሌላውን
ዓለም በቅኝ ግዛት ለመያዝ ‹‹አፍሪካውያን እጅግ ኋላቀሮች፣አውሬዎች፣ግማሽ ሰውና ጭራቆች ስለሆኑ በሐይል ወረን በቀኝ ግዛታችን
ስር በማስገባት ልናስተምራቸው፣ ልናዘምናቸው፣ ከግማሽ ሰውነት ወደ መሉ ሰውነት ልናሸጋግራቸው፣ ልናላምዳቸውና ከጭራቅነት አውጥተን
ልናበለፅጋቸው ይገባል›› ከሚል መነሻ ነበር፡፡በሌላ አባባል፣አውሮፓውያን አፍሪካም ሆነ ሌላውን ዓለም በሐይል የተቆጣጠሩበት ምክያት
እጅግ ኋላ ቀርና አውሬ የነበረውን ዓለም ለማዘመን በሚል ሰበብ ነበር፡፡ያው ቅኝ ግዛት አውሮፓውያን ለቅኝ ተገዢዎች የከፈሉት መስዋእትነትና
በቸርነት ያበረከቱት ስጦታ ነበር እንደማለት ነው፡፡ይህ አስተሳሰብ፣ ሌላው ዓለም ከአውሮፓውያን ቅኝ ግዛት ‹‹ነፃ›› ከወጣ በኋላም
በኒዮኮሎኒያሊዝም መልክ ተከስቶ እንደ ነበር የሚታወቅ ነው፡፡
በተለይ፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ እንደ ብቸኛው
የእድገትና የብልፅግና መመርያ ተቆጥሮ በብዙ ሀገሮች ሲሞከር የነበረው ‹‹ሞደርናይዜሸን አፕሮች›› ወይም ድሀ አገሮችን የማዘመን
ስልት የዚሁ ሁነኛ ምሳሌ ነው፡፡በዚሁ እሳቤ መሰረት፣ ዓለማችን በሰሜንና ደቡብ፣ በበለፀጉትና በኋላ ቀር ሃገሮች፣መሀልና ዳር ብለው
ከፋፍለዋት ነበር፡፡ሰሜኖች፣ የበለፀጉና መኃል የሚባሉት ባብዛኛው ሰሜን አሜሪካና አውሮፓን ያጠቃልላል፡፡በተቃራኒው ያሉት ደግሞ
አፍሪካ፣ ደቡብ አሜሪካና ደቡብ ኤዥያን የሚያካትት ነበር፡፡እናም፣ ሰሜኖቹ ደቡቦቹን በእውቀት፣ በቴክኖሎጂና በገንዘብ እየረዱ ማዘመን
እንዳለባቸው የሚሰብክ እሳቤ ነው፡፡እስከ 1970ዎቹ ድረስም እንደ ዋነኛው የብልፅግና መንገድ ይወሰድ ነበር፡፡ኋላ በላቲን አመሪካውያን፣
በአፍሪካውያንና በደቡብ ኤዥያውያን ጠንካራ ተቃውሞ ገጥሞት በ‹‹ዲፐንደንስ አፕሮች›› ሊቀይር መቻሉን ይታወቃል፡፡
በውቀቱ ‹‹ቅድመ ምኒልክ›› እያለ የሐረሪ፣
የወላይታ፣ የከፋና የአርሲ ህዝቦችን በፈረንጆቹ አስረጂነት አውሬ አስመስሎ የሚያቀርብበት ምክንያትም ከአውሮፓውያኑ የተለየ አይደለም፡፡አርሲዎች፣
ሐረሪዎች፣ ወላይታዎች፣ ከፋዎች ወዘተ. በምኒልክ አገዛዝ ስር ከመውደቃቸው በፊት ኋላ ቀርና ጭራቆች ስለነበሩ ምኒልክ እነርሱን
