Saturday, September 27, 2014

ህወሓት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የፈፀማቸው ታሪካዊ ስህተቶች



ህወሓት በኢትዮጵያና ህዝቦችዋ ላይ ብዙ ታሪካዊ ስህተቶች የፈፀመ ቢሆንም ዋናው ግን በድርጅቱ የነበሩ( አሁንም ብዙዎች አሉ) አድራጊ ፈጣሪ ባለስልጣናት ‹‹ኤርትራውያን ናቸው›› ለማለት በሚያስደፍር ሁኔታ ሃገራቸውንና ህዝባቸውን ችላ በማለት ለኤርትራ ፍላጎቶችን ሽንጣቸው ገትረው በመከራከር ኢትዮጵያችን ያለባህር በር ማስቀረታቸው ነበር፡፡አንዳንዶቹ ‹‹ኢትዮጵያን ያለ ወደብ ያስቀረናት ታሪካዊ ህግጋቶችን ባለማወቃችን ነበር›› በማለት ፀፀታቸውን እየገለፁ ይገኛሉ፡፡ስህተቶች መስራታቸውን አምነው፣ እነዝያ ስህተቶች ለመድገም ባለፈለጋቸውም የነበራቸው ስልጣንም ሆነ ድርጅቱ በፍቃዳቸው ለቀው መውጣታቸው የሚታወስ ነው፡፡
ከእነዚህ አንጋፋ የድርጅቱ መሪዎች አንዱ ገብሩ አስራት ነው፡፡ገብሩ ከ1971 እስከ 1993 ዓ.ም ድረስ የህወሓት ማእከላይ ኮምቴና ፖሊት ቢሮ አባል እንዲሁም የኢህአዴግ የስራ አስፈፃሚ አባል በመሆን መስራቱ ይታወቃል፡፡በተጨማሪም ከደርግ ውድቀት በኋላ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 1993 ዓ.ም ህወሓት ለሁለት እስኪሰንጠቅ ድረስ የትግራይ ክልል ፕረዚደንት ሆኖ አገልግሏል፡፡አሁን በትግራይ የሚገኙት የትእምት ፋብሪካዎችም ሆነ ድርጅቶች(አልመዳ፣ዓዲ ግራት መድሐኒት ፋብሪካ፣መስፍን እንዳስትርያል እንጂኔሪንግ፣ መሰቦ ስሚንቶ ፋብሪካ…)፣መቐለ ዩኒቨርሲቲ፣ ዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል፣ሁሉም ለማለት በሚቻል መልኩ የተቋቋሙት ገብሩ የትግራይ ክልል ፕረዚደንት በነበረበት ወቅት ነው፡፡ከ93ቱ የድርጅቱ መከፋፈል በኋላ ግን ‹‹የጎልጎል ራያ ፕሮጀክትን›› ጨምሮ በጅምር የቀሩ ብዙ ፕሮጀክቶች ዛሬም ድረስ ብዙ የትግራይ ተወላጆች የሚቆጩባቸው ናቸው፡፡
ከክፍፍሉ በፊት ከህወሓት ቁልፍ ሰዎች ጋር እኩል ይጠቀሱ የነበሩት እነ ተወልደ ተወልደማርያም፣አበበ ተክለሃይማኖት፣ፃድቃን ገብረትንሳኤ፣አለምሰገድ ገብረአምላክ ወዘተ በመገናኛ ብዙሓን የተረሱ ይመስላሉ፡፡በተለይ ተወልደና አለምሰገድ የት እንደገቡ አይታወቅም፡፡ምናልባት ግን ከክፍፍሉ ጋር ተያይዞ ህወሓት ስማቸውን ለማጥፋት ባደረገው ዘመቻ ተስፋ ሳይቆርጡ አልቀሩም ባይ ነኝ፡፡ገብሩ፣አረጋሽና ስየ ግን ከፖለቲካው ዓለም ሙሉ በሙሉ አልጠፉም፡፡ከሁሉም ግን ዛሬም ድረስ አንጋፋነቱ ያልደበዘዘው ገብሩ አስራት ነው፡፡ዓረና ትግራይን መስርቶ በመምራት አሁን ላለችበት ደረጃ ካደረሱ ሰዎች ግንባር ቀደም ነው፣ አቶ ገብሩ፡፡ሰሞኑን ደሞ ‹‹ሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ›› የሚባል 524 ገፅ ያለው መፅሐፍ ለአንባብያን በማበርከት እውነተኛ ታጋይነቱን አስመስክሯል፡፡

Wednesday, September 17, 2014

ለምን እፅፋለሁ?




በአጭሩ፣እኔ የምፅፈው  ሰው ስለሆንኩ ነው፡፡ሰው በመሆኔ ብቻ ሐሳቤን በነፃነት የመግለፅ ሰብአዊ ፍላጎት አለኝ፡፡ ፖለቲካ፣ ሃይማኖት፣ ባህል፣ ብሔር ወዘተረፈ ኋላ የሚከተሉ  ማህበራዊ ዳራዎች ናቸው፡፡ማንም ለማስደሰት ወይም ለማበሳጨት አይደለም የምፅፈው፡፡ ለእንጀራ፣ ለሹመት፣ለአጉል ሙገሳም ፅፌ አላውቅም፣ ለወደፊቱም እቅድ የለኝም፡፡ብፈልግም ይቻላል ብዬ አላምንም፡፡
ማንኛውም ሰው  የሆነ ድምፅ ስምቶ፣ የሆነ ፅሑፍ አንብቦ ወይንም የሆነ ምልክት አይቶ የሚደሰተውም ሆነ የሚበሳጨው ከአእምሮው በሚመነጨው ሁካታና ጭኾት እንዲሁም ሽብር ነው፡፡
የእነዚህ ነገሮች ትርጉም ሊኖርም ላይኖሩም የሚችለው ጭንቅላቱ ከመቃኘትና አለመቃኘት የሚመነጭ ብቻ ነው፡፡በጭንቅላቱ የተቃኘው ትርጉም መጥፎ ከሆነ መጥፎ ነው ብሎ ነው የሚያምነው፤ ትርጉሙ ጥሩ ከሆነ ደሞ ጥሩ ነው ብሎ ያምናል፡፡ምስሎቹ፣ ድምፆቹ፣ቃላቱ እንዲሁም ቅርፃ ቅፆቹ ግን በራሳቸው ትርጉም የላቸውም፡፡ትርጉም የሚሰጣቸውም ሆነ የሚነፍጋቸው ጭንቅላትህ ነው፡፡ ጭንቅላትህ ትርጉም የሚሰጣቸው ደሞ ከተገራባቸው ሁኔታዎች አንፃር ነው፡፡

ለምሳሌ ‹‹የለም›› የሚለው ቃል እንውሰድና ትርጉሙን ከሁኔታዎች አንፃር እንየው፡፡የለም ማለት ጥሬ ቃሉ ብቻ ወስደን ብንተረጉመው የአንድ ነገር አለመኖርን ያመለክታል፡፡ አንድ ሰው‹‹ባንዴራችን አረንጓዴ፣ብጫ፣ ቀይ በመሆኑ የኦርቶዶክስ እምነት ብቻ ያንፀባርቃል›› ሲል፣ ሌላው ‹‹የለም እነዚህ ቀለሞች በክርስትኖች አልተፈጠሩም፤ ነበሩ ለወደፊቱም ይኖራሉ፡፡የኦርቶዶክሶች እምነት የሚያንፀባርቅ ቢሆን ኑሮ ባንኛውም የኦርቶዶክስ ቤተክርስትያንም እነርሱ በሚበዙባቸው ሃገሮች የሚገኙት ባንዴራዎች አረንጓዴ፣ብጫና ቀይ ይሆኑ ነበር፡፡ ግን አይደሉም፡፡ የራሽያ ባንዴራ ብጫና አረንጓዴ ቀለም የለውም›› ሊል ይችላል፡፡አሁን ‹‹የለም›› ሲል አይደለም፣ ተሳስተሃል ማለቱን ነው፡፡

እስኪ በሌላ ሁኔታ ደሞ እንየው፡፡ ሰው ነህና ትበላለህ፣ትጠጣለህ፡፡ ከዛም መተንፈስ ተፈጥራዊ ስጦታህ ስለሆነ ሽንት ቤት ሄደህ መፀዳዳት ያስፈልገሃል፡፡ሽንት ቤቱ ተዘግቶ አገኘኸው፡፡ኳ..ኳኳኳ…ኳኳኳ እርገህ ታንኳኳና ‹‹ሰው አለ?›› ብለህ ትጠይቃለህ፣ ‹‹የለም›› የሚል መልስ አዳምጠሃል፡፡ያኔ በሩን ከፍተህ አትገባም፡፡ ትጠብቃለህ ወይም አማራጭ ካለ ሌላ ሽንት ቤት ፍለጋ ትሔዳለህ፡፡ ምክንያቱም ‹‹የለም›› ማለት ‹‹አለ›› መሆኑን ስለሚገባህ ነው፡፡በልምድ የምታውቀው ግን የለምና አለ ተቃራኒዎች መሆናቸውን ነው፡፡

