«እንጋባ» ሲል ጠየቃት፣ አሳምነው።
አልተቀበለችውም አስማሩ። «ወንድምና እህትነቱ ይበልጣል» አለችው።
ተስማሙ።
ቤቷ እየመጣ ይጠይቃታል።
ቡና ታፈላለች ይጠጣሉ፣ካላት ታቀርባለች - ይበላሉ።
አውግተው ይለያያሉ።
የትዳር ነገር ዳግም አለተነሳም።
አሳምነው አንድ ቀን በጠራራ ፀሐይ መጣ።
እንደመጣ የደረበውን ሹራብ አውለቆ አስቀመጠ።ስለሙቀቱ ብዙ አውርተው ተለያዩ።
አስማሩ አሳምነው ረስቶት የሄደውን ሹራብ ልብሷን ስታጥብ አጠበችለት።
ዳግም ሲመጣ ደርቦ ደራርቦ ነበርና የሚያወልቀው እንጂ የሚደርበው ልብስ አላስፈለገውም።
ጃኬቱን አውልቆ ሄደ።
አስማሩ እሱንም አጥባ አኖረችው።
ሱሪውን ደርቦ መጣ «ወበቀኝ» አወለቀው።
አስማሩ አጥባ አኖረችው፣
ካፖርቱን ጥሎ ሄደ፣
አጥባ አኖረችው።
አንድ ቀን በጠራራ ፀሐይ ብርድ ልብሱን ለብሶ መጣ፣
አስማሩ «ምነው?» አለቸው።
«በጠራራ ፀሐይ ብረድ ሆዴ ገባ» አላት።
«ምች ይሆናል፣ አለችው። የምች መድኃኒት ብታሽለት ተሻለው።
ሲሻለው ብርድ ልብሱ አላስፈለገውም ጥሎት ሄደ።
አስማሩ አጥባ አኖረችው።
ትንሽ ቆይቶ፣ ፈራሹን ተሸክሞ መጣ።
«ምነው?» አለችው።
«ላሳድሰው መሄዴ ነው።አይቼሽ ልለፍ ብዬ ነው» አላት።
አመነችው።
ጨዋታው ደራ፣ ፍራሹን እረስቶት ሄዶ ኖሮ እኩለ ሌሊት ቢመጣ አስማሉ ቦታ ስላጣች ፍራሹን ላይ ደርባው ደረሰ። ያኔ
«ተነሽ» ከማለት «ጠጋ በይ» ማለት ቀልሎ ተገኘ።
ማስታወሻ፡ ይህ ፅሑፍ ኩርቢት ከተባለ የአለማዮህ ገላጋይ መፅሓፍ የተወሰደ ነው።
No comments:
Post a Comment