Saturday, May 3, 2014

ነገረ ኢትዮጵያውያን፡ ‹‹…አበበ በሶ በላ…ጫላ ጩቤ ጨበጠ…››


ይህን ፅሑፍ የሚያንብ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሶ በልቶ ብያውቅም ባያውቅም፣ ጩቤ ቢጨብጥም ባይጨብጥም ‹‹አበበ በሶ በላ››ና ‹‹ጫላ ጩቤ ጨበጠ››ን መቼም የሚረሳቸው አይመስለኝም…ልክ እንደ እጆቹ ጣት ማንኛውም ነገር ባከናወነ ቁጥር የሚያስታውሳቸው ይመስለኛል፡፡በተለይ ሲበላ እነዚህ አረፍተ ነገሮች ሳያስታውሳቸው አይቀርም…ቁርጥ ሲበላ ጩቤ…ሌላ ነገር ሲመገብ ደሞ በሶ፡፡ምክንያቱ ደሞ አማርኛ የተማረ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ...አእምሮው ምንም እንዳልተፃፈበት ነጭ ወረቀት ንፁሕ እያለ ነበረና የተቀረፁበት፡፡
በአንደኛ ክፍል የአማርኛ ክፍለ ጊዜ ጮሕ ብሎ ‹‹…አበበ…በሶ…በላ…ጫላ…ጩቤ…ጨበጠ…›› እያለ እንዲያስተምር ታዞ የሚያውቅ ካለማ ከስጋና ደሙ ጋር ሳይዋሃዱበት አይቀሩም፡፡ይሆነው ሆኖ ግን ሁላችንም የእነዚህ አረፍተ ነገሮች ዘመን አሽሬ ትውስታዎች አሉን ብቻ ሳይሆን ከእለት ተእለት ንሯችን ጋራ የተሳሰሩ ሆኗል፡፡በእንዱ ጫፍ በሶ በሊታ አበበዎች ለመብላት አሰፍስፈው ይጠባበቃሉ…በሶ ይበላሉ…በሶ በጥብጠው ይጠጣሉ፡፡በሌላኛው ጫፍ ደሞ ጩቤ የጨበጡ ጫላዎች ጩቤ ለመርገጥና ለማስረገጥ ሁሌም በተጠንቀቅ ቆሞው ይኖራሉ፡፡እናም በአጠቃላይ ፊደል ቀመስ ኢትዮጵያውያንን በሁለት ከፍለን ማየት እንችላለን፡፡