ሌላ ምሳሌ ልንገርህ፤‹‹እናንተ ሸክም የከበዳችሁ ወገኖች ሆይ፣ ወደእኔ ኑ›› የሚለው ጥቅስ ወይም አረፍተ ነገር ለክርስትያኖች ምንጩ መፅሐፍ ቅዱስ እንደሆነ ብቻ ነው የሚገባቸው፡፡ለእኔ ግን በመፅሐፍ ቅዱስ ስለመቀመጡ ትርጉም አይሰጠኝም፡፡ ይበልጥ ትርጉም የሰጠኝና ለብቻየ ከትከት ብዬ እንድስቅ ያደረገኝ በአንዱ ዩኒቨርሲቲ በሚገኘው ሽንት ቤት በር ላይ ተፅፎ ሰነበው ነው፡፡ጥቅሱ ያሽንት ቤት የፃፈው ባይሆንም ለእኔ ግን በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሳነበውና በሽንት ቤቱ በርላይ ተፅፎ ሳነበው ልዩነቱ ሰማይና ምድር ነው፡፡ለምን ብትል በጭንቅላቴ የተቀረፀው ሽንት ቤት እውነትም ሸክም የከበዳቸውን ተቀብሎ እረፍት እንደሚሰጣቸው ስላሳመንኩት ነው፡፡በልቶ ጠጥቶ ሽንት ቤት ባሰኘኝ ጊዜ የሚሰማኝ ሸክም ወደር የለውም፡፡
አየህልኝ ወገኔ? እኛ የፈጠርናቸው ነገሮች እኛ እንደፈለግነው ወይም እንደተቃኘነው ነው የምነተረጉማቸው፡፡የቻይንኛ ቋንቋ ፊደሎች ላንተ የተበተነ ሳር መስለው ሊታዩህ ይችላሉ፡፡የማታውቃቸው ፊደሎች፣ቅርፃ ቅርፆች፣ድምፆች፣ምስሎች እንዳለም ለንተ ስሜት አይሰጡም፡፡ስሜት እንዲሰጡህ ተደርገህ ስላልተገራህ፡፡አዲስ ቋንቋ፣ ባህል፣ ሃይማኖት፣ ርእዮተ ዓለም፣ቴክኖሎጂ፣ ቀመር ወዘተ የምትማረው ታድያ ስሜት እንዲሰጡህ አእምሮህ መቃኘት ስላለበት ነው፡፡
ለዚህም ነው ማንም ለማስደሰትም ሆነ ለማበሳጨት ብዬ የማልፅፈው፡፡የምፅፈው ሐሳቤን ለመግለፅ ብቻ ነው ያልኩበት ምክንያትም እነዚህና መሰል ቅኝቶች የተለያየ ትርጉም እንዳላቸው ስለማውቅ ነው፡፡በመሰረቱ ግን አንድ ሰው የሚደሰተውም ሆነ የሚበሳጨው በአስተሳሰቡ ብቻ እንጂ በሌላ ምክንያት አይደለም፡፡በዛፍ ላይ ተንጠልጥሎ የሚኖር ሰው ዛፉ በተንቀሳቀሰ ቁጥር መረበሹ አይቀሬ ነው፡፡ደስታውም ሆነ ብስጭቱ የሚቀኘው በአየር ፀባዩ ይሆናል፡፡ንፋሱ ሲበረታ ብስጭቱም ይበረታል፣ ንፋሱ ሲረግብ ደሞ ረገብ ይላል፡፡ዝሮ ዝሮ ግን ኑሮውና ስሜቱ ሁሌም በጊዝያዊ ብስጭትና ደስታ መካከል ዥዋ ዥዌ እያለ ነው የሚኖረው፡፡
መድሐኒቱ ደሞ ከተንጠላጠለበት ዛፍ ወርዶ ርሱን ችሎ መቆም ብቻ ነው፡፡ራሱን ችሎ ለመቆም የበቃ ሰው ግራም ነፈሰ ቀኝ አይገደውም፡፡ምክንያቱም መሰረቱ ዛፍ ወይም ሌላ ነገር አይደለምና፡፡የሚበሳጨውም ሆነ የሚደሰትበት ምክንያት አለው፡፡ምክንያቶቹ ደሞ ከውስጣዊ ማንነቱ እንጂ ውጫዊ ከሆኑ ነገሮች አይመነጩም፡፡አህዮች ሲያናፉም ሆነ ሲራገጡ አይቶ አይበሳጭም፡፡አሳሞቹ ብዙ ሲበሉ አይቶም አይበሳጭም፡፡በጎቹ ዝም ስላሉም አይበሳጭም፡፡ምክንያቱም አህዮቹ ቢያናፉም ባያናፉም፣ ቢራገጡም ባይራገጡም፤ አሳሞቹ ቢበሉም ባይበሉም፣ በጎቹ ባዓዕ ቢሉም ባይሉም ጉዳዩ አይደለም፡፡
ሁለመናው የተቃኘው የእኔ ብሎ በተቀበላቸው፣ከሰብአዊ ምርሆቹና እሴቶቹ ጋራ ቁርኝት ባላቸው ነገሮች ብቻ ነው፡፡እነ እንትና ምንም ይሁኑ ምን፣ ከይትም ይምጡ፣ ወዴትም ይህዱ ስሜት አይሰጡትም፡፡

ለማጠቃለል ያህል፣ አንድ ፅሑፍ ከፍም አለ ዝቅ፣ አጠረም ረዘመ፣ስሜትህ ቢነካውም ባይነካውም ትርጉሙ ከውስጥህ ፈለገው እንጂ ከፃሐፊው ጋር አታገናኘው፡፡ዘፈንም ሆነ ባዶ ጭሆት በሰማህ ቁጥር አትረበሽ፣ አትበሳጭ፡፡ዘፈነም ጨሆ፣ ፃፈም አነበበ፣ መጣም ሄደ አንተን እያሰበ አይደለም የሚያከናውናቸው፡፡ስሜቱ ፈንቅሎት ነው፡፡አንተ በልተህ ጠጥተህ ፍኛህ ሲወጠር ወደ ሽንት ቤት አንደምትሮጠው ሁሉ ሌላውም አንብቦና አስቦ ዝም ማለት ሲያቅተው እንደአቅምቴ መፃፍ ይሞክራል፤ ስሜቱን ለመግለፅና ለመተንፈስ፡፡አንተ ትርጉም ካላበጀህላቸው ትርጉም የላቸውምና፡፡









Sunday, September 14, 2014

በጋምቤላ ክልል የሚገኙ የትግራይና የወሎ ተወላጆች ማረፍያ ያጣች ወፍ ሁኗል




ግፉ ለዘመናት ሲንከባለል የመጣ ነው፡፡ በ1977 ዓ.ም ትግራይና ወሎ በድርቅ ተመትተው የሚላስ የሚቀመስ ጠፋ፡፡ መቐለና ደሴ ይቆጣጠር የበረው አምባገነናዊው የደርግ መንግስት ከዓለም አቀፍ ለጋሾች ያገኘው እርዳታ በአብዛኛው ለጦር መግዣ ብያደርገውም የተወሰነውን በከተሞቹ ለተሰበሰበው ህዝብ ያከፋፍል ነበር፡፡ ይህ ተግባር በጠኔ ለሚሰቃየው ህዝብ መልካም ዜና ነበር፡፡ በመሆኑም ከተለያዩ የገጠራማው አከባቢዎች የተመመው ህዝብ ከተሞቹን ማጥለቅለቅ ጀመረ፡፡

የደርግ መንግስት ግን የሚበላ መስጠቱን ትቶ እንደ ደሮ እያነቀ ወደ ጋምቤላ ጫካዎች ይወረውራቸው ገባ፡፡ጋምቤላ ክልል ለም ቢሆንም በጣም ሙቀታማ ስለሆነና በጫካዎቹ የሰፈረው ህዝብ ህክምና ሰለማያገኝ በወባና ተዛማጅ በሽታዎች ረገፈ፡፡አይቶትም ሆነ ሰምቶት በማያውቀው አከባቢ በግዳጅ የሰፈረው ህዝብ አከባቢውን ለመላመድ ብዙ መስዋእትነት ከፍሏል፡፡እንደገና ጎጆ መቀለስና ኑሮውን ማስተካከል ነበረበት፡፡

