ስሜት
በውቀቱ ስዩም ዘመኑ ካፈራቸው ደንቅ የስነ ፅሑፍ ሰዎች አንደኛው ነው፡፡ በቅርቡ ‹‹ከአሜን
ባሻገር›› የተሰኘው መፅሐፉን ለሕትመት ማብቃቱን ስሰማ ደስታየ ወደር አልነበረውም፡፡ የእርሱ መፅሐፍ ለማንበብ የነበረኝ ጉጉት
የላቀ ስለነበረም የመጀመርያው እትም ገዝቼ ማንበብ ችያለሁ፡፡
የበውቀቱ ሽሙጦች ባነበቡኩኝ ቁጥር እንባየን መቆጣጠር እስኪያቅተኝ ድረስ በሳቅ እንፈረፈራለሁ፡፡በመሆኑም
የሆነ ደባሪ፣ረዥምምምና ጨፍጋጋ ጊዜ መግደል ሲያስፈልገኝ ‹‹መውጣትና መግባት››ና ‹‹እንቅልፍና እድሜ›› የተሰኙ መፃሐፎቹን ደጋግሜ
አነባለሁ፡፡ከ‹‹አሜን ባሻገር››ን ሳነበም ሁለት ነገሮች እንደ እብድ ብቻየን እንድስቅ አስገድደውኛል፡፡አንደኛው የበረራ አስተናጋጆች(ወይም
በወንበሩ በተገጠሙት ስክሪኖች አማካኝነት የሚታየው መመርያ) በአደጋ ጊዜ እንደህ አድርጉ እንድያ በሉ እያሉ ተጓዦችን የሚያስቡኩበት
ክፍለ ጊዜ የገለፀበት ፅሑፍ ላይ፣
‹‹ለመሆኑ በአደጋ ሰዓት ከወንበሬ ስር መንሳፈፍያ ከረጢት መኖር አለመኖሩን ይቅርና፣ ወንበር
ላይ ልቀመጥ ጉቶ ላይ እንዴት ትዝ ሊለኝ ይችላል? ሰው አለቅጥ ሲደነግጥ እንዲህ ያለውን የጥንቃቄ ዝርዝር ይቅርና በሽንት ቤት
እና በሱሪው መካከል ያለውን ልዩነት እንኳን ይረሳዋል፡፡ለዚህ ነው ብዙ ደንጉጦች በአደጋ ሰዓት ሽንታቸውን ለሱሪያቸው የሚያስረክቡት፡፡››
የሚለውን ሳነብ በጣም ስቄያለሁ፡፡ አሁንም እየሳቅኩኝ ነው የምፅፈው፡፡(ገፅ 41)
ሌላው በጣም ያሳቀኝ ደሞ፣ በቢላደን ምክንያት ፂማም ሰዎች ሁሉ አሸባሪዎች እንደሚመስሉት ይገልጥና፣
ካጠገቡ የተቀመጠው ፂማም ተሳፋሪም አሸባሪ እንዳይሆን ስለጠረጠረ ሰውየው ‹‹ጠብደል ከመሆኑ የተነሳ›› አውሮፕላንዋን
አንዳይጠልፋት መስጋቱን ይተርካል፡፡ከዛም፣ ያ አሸባሪ ሊሆን ይችላል ብሎ የገመተው ሰውዬ አውሮፕላንዋን ሳይሆን ሽንት ቤቱን መጥለፉ(
ሽንት ቤት ውስጥ በጣም መቆየቱን) ይታዘባል፡፡ያኔ፣ ‹‹ሰውዬው ኑሮውን ነው እንዴ የሚፀዳዳው?›› የሚለውን መስመር ሳነብ በሳቅ
ፍርስ ብያለሁ፡፡(ገፅ 43)
የስነ ግጥም ጥበብ መግጠሙ ላይ ብቻ ሳይሆን አነባበቡም የተለየ ተሰጥኦና ክህሎት የሚጠይቅ
ይመስለኛል፡፡ለዛም ሳይሆን አይቀርም በሃገራችን በገጣሚነታቸው ወደር የለሽና አንቱ የተባሉ ገጣሚዎች የገጠሙት ግጥም ራሴ ሳነበው
ያን ያህል ስሜት አይሰጠኝም፡፡በተለይ ግጥሙ በጣም ረዥም ከሆነ፣ያለወትሮየ እንቅልፍ እንቅልፍ ይለኛል፤ አሁንም አሁንም ያፋሽገኛል፡፡እናም
ሳልጨርሰው በጅምር ይቀራል፡፡ገጣሚዎቹ ሲያንቆረቁሩት ማዳመጥ ግን የሆነ ለመግለፁ የሚከብደኝ የመንፈስ ልዕልና ይሰማኛል፡፡
የበውቀቱ አጫጭር ግጥሞች ግን ከዚህ የተለዩ ሆኖው አግቻቸዋለሁ፡፡ገጣሚው ሲያነባቸውም ሆነ
ራሴ ሳነባቸው፣ ህሊናየን እንደ ምግብ ያጠግቧታል፣ ለነብሴም መድሓኒት ሆኖው ይፈውሷታል፡፡ራሱ የገጠማቸው ግጥሞች ብቻም ሳይሆን
የሚፅፋቸው መጣጥፎች ጥልቅ የሆነ መልእክት እንዲያስተላልፉለት የሚመርጣቸው ግጥሞችም አስደናቂ ናቸው፡፡
የሰው ልጅ ተግባቦት ልሂቃን(human communication experts) የአንድ ቃል ትርጉም
የሚበየነው ቃሉ የገባበት ዓውድ በማጤን ነው የላሉ፡፡ዓውድ(context) ቃሉ የተጠቀምንበት ጊዜ፣ ቦታና ሁኔታ ማለት ነው፡፡በውቀቱ
የሚመርጣቸው ግጥሞች ከዚህ አንፃር ስትመዝናቸው የሚሰጡት ትርጉም እጅግ የላቀ ነው፡፡በመሆኑም ለደራሲው የለኝ ክብርና አድናቆት
የዚያን ያህል በጣም የላቀ ነው፡፡በቃ፣ ሰውዬው የተንጨበጨበለት ዋዘኛና ድንቅ ገጣሚ ነው፡፡እጅግ የላቀው የቋንቋ እውቀቱና ክህሎቱ
ነገሮችን የመግለፅ ብቃቱ ወደር የለሽ አድርጎታል፡፡
በቀለድ፣በሽሙጥ፣በፌዝና በግጥም መልክ የሚቀርቡ ፅሑፎች ከጥልቅ ስሜት የሚመነጩ ስሜት ቀስቃሽ
የተግባቦት ዘርፎች ናቸው፡፡ላንዱ ሽንቱን መቆጣጠር እስኪያቅተው ድረስ የሚያስቀው ቀልድ ለሌለው ስሜቱን መግታት እስኪሳነው ድረስ
ሊያበሳጨው፣ሊያሳዝነው፣ሊያስቀይመው ብሎም ለድብድብ ሊያነሳሳው ይችላል፡፡ይህን ለማስረገጥ፣ በውቀቱ ስለ አቡነ ተክለሃይማኖት የከተባት
ቀልድ ምን እንዳስከተለች እንደምሳሌ ማንሳቱ ተገቢ ነው፡፡ያቺ ቀልድ ብዙዎችን ማሳቋን የሚታበል አይመስለኝም፤ ሆኖም ግን የሆኑ
ሰዎችን ክልክ በላይ አበሳጭታ ለድብድብ አነሳሳችና በውቄ ዱላውን እንዲቀምስ ሰበብ ሆናለች፡፡
ስለዚህ ለስሜታዊ ፅሑፎች የምንሰጠው ግብረመልስ ስሜታዊ ነው ማለት ነው፡፡ሳቅም ሆነ ብስጭት
ከፍ ሲልም ድብድብ የስሜት መገለጫዎች ናቸው፡፡እንደየ አመለካከታችን ግን ስቀን ወይም ንቀን ልናልፋቸው እንችል ይሆናል፡፡በመሆኑም፣እስካሁን
ድረስ ያነበብኳቸው ሽሙጦች፣ቀልዶችና ፊዞች ስቄ፣ንቄ ወይም አድንቄ አልፋቸው ነበር፡፡በቅርቡ ለህትመት የበቃው ‹‹ከአሜን ባሻገር››
የተሰኘው መፅሐፉን ግን እንዲሁ ችላ ልለው አልቻልኩም፡፡በመፅሐፉ የቀረቡ ‹‹ጉዞ፣ታሪክና ፖለቲካ ቀመስ›› ፅሑፎች እንደ ዋዛ የሚታለፉ
ሆነው አላገኘኋቸውም፡፡ለጊዜው የሚከተሉት ምክንያቶች ላስቀምጥ፡፡
የመጀመርያው ምክንያት፣በውቀቱ ከስሜታዊነት ወደ ምክንያታዊነት የተሸጋገረበት መፅሐፍ ነው፤
‹‹ከአሜን ባሻገር››፡፡በእዚህ መፅሐፍ፣ የአፃፃፍ ስልቱን በእጅጉ ቀይሮታል ማለት ይቻላል፡፡ከሚታወቀው ስሜታዊ(አሽሙር፣ ስላቅ፣ ማላገጥ፣ ወዘተ.) የአፃፃፍ
ስልቱን ወጥቶ ወደ ሳይንሳዊ የአፃፃፍ ዘድየ እየተንደረደረ መሆኑን የሚጠቁሙ ምክኒያቶች
አስተውያለሁ፡፡በመሆኑም፣ደራሲው ምን ያህል ምክንያታዊና ገለልተኛ ነው? የሚለው ጥያቄ መልስ ይፈልጋል፡፡ቀልድና
ቁምነገር መቀላቀል ያስፈለገበት ምክንያትም ግልፅ ሊሆን ይገባል፡፡
ሁለተኛው ምክንያት፣ ድሮና ዘንድሮን ያየበት መነፅርና የሃገራችን ፖለቲካና ታሪክ ለመዳሰስ የተከተላቸው ስልቶች እንዲሁ
በዋዛ የማይታለፉ ስለሆኑ ነው፡፡የመጣጥፎቹ ይዘት ‹‹አላግባብ የተወቀሱትን ከማወደስ፤ አላግባብ የተረሱትን
ከማስታወስ ያለፈ ዓላማ›› ያነገቡ ናቸውና እንዲሁ በቸልታ የሚታለፉ አይደሉም፡፡
ሶስተኛው አፅንኦት የሚሰጠው ጉዳይ፣ በውቀቱ የዘመኑን ትውልድ ያየበት መነፅር ነው፡፡ራሱን
መንፈሰ ጠንካራና ለዓላማው ሟች አድርጎ ሲያስቀምጥ ትውልዱን ግን ‹‹ቀቢፀ ተስፋ›› ባጨለመው ‹‹ደስታ›› የሚነዳ የሰዶምና ጎመራ
ትውልድ አስመስሎ ስለሳለው እይታው መጠየቅ አለበት፡፡
የአንድ መፅሐፍ የዘትና አቀራረብ የሚመዘነው
ፀሐፊው(ደራሲው) ባለው የቋንቋና የመፃፍ ክህሎት ብቻ አይደለም፡፡ፀሐፊው የተከተላቸው የአፃፃፍ ዘዴዎችና የፅሑፉ ይዘት ከስነ አመክንዮ፣
ከስነ ምግባርና ከሰብአዊነት አንፃር መመዘንም ወሳኝ ነው፡፡ስለዚህ፣ ‹‹ከአሜን ባሻገርን›› በዚህ መልኩ መዳሰስ ግድ ይለናል ማለት
ነው፡፡
ምክኒያታዊነት
‹‹ከአሜን ባሻገር›› 246 ገፆችና 20 መጣጥፎች ይዛለች፡፡የመፅሐፏ አሳታሚ ፋርኢስት ትሬዲንግ
ኃላፊነቱን የተወሰነ የግል ማሕበር ሲሆን ዋጋው 70 ብር ነው፡፡የመፅሐፉ ሽፋን ልዩ ምልክት ብስኪሌት(ባይሲክል) ናት፡፡ የሳይክሏ
የፊትጎማ የዳግማዊ ምኒልክ ምስል ያለው ሳንቲም ሲሆን የኋለኛው ጎማ ደግሞ በ2002 ዓ.ም ታትሞ በማገልገል ላይ ያለው ብረቱ የአንድ
ብር ኖት ነው፡፡የሳይክሏ በዚህ መልኩ መቅረብ የሚጠቁመው ድሮና ዘንድሮ የኢትዮጵያ የማይነጣጠሉ ገፅታዎች መሆናቸውን ነው፡፡ወይም
ድሮ ያለዘንድሮ መንቀሳቀስ አይችልም ማለት ነው፡፡ታሪካችን አንድ ዝላይ ወደፊት መዝለል የሚችለው ርቀት ወደ ኋላ ተንደርድሮ የሮጦው
ፍጥነት ወሳኝ የሆነውን ያህል፣ የዛሬው የሃገራችን እርምጃም ትናንት ስትራመደው በነበረው ፍጥነት ይወሰናል፡፡
ደራሲው ድሮና ዘንድሮ ምንኛ እንደተዋኸዱ ሲገልፅ፣‹‹የዛሬው ዘመን ምን ቢታገል ካለፈው ዘመን
ተለይቶ ጎጆ መውጣት አይችልም፡፡ያለፈው ዘመንና የዛሬው ዘመን እንዳይፋቱ ሆነው ተቆራኝተዋል፡፡አንዳንዴ ሳስበው፤ ‹ዘንድሮ› በሚለው
ቃል ውስጥ ‹ድሮ› የሚለው ቃል መገኘቱ ባጋጣሚ አይመስለኝም፡፡›› ብሏል በገፅ 9 ላይ፡፡
እዚ ጋ፣ አንድ ጥያቄ መነሳት አለበት፤ድሮና ዘንድሮ ይህን ያህል የተቆራኙ ከሆኑ ዘንድሮን
ከድሮ ነጥለን መተቸት እንችላለን ወይ? የትናንቱ ታሪካችን ያተነፈሰው ጎማ፣ ዛሬ በፈለግነው ፍጥነት ሊያንቀሳቅሰን ካልቻለ ዘንድሮን
ነው መኮነን ያለብን? ድሮና ዘንድሮ ይህን ያህል የተቆራኙ ከሆኑ ‹‹ታሪክን ቁርጭምጭሚታችን ላይ እንደ ታሰረ አለሎ የሚያከብዱብን
የዘመናችን ደረቅ ብሔርተኞች ናቸው፡፡›› ብሎ መፍረዱ ከስነ አመክንዮ አንፃር ተገቢ ነው? ‹‹ደረቅ ብሔርተኞች›› ዘንድሮ የተፈጠሩ
ከሆነ አንድም ድሮና ዘንድሮ ላይታረቁ የተፋቱ ናቸው አልያም እነዚህ ‹‹ደረቅ ብሔርተኞች›› ድሮ የፈጠራቸው ናቸው፡፡ስለዚህ፣ ድሮና
ዘንድሮ እኩል ሊሞገሱ ወይም ሊተች ይገባል፡፡ምኒልክን እያወደሱ ኢህአዴግን ይህን ያህል አምርሮ መተቸት አይቻለም፡፡ሁለቱም አገዛዞች
‹‹ላይፋቱ የተቆራኙ›› የድሮና ዘንድሮ ውጤቶች ናቸውና፡፡
ደራሲው፣በጉዞ ቀመስ መጣጥፎቹ መግብያ ላይ፣
‹‹አንች ወድያ ማዶ፤ እኔ ወዲህ ማዶ
አንገናኝም ወይ፤ ተራራው ተንዶ›› በሚባለው የቆየ ዘፈን የሚገኘው ‹‹ወድያ ማዶን ከወዲህ ማዶ ለይቶት የቆየው ተራራ በቴክኖሎጂ ድማሚት ፈርሷል፡፡››
ይላል፡፡ እናም ‹‹ስእላዊ ዘገባ›› ሳይሆን ፃሐፊው የግሉ እይታ እንደሚቀርብ ያትታል፡፡
