…ከ37 ዓመታት በፊት መስከረም 1969 ዓ.ም ኢህአፓ በአንባገነናዊው የደርግ መሪ መንግስቱ
ሃይለማርያም ላይ የግድያ ሙከራ አድርጓል፡፡ያኔ ሂወት ተፈራ እና ገታቸው ማሩ ከኢህአፓ አባልነታቸውም ባሻገር በጣም የሚዋደዱ የቁርጥ
ቀን ፍቅረኞች ነበሩ፡፡ጌታቸው ማሩ ‹‹የታዎር ኢን ዘ ስካይ›› ዋና ገፀ ባህሪ ሲሆን በወቅቱ የአብዮት መስራች፣ ኋላም የኢህአፓ
የፖሊት ቢሮ አባልና የወጣቶች ሊግ አስተባባሪ ነበር፡፡ እናም ሂወት ‹‹ በመንግስቱ ላይ ስለ ተፈፀመው የግድያ ሙከራ ምን ታስባለህ?››
በማለት ጌታቸውን ትጠይቀዋለች፡፡
የጌታቸው መልስ ‹‹ መግለፅ ከምችለው በላይ ቅጥ ያጣ እብደት ነበር፡፡የሃገር መሪን ለመግደል
መሞከር መፈንቅለ መንግስት ሲሆን ግለ ሰቦችን መግደል ደሞ ከግበረ ሽበራ ተግባር ይቆጠራል፡፡እንደኛዎቹ ዓይነት ፓርቲዎች በዚሁ
ተግባር መሳተፍ የለባቸውም፡፡የከተማው የትጥቅ ትግል ሐሳብ ፓርቲው ይዞት ከተነሳው አቅጣጫ ያፈነገጠ ነው፡፡ ፓርቲው በጥፋት መንገድ
ላይ እየተራመደ ይገኛል…›› የሚል ነበር፡፡ወቅቱ የስልሳዎቹ አብዮት ሙሉ በሙሉ ተቀጣጥሎ የሚንቀለቀልበት የዕብደት ጊዜ ነበርና
የእነ ጌታቸው ማሩ ጥልቅና ዘመን ተሻጋሪ እይታ ማንም ሊረዳው አልቻለም ነበር፡፡ጌታቸው ተቀባይነት አላገኘም…እናም በአንጃነት ተፈርጆ
ተገደለ፡፡ሆኖም ግን የጌታቸው ማሩ ግድያ የግለ ሰብ ግድያ አልነበረም…የሃገርና የትውልድ ግድያ እንጂ፡፡
መቼስ የሰው ልጅ ከእንስሳት የሚለው ማሰብ እስከ ቻለ ድረስ ብቻ ነው፡፡ማሰብ ካቆመ፣ ሁሉንም
ነገር የሚያከናውነው በደመነፍስ ነው… መነጋገር… መደማመጥ…ሐሳብ ለሐሳብ መለዋወጥ አይታሰቡም፡፡በቃ! ዓይኖቹን ጨፍኖ ወደፊት ነው…ከፊት
ለፊቱ ማንኛውም ጋሬጣ ቢያሰናክለው አንዴም ዧ! ብሎ መውደቅ ነው አልያም ዘሎ መለፍ፡፡የእነ መርክስ የእነ ምንትስ፣ እነ ለሊን
የእነ ምናምን… የእነ ቼ ጉቬራ የእነ ደንቃራ፣ የእነ ሆ ቺ ሚኒ የእነ ጅኒ የዝላይ ‹‹ጥበቦች›› የዘመኑ ብቸኛ መንዶች ያደርጋል፡፡የስልሳዎቹ
እብዶች ጋሬጣውን መዝለል አልቻሉም…ዧ! በለው ወደቁ፡፡እናም ያኔ ‹‹ከኛ ወድያ ተራማጅ ላሳር ነው›› በሚል ጭፍን አካሄድ ሃገራችንም
ከእነሱ ጋር ዧ! በላ ወደቀች… ተሸመደመደች… ‹‹ከድጡ ወደ ማጡ›› እንዲሉ፣ ያቺ በቋፍ ላይ የበረችው ኢትዮጵያ ወደ ባሰው መቀመቅ
ወረደች፡፡ልጆቿ እንደ ቅጠል ረገፉ…የጦር አውድማ ሆነች፡፡ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምስራቅ እስከ ምእራብ ድረስ በደም ማዕበል ተናጠች፡፡የእነ
ፈረንሳይ፣የእነ ራሽያ ነፍሰበላ አውዳሚ አብዮቶች አማራጭ አልባ አዲስ ግኝቶች ተባሉና በሃገረ ኢትዮጵያ እንደ አዲስ ተደገሙ፡፡