ያ ሁሉ ችግር አሳልፎ ለዛሬ የበቃ፡፡ሆኖም ግን ከ26 ዓመታት በኋላ ‹‹በእድ ነህና አከባቢያችንን ለቀህ ሂድ›› እየተባለ ይገኛል፡፡‹‹ፈሪሖምያ ናብ ኦም ይድይቡ እሞ ነብሪ ይፅንሖም›› ነው ነገሩ…‹‹ፍርቶ ዛፍላይ ቢወጣ በዛፉ ላይ ነብር ጠበቀው›› እንደ ማለት ነው፡፡የትግራይና የወሎ ህዝብ ተፈጥሮ ጨክናበት፣ የሚላስና የሚቀመስ አጥቶ በርሃብ እንዳይሞት ፈርቶ ነበር ደርግ ወደ ሚቆጣጠራቸው ከተሞች የገባው፡፡ ደርግ ሆየ እንደ ጫጩት እያፈነ ወደ ጋምቤላ ጫካዎች ጣላቸው፡፡ዛሬ ደሞ የጋምቤላ ተወላጆች ‹‹አከባቢያችን ለቃችሁ ካልወጣችሁ ሞት ይገባቹኋል›› ብለው በነፍጥና በገጀራ እየገደሏቸው ይገኛሉ፡፡

መገዳደሉ ከተጀመረ ቆይቷል፡፡የአከባቢው ተወላጆች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሰፋሪዎቹን(የትግራይና የወሎ ተወላጆች) መግደል ስራየ ብለው ከተያያዙት ብዙ ዓመታት ተቆጠሯል፡፡ለአከባቢው ባለስልጣናት አቤት ብለው ሰሜ ጀሮ እንዳላገኙ ነው የሚናገሩት፡፡ትእግስታቸው ተሟጥጦ ያለቀው ሰፋሪዎችም አልፎ አልፎ ደም መመለስ መጀመራቸው ይነገራል፡፡ይህን መሳይ ድርጊቶች ሲፈፀሙ የአከባቢው ታጣቂዎች፣ ፖሊሶችና ባለስልጣናት ‹‹እናንተ ወፍ ዘራሾች ደሞ በሃገራችን ሰፍራችሁ መግደል አማራችሁ?›› እያሉ ፋዳቸውን ያበዙባቸዋል፡፡

የአሁኑ ግጭት የተነሳው ግን መዠንግሮቹ ባለፈው ሳምንት(ሮብ ማታ) እንዲት እርጉዝ ሴት ቤት ዘግተው በማቃጠላቸው መሆኑን ይነገራል፡፡ይህንን ግፍ ይዘው ለአከባቢው ሐላፊዎች አብየት ለማለት የሄዱት ሰፋሪዎች ‹‹በጥባጦቹ እናንተው ናችሁ›› ተብለው ሲታሰሩ ነበር ቁጣቸው የገነፈለው፡፡ የእንቁጣጣሽ በዓል ለእነሱ በዓል አልነበረም…ቅልጥ ያለ ጦርነት እንጂ፡፡ከ10 በላይ ቀበሌዎች የተሰባሰቡ ህፃናት፣ሴቶችና ሽማግሌዎች ቴፒ ከሰፈሩ ብዙ ቀናት አስቆጥሯል፡፡ቴፒ በሚገኙ አብያተ ክርስትያናት፣ትምህርት ቤቶች እንዲሁም በአየር ማረፍያው ሜዳ ላይ ሆጭ ብለው ይገኛሉ፡፡ምግብ የለም መጠለያ የለም!

ትናንት ማታ ፌደራል ፖሊስና መከላከያ ወደ አከባቢው በመድረሳቸው ከቀያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ወደየመጡበት መመለስ ጀምረው ነበር፡፡ጦርነቱ እንደገና በማገርሸቱ ግን ወደ ቴፒ ተመልሷል፡፡በቅርቡ አንድ ትራፊክ ፖሊስና የፍርድ ቤት ሐላፊ ተገድሏል፡፡ገዳዮቹ የክልሉ መንግስት ያስታጠቃቸው ፖሊሶች እንደሆኑ ነው የሚነገረው፡፡

በስልክ ያነጋገርኳቸው የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ አስተማሪዎች የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ለእረፍት ወደየ አከባቢያቸው ባይበተኑ ኑሮ ግርግሩ ይባባስ እንደነበር ገልፀውልኛል፡፡ሆኖም ግን የመገናኛ ብዙሃን ሽፋን ማግኘት ይችል ነበር ባይ ናቸው፡፡


ከቴፒ አየር ሜዳ ደውየ ያነጋገርኳቸው ወገኖች የመከላከያ ሰራዊት አባላት‹‹አይዟችሁ፣ አሁን ይረጋጋል፣ወደየቤታችሁ ትመለሳላችሁ›› እያሉ ሊያረጋጉን ቢሞክሩም ቁጥራቸው በጣም አናሳ በመሆኑ ግጭቱ ሊያረጋጉት እንዳልቻሉ ነግረውኛል፡፡በተለይ የክልሉ ፕረዚዳንትና የፌደራል ፖሊስ ሐላፊዎች ወደ አከባቢው መጥተው የነበረ ቢሆንም ለችግሩ መፍትሔ ሳያበጁለት መመለሳቸው እንዳበሳጫቸው ነው የገለፁልኝ፡፡

Saturday, September 13, 2014

ሰበር ዜና #Breaking_News


በጋምቤላ ክልል ጎደሬ ወረዳ በተነሳው ግጭት ዘጠኝ ባለስልጣናት ጨምሮ ብዙ ዜጎች ተገድሏል

የአማራና የትግራይ ተወላጆች እየተጨፈጨፉ ነው

በጋምቤላ ክልል፣ጎደሬ ወረዳ መጢ ከተማና አከባቢው በደርግ ዘመን የሰፈራ ፕሮግራም በክልሉ የሰፈሩ የአማራና የትግራይ ተወላጆች ‹‹አከባቢያችን ልቀቁ›› በሚል ሰበብ እየተጨፈጨፉ ነው፡፡አከባቢያችንን ልቀቁልን ባዮቹ አማፂዎች የህፃናትና ወጣቶች አንገት በገጀራ እንደሚቀሉ ምንጮች አሳውቀዋል፡፡ጨፍጫፊዎቹ የአከባቢው ባላባቶች ነን ባዮች ሲሆኑ የታጠቁ ፖሊሶችና ማልሻዎችም እንደሚገኙበት ታውቀዋል፡፡

