በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ19ኛው ክፍለ ዘመን እንደተገኘ የሚነገርለት የቤተ ሙከራ ውጤት ከሳይንሳዊ ጭብጦቹን ይልቅ ዛሬም ድረስ ነባራዊ ሁኔታዎችን ቅልብጭ አድርጎ በማሳየቱ በኩል ጎልቶ የሚታወቅ ተምሳሌታዊ ወግ ሆኗል፡፡ፈረንጆቹ የምትቀቀለው እንቁራሪት(The boiling frog) ይሉታል፡፡መነሻ ሃሳቡ አንዲት እንቁራሪት ፈልቶ በሚንፈቀፈቅ ውሃ ውስጥ ብትከታት ወድያው ተስፈንጥራ ትወጣለች፤ቀዝቃዛ ውሃ ውስጥ ከተህ በተቻለ መጠን ውሃው ቀስ በቀስ ብታሞቀውና ብሎም ብታፈላው ግን የግለቱ አደገኛነት ስለማታስተውለው ተቀቅላ እስክትሞት ድረስ እዛው ትቆያለች የሚል እንአድምታ አለው፡፡
የዘመናችን የስነ ህይወት ተማራማሪዎች ትርክቱ ሳይንሳዊ እውነታ እንደሌለው አረጋግጠናል ቢሉም ከጊዜ ወደ ጊዜ በለሆሳስ እየተባባሱ ሄደው የጋራ ጥፋት የሚያስከትሉ ማህበራዊ ቀውሶችን ከሚያስረዱ ዘይቤያዊ አነጋገሮች አንዱ ለመሆን ግን ያስቆመው የለም፡፡የፖለቲካዊ፣ማሕበራዊና ባህላዊ እሴቶች መላሸቅ ለመተንተን እንደ መንደርደርያ ከሚያገለግሉ ምሳሌዎች ቀድሞ የሚጠቀስ ነው፡፡የምዕራቡ ዓለም ልሂቃን የአየር ንብረት ለውጥና የኢኮነሚ መንኮታኮት ለመተቸት ተጠቅመውበታል፡፡
እኔም የሃገራችን ፈርጀ ብዙ ችግሮችን ባስተዋልኩ ቁጥር እምዬ ኢትዮጵያ ቀስ በቀስ በሚፈላ ውሃ የምትቀቀለው እንቁራሪት መስላ ትታየኛለች፡፡በየጊዜው የሚከሰቱት ችጋሮች ቀስበቀስ ከርሃብነት ወደ ጠኔ እስኪሸጋገሩ ድረስ የሚያስተውላቸው የለም፡፡የወሎ ርሃብ ወደ ጠኔ ደረጃ ከመድረሱ በፊት ያስተዋለው አልነበረም፡፡ነገሮች ከቁጥጥር ውጪ ከሆኑ በኋላ ግን ደርግ እንደ ትልቅ የፖለቲካ ውድቀት አድርጎ በማራገብ ንጉሳዊ አገዛዙን ለማብጠልጠል ተጠቅሞበታል፡፡እነ ጥላሁን ገሰሰም
‹‹ዋይ! ዋይ! ዋይ! ሲሉ
የርሃብ ጉንፏን ሲስሉ›› እያሉ በለቅሶ የታጀበ ዜማ አዚመውበታል፡፡ዘፈኑም ሆነ የፖለቲካ ውዥንብሩ ግን በወቅታዊ ግለቱ ፈልተው ከመንፈቅፈቅ ውጪ የችግሩ ምንጭ ለይቶ በመምታት ለወደፊት እንዳይከሰት ያደረጉት ጥረት አልነበረም፡፡ለዛም ነበር ሃገራችን በ1977 ዓ.ም ሌላ አስከፊ ርሃብ ለማስተናገድ የተገደደችው፡፡በንጉሳዊው አገዛዝ ሲያላግጥ የነበረው ደርግ ‹‹ኢትዮጵያ ትቅደም›› ከሚለው ባዶ መፈክሩ በስተቀር ያመጣው ለውጥ አልነበረም፡፡‹‹መሬት ላራሹ›› የሚለው የ60ዎቹ ልሂቃን ጥያቄ መልሻለሁና የእኔ መፈክሮች ከማስተጋባት አልፎ ሌላ አስተሳሰብ የሚያራምድ ካለ ነፃ እርምጃ እወሰድበታል ብሎ አወጀ፡፡አዋጁ ቀይሽብርን አስከተለ፡፡ሃገርና ህዝባችንን በቁሙ ተቀቀለ፡፡