የታሪካዊ ጠላቶቻችን የምንጊዜም ፀሎት ሰመረ፡፡እናም በደስታ ብዛት ደረታቸውን እየደለቁ ጭራሮና
ጋዝ ማቀበሉን ስራየ ብለው ተያያዙት፡፡ሁለት ወንድማማቾች ተጣልተው አንገት ለአንገት ሲተናነቁ እያዩ ‹‹ተው ጋላ›› ብለው እንደ
መገላገል፣ ለአንዱ ሽጉጥ ለሌላኛው መተረየስ በማቀበል አፋጇቸው፡፡ወንድም ወንድሙን ገድሎ የስልጣን ባለቤት ሲሆን የሟቹ ወንድም
ቤተሰቦችን የሚያፅናኑ በመምሰል ሌላ እልቂት…ሌላ ፍጅት… ሌላ ውድመት ለማቀጣጠል ቆርጠው ተነሱ፡፡የያኔው የጥፋት ምክንያቶች
‹‹ምርጫ የለም፣ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶቻችን አልተከበሩም…››የሚሉ ነበሩበት፡፡አሁን ደሞ ‹‹ምርጫ አለ…ነገር ግን እኛን
የስልጣን ባሌቤት የማያደርግ በመሆኑ ለይምሰል ነው…›› እናም ቅድመና ድህረ ምርጫዎች ‹‹የቀለም አብዮት ማቀጣጠያ ክብሪት መሆን
አለባቸው›› ተባለ፡፡ታድያ ዛሬ ምርጫ በተቃረበ ቁጥር ሃገራችንና ህዝቦቿ የለውጥ ተስፋ ከመተንፈስ ይልቅ የባሰውን እየመሸ ይጨልምባቸዋል፡፡የበጎ
ለውጥ መሳርያው ሃገራዊ ምርጫ ሃገርና ህዝቦቿ አደጋ ውስጥ የሚከት የጥፋት ደመና ወደ መሆን ተቀይሯል፡፡
ድሮ ትምህርት ለመቅሰም የተላኩት ኢትዮጵያውያን ያለ ምንም ማንገራገር በማርክሲዝም…ሌኒኒዝም
መጤ እምነቶች ተጠምቀው ‹‹ከጳጳሱ በላይ ካቶሊክ›› ሆኑና ሃገራችንን አርማጌዶን አደረጓት፡፡ዛሬ ደሞ ‹‹የቀለም አብዮት›› በሚሉት
‹‹ሰላማዊ ዓመፅ›› ተጠምቀው በየቀኑ፣በየወሩና በየዓመቱ የዓመፅ ስብከቶችን በማስተጋባት ላይ ተጠምደው ይገኛሉ፡፡ለሃገር አንድነትና
ሰላም ሲባል ዓመፅ!…ህገ መንግስቱን ለማክበር
ሲባል ዓመፅ!...ለሃገር እድገትና ብልፅግና ሲባልም ዓመፅ፡፡የእኛ ነገር ዓመፅን በዓመፅ ነው…እሾህን በእሾህ ነው…ጥፋትን በሌላ
ጥፋት፡፡ እንደ ግመል ሽት ሁል ጊዜ የኋሊት ሩጫ…ከድጥ ወደ ማጥ፡፡‹‹በቃ!...ድምፃችን ይሰማ!...የምንትሶች ድምፅ...ሆይ…ሆይ…
አካኪ ዘራፍ!!!›› በህገ መንግስቱ መሰረት በሰላም ለመታገል ቃል የገባውን ‹‹በቃ የሰላም መንገድ አበቃ›› ብሎ ጦርነት ያወጀውም
እኩል ይሸልላል፡፡የሁሉንም ማዳረሻ ስልጣንና ስልጣን ብቻ ነውና፡፡
ያ የስልሳዎቹ ጅኒ ዛሬም ድረስ እንደ እንዝት የሚያሾረው ‹‹መንግስት›› ተብየም እየለቀመ ወደ ቃሊቲ፡፡ ቃሊቲ የገቡትን
ለማስፈታት ሌላ ዓመፅ…ሌላ ግርግር…ሌላ ድምፃችን ይሰማ…ሌላ ትእግስታችን አለቀ…በቃ! ሌለ አገሯ ዘለል…ቀረርቶ… ‹‹እንትና የኛ
የዘመኑ ወደረ የለሽ ጀግና…የለምንም ቅድመ ሁኔታ ይፈታ! ምንትስ ትፈታ…ታ…ታ…ታ›› ህገ መንግስት የለ…ህገ እግዚአቢሄር የለ…ተደረማምሰው
በህገ አራዊት…ብህገ መንጋ መተካት፡፡ይህንን ሁሉ የሚደረገው ‹‹ለሃገር ፍቅር ሲባል›› ነው፡፡አሳዛኝ ሃገር!!!