የፌደራል ፖሊስ ትናንት የደረሰ ቢሆንም በጣም ዘግይቶ በመድረሱ የዜጎች ህይወትና ንብረት ሊታደግ አልቻለም፡፡በአሁኑ ሰዓት የፌደራል ፖሊስና መከላከያ ግርግሩን ለማብረድ ወደ አከባቢው ቢንቀሳቀሱም ቀውሱን ሊቆጣጠሩት እንዳልቻሉ ነው የሚነገረው፡፡ አብዛኛዎቹ የአማራና የትግራይ ተወላጆች ቤትና ንብረታቸውን ጥለው ከ19 ኪ.ሜ በላይ በእግራቸው በመሸሽ በደቡብ ክልል ቴፒ ከተማ እንደሚገኙ ምንጮቼ ገልፀውልኛል፡፡


እነዚህ ዘጎች ቤትና ንብረታቸው ጥለው ለመሸሽ በመገደዳቸው ያለ ምግብና መጠለያ በቴፒ አየር ሜዳ ላይ ይገኛሉ፡፡በመሆኑም ወደ ቤተሰቦቻቸውን በመደወል የድረሱልን ጥሪዎች እያሰሙ መሆኑን ታውቀዋል፡፡

Thursday, September 11, 2014

‹‹ኣለኻ ዶ? ኣለኹ እወ! ጥራይ ምቕናይ››



እዛ ደርፊ እዚኣ ዳምፅ ከለኹ ክልሻዕ ከብደይ ሕምብጭ ብጭ ይብል፡፡ ናይ ዛ ዓለም እዚኣ ነባሪ ምዃነይ ካብ ዝፈልጥ ጀሚሩ ዝተላለኹዎም መናእስተይ፣ መታዓብይተይ፣ መማህርተይ ሓዳ ብሓደ ኮለል ኢሎም ይራኣዩኒ፡፡ናፍቖቶም ድማ ምሒር ይብርትዐኒ፡፡ ገሊኦም ብሂወት የለውን…ኣለኻ ዶ? ምስ ዝብሎ ‹‹ኣለኹ እወ›› ኣይብሉንን እዮም፡፡ ምስ ገሊኦም ናብራ ዓለም ኣራሓሒቓትናስ ዓይኒ ንዓይኒ ካብንርኣአ ዓሰርተታት ዓማውቲ ሓሊፎም፡፡ ስልኮም ኣታኣላሊሸ እንትድውለሎም ዘይዝክሩኒ ብዙሓት እዮም፡፡ ንምንታይ? ‹‹ካብ ዓይኒያ ዝራሓቐስ ካብ ልቢ ርሓቐ›› ሐቂ ስለዝኾነ? ንምንታይ ዳኣ ካብ ልበይ ዘርይርሕቑ?

ብዝኾነ ከምዚ ዝዓይነቶም ደርፊታት ቐደም ንድሕሪት ምልስ ኢለ ብዙሕ ከስተንትንን ክዝክርን ስለዝገብሩኒ ኣብዚሐ ዘዳምፆም ከምዚ ሎሚ መዓልቲ ዝበሉ ኣገደስቲ ምዓልቲታት ጥራሕ እዩ፡፡ሎሚ መዓልቲ ክዝክሮም ግድን እዩ፡፡ይትረፍ ምስቶም ብዙሕ ሕማቕን ፅቡቕን ሐቢርና ዘሕለፍናስ እቶም ጎቦታት፣ ሽንጥሮታት፣ ጎላጉልን ሜዳታትን እውን ማዕሪጎምን ፀቢቖምን ይርኣዩኒ፡፡ውሓዝቲ ሩባታት ኩሕሊ መሲሎም ዝፀርዩሉ፣ጎቦታት ሰንጢቖም ቁልቁል እንትወርዱ ኣማዕድዩ ንዝምልከቶም ተሓፂቡ ዝተሰጥሐ ኣዝዩ ነዊሕ ጋቢ ዝመስሉሉ፣ ዕምበባታት ዝዕብብሉ፣ ዝተፈላለዩ ዓይነት ኣዝርእቲ ዋልዳን ጭላዳን ዝኾኑሉ…በፃሕና በፃሕና ዝብሉሉ፡፡ተፈጥራዊ ዑደት ብተግባር ዝትርእየሉ መስታወት ዓለም ዝዓበኹሉ ገጠር ትግራይ…
ናይዛ ዓለም ጓጓ ዝትዕዘበሉ…ተፈጥራዊ ምዓርጋን እስትንፋሳን ዝትሙዕገሉ…ሙዒግካ እትረውየሉ፡፡‹‹ግዜ ሲ ሓሊፉ ትዝታታት ገዲፉ…›› ዶ በለ ኣብራሃም ኣፈወርቂ? ክንደይ ትዝታ እዩ ሓሊፉ!
ዘኪረ ዝሓለፈ…
ተዓዚሩ ግዜ ምስ ኣርከበ ዕብየት
ሓዳር ተመስሪቱ ዘር ምስበለ ስቤት  
ዓርከይ ኣዘኪረ ግዜ ናይ ንእስነት
ዓርኽተይ ጥራሕ ኣይኾንኩን ዘኪረ… እቲ ዝዓበናሉ ከባቢ እውን ከም ሰብ እዩ ዝናፍቐኒ ዘሎ፡፡ ‹‹ወይ አዲስ አበባ ወይ አራዳ ሆይ…ሃገርም እደሰው ይናፍቃል ወይ…›› ድዮም ዝብሉ ደረፍቲ? አዲስ አባባ እኳ ተናፊቓ ደማ ገጠራት ትግራይ? ኣዲስ ኣበባ ህንፃኡ መስታወት…ሰቡ መስታወት…ብልጭልጭ…ዓመት ሙሉእ ብልጭልጭ…እስመ ኣልቦ ለውጢ!
ኣዕርኽተይ መናእስተይ ክዝክሮም ክዝክሮም
ኣዕርኽተይ መፃውተይ ኣበለኹም ኣበለኹም
ኣዕርኽተይ መፃውተይ ኣለኹም ዶ ኣለኹም ዶ
ደቂ ዓደይ መዓረይ! ኣብዘሉኹም ሃሊኹም ኣለኹ በሉኒ፡፡የለኹን ፅቡቕ ኣይኾንን፡፡ ይሕመቕ ይፀብቕ ምህላው ዋና! ኪሮስ ‹‹ምቕናይ ፅቡቕ እዩ ዋላ ሓደ ሰሙኔ›› እንትብል ዝተዓሸው ከይመስለና፡፡ምሽጥር ምንባርን ዘይምንባርን ስለዝተበረሆ እዩ፡፡ኣነ አለኹ ‹‹ኣለኹ እየ ዝብል…›› ደቂ ዓደይ እውን ሃልውለይ!
ርሑስ ሓድሽ ዓመት!