 1.  አበበ በሶ በላ…
አንድ ኢትዮጵያዊ በ‹‹አበበ በሶ በላ›› የሚመደበው በሁለት ጉልህ ምክንያቶች ሲሆን እነሱም አንድን ነገር ሁሌም እየደጋገመ የሚያሰለችና ለእኔ ብቻ የሆነው ስግብግብ ናቸው፡፡
 1.1.        ‹‹የሞኝ ለቅሶ መልሶ መላልሶ››፡- በአንድ ነገር ላይ ሙጭጭ ብሎ ነጋ ጠባ የሚቸከችክ፣ መንቻካ፣አታካችና አስልቺ የሆነ ሰው በዚህ ምድብ ይከፈላል፡፡በዚህ ምድብ የሚመደቡ ሰዎች ተወልደው እስኪሞቱ ድረስ በአስተሳሰብ፣በአኗኗር፣ በፀባይ፣ በስራ፣ በአነጋገር ያው ናቸው፡፡ከሃያ ዓመታት በፊት የተናገሩት ነገር ዛሬም ልክ እንደ አዲስ ይደጋግሙታል፡፡መቼስ አንድ የአንደኛ ደረጃ የአማርኛ መምህር በያዓመቱ ‹‹አበበ በሶ በላ..›› እያለ ቢያስተምር ላይፈረድበት ይችላል…ከአበበ በሶ በላዎችም ላይመደብ ይችላል…ስራው ስለሆነ፡፡የአንድ ትልቅ ድርጅት ወይም የሃገር መሪ ሆኖ የህዝብ ተወካዮች ፊት በቀረበ ቁጥር ወይም ህዝብ በተሰበሰበበት ሁሉ አንድ ዓይነት የሚናገር ከሆነ ግን ‹‹አበበ በሶ በላ›› ልንለው እንችላለን፡፡ለምሳሌ የኢህአዴግ መሪዎች ስለሃገራችን እድገት ሲያወሩ ሁልጊዜ በ11 ድጅት ማደጋችንን ነበር የሚናገሩት፡፡ዘንድሮ ግን ለራሳቸውም ሰለቻቸው መሰለኝ በ9.7 ነው ያደግነው ብሏል፡፡በዚሁ ከቀጠሉና በሌላው ዘርፍም አንድ ዓይነት ነገር መደጋገም ካቆሙ ግን ‹‹አበበ በሶ በላ›› አይደሉም ልንል እንችላለን፡፡ምርጫ በመጣ ቁጥር ተቃዋሚዎችን የሚወቅሱበትና የሚያጣጥሉበት መንገድም ሁሌም ያውና አንድ ዓይን ነው…‹‹ጥርት ያለ የፖለቲካ ፕሮግራምና ሃገራዊ አቋም ይላችሁም!››፡፡ ደሞ የህዝብ ችግሮች መኖራቸው የሚያምነውና ‹‹ችግሮቹን ከስረ መሰረታቸውን አጥንቶ ለንዴና ለመጨረሻ›› እንደሚፈታቸው ቃል የሚገባውም ምርጫ ሲደርስ ብቻ ነው፡፡ምርጫውን በአሸናፊነት ከተወጣ በኋላ ግን እስከሚቀጥለው ምርጫ ድረስ የህዝብ አብዮትታ የሚሰማበት ጀሮና የሚያይበት ዓይን አይኖረውም፡፡የሄ ምርጫ በደረሰ ቁጥር አንድ ዓይነት ቃል እየገቡ መደጋገም ‹‹አበበ በሶ በላ››ይባላል፡፡

በዚሁ የሚመደቡት ግን የኢህአዴግ ቱባ ቱባ ባለስልጣናትና ካድሬዎች ብቻ አይደሉም፡፡በተቃዋሚው ጎራም ብዙ ‹‹አበበ በሶ በላዎች›› አሉ፡፡ነጋ ጠባ ‹‹የፖለቲካ ምህዳሩ ጠቧል›› እያሉ ሁለጊዜ ገዢውን ፓርቲ ሲወቅሱና ለአምስት ዓመታት ድምፃቸው አጥፍተው ከርመው ምርጫ በደረሰ ቁጥር የአየር ምህዳሩን ሲበጠብጡት ይሰተዋላል፡፡ምርጫ ሲቃረብ ከየት እንደሚመጡ አይታወቅም…ሃገሪቷን እንዳለ የገበያ ማዕከል ያስመስሏታል፡፡ቆይ ግን ‹‹ስልጣን ከገበያ ይሸመታል›› የሚሉት ቲዮሪ(ክልሰ ሐሳብ) አለ እንዴ? ምርጫ በደረሰ ቁጥር ያለው ጋጋታና ሆይ ሆይታ አስተውላችኋል? የመርካቶው ነጋዴ እንዳለ ግልብጥ ብሎ የፖለቲካ ገበያውን የተያያዘው እኮ ነው የሚመስለው፡፡በየአምስት ዓመቱ አንድ ዓይነት ምክንያት፣አንድ ዓይነት የስልጣን መቆናጠጫ መንገድ፣ እንድ ዓይነት የፖለቲካ መርህና ሃገራዊ አቅጣጫ ይዘው እንደ አሸን ይፈላሉ፡፡እንድ አንድ ጊዜማ በቴፕ፣በካሴት ወይም በሌላ መቅጫ መሳርያ ተቀርፀው የተቀመጡ ድምፆች በድምፅም መጫወቻው ከተው የሚያሰሙን ሁሉ ይመስለኛል፡፡ሁሌም አንድ ዓይነት ካሴት በአንድ ቴፕ! የሄ አይነቱ ቅጥ ያጣ ድግግሞሽ ‹‹አበበ በሶ በላ›› ነው፡፡