ዓመፆች ሌላ እልፍ አእላፍ ዓመፆችን እየወለዱ… ሃገር ከትርምስ ወደ ትርምስምስ እያመራች ህገ መንግስቱ መቼ ይከበራል?
የህግ ተቋማት…ፍርድ ቤቶች…የፖሊስ…የመከላከያ ሃይሎች…የአገር ቀጣይነት ያለው ሰላምና ብልፅግና ከቶ እንዴት ይታሰባል? እስከ መቼ
ነው የአፍርሶ መገንባት ጨዋታው የሚዘልቀው? በመጠቃቃትና በደመነፍሳዊ ግብረ መልስ እየተጫረስን የምንቀጥለው እስከ መቼ ድረስ ይሆን?
ከ40 ዓመታት በፊት የተቀጣጠለው አብዮት የበላውን በልቶ ሃገራችንንና ህዝቦቿን ‹‹ሉሲ›› አስመስሎ አለፈ፡፡ ያለው ዓመጽ ከ31
ዓመታት በኋላ ተመልሶ ከ10 ዓመታት በፊት (97) ደሞ ሌላ ዓመፅ ወለደ…ወደ 200 የሚጠጉ ወጣቶች በአጭሩ ተቀጩ…ንብረት ወደመ፡፡
አሁን ደሞ ሌላ ዓመፅ ለማስነሳት ሽር ጉድ እያሉ ይገኛሉ፡፡ጌታቸው ማሩ እንዳለው የሄ ቅጥ አምባሩ የጠፋበት እብደት ነው…ውጤቱ
ምን ሊሆን እንደሚችል እያወቁ በአንድ ነገር ላይ ሙጭጭ ብሎ ነጋ ጠባ መቸክቸክ፡፡እናም የተለየ ውጤት መጠበቅ…
ወደ ተነሳሁበት ጉዳይ ስመለስ፣ የአሁኑ የአንድነትና የሰማያዊ ፓርቲዎች አካሄድ ‹‹ያ ትውልድ››
ከተከተለው የጥፋት መንገድ የሚለው ነገር የለም፡፡ዋና ዓላማው የሃገራችን ፈርጀ ብዙ ችግራችን አጥንቶ ዘላቂና ስር ነቀል መፍትሔ
ማምጣት ሳይሆን ጉልቻን በጉልቻ መቀየር ብቻ ነው፡፡ ገዢውን መንግስት በዓመፅ አስወግዶ ሌላ አምባገነናዊ ስርዓት መመስረት፡፡ዞን9ኞች
የእዚሁ አላማ ተላላኪዎች ናቸው፡፡ባለወንጭፎቹ የስልሳዎቹ ትርፍራፊዎች ሲሆኑ ጠጠሮቹ ደሞ ዞን ዘጠኝና መሰሎቻቸው ናቸው፡፡እነዚህ
ልጆች ቃሊቲ ድረስ እየተመላለሱ በእነ እስክንድር ነጋና ርእዮት አለሙ የአብዮት ፈንጅ እንዴት እንደሚጠመድና እንዴት ማፈንዳት እንደሚቻል
የተማሩ አፍቃሬ ‹‹ቀለም አብዮት›› ናቸው፡፡
የፌስቡክ መንጋ ግን…ዞን ዘጠኞች ለምን እንደታሰሩ ምንም ሳያውቅ ‹‹ሃሳባቸው በነፃነት ስለገለፁ
ከሆነ…›› እያለ በጥንቆላ ይወነጅላል…‹‹ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ›› እንዲ ለቀቁለት ይደነፋል…ልክ በእነ ኢህአፓ፣መኢሶንና ደርግ