Wednesday, September 10, 2014

‹‹ወይ ዘንድሮ…ወይ ዘንድሮ…ወይ ዝንድሮ…››አለ ያለው እፍሬም ታምሩ


ዓምና እንደዛሬው ማታ ስለ አብርሃ ደስታ እየፃፍኩ ነበር፡፡ ዓረና ትግራይ በጳጉሜ ሁለትና ሶስት 2005 ዓ.ም ባካሄደው ሶስተኛው ድርጅታዊ ጉባኤ አብርሃ ደስታን የድርጅቱ ማእከላዊ ኮሚቴና የስራ አስፈፃሚ አባል አድርጎ መርጦት ነበር፡፡

 

ያንኑ ክስተት ተንተርሼ ነበር ‹‹አብርሃ ደስታ በከፍተኛ ሹመት ወደ አዲሱ ዓመት›› በማለት የፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆኑን የተቃወምኩት፡፡አብርሃ ደስታ የማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባል እንዲሆን አልፈልግም ነበር፡፡ከዩኒቨርሲቲ አስተማሪነቱ ጎን ለጎን የሃገራችን ባህላዊ፣ማህበራዊ፣ ኢኮነሚያዊና ፖለቲካዊ ህፀፆችን በጥናት እያስደገፈ የሚተች ታላቅና ገለልተኛ ምሁር እንዲሆን ነበር ምኞቴ፡፡

 

እንደ እኔ ምኞት ቢሆን አብርሃ እንደነ ሶቅራጠርስ፣ዲዮጋን፣ ናኦም ቾምስኪ ወዘተ. የአደባባይ ምሁርና ተቺ (public discourse and social critic) እንዲሆን ነበር፡፡ አልሆነም፡፡ ይልቁንስ የዓረና ከፍተኛ አመራር በመሆን ከሃገራችን ፖለቲከኞች አንዱ ለመሆን መረጠ፡፡አሁን ግን በማእከላዊ እስር ቤት እየማቀቀ ይገኛል፡፡በእርግጥ በሰባሰበቡ እስር ቤት እየማቀቁ ያሉ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ብዙ ናቸው፡፡የአብርሃ ደስታን ያህል ግን የተቸሁት የለም፡፡በመሆኑም አሁን ያለው ሁኔታ በእጅጉ ስሜቴን ነክቶታል፡፡

 

ተጨማሪ መረጃ ለማሰባሰብና የሰበሰብናቸው መረጃዎች ለማስተርጎም ተጨማሪ 28 ቀናት ይሰጠን እየተባለ የሰቀቀን ቀናቱን በየወሩ በ28 ቀናት እየተራዘሙ ይገኛሉ፡፡ይገርማል፣ የኢትዮጵያ አብዮቶች መቼ ይሆን ወላፈናቸው ዜጎችን መለብለቡን አቁሞ በድህነት፣ኋላ ቅርነት፣ በሙስና፣ በመልካም አስተዳደር እጦት፣በአጠቃላይ በፀረ ዲሞክራሲያዊ አሰራሮች ላይ መዝመት የሚጀምረው?መቼ ይሆን የሃገራችን ፖለቲካ ነፍሰገዳይ ኮረንቲ መሆኑን አብቅቶ ጨለማና ድህነትን የሚያጠፋ ሃይል የሚሆነው?

 

ሳስበው የሃገራችን ፈርጀ ብዙ ችግሮች ምንጭ ፖለቲካችን ሳይሆን አይቀርም፡፡‹‹ቁጥር አንድ ጠላታችን ድህነት ነው›› እንላለን እንጂ የድህነታችን ምንጭ የሆነው ፖለቲካችን ግን አውቀንም ይሁን ሳናውቅ መፍትሔ ስናስብለትም ሆነ ስንፈልለት አይታይም፡፡የፖለቲካችን እንካስ ላንትያ መነሻና መድረሻው ተለይቶ እስካልታወቀ ድረስ መሔድ መመለሳችን፣ መውደቅ መነሳታችን መቋረጫ የሌለው ዥዋዥዌ መሆኑን የሚያበቃ አይመስልም፡፡

 


ለማንኛውም የአጥፍቶ መጥፋቱ የጥላቻ ፖለቲካችን አብቅቶ ምክንያታዊነትና የህዝቡ ሉዓላዊነት የሚነግሱበት ዘመን ያድርግልን፡፡


Wednesday, September 3, 2014

ጨለማውን ለምን ፈራሁት?