 1.2.        ለሆዱ ያደረ ስግብግብ፡-ማንኛውም ነገር ከገል ጥቅማቸው ጋር የሚያያይዙ፣ምንም ባይቸግራቸውም አንድን ነገር ለማግኘት ሲሉ ሌሎችን ይቅርና ራሳቸውም ጭምር ከመሸጥ አይናቸው የማያሹ ወገኖች ‹‹አበበ በሶ በላ›› ይባላሉ፡፡በሶ አለ ከተበለ ህሊና ብሎ ነገር አይታሰብም፣ የት ነው ያለው፣እንዴትስ ይገኛል… አይጠየቅም፡፡መቼስ ጅብን የሚወዳደር ስስታም አውሬ የለም ይባላል፡፡በተለይ በስጋ አያስችለውም፣ ጅብ ለጅብ አብረው ሲጓዙ ራሱ ጎን ለጎን ሆነው እንጂ ቢሞቱም ፊትና ኋላ ሆነው አይንቀሳቀሱም፡፡እናም አንድ ቀን ለዓመታት ተጥሎ ከኖረ አጥንት ጋር ሲታገል ያገኙትና ‹‹አያ ጅቦ፣ ስጋ እያለ ከዓጥንት ጋር ትታገላለህ እንዴ?›› ብለው ቢጠይቁት ስጋው ያለበት አከባቢ ሳይጠይቅ አጥንቱን ጥሎ እልም ብሎ ጠፋ ይባላል፡፡ሁዱ አምላኩ የሆነው ምድረ በሊታም ማንኛውም ነገር የሚያወራርደው በሚያገኘው የበሶ መጠን ብቻ ነው፡፡ጀሮው መቀበል እንጂ መስጠት የሚሉት ቃል መስማት አይችልም፣ እጆቹም ለመቀበል እንጂ ለመስጠት አይዘረጉም፣ስጥ ከምትሉት እጆቹን ብትቆርጡበት ይመርጣል፡፡ ለበሶ ሲባል የማያደረገው ነገር የለም…መግደልም ጭምር…ሃገርና ህዝብን ከዶ ከውጭ ወራሪ ሐይሎች ጋር መተባበርም ጭምር፡፡ወተት ባለበት ሁሉ ዝምብ እንደማይጠፋው ሁሉ በሶ ባለበት ሁሉ በሶ በሊታ አበበዎች ይርመሰመሳሉ፡፡በህይወት ዘመናቸው እውን ለማድረግ የሚፍጨረጨሩበት ትልቅ ጉዳይ ቢኖር በሶ ማግኘትና መብላት ብቻ ነው፡፡ቢነግዱ ለበሶ ነውና የገበያ ህግ ስለማክበር አይጨነቁበትም፣ ስልጣን ብይዙም ለበሶ ነውና ሙስናን አይፀየፉም…ባገኙት ቀዳዳሁሉ የገኙትን ነገር ይመነትፋሉ፡፡እነዚህ የበሶ ጥምብ አንሶዎች ለበሶ ይኖራሉ…ለበሶ ይሞታሉ፡፡

 2.  ጫላ ጩቤ ጨበጠ…
በዚሁ የሚመደቡት ሰዎች ደሞ ለማንኛውም ነገር መፍትሔው ጩቤ ነው ብለው የሚያምኑ ናቸው፡፡በአስተሳሰብ፣በስነ አመክንዮ፣በመነጋገር፣እርሰ በርስ በመደማመጥና በመመካከር ለውጥ ይመጣል ብለው አያምኑም፡፡ማንኛውም በራሪ ወሬ በሚሰሙ ለማጣራት አይጨነቁም፣ ጩቤያቸውን ከአፎቱ መዥረጥ አድረገው መሮጥ ብቻ  ነው፡፡ከዛም መሞት ወይም መግደል...ሁለተኛ፣ ