Sunday, April 27, 2014

ዞን ዘጠኞች አልታሰሩም…ከሸሪኮቻቸው ጋር ተቀላቀሉ እንጂ





…ከ37 ዓመታት በፊት መስከረም 1969 ዓ.ም ኢህአፓ በአንባገነናዊው የደርግ መሪ መንግስቱ ሃይለማርያም ላይ የግድያ ሙከራ አድርጓል፡፡ያኔ ሂወት ተፈራ እና ገታቸው ማሩ ከኢህአፓ አባልነታቸውም ባሻገር በጣም የሚዋደዱ የቁርጥ ቀን ፍቅረኞች ነበሩ፡፡ጌታቸው ማሩ ‹‹የታዎር ኢን ዘ ስካይ›› ዋና ገፀ ባህሪ ሲሆን በወቅቱ የአብዮት መስራች፣ ኋላም የኢህአፓ የፖሊት ቢሮ አባልና የወጣቶች ሊግ አስተባባሪ ነበር፡፡ እናም ሂወት ‹‹ በመንግስቱ ላይ ስለ ተፈፀመው የግድያ ሙከራ ምን ታስባለህ?›› በማለት ጌታቸውን ትጠይቀዋለች፡፡

የጌታቸው መልስ ‹‹ መግለፅ ከምችለው በላይ ቅጥ ያጣ እብደት ነበር፡፡የሃገር መሪን ለመግደል መሞከር መፈንቅለ መንግስት ሲሆን ግለ ሰቦችን መግደል ደሞ ከግበረ ሽበራ ተግባር ይቆጠራል፡፡እንደኛዎቹ ዓይነት ፓርቲዎች በዚሁ ተግባር መሳተፍ የለባቸውም፡፡የከተማው የትጥቅ ትግል ሐሳብ ፓርቲው ይዞት ከተነሳው አቅጣጫ ያፈነገጠ ነው፡፡ ፓርቲው በጥፋት መንገድ ላይ እየተራመደ ይገኛል…›› የሚል ነበር፡፡ወቅቱ የስልሳዎቹ አብዮት ሙሉ በሙሉ ተቀጣጥሎ የሚንቀለቀልበት የዕብደት ጊዜ ነበርና የእነ ጌታቸው ማሩ ጥልቅና ዘመን ተሻጋሪ እይታ ማንም ሊረዳው አልቻለም ነበር፡፡ጌታቸው ተቀባይነት አላገኘም…እናም በአንጃነት ተፈርጆ ተገደለ፡፡ሆኖም ግን የጌታቸው ማሩ ግድያ የግለ ሰብ ግድያ አልነበረም…የሃገርና የትውልድ ግድያ እንጂ፡፡

Wednesday, April 23, 2014

ነፍጠኛ ማን ነው?



ምንጭ፡EduardoByrono
በእኔ እሳቤ ነፍጠኛ ማለት አማራ ማለት አይደለም(በተለይም ከልክ በላይ የዋህና ርህሩሆቹን የገጠር አማሮችን አይወክልም)፡፡ነገር ግን በብሔረ አማራ ነፍጠኞች አልነበሩም፣ የሉም ለወደፊቱም አይኖሩም ማለት አይቻልም፡፡ ትናንት ነበሩ፣ ዛሬ አሉ፣ በዚሁ አካሄዳቸው ከቀጠሉ ደሞ ነገም ይኖራሉ… የብሔሩ ተወላጆች እስኪያስወግዷቸው ድረስ፡፡
ነፍጠኛ ማለት ትግራዋይ፣ኦሮሞ፣ወላይታ፣ዓፋር፣ ሰማሌ፣ሐረሬ፣ጉራጌ ወዘተ ማለትም አይደለም፡፡ነገር ግን በእነዚህ ብሔሮች ነፍጠኞች አልነበሩም፣የሉም ለወደፊቱም አይኖሩም ማለት አይቻልም፡፡ምክንያቱም ትናንት ነበሩ፣ ዛሬ አሉ፣ በዚሁ አካሄዳቸው ከቀጠሉ(ነፍጠኛ ያልሆኑ ኢትዮጵያውያን ካላስወገዷቸው በስተቀር) ደሞ ነገም ይኖራሉ፡፡

Saturday, April 19, 2014

ታስሮ የከረመው ውሻ ሲለቀቅ…



ነገ የፋሲካ በዓል ነው፤ በዓሉን በጉጉት ስትጠባበቁ ለነበራችሁ ምእመናን በሙሉ እንኳን አደረሳችሁ ማለት እወዳለሁ፡፡በእርግጥ፣ እንኳን አደረሳችሁ መባል አለባችሁ፤ ይገባችኋል፡፡ቃሊቲ ባትወርዱም ታስራችሁ ከረማችኋልና… እንኳን ልጓመ ፆሙን ፈታላችሁ፡፡ለአርባ ምናምን ቀናት ስጋ የለ፣ እንቁላል የለ፣ወተት የለ … ነጋ ጠባ የፈረደባት ሽሮሮሮ… የሁዳዴው ፆም የበሬ፣የበግ፣የፍየልና የደሮ የእፎይታ ወቅት ነበር፡፡ስንት ስጋ ቤት ነው ተዘግቶ የከረመው?

Monday, April 14, 2014

ተመስገን ደሳለኝና የዓመፅ ጥሪዎቹ



የሃገራችን ፖለቲካ በሁለት የማይታረቁ፣ ማዶ ለማዶ ሆነው በጎሪጥ በየሚተያዩ፣ አንዱ ካልጠፋ በቀር ሌላኛው ይኖራል ተብሎ በማይታሰቡ ፅንፎች መከፋፈሉን ይታወቅል፡፡በአንደኛው ፅንፍ ኢህአዴግ አለ … የስልጣን ዘመኑን ለማራዘም በራሱ ይሁንታ ያፀደቀው ህገ መንግስት ሳይቀር ለመጣስ ወደ ኋላ የማይል፣ህዝቡን የምኞት ህብስት የሚመግብ፣ ለፈርጀ ብዙ ኢኮነሚያዊና ማሕበራዊ ቀውሶች አፋጣኝ መፍትሔ ሳይሆን ተደጋጋሚና አሰልቺ ተልካሻ ምክንያቶችን የሚደረድር፣ ጀሮውን ቢቆርጡት የህዝብ ሮሮ የማይሰማ የግብዞች ስብስብ ነው፡፡

Thursday, April 10, 2014

‹‹በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብር ዥንጉርጉርነቱን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን?››


ኢትዮጵያዊነት በየዓይነት ነው፤ ዓይነት በተጨመረበት ቁጥር የሚጣፍጥ፡፡
ይህ ጥቅስ የእግዚአቢሔር ቃል እንደሆነ በሚነገርለት መፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ በትንቢተ ኤርምያስ ምዕራፍ 13፤ ቁጥር 23 ላይ ተከትቦ ይገኛል፡፡ብዙ ኢትዮጵያውያን ምሁራን ደጋግመው የሚጠቅሱት ጥቅስ ነው፤ በተለይም በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮችና ሰባኪዎች ተደጋግሞ የሚጠቀስ የፈጣሪ ቅዱስ ቃል ነው፡፡እኔም ኢትዮጵያዊ ነኝና ስለሃይማኖት ለመስበክ ሳይሆን ኢትዮጵያዊነትየን ለማስረዳትና አስረገጨ ለመሞገት ምርጫየን አድርጌዋለሁ፡፡በተለይ ደሞ ከሁለት ሳምንታት በፊት ‹‹ኢትዮጵያዊነትማንነት ሳይሆን ዜጎች በህግ የሚጎናጸፉት ማሊያ ነው!›› ብለው እንደ ፍካሬ እየሱስ በቀይ ቀለም ለፃፉት ዲያቆን ሙሉጌታ ወልደገብሪኤል በዚሁ የመፅሐፍ ቅዱስ ጥቅስና ሌሎች ምክንያቶች ልሞግታቸው እሻለሁ፡፡
ዲያቆን ሙሉጌታን በዚሁ ጥቅስ ልሞግታቸው የተነሳሁት ስለኢትዮጵያና ስለማንነት በመፃፋቸው ‹‹የኢትዮጵያን ክብር አቃልሏል››፤ በመሆኑም ‹‹ፀረ አንድነት›› ናቸው ብዬ ስለማምን ሳይሆን ‹‹ማንነትንና  ኢትዮጵያዊነትን እተረጉማለሁ›› ከሚል ቅንነት ቢነሱም የሁለቱም ቃላት ትርጉም አንድም ከእውቀት ማነስ ትርጉማቸውን አበላሽቷቿል፣ሁለትም አንድ አንድ ወገኖች ‹‹በኢትዮጵያዊነት ላይ የአንበሳ ድርሻ ያላቸው ያህል›› ስለኢትዮጵያዊነት ሲፃፍ በፀረ ኢትዮጵያዊነት እየፈረጁ እልህ ውስጥ ስለከተቷቸው እነሱን ለመበቀል በማሰብ የተሱበት ዓላማ ትተው(ረስተው) በመጠኑ የቆሸሸውን ‹‹ኢትዮጵያዊ መግባባት›› ለማደፍረስ ሞክሯል ብዬ ስለማምን ብቻ ነው፡፡