በፖለቲካ ቀመስ መጣጥፎቹ መግብያ ደሞ የአንጋፋ ፖለቲከኞች ስክነት ወይም ከፖለቲካው ራሳቸውን
ማግለልና የአዳዲስ ፖለቲከኞች ስሜታዊነት ከብርቱካን ሚደቅሳ ጋራ በአሜሪካ ተገናኝተው ሲጨዋወቱ እሱ በስሜት ጠረጴዛውን በቡጢ እየደበደበ
ሲያወራ እርሷ ግን በአስተዋይነት ስትመለከተው እንደምሳሌ አድርጎ ያቀርባል፡፡‹‹በርግጥ›› ይላል በውቀቱ፣ ‹‹ተናግሮ ማሳመን፣
ታግሎ መጣል ሁልጊዜ አይሳካም፡፡ያም ሆኖ፣ እስክረታ ድረስ ካልታገልሁ፤ እስክታፈን ድረስ ካልተናገርሁ፤ የረባ ኑሮ ኖርሁ ማለት
ይከብደኛል፡፡›› እናም፣ መታገሉም ሆነ መናገሩ እስከ መጨረሻ እቀጥልበታለሁ የሚል እንድምታ ያለው መልእክት አስተላልፏል፡፡
በውቀቱ፣ የራሱን የዓላማ ፅናትና አይበገሬነት በዚህ መልኩ ሲያስቀምጥ የዘመኑን ትውልድ ግን
ከገፅ 19 እስከ 24 ባለው ‹‹ደስታና ቀቢጸ ተስፋ›› በሚለው መጣጥፉ ‹‹ከቀቢጸ ተስፋ›› በመነጨ
ድቅድቅ ጨለማ የተሸበበ ተስፋ ቢስ፣ ቀልበ ቢስ፣ወኔ ቢስና ዓላማ የለሽ፣በልቅ ወሲብ፣ በጫት፣ በሐሽሽ፣ በመጠጥ፣ በአጠቃላይ በሱስና
በጊዚያዊ ደስታ የታወረ ልክስክስ አድርጎ አቅርቦታል፡፡
‹‹የዘመኔ ጀግና እንዲህ የሚል የመስለኛል›› ይላል በውቀቱ ከገፅ 23 እስከ 24 ባለው የማጠቃለያ
ፅሑፉ(ይህ ፅሑፍ፣ በመፅሐፉ የኋላኛው ሽፋንም ይገኛል)…
‹‹በኔ ዘመንና በጥንት አቴናውያን የቸነፈር ዘመን መካከል መሠረታዊ መመሳሰል አለ፡፡በሁለቱም
ዘመኖች ውስጥ ለነገ ተስፋ ማድረግ የሚባል ነገር የለም፡፡ ለፍቼ የሠራሁት ቤቴን ባበር ይሁን ሰርጓጅ መርከብ በውል ያልታወቀ ነገር
ጥሶት የሚያልፍ ከሆነ ቤት ለመሥራት እንዴት ላቅድ እችላለሁ? ሰባት መቶ ሺህ ብር የገዛሁት ቤቴን በክረምት አፍርሶ ደርዘን ጃንጥላ
የማይገዛ ፍራንክ ሸጎጥ አድርጎ፣ ቤተመቅደስ እንደገባች ውሻ አካልቦ የሚያባርረኝ ባለሥልጣን ባለበት ሃገር ውስጥ ጎጆ ለምን እቀልሳለሁ፡፡
ጌቶች፣ ለችግር ቀኔ ያጠራቀምኩትን በር በጥጋብ ዘመናቸው የሚወርሱብኝ ከሆነ የባንክ ደብተር የማወጣው ለምንድነው? ልጄ በሕይወት
እያለሁ እጓለ ማውታ ሊሆን እንደሚችል እያወቅሁ፣ ‹የዛሬ ዓመት የማሙሽ ልደት› እያልሁ የምዘፍንበት ምክንያት ምንድነው? ‹ኢትዮጵያ
ለዘላለም ትኑር› ከሚለው መፈክር በስተቀር ኢትዮጵያን ለዘላለም የሚኖራት መሠረት መፍረሱን እያወቅሁ ለሚቀጥለው ዓመት እንዴት ላቅድ
እችላለሁ? ተው ባክህ! እኔም እንደ ጥንቱ አቴናውያን የሞት ፍርድ እንደተፈረደበት ሰው እኖራለሁ፡፡ መስቀያው ገመድ እንገቴ ውስጥ
እስቲገባ ድረስ የጥንቱ ግጥም በቃሌ እወጣለሁ፡፡›› ይህልና የሚቀጥለው የቆየ ግጥም ያክላል፡፡
‹‹የራበህም ብላ፤ የጠማህም ጠጣ፤
ከዚህ የተሻለ፤ ምንም ቀን አይመጣ፡፡
ላገኝ ነው በማለት፤ ሞትኩኝ በሰቀቀን፤
ሂዶ ሂዶ አለቀ፤ የምጠብቀው ቀን፡፡››
ይህ፣ ምልከታው የሃገራችን እውነታ ያንፀባርቃል ብሎ የሚያምን ካለ የበእውቀቱ መነፅር ያጠለቀ
መሆን አለበት፡፡እውን ግን፣ የዛሬው ትውልድ ‹‹ከዚህ የተሸል፤ ምንም ቀን አይመጣ፡፡›› በሚል ጭፍን ጨለምተኝነት የታወረ ነው?