'

 በህልሜ ይሁን በእውኔ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ብቻ አንድ ይሆናል ብየ ያልጠበቅኩት ነገር ተከስተዋል፡፡ያለሁበት ስፍራ ድቅ ድቅ ጨለማ ነው፤ ዓይንህን እስኪጠነቁሉህ ድረስ በማታይበት፡፡በመጀመርያው አከባቢ ሌሊት መስሎኝ ነበር፤በደመናና ጉም የታጀበ የክረምት ጨለማ፡፡ የጊዜው ርዝመት ሳስበውና ሰሰላስለው ግን ሌሊት አለመሆኑን እርግጠኛ ሁኛለሁ፡፡የሌሊት ርዝመት ከ12 ሰዓት አልፎ ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል የረዘመው እስከ መቼ ነው? በፍፁም ሊሆን አይችልም፡፡የእኔ እድሜስ ከመቼው ግማሽ ክፍለ ዘመን ሞላው?

ከአጠገቤ ማንም የለም፡፡ወይም ይኑር አይኑር ማየት አልቻልኩም፡፡ በጣም አሳስቦኛል፡፡የቀበሮና የጅብ ጭሆት ከሩቅ ይሰማኛል፡፡የሆኑ ሰዎች ላምባዲና አብርተው ወድያ ወዲህ ሲሉ ይታዩኛል፡፡ በእርግጥ ሰዎቹን መለየት አልችልም፤ ምናልባትም ከቅርብ ርቀት አስፓልት ሊኖር ይችላል፡፡ውልብ ውልብ የሚልብኝ ብርሃንም የመኪኖች የፊት መብራት ሊሆን ይችላል፡፡የጅቦቹ ጭሆት ወደ እኔ እየቀረበ ነው፡፡ከሩቅ ይታዩኝ ነበሩ መብራቶችም እየተጠጉኝ ያሉ ይመስለኛል፡፡እኔን ለማጥፋት ወይንስ እኔን ለማዳን? ግን ጨለማው ዛሬ ደርሶ ለምን አስፈራኝ? ወዳጅ ከምቀኛ ለይቼ እንዳላውቅ ስለጋረደኝ ይሆን?

እኔን የሚፈልጉ ሰዎች ይሆኑ እንዴ?ለምን ይፈልጉኛል? ፈርቻለሁ ልበል? አዎ! ፈርቻለሁ፤ ፍርሃቱ ግን ይለያል፤ህፃን እያለሁ ብቻ ነበር ይህን ዓይነቱ የፍርሃት ስሜት የተሰማኝ፡፡‹‹ደርግ የተባለ ጭራቅ መጥቶ ይበላችኋል›› ተብለን የመንደራችን ኗሪዎች እንዳለ በአንድ ዋሻ ውስጥ ተደብቀን እያለ የተሰማኝ ፍርሐት ነው አሁን እየተሰማኝ ያለው፡፡ግን ደርግ ከተደመሰሰ 23 ዓመታት አልፈዋል፡፡አካሌ ውርጭ ላይ እንዳደረ ሰው ይርገፈገፋል፡፡ለብ ያለ ላብ ጀርባየን ሰንጥቆ ቁልቁል እየወረደ ነው፡፡ እጆቼም ላብ በላብ ሆኗል፡፡
በአሁኑ ወቅት ለምን በዚህ ስፍራ ተገኘሁ?በህይወት አለሁ፣ ወይስ ሙቻለሁ? በህይወት ከሌለሁ ችግር የለውም፡፡ ግሃንም ውስጥ ነኝ ማለት ነው፤የድያብሎስ ጭፍሮች እያፈላለጉኝ ይሆናል፡፡በህይወት ካለሁ ግን በእርግጠኝነት አደጋ ውስጥ ነኝ፡፡በህይወት እያሉ በዲያብሎስ ጭፍሮች ከመሰቃየት መሞት ይሻላል፡፡  

እነዚህ ሰዎች ወደ እኔ የሚመጡት? እዚህ ጋር መሆኔን ማን ነገራቸው? ኮቴያቸው በደምብ ይሰማኛል…ያ ህፃን እያለሁ…ከወላጆቼ ጋር ዋሻ ውስጥ ተደብቀን ሳለን ይሰማኝ ነበረው …የወታደሮች ኮቴ! አያቴ ትዝ አለችኝ…የወታደሮቹ ኮቴ ከተደበቅንበት ዋሻ ላይ ይሰማን ነበር፡፡ ቢሆንም ግን ድምፅ እስካላሰማን ድረስ ወታደሮቹ ሊያገኙን አይችሉም ነበር፤ከላይ ሲታይ ዋሻ መኖሩን ስለማያስታውቅ፡፡የአከባቢው ተወላጅ ካልሆነ በስተቀር ማንም ፈልጎ ሊያገኘው አይችልም፡፡ቢሆንም ግን ድምፅ እንዳላሰማ አፌን ጥርቅም አድርጋ ይዛኝ ነበር…አያቴ፡፡ምን አለ አሁንም በህይወት በኖረችልኝ? አጠገቤ ሆና ‹‹አይዞ ማንም አያገኘንም›› እያለች እንደታበረታታኝ፡፡ለጥቄዎቼ ሁሉም ሳይታክታት ትመልስልኝ ነበር፡፡ለምንድ ነው ቤታችን ትተን እዚሁ የተደበቅነው አደዋየ? ሽፍቶች እንዳይገድሉን ነው ልጄ፡፡በገዛ ቤታችን ለምን ይገድሉና፣ ምን አጠፋን? ምንም አላጠፋንም፤ ሽፍቶች ስለሆኑ ብቻ ሰው ይገድላሉ፣ቤት ያቃጥላሉ፣በግ፣ከብትና ፍየል ያርዳሉ፡፡የተረፉትም ይዘው ይሄዳሉ፡፡

ልጆች እያለን ከጓደኞቼ ጋር ለሁለት ተቧድነን ሽፍታ ሽፍታ እንጫወት ነበር፡፡ቡድኖቹን የሚመሩት በዕድሜ ተለቅ ተለቅ ያሉ ልጆች ሲሆኑ አሸናፊው ቡድን የተሸናፊው ቡድን አባለት እንዳለ ገድሎ፣ቤት አቃጥሎ፣አንዳች የቤት እንስሳ ሳያስቀር ይዞ ይሄዳል፡፡ሆኖም ግን ተሸናፊው ቡድን በተራው አሸናፊ ይሆንና የባላንጣው ቡድን አባላትን ይገድላል፣ቤት ያቃጥላል…የቤት እንስሳት ያርዳል…ይዘርፋል፡፡ጨዋታው የምናካሄደው የወዳደቁ እንጨቶች፣ፍልጥና ዱላ እንደ ጠብመንጃ ተጠቅመን ነበር፡፡

አብዛኛው ጊዜ እኩል ነበር የምነሸናነፈው፡፡አንዳንዴ ግን ከሁላችን የሚበልጠው ጉልቤ ሁሌም ካላሸነፍኩ እያለ ስለሚረብሽ በመሃል እንጣላ ነበር፡፡የምር ተደባድበን፣ ተላቅሰን የምንለያይበት ጊዜ ነበር፡፡በነጋታው ግን ትናንት የሆነውን እንዳለ ረስተን ጨዋታችንን እንቀጥላለን፡፡ኋላ ላይ ግን እንደ አያቴ አባባል የምር ሽፍቶች መጡብን፡፡ሁለቱም ሽፍትች እኛን ለመታደግ እንደመጡ ነበር የሚነግሩን፡፡የአንደኛው የሽፍትች ቡድን አባላት ሲገድሉም ሆነ ሲዘርፉ አይታዩም፡፡የማይታዘዙ የአከባቢው ምሁራንና ባላባቶችን አፍነው በመውሰድ መጨረሻው እንደማይታወቅ ጉድጓድ ዋጥ አርድርገዋቸው ቀርተዋል፡፡የሌላኛው ሽፍታ አባላት መስለው በመምጣትም ሴቶች አስገድደው ይደፍሩ፣ ቤት ያቃጥሉ፣ የቤት እንስሳት ይዘርፉ፣ ክምሮች ያቃጥሉ እንደነበርም ይወራል፡፡ይህን ሁሉ ግን በሽክሹክታ እንጂ በግልፅ አይወራም፡፡በግልፅ ሲያወራ የተገኘ ሰው እንደ ጅብ ሌሊት መጥተው አፍነው ይወስዱታል፡፡ከዛ በኋላ የት እንደ ገቡ አይታወቅም…የሚጠይቅም አይኖርም…ጆርጅ ኦርዌል እንዳለው እንዲተኑ ይደረጋል፡፡

እውነትና ውሸት፣ ብርሃንና ጨለማ በዚህ መልኩ ነበር የተደበላለቁት፡፡ እነርሱ እውነት ነው ያሉት ውሸት በቃ እውነት ነው፡፡ማንም አይደለም ማለት አይችልም፡፡ በጠራራ ፀሐይ ጨልሞብናል ካሉ ‹‹ፃሐይዋ ስትጠልቅ?›› ብሎ መጠየቅ ያስቀጣል፡፡ይኸው አሁንም አንኔን ጨልሞብኛል…በአከባቢየ ከሚሰማኝ የጅብና የቀበሮ ጭኾትና ውልብ ውልብ የሚሉት መብራቶች በስተቀር ምንም ነበር አይታየኝም፡፡ወዴት መሸሽ እችላለሁ…የት ልሸሸግ? ለምንስ እሸሻለሁ…እሸሸጋለሁ? ምን አለ አሁን ጭለማው እንደ ጥቁር ልብስ ግፍፍ ብሎ ቢጠፋ? አሳዳጆቼ በግንባሬ ላይ መትረየስ ደግነው ቢታዩኝስ? አይጣል እኮ ነው! የትናንቶቹ የእኔ አለኝታዎች እኔን ሊገድሉ? አድርገውታል እኮ፣ አያደርጉትም አይባልም፡፡

የአውሬዎቹ ድምፅና የወታደሮቹ ኮቴ አጠገቤ ደርሰዋል፡፡ ማናቸው ቀድመው ይደርሱብኝ ይሆን? ወይንስ ገጭ ገጭ የሚለው ድምፅ የአውሬዎቹ ጥርሶች ናቸው? እናንተ የምታዩኝ፣ እኔ እማላያችሁ፣ ሽሽቼ እማላመልጣችሁ አሳዳጆቼ ሆይ ዞሮ ዞሮ የትም አልሄድባችሁም፤ ብትተውኝ ምን አለበት?ከአውሬዎች መንጋ መሃል ትተውኝ ሄደው ይሆን እንዴ? በቃ፣ አላወቅኩም እንጂ ለካ የአውሬዎች እራት ለመሆን ተፈርዶብኛል፡፡ ወደ እኔ የሚመጡ መስለው ይታዩኝ የነበሩ መብራቶች አሁን አይታዩኝም፡፡ ድቅ ድቅ ጨለማ ውጦኛል፡፡ መንቀሳቀስ አቃተኝሳ… ታስሬያለሁ እንዴ? አዎ፣ ታስሬያለሁ፡፡እዚሁ የጅቦች እራት መሆኔን ነው… ጅብ በልቶታል ተብሎ ይወራብኛል፡፡ ማንም ተጠያቂ አይኖርም፤ እንዲህ ነው መትነን ማለት…አልበርኩም የለሁም!

የኸው ጅቦቹ እያሸተቱኝ ነው…ኧኧኧኧዓዓዓዓዓዕዕዕ…ህእ…እ…