ለማዘመን መስዋእት ከፍሏልና ‹‹አላግባብ›› አትውቀሱት ነው፡፡እንዲህ ያለው ዓይናውጣ ድፍረት ይቅር ታሪክ ሊያቃና ሌላ የታሪክ
ቁርሾ አለማስከተሉም እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡
ይህ አባባል ትልቅ የአስተሳሰብ ህፀፅ አለበት፡፡ጣልያኖች
በማይጨው ጦርነት በዓለም ዓቀፍ ሕግ የተከለከለው የነርብ ጋዝ ለመጠቀም የተገደዱት ሐበሾች የሀገራችን ሉአላዊነት አናስደፍርም፣
የነጮች የቅኝ አገዛዝ አንቀበለም በማለታቸው ነው ብሎ እንደማስተባበል ነውና፡፡ጣልያኖች የየካቲት 12 ሰማዕታትን የጨፈጨፉበት ምክኒያት
አብረሃ ዶቦጭና ሞግስ አስገዶም በግራዝያኒ ላይ የእጅ ቦንቦችን ወርውረው ጉዳት በማድረሳቸው ነው ብሎ ከመከራከርም አይለይም፡፡ይህም፣
የጣልያኖቹን ክፋት በሐበሾች ላይ እንደማላከክ ነው፡፡በማይጨውም ሆነ በአዲስ አበባ ጣልያኖች መጡብን እንጂ አልሄድንባቸውም፡፡አጼ
ምኒልክም አርሲዎችንና ሐረሮችን ሄዱባቸው እንጂ አልመጡባቸውም፡፡ስለዚህ፣መወቀስ ካለባቸው ክንድ፣ እግር፣አንገት፣ ዕድሜ የቆረጡ
ምኒልክ እንጂ አርሲዎች፣ ወላይታዎች፣ ከፋዎችና ሐረሮች አይደሉም፡፡በሌላ አባባል አጼ ምኒልክ ሌሎችን ለማስገበር የወሰዱት የሐይል
እርምጃ ለማስተባበል ይህን ያህል መፍጨርጨር የቅኝ ገዢዎች የሐይል አርምጃ እንደ ማድነቅ ይቆጠራል፡፡
ይልቅስ በውቀቱ እነ ገብረሕይወት
ባይከዳኝን ‹‹የቀኝ ግዛት ናፋቂዎች›› ብሎ ከመክሰሱ በፊት የራሱ አመለካከት መፈተሸ አለበት ያስብላል፡፡ ‹‹…አንዳንድ
የዘመኑ ሊቃውንት የቀኝ ግዛት ናፍቆታቸውን በግልጥ እስከመናዘዝ ደርሰዋል፡፡ ለምሳሌ የገብረእግዚአብሔር አድናቂ የነበረው ገብረሕይወት
ባይከዳኝ፤
‹በዙርያችን ያሉትን አገሮች ብንመለከት አእምሮ
ያላቸው ሕዝቦች በብዙ ትጋት ሲያለምዋቸው እናያለን፡፡ይልቁንም በድርቡሾች ጠፍቶ የነበረውን የሱዳንን መሬት ብናይ እንግሊዞችን የሚመስል
ያእምሮ ሕዝብ ሲገዛው ምድረ በዳም ቢሆን የደስታ ገነት እንዲሆነ ይመሰክርልናል፡፡በዙርያችን ቅኞችን የኮሎንዮችን ይዘው ያሉ ሕዝቦችም
ያእምሮዋቸው ኃይል እንቅፋትን ሁሉ እያሸነፈ ወደ ፊት ይጓዛል› በማለት ሲጽፍ፤
በልጅነት ሩስያ ተሻግሮ ያደገው ተክለሐዋርያት
ተክለማርያም በበኩሉ፤‹አንዳንዴ ሳስበው ምናልባት ሌሎች የሰለጠኑ ህዝቦች ጥቂት ዘመን አስተዳድረውንና አሰልጥነውን ቢሆን ይሻል
ኖሯልን? እያልኩ ራሴን አስከመጠየቅ እደርሳለሁ፡፡እንግሊዞች ካንድም ሁለት ጊዜ እድሉን አግኝተው ነበር፡፡ግን ለመርዳት ስላልፈለጉ
ምንም ሳያቋቁሙ ከሀገር ወጥተው ሄዱ› በማለት የአዞ እንባውን ረጭተዋል፡፡ (ገፅ 122)
ከላይ የተጠቀሱት የገብረሕይወት ባይከዳኝና የተክለሐወርያት
ተክለማርያም ጥቅሶች ግን በምን መልኩ ነው አንድ አይነት የሆኑት? ገብረሕይወት በቅኝ እንገዛ የሚል ቃል አልወጣባቸውም፡፡የተማረ
ህዝብ ተፈጥሮን የማንበርከክ ብቃት እንዳለው ነው እንግሊዞችን በዋቢነት የጠቀሱት፡፡ከምን ተነስቶ ገብረሕይወትን ከአፈቄሳሮችና የቅኝ
ግዛት ናፋቂዎች ጋር አደባልቆ እንደሚከሳቸው ግን ለማንም ግልፅ ነው፡፡ገብረሕይወት አጼ ምኒልክን በሰላ ብእራቸው በመተቸታቸውና
የአጼውን መሰሪ ስንክሳሮች በመከተባቸው በውቀቱን ክፉኛ አቁስሏ፡፡በመሆኑም፣ አጼ ምኒልክን ለመታደግ ቆላና ደጋ የሚረግጠውን ያህል
የገብረሕይወትም ሆነ የሌሎች ስም ለማጉደፍ የቃላት ዥዋዥዌ ይጫወታል፡፡በተለይ፣ ገብረሕይወትን በገፅ 219 ላይ ‹‹እንኳን አእምሮ
ያላቸው ነገሥታት ኦሮሞውም ቢሆን…››ብሎ በመፃፉ መላውን ኦሮም በጅምላ ሰድቧል በማለት ይከሰዋል፡፡
ወረድ ብሎም ‹‹አፈወርቅና ገብረሕይወት…››
በማለት ከአፈቄሳሩ አፈወርቅ ገብረየሱስ ጋር እኩል አድርጎ ስሙን ለማጥፋት ሲጣጣር ተታዘባለህ፡፡የአፈቄሳርና የተክለሐወርት ፅሐፎች
ግልፅና የማያሻሙ ናቸው፡፡ የገብረሕይወትን ፅሐፍ የተረጎመበት መንገድ ግን ከዓውድ ውጪ ነው፡፡ደግሞ ጥቅሱን ቆርጦ ማቅረቡ ሴራ
መሆኑን አመላካች ነው፡፡የሐረጉ ሙሉ ትርጉም ከሐረጉ በፊትና ኋላ ባሉት አረፍተ ነገሮች የሚወሰን ነውና፡፡ነገሩ ወዲህ ነው፤ አጼ ምኒልክ በመታመማቸው
የሃገራችን መኳንንት ወደ አዲስ አበባ ተጠርተው ነበር፡፡እነዚህ ነገርሥታት ቤተሰባቸውና አሽከሮቻቸውን አሰባስበው ወደ አዲስ አበባ
ሲጓዙ የአማራ ተወላጆችም ጓዛቸውን ጠቅልለው ወደ አዲስ አበባ ይገባሉ፡፡ይህን ያስተዋለ የኦሮሞ ህዝብ ንጉሡ ብሎ አስወራ፤ ለመሸፈትም
ከጀለ፡፡
ከዚህ በመነሳት ነው ነጋድራስ ገብረሕይወት ‹‹እንሆ እንኳን አእምሮ
ያላቸው ነገሥታት ኦሮሞውም ቢሆን የመንግሥታችን ችሎት ነዋሪ ነው አይልም፡፡ንጉሥ ቢሞት መንግሥታችን የሚሞት ይመስለዋል፡፡ እውነት
ነው፡፡ትምሕርት በሌለው ሕዝብ ዘንድ ንጉሥ ማለትና መንግሥት ማለት ትርጉሙ አንድ ነው፡፡›› ያለው (ቃላቱን ያሰመርኩባቸው
እኔ ነኝ፤ ነጋድራስ ገብረሕይወት ስራዎች፣ ገፅ 9)፡፡ከስር የተሰመረባቸው ቃላት ልብ ብለን ብናስተውል፤ ከላይ ‹‹አእምሮ›› ተብሎ
የተፃፈው ቃል ወረድ ብሎ ‹‹ትምሕርት›› በሚል ቃል ተቀይሯል፡፡ትክክለኛ ትርጉሙም እሱ ነው እንጂ በውቀቱ ሊተነትነው እንደ ሞከረው
የኦሮሞ ህዝብ ‹‹ትምህርት አይገባውም፣ አይሰለጥንም›› ለማለት አልተፃፈም፡፡
ለነገሩ፣ የበውቀቱ ዋና ዓላማ አቅጣጫ ማሳት
መሆኑን ግልፅ ነው፡፡እጅና እግር የቆረጠው፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ንፁኀን የኦሮሞ፣ የሐረሪ፣ የወላይታና የከፈ ህዝቦች በግፍ የፈጀውና
ያስፈጀው ምኒልክን ‹‹በጊዜው መንፈስ›› እንዳኘው እያለ በደሎቹን ሲያስተባበል ቆይቶ ገብረሕይወትን በአንዲት ቃል ለዛውም በተሳሳተ
አተረጓጎም የታሪክ ተጠያቂ ለማድረግ አይሞክርም ነበር፡፡ይህ አካሄድ፣ በእውነቱ በጣም አስቀያሚና መሰሪነት ነው፡፡ምኒልክን ‹‹በዘመኑ
መንፈስ›› ስንዳኝ ገብረሕይወትም ሆነ ሌሎችን በዘመኑ መንፈስ የማንዳኝበት ምክንያት ምንድን ነው? ፍርደ ገምድልነት፡፡
በውቀቱ የአጼ ምኒልክ ጭራቃዊ ግፎች ለማስተባበል
ምንኛ እንደሚጠማዘዝና የቃላት አክሮባት እንደሚጫወት ከመፅሐፉ ቀንጭበን እንመልከት፡፡አጼ
ምኒልክ ሐረረን በሐይል እንደተቆጣጠሩ ለጁለየ ቦረሊ በላኩት ደብዳቤ ውስጥ ያሉት ቃላት ለመተርጎም የተከተለበት መንገድ በጣም አስቅኝ
ነው፡፡ በገፅ 167 ላይ ‹‹ሰውን ፈጀሁት›› በሚለው ሐረግ ያለው ‹‹ሰው›› የሚለው ቃል ያኔ በነበረው አማርኛ ‹‹ወታደር››
ማለት ነው ብሎ ለማስተባበል ይሞክራል፡፡እንዲህ ይላል፤ ‹‹በተጠቀሰው ደብዳቤ ውስጥ ‹‹ሰው›› የሚለው ቃል ‹‹ሰራዊት›› የሚል
ትርጉም ነው ያለው፡፡›› በያኔው አማርኛ ‹‹ህዝብ›› የሚባል ቃል አልነበረም ማለት ነው? ‹‹አእምሮ ያላቸው ነገሥታት›› በሚለው
ሐረግ ውስጥ ‹‹አእምሮ›› የሚለው ቃል የተለየ ትርጉም አልነበረውም? ለምሳሌ የተማረ፣ የሰለጠነ የሚል ትርጉም አይሰጥም? የበውቀቱ
ጥረትስ ምን ያህል እውነትነት አለው?
ይህን ለማረጋገጥ የትም መሄድ
አይጠበቅብንም፡፡ ‹‹ሰው›› የሚለው ቃል ‹‹ሰራዊት›› ማለት ነበር የሚለው የበውቀቱ ሙግት ተቀብለን ወደ ገፅ 177 እናምራ፡፡በውቀቱ
የሐረሪ ሕዝብ ቁጥሩ የተመናመነው በምኒልክ ሰራዊት ተገድሎ ሳይሆን ያኔ በነበረው የንፋስ(የግሪፕ) ወረርሽን መሆን አለበት በማለት
ይከራከራል፡፡እናም ያን ጊዜ የሐረር አስተዳዳሪ የነበሩት ራስ እምሩ ‹‹1911 ዓ.ም ባውሮፓና በእስያ አድርጎ የመጣው የነፋስ(የግሪፕ)
በሽታ በኢትዮጵያም በመላው ሀገር ገብቶ ብዙ ሰው ሞተ፡፡ ያን ጊዜም ሐረር ነበርኩ…›› የሚል ምስክርነት መስጠታቸውን
ያትታል፡፡እንግዲህ፣ በውቀቱ እንዳለው ‹‹ሰው ሞተ›› ሲባል ‹‹ሰው›› የሚለው ቃል ‹‹ሰራዊት›› ብለን መውሰድ አለብን ማለት
ነው፡፡ይህ አካሄድ ግን የሚያዋጣ አይመስለኝም፡፡እስኪ ደግሞ፣ አጼ ምኒልክ ለንግስት ቪክቶርያ በፃፉት ደብዳቤ ያለው ‹‹ሰው››
የሚል ቃል እንይና የትኛው ቃል ሰራዊት የትኛው ደግሞ ህዝብ እንደሆነ እንለይ፡፡
ይህ የበውቀቱ ፍርደ ገምድል የቃላት ጨዋታ
‹‹Alice’s Adventures in Wonderland›› በሚባል በልዊስ ካሮል የተፃፈ መፅሐፍ ውስጥ ያለው ቃላትን
እንደፈለጉ መጠቀም የሚያስችል ምትሐታዊ ስልጣንን የመፈለግ አባዜ ያስታውሰናል፡፡
‹‹When I use a word,”
Humpty Dumpty said in rather a scornful tone, “it means just what I choose it
to mean — neither more nor less.”
“The question is,” said Alice, “whether you can make words mean so many different things.”
“The question is,” said Humpty Dumpty, “which is to be master — that’s all.›› (የሆነ ቃል ስጠቀም፣ ትርጉሙ በእኔ ምርጫ ነው የሚበየነው፡፡ጥያቄው፣ ቃላት የተለያየ ትርጉም እንዲሰጡ ማድረግ ይቻላል ወይ የሚል ነው፡፡በቃ፣ ጥያቄው ጌታ የመሆን ነው፡፡)
“The question is,” said Alice, “whether you can make words mean so many different things.”
“The question is,” said Humpty Dumpty, “which is to be master — that’s all.›› (የሆነ ቃል ስጠቀም፣ ትርጉሙ በእኔ ምርጫ ነው የሚበየነው፡፡ጥያቄው፣ ቃላት የተለያየ ትርጉም እንዲሰጡ ማድረግ ይቻላል ወይ የሚል ነው፡፡በቃ፣ ጥያቄው ጌታ የመሆን ነው፡፡)
ለመሆኑ ገብረሕይወትን በቅኝ ግዛት ናፋቂነት
ስላስረጀው ጥቅስ የታሪክ ኤሜሪተስ የሆኑት ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ ምን ይላሉ? ‹‹የነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ ስራዎች›› ተብሎ
ባለፈው ዓመት ለሕትመት በበቃው መፅሐፍ መግብያ አንድ (ገፅ 10) ላይ የሚከተለውን ምስክርነታቸው ሰጥተውበታል፡፡
‹‹
‹በዙርያችን ያሉትን አገሮች ብንመለከት አእምሮ ያላቸው ሕዝቦች በብዙ ትጋት ሲያለምዋቸው እናያለን፡፡ይልቁንም በድርቡሾች ጠፍቶ
የነበረውን የሱዳንን መሬት ብናይ እንግሊዞችን የሚመስል ያእምሮ ሕዝብ ሲገዛው ምድረ በዳም ቢሆን የደስታ ገነት እንዲሆነ ይመሰክርልናል፡፡
ቡርያችን ቅኞችን የኮሎንዮችን ይዘው ያሉ ሕዝቦችም ያእምሮዋቸው ኃይል እንቅፋትን ሁሉ እያሸነፈ ወደ ፊት ይገፋል፤ መሬት ጠቦታልና፡፡አእምሮም
በአእምሮ ካልሆነ በቀር በሌላ አትታገድም፡፡ስለዚህ ወዮለት በድንቁርናው ለሚቀመጥ ሕዝብ ውሎ አድሮ ይደመሰሳልና፡፡› ››
‹‹ቀጠል
አድርገውም፣ አርነት(ነፃነት) ማለት የራስን መንግስት ማቋቋም ብቻ ሳይሆን፣ ራስን መቻልንም እንደሚጠይቅ ይናገራሉ፡፡ በዚህ ስሌትም
የኢትዮጵያ ሕዝብ ራሱን ስላልቻለ ነፃ ነው ብሎ አፍ ሞልቶ መናገር ያዳግታል ይላሉ፡፡
ይህም
የሚያስረዳው፣ ነጋድራስ ገብረ ሕይወት መሰረታዊ ነጥብ እንደ ሱዳንና ኬንያ ቅኝ አገዛዝ ስር ብንወድቅ ይሻላል ለማለት ሳይሆን፤
ራሱን የቻለ የልማት ጎዳና መቀየስ አለብን ነው፡፡ይህም አስተሳሰብ መንግስትና የሕዝብ አስተዳደር በሚለው ሰፋ ባለው በሁለተኛው
መፅሐፋቸው ይበልጥ ተብራርቶ ይገኛል፡፡››
የታሪክ ሊቁ እይታና የበውቀቱ እይታ ይህን ያህል
የተለያየ ነው፡፡እኔ በበኩሌ የታሪክ ኤሜሪተስ ፕሮፌሰሩን ምልከታ እጋራለሁ፡፡
የእኔ መልእክት ሲጠቃለል፣ በውቀቱ ከህፀፆች፣
ከወገንተኝነትና ከግለኝነት ነፃ ይሁን አይደለም፡፡ምንናችንም ቢሆን በተለያዩ ምክንያቶች ለተለያዩ
ጫናዎች የተጋለጥን ነን፡፡ስለዚህ ብያንሰ ብያንስ የተለያዩ እይታዎች ስላሉን የተለያዩ እውነታዎች እንደሚኖሩን ማመን አለብን፡፡እኔ
ያልኩት ብቻ ነው ትክክል፤ ሌላው የተሳሳተ ስለሆነ መታረም አለበት የሚል ዲስኩር ከማሰማታችን በፊት የራሳችን እይታና እውነታ ምን
ያህል ትክክል መሆኑን ማጤን ያስፈልገናል፡፡ከሁሉም በላይ ግን ፅሑፎቻችን ሁሉ በሌላው ላይ ነጥብ ለማስቆጠር ያለሙ መሆን የለባቸውም፡፡
ይህን ካልኩኝ ዘንዳ በውቀቱ ከላሌበላ ወደ አክሱም በመጓዝ ላይ እያለ ኦቦ ማናየ ከተባሉ ሰውዬ ጋር ባደደረጋት ቃለ ምልልስ ፅሑፌን
ላጠቃልል፡፡
‹‹ ‹ሀገርህ የት ነው?›
ብለው ጠየቁኝ
የትውልድ ሀገሬን ነገርኳቸው፡፡
‹እሱማ ሀገርህ አይደለም›
‹ኢትዮጵያ› አልሁ ያሻሻልሁ
መስሎኝ፡፡
‹እሱም ሀገርህ አይደለም›
‹ታድያ ምንድን ነው?›
‹ሀገርህ ምግባርህ ነው፤
የሰው ሀገሩ ምግባሩ ይባላል› ››
ሰላም!

When u see an error on the title it just doesn't feel it is worthy of reading it. Please fix the title.
ReplyDelete