ከላይ የተዘረዘሩት የበውቀቱ መላ ምቶችስ ምን ያህል እውነት ናቸው?ስንቱ የአዲስ አበባ ኗሪ ለጋራ መኖርያ ቤት በየወሩ ይቆጥባል?
ስንቱስ 100 ፐርሰንት ከፍሏል? እስኪ የ40/60 የቤቶች ቁጠባ ለናሙና እንመልከት፡፡
በሃገራችን ስንት ዩኒቨርሲቲዎች አሉ? 30 ይሆናሉ አይደል? ስንት ተማሪ በቀንና በማታ ክፍለ
ጊዜ እየተማረ ይገኛል? አዲስ አበባና መቐለ ዩኒቨርሲቲዎች በደምብ አውቃቸዋለሁ፡፡የቀኑን ይቆይልን፤ የማታው ክፍለ ጊዜ ተማሪ ብዛት
አሸን ነው፡፡ስድስት ኪሎ፣ አራት ኪሎ፣ አምስት ኪሎ፣ ኮሜርስ የመርመሰመሰው ትውልድ በውቀቱ እንዳለው ለነገ የማያስብ በቀቢፀ ተስፋ
የታወረ ነው?
ወመዘክርና ስድስት ኪሎ(ከአምስተኛ በር ወረድብሎ) የሚገኙት ቤተ መፃሕፍት ሁሌም እጎበኛቸዋለሁ፡፡ምንጊዜም
ጥቅጥቅ ብለው እንደሞሉ ናቸው፡፡መቀመጫ አጥቶ የሚመለስ ለመቁጠር ያታክታል፡፡ደግሞ አብዛኛው አንባቢ እንደ ድሮ አሮጌ መፅሐፍ ከፊት
ለፊቱ ዘርግቶ የሚያነብ እንዳይመስላችሁ፡፡የነተበ መፅሐፍ የሚያነብ እጅግ ጥቂት ነው፡፡አብዛኛው በላፕቶፑ የጫነው መፅሐፍ ነው የሚያነበው፡፡የሕትመት
ውጤቶችን ሲያነብ የምትመለከተው በጋዜጣና መፅሔት እንዲሁም የአማርኛ መፃሕፍት ክምችት ባላቸው ቤተ ንባቦችን ነው፡፡ይህ በራሱ፣
የዘንድሮው የብርሃን ጭላንጭል፣ የነገው የተስፋ ጮራ የሚያመለክት ነው፡፡‹‹ድጂታል›› የሆነ ትውልድ እየተፈጠረ ነው፡፡
ለማንኛውም ግን፣ የበውቀቱ የአዲስ አበባ ብሎም የመላው ኢትዮጵያ እይታ ይህ ከሆነ በአውሮፓና
አሜሪካ ተዘዋውሮስ ምን ተመልክቶ ይሆን? የአህጉሮቹ የቴክኖሎጂ ምጥቀት? የዩኒቨርሲቲዎቻቸው የጥናትና ምርምር ውጤት? የትምህርት፣
የምጣኔ ሃብት፣ የፖለቲካና የታሪክ ስልጣኔ ምንኛ እንደ ተወነጨፈ? ስርዓታቸው ምን ይህል እንደላቀ? አውሮፓና አሜሪካ ሄዶ የሙዜሞች
ብዛትና ጥራት፣ የሕትመት ውጤቶች ብዛትና ጥራት፣ የስነ ጥበብና የኪነ ጥበብ ምጥቀት፣ የፊልምና የትሪዝም እንዳስትሪ መስፋፋት፣
የከተሞች ስልጣኔ ነው የተመለከተው? ስለ ‹‹ድጂታል ሲቲስ›› ያለው እይታ ነው ያካፈለን?
በሚያሳዝንና በሚያሳፍር ሁኔታ በውቀቱ እንዚህን አላየም ወይም ስለነዚህ ነገሮች አልፃፈም፡፡በእርግጥ
ስለ ‹‹ስሊከን ቫሊ›› ይተርካል ብየ አልጠበቅኩም፡፡እይታው እንዲህ ይሆናል ብየ ግን አልገመትኩም ነበር፡፡እንግሊዞች ባቡር ይተኩሳሉ
እንጂ ይነዳሉ ማለት አይቻለም ከምትልዋ የለንደን ባቡሮች ፍጥነት ሌላ ጠብ የሚል አላየሁበትም፡፡
በውቀቱ ለንደን ሄዷል፡፡ ምን ተመለከት? ወይም ስለምን ፃፈ? መልሱ፣ ስለ ምግብ፣ ስለ መጠጥና
ጫት፣ስለ ስካርና ድብድብ፣ ስለ ኮንደምና ወሲብ ይለናል ‹‹ከአሜን ባሻገር››፡፡ካላመንከኝ አንድ በአንድ እንያቸው…ተከተለኝ፡፡
በእርግጥ ስለ ኑሮ ውድነትም ፅፏል፡፡ጓደኛው የኑሮ ውድነቱን እንዲህ ገልፆታል ይላል ‹‹የኑሮው
እሣትነት አንስቼ ሳማርር የሰማ አንድ የለንደን ኗሪ አበሻ እንዲህ አለኝ፤ ‹ይገርምሃል፡፡በለንደን አንድ ፓኬት ኮንደም አራት ፓውንድ
ነው፡፡በዚህ ዋጋ አዲስ አበባ ካዛንችስ ሴት መግዛት ይቻላል፡፡› ›› (ገፅ 55) በውቀቱና ጓደኛው የምጣኔ ሃብት ልሂቃን መሆን
አለባቸው፡፡የአራት ፓውንድ የመግዛት አቅም በለንደንና በአዲስ አበባ ምን እንደሚመስል በሚገርም ንፅፅር አስቀምጠውታል፡፡
ከላይ በተጠቀሰው ገፅ ደግሞ ‹‹የጥንት አለቃየ ዐቢይ ተክለማርያም ከሚማርበት ኦክስፎርድ በባቡር
እየሰገረ መጣና፣ ‹ምን እንዳስጎበኝህ ትፈልጋለህ?› ሲል ጠየቀኝ፡፡ ብሪትሽ ሙዚየም ውሰደኝ እንድለው ጠብቆ ይሆናል፡፡ ምሣ ሥዓት
ስለነበር በቅርብ የሚገኝ የአበሻ ሬሽቶራንት እንዲያስጎበኘኝ ለመንሁት፡፡›› ይላል፡፡ከዛም ምን እንደበላ ምን እንደ ጠጣ ይፅፋል፡፡ለነገሩ
አዲስ አበባ ሆኖ የፃፋቸው የድሮ መጣጥፎቹም ከሻይ ቤትና ከምግብ ቤት የሚዘሉ አልነበሩም፡፡
በገፅ 57 ደግሞ ‹‹በለንደን የሚኖሩ አበሾች በሥራ ስዓት ሽንጣቸውን ገትረው ይዝናናሉ፡፡በእረፍት
ሠዓት ደሞ ሌላ ነገር ገትረው ይዝናናሉ፡፡ከዋና ዋና መዝናኛዎች አንዱ ጫት ነው፡፡ዝነኛው ማሙዬ ጫት ቤት ውስጥ ኢትዮጵያውያንና
ኤርትራውያን ተደባልቀው ተቀምጠው ቅጠሉን ከወሬው ጋር ያደቁታል፡፡በአንድነት መኖር ያልቻሉት ወንድሞቻችን ባንድነት መቃም አላስቸገራቸውም፡፡
ይህን ስመለከት፡-
‹ ድንበር ቢለያችሁ
ሱስ አገናኛችሁ›
በማለት በልቤ አንጎራጎርሁ፡፡›› ይላል፡፡
የኸው ነው እንግዲህ፤ለንደንም በጫት ቤቶች የተወረረች
አስመስሏታል፡፡ፈረንጆች ‹‹We see what we want to see›› ይላሉ፡፡እንዲህ የሚሉት ግን በዘፈቀደ አይደለም፡፡በጥናት
አረጋግጠውታል፡፡ነገሩ እንዲህ ነው፤ በጥናቱ ላይ በፍቃደኝነት የተሳተፉት ሰዎች የቅርጫት ኳስ ጨዋታ የሚያሳይ ቪድዮ ይከፍቱላቸውና
በጫወታው ወቅት የተከናወኑ የኳስ ቅብብሎሽ ብዛት እንዲቆጥሩ ይነግሯቸዋል፡፡በዚህ መሐል ግን ጎሪላ የሚያስመስል ፀጉራም ልብስ የለበሰ
ሰው በቅርጫቱ በኩል እንዲያልፍ ይደረጋል፡፡በጣም የሚገርመው ግን ከተሳታፊዎቹ ማንም አላየውም፡፡ይህ ብቻም አይደለም፣ ጎሪላ የሚመስል
ምስል ማለፉን ሲነገራቸው ራሱ ማመን አልቻሉም፡፡ቪድዮ በድጋሚ ሲመከቱት ግን ጎሪላ ምስል ተላብሶ የሚያልፈው ሰው አዩተው በጣም
ተገርመዋል፡፡ካላመንከኝ ከላይ ያለውን ማስፈንጠርያ ተጭነህ እውነትነቱን ማረጋገጥ ትችላለህ፡፡
በገፅ 58 ደግሞ የሚከተለው ፅሑፍ ሰፈሯል፤‹‹በለንደን ምግብ ቤቶችኝ በአምባጓሮ የሚቀውጡ ጉልቤዎች
ሞልቷል…ጉልቤው ስደተኛ የቢራ ጠርሙሱን ወደ ጦር መሳርያ ለመቀየር አልተቸገረም፡፡›› በለንደን ከተማ ውስጥ ግን ከምግብ ቤትና
መጠጥ ቤት በስተቀር ሌላ ነገር የለም እንዴ? በዛች ከተማ ውስጥ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ስንት ፕሮፌሰሮች፣ ስንት ተማሪዎች ይኖሩሉ?
ብሎ ራሱን አለመጠየቁ አይገርምም? ሌላም ሌላም ብዙ ነገር ይኖር ይሆናል እኮ፡፡ችግሩ ግን ‹‹We see what we want
to see›› ነው፡፡
ጓድ በውቀቱ፣ የኔዘርላንድዋ ድንቅ ከተማ አምስተርዳም ሄዶስ ምን ጎበኘ? ‹‹ከአሜን ባሻገር››
ከተማዋን እንደሚከተለው ያስቃኘናል፡፡ ‹‹በዳም አደባባይ እግር ጥሎህ ስትራመድ አፍንጫህን የሚያውድው የሀሸሽ ጠረን እንጂ የቤተመቅደስ
እጣን አይደለም፡፡›› አሁንም፣ ‹‹ማየት ምንሻው ነው የሚናየው›› የሚለው የፈረንጆች አባባል ልብ በልልኝ፡፡ በዚሁ ከተማ ውስጥ
‹‹ሬድ ላይት›› በሚባል ሰፈር ሀሸሽና ልቅ ወሲብ በጠራራ ፀሐይ እንደሚፈፀም ጎጉልም ይነግርሃል፡፡ሆኖም ግን፣ በዚሁ አከባቢ 15 የሚያህሉ ድንቅ ሙዜሞች እንዳሉም አይደብቅብህም፡፡እርሰበርሳቸው በተጠላለፉ ድሊዮች ያሸበረቀ ትልቅ ወንዝ እንዳለም ሳይደብቅ
ያስቃኝኀል፡፡የበውቀቱ አፍንጫ ግን የሀሽሽ ጠረን የሚስብ ማግኔት ሳይሆን አይቀርም፡፡
ወንድማችን በውቀቱ አሜሪካ ሄዶስ ስለምን ፃፈ? በቬጋስ ከተማ በጠራራ ፀሐይ ወሲብ እንደሚነገድ፣
ስለ ምግብ፣ስለ ሴት ዳሌ፣ ስለ ሆድ፣ስለ ፍሪጃቸው ትልቅነት፣ ስለ ኮንደም፣ስለ ሱሪና ስርያ…
ልብ እንበል፤ አሁንም የመልሱ ባለበት ‹‹ከአሜን ባሻገር›› ነው፡፡
‹‹አሜሪካ አንድ ትልቅ ሆድ ማለት ነው፡፡›› ይልሃል በውቀቱ፡፡‹‹እንደ አሜሪካኖች ያለ ሆዳም
አለ?!›› ሲልም ያክላል፡፡ቀጥሎም፣ ‹‹የአሜሪካ ጥቁር ወንድሞቻችንን ሱሪና በሱሪያቸው ውስጥ ያለውን መጠን የተመለከተ ሰው ተስፋ
ቆርጦ ወደ አገሩ መመለሱ አይቀርም፡፡›› (ገፅ 232) ውድ አንባቢ ሆይ፣ የሚቀጥለው ፅሑፍም ስለ ምግብ ነው፡፡የራበህ እንደሆነ
ምግብ በልተህ ብትመለስ ይሻላል፡፡አልያም፣ ምሳ ወይም እራት እየበላህ አንብበው፡፡
‹‹አሜሪናኖች ምሳ ሰአት ላይ ምን ያደርጋሉ? መጀመርያ ሄሌኮፍተር ማሳረፍ የሚያስችል ጠረጴዛ ይዘረጋሉ፡፡በላዩ ላይ ኢትፍሩት
ባመት የሚያመርተውን ያህል ፍራፍሬ ይከምሩበታል፡፡ ቀጥለው ኤልፎራ ለፋሲካ የሚያቀርበውን ያክል ሰሀን አንግበው መንሽ የሚያህል
ሹካ ታጥቀው ‹ፈረስት ኮርስ ሰከንድ ኮርስ› እያሉ በምግቡ ላይ ይዘምቱበታል፡፡›› እያለ ስለ አመጋገባቸው ያስቃኝህና ሞቅ ሲለው
ደግሞ የሚከተለውን ይከትብልሃል፡፡‹‹ገና አሥራ ስምንት ያልደፈኑ ኮረዶች መቀመጫቸውን በቁምጣቸው…ትንሽ ሞቅ ሲለኝ ኳሱን መከታተል
ትቸ ቆነጃጅቱን መከታተል ጀመርሁ…Can I get you something sweetheart? ብላኝ ስታልፍ መቀመጫዋን በጥፊ ቸብ
ለማድረግ እጄን ብድግ አደረግሁት፡፡›› (ገፅ 233)
‹‹አንዱ ባለፈው፣ ቦሌ አየር ጣብያ ላይ በፈታሾች አንድ ሻንጣ ሙሉ ኮንደም ተማረከበት፡፡…እናት
አገሩን ለመድፈር ሲዘጋጅ በቁጥጥር ሥር ውሏል ተብሎ ተከሰሰ፡፡›› (ገፅ 234)
‹‹አንዳንዱ አክራሪ አስመላሽ ኮንደም ከተጠቀመ በኋላ ‹ስሞክረው ሰፋኝ የዝሆን ከንዶም ነው
እንዴ የሰጣችሁኝ?› ወይም ‹ልጠቀምበት ብለካው እየተንሸራተተ አስቸገረኝ ከተልባ የተሠራ ኮንደም ነው እንዴ የሰጣችሁኝ?› ሊል ይችላል፡፡›› (ገፅ 236)
‹‹የቨርጂኒያው ወዳጄ በኃይሉ ዘሪሁን፣ ቬጋስን ጎብኝቸ ስመጣ፤ ‹ቬጋስ እንዴት ናት› ሲለኝ
‹ትጣፍጣለች› አልኩት፡፡
‹ወትሮም ኀጢአት ጣፋጭ እንደሆነ የታወቀ ነው፡፡› ሲል መለሰልኝ፡፡››
