በዚህች ዓለም ስኖር ሶስት ዓይነት ሰዎች አጋጥመውኛል፡፡የመጀርያዎቹ ለከፍተኛ አደጋ ዳርገውኛል…የመኖርና ያለመኖር
የህይወት ጥያቄዎችን እንዳስተናግድ አስገድደውኛል፡፡የመኖር ፈተና ከብዶኝ ለመውደቅ ስንገዳገድ ወደማልወጣው አዘቅት ገፍትረውኛል፡፡ክፉ
ስለሆንኩኝ ግን አልነበረም፡፡ብቻ፣ እንደ ሰው መኖሬን ያበገናቸው፣ ስያዩኝ ደም ደም የሚሸታቸው ነበሩ፡፡ሁለተኛዎቹ የመጀመርያዎቹ
ከደቀኑበኝ የመኖርና ያለመኖር አደጋ የታደጉኝ የህይወቴ መድህን ናቸው፡፡በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እስከዛሬ ድረስ እንድኖር ረድተውኛል፡፡ጥላ
ከለላ ሆኖውኛል፣ ሳዝን አፅናንተውኛል፣ ተስፋ ስቆርጥ አበረታተውኛል፣ ተዳክሜ ለመውደቅ ስንገዳገድ ደግፈውኛል…ቁሜ እንድራመድ ረድተውኛል፡፡ሶስተኛዎቹ
አልፎ ሂያጆች ናቸው…አልጎዱኝም፤ አልጠቀሙኝምም፡፡ምናልባት ግን፣ በተዘዋዋሪ ጠቅመውኝም ጎድተውኝም ሊሆን ይችላል፡፡
በህይወቴ አለኝ የምለው፣ ምንጊዜም የሚያስደስተኝ፣ ሳዝን የሚያፅናናኝ፣ ቀን ሲጎድልብኝና የተስፋ ወገቤን ሲያጎብጠኝ
ተስፋ የሚያሰንቀኝ፣ ፍረድሪክ ኒች ‹‹That doesn’t kill you makes you stronger››(የማይገድሉ ፈታኝ አጋጣሚዎች
ይበልጥ ያጠነክሩሃል) እንዳለው የመኖር ዕዳና ሸክም ካቅሜ በላይ ሆኖ ከሚሰብረኝ ይልቅ ይበልጥ እንዲያጠነክረኝ የረዳኝ ብቸኛው
ስጦታየ የንባብ ችሎታየ ነው፡፡ለማንበብ ያለኝ ፍቅርና ጉጉት ወደር የለውም፡፡ሱስ የለው፣ ጭስ የለው፣ ድካምና ጭንቀት የለው፣ ፀፀትና
ቁጭት የለው…ደስታ ብቻ፡፡ብዙ አሳዛኝ ልበ ወለዶችና እውነተኛ ታሪኮች አንበቤያለሁ፡፡ሆኖም ግን፣ ለካ እንዲህም አለ? ብየ ከመገረምና
ከመደነቅ አልፌ በማንበቤ የተቆጨሁበት ቀን የለም፡፡ይልቅኑስ፣ የሚነበብ ፍለጋ እሰማራለሁ፡፡በጣም የጠቀሙኝ ሰዎች እንግዲህ ማንበብ
እንድችልና የሚነበብ እንዳላጣ የረዱኝ፣ በተአምረኛ የአፃፃፍ ችሎታቸው ቀልቤን ስበው አድናቄያቸው እንድሆን ያደረጉኝና እያደረጉኝ
ያሉት ናቸው፡፡
‹‹ዋው! ኧረ እንኳን ተወደልድኩ…ኧረ በስሜት ተገፋፍቼ እንኳን እራሴን አላጠፋሁ›› ካስባሉኝ ምክንያቶች አንዱ በአካል
ሳይሆን በንባብ የተዋወቅኳቸውና የዚህች ዓለም ብርሃን እንዳላይ የጋረደኝ የአመለካከት ግርዶሽ ያለ ምንም ስቃይና ጠባሳ በቀዶ ጥገና
ያስወገዱልኝ የተለያዩ ዓይነት ደራሲዎች ናቸው፡፡በተለይ እማ ስለህይወትና ስለሰው የሚፅፉ የጥበብ ዕንቆች፡፡