የታሪክ አተላዎች እንደሚመራው መርዘኛው ድያስፖራ…ታፔላ መሸከም ብቻ ነው የቀረው…ለነገሩ የሌላሰው ፎቶ መጠቀሙ በእርሱ ቤት ታፔላ
መሸከሙን ነው፡፡በ60ዎቹ ‹‹ያለ ቅድመ ሁኔታ ይገደል…አብዮታዊ እርምጃ ይፋፋምበት…ነፃ እርምጃ ይወሰድበት አሁን…›› እየተባለ
የአንድ ዘመን ትውልድ አለቀ፡፡አሁን ደሞ ወንጀለኛውም ምኑም ‹‹ያለ ቅድመ ሁኔታ ይፈታ…››አድሮ ቃርያ የሆነ ትውልድ፡፡በጣት የሚቆጠሩ
አርቆ አሳቢዎች፣ ነገርየው እስኪጣራ ተረጋጉ ቢሉ የዘለፋ ዘመቻ ይካሄድባቸዋል…ያለ የሌለ ስም ይለጠፍባቸዋል፡፡የተለየ ሐሳብ የሚያራምዱ
ወገኖች በጭፍን ይዘለፋሉ…ይፈረጃሉ፡፡እናም መንጋው በነፃነት ስም የህግ ሂደቱን ይሽራል፡፡
ዞን ዘጠኞች ግን ድሮም እስር ቤት ላይ እንደነበሩ የሚያምኑ የሐሳብ እስረኞች ናቸው፡፡ይህን
የምንረዳው ደሞ የብዱኑ ስም ምን ማለት እንደሆነ ስናውቅ ነው:: ደሞ ሰሞኑን የታሰሩት ዞን ዘጠኞች ብቻ አይደሉም የሰማያዊ ፓርቲ ከፍተኛበለስልጣናትም ይገኙበታል፡፡እናም ነገርየው ‹‹ስለሚያገባን እንጠሙራለን›› ከሚሉት ጉዳይ በላይ የተለጠጠ የፖለቲካ ጨዋታ ነው፡፡ያው
የሃገራችን የፖለቲካ ጨዋታ ደሞ ምን እንደሚመስል ይታወቃል፡፡የፌስቡኩ መንጋ ግን ይህን አያውቅም ወይም እስኪያውቅ ደረስ አይታገስም…መንጋ
ነውና ከመንጋው የተለየ አስተሳሰብ አያራምድም፡፡ለነገሩ የሚያደርገውን ብያውቅ ንሮ እንዲሁ በደመነፍስ አይደነፋም ነበር፡፡
በኦሮምያ በሚገኙ የኒቨርሲቲዎች ያለው የተማሪዎች ዓመፅ ሰማያዊ ፓርቲ ከጠራው የእሁዱ( ሚያዝያ 19፤2006)
‹‹ሰላማዊ ሰልፍ›› ጋር ተዳምሮ ምን ዓይነት ውጤት እንደሚያመጣ ለሚገነዘብ ሰው ግን ይሄ የፌስቡክ ሆይ ሆይታ የደመነፍስ ጭሆት
መሆኑን ያውቃል፡፡እነ ዙከርበርግ በፌስቡክ አማካኝነት ጆሯቸው ብትቆርጣቸው የማይሰሙ ባለፀጎች ሆኗል…ራሳቸውን አክብረው ሃገራቸውን
አክብሯል፡፡ሐበሻ ግን ከዚሁ ተምሮ እራሱንና ሃገሩን ከማበልፀግ ይልቅ ለጥፋት ይጠቀምበታል፡፡ምስኪን ሐበሻ!…ሁለመናው ኩርምትምት
ያለ ያጣ የነጣ ድሃ መሆኑን እንኳን የማያውቅ የአስተሳሰብ ድሃ፡፡ከታሪካዊ ስህተቱ ተምሮ የማይለወጥ…ታጥቦ የማይፀዳ ሽንፍላ ነገር፡፡

No comments:
Post a Comment