‹‹ቬጋስ፣ ባደባባይ ወሲብ የምትቸረችር ሀገር በመሆኗ የኀጢአት ሀገር ትባላለች፡፡›› (ገፅ
37)
ይህ ሁሉ ሲደመር ምን የሚል ትርጉም ይሰጠናል? በውቀቱ ለንደን ሄዶ ስለ ጫት፣ መጠጥና ምግብ
ነው የፃፈው፡፡አምስተርደም ሄዶም ስለ ሀሸሽ ነው የፃፈው፡፡ አሜሪካ ሄዶም ስለ ምግብ፣ ስለ መጠጥ፣ስለ ሰውነት መግዘፍና ሱሪ መስፋት፣
በወንዶች ሱሪ ውስጥ ስላለው እቃ፣ ስለ ሴቶች ዳሌ፣ ሰለ ወሲብና ስለ ኮነደም ነው የፃፈው፡፡በአዲስ አበባም ሌላ ነገር አልተመለከተም፡፡‹‹ማየት
የምንሻው ነው የምናየው›› የሚሉት አባባል ምንኛ እውነት መሆኑን ለመረዳት የበውቀቱ መጣጥፎች ማንበብ በቂ ነው፡፡ወሲብ፣ ጫት፣
ሀሸሽ፣ምግብ፣ መጠጥ፣ ኮንደም ወዘተ. የመሳሰሉ ነገሮች በዓይኖቹ የተተከሉ አይመስሉም? ስለእነዚህ ነገሮች አዘውትሮ ከመፃፉ የተነሳ
ጨው እንደ ለመደች ፍየል እያነፈነፈ የሚያገኛቸው ይመስለኛል፡፡ አሜሪካም ሆነ አውሮፓ ከምግብ፣ ከመጠጥ፣ ከወሲብ፣ከኮንደም፣ ከሱስ፣
ከሱሪና ስርያ ያለፈ ነገር የለም ያለው ማን ነው? እንግዲህ፣ አዲስ አበባ፣ ለንደን፣ አምስተርዳምና ቪጋስ የሚያመሳስላቸው ምንድነው?
ብለን በውቀቱን ብንጠይቀው መልሱ ገልፅ ነው፡፡
ለምንኛውም፣ የአዲስ አበባ የወሲብና የሱስ ቤቶች ‹‹እንደ ክረምት አግቢ›› መፍላትና የትውልዱ
‹‹በደስታና ቀቢጸ ተስፋ›› የመለከፉ ምክንያት የሚከተሉትን ዘርዝሯል፡፡
- ‹‹የዜጎች ጠባይ ከገዛዝ ሥርዓት ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው››
- ‹‹የፖለቲካ ጭቆና በበረታበት ሀገር ውስጥ፣ ወሲባዊ ልቅነት የመጨረሳው የነፃነት አማራጭ ተደርጎ ይወሰዳል›› እና ‹‹አመንዝራነት፣ ዜጎች ሌላው ቢቀር ብልታቸው በመንግስት ቁጥጥር ሥር አለመሆኑን የሚያሳዩበት መንገድ ነው››
- ‹‹አባቶቻችን ከእኛ የተሻለ የደስታ ምንጮች ነበሯቸው፡፡ ብያንስ ከጀብድ የሚገኝ ደስታ ነበራቸው፡፡››
- ‹‹ቀደምቶቻችን ራሳቸውን ከሌሎች አገሮች ብልጽግና ጋር አነጻጽረው እርር ድብን የሚሉበት አጋጣሚ አልነበረም››
ይኹን እንጂ፣ ከላይ እንደተገለፀው ልቅ የወሲብ ንግድ፣ የሀሽሽና የጫት መዓት በዲሞክራሲያዊነታቸው
በሚታወቁት የአውሮፓና የአመሪካ ከተሞችም እንዳሉ ደራሲው መስክሯል፡፡ስለዚህ ከላይ የተዘረዘሩ ምክንያቶች እውነትነት የላቸውም ማለት
ነው፡፡ምክንያቶቹ ከመንግስታችን ጨቋኝነት፣ ከዓለም አቀፋዊነትና የደስታ አማራጮችን ከማጣት የተያየዙ አይደሉም፡፡ በአዲስ አበባ
ወሲብ የሚያጧጥፉ ማሳጅ ቤቶች፣ፔንሴኖች፣ ጫት ቤቶች፣ ሽሻና መጠጥ ቤቶች ከልክ በላይ በዝተው የታዩት ስለ እነርሱ ስለሚያስብ፣
ወደ ነርሱ አዘውትሮ ስለሚመላለስ በአጠቃላይ ስነ-አእምሮው በነዚህ ነገሮች ስለተቃኘ ነው ሊሆን የሚችለው፡፡
ይህም በውቀቱ ካንገት
በላይ ስላለው የሰው ልጅ ድንቅ ስጦታ ሳይሆን ካንገት በታች ባሉት ነገሮች ላይ ነው የሚያነጣጥረው ብለህ እንድትደመድም ያስገድድሐል፡፡
እንደዛ ባይሆን ኖሮ ለንደን፣ አምስተርዳምና ቬጋስ ሄዶም ስለ ወሲብ፣ ጫት፣ ምግብ፣ መጠጥ፣ ኮንደም አይፅፍም ነበርና፡፡በነገራችን
ላይ፣ወደ ቫቲካን ሲቲ ጎራ ቢል ስለ ወሲብና ተመሳሳይ ነገሮች አይፅፍም ትላላችሁ?
ለዛሬ በዚሁ ይብቃን፡፡በቀጣዩ ክፍል ያገናኝን!
No comments:
Post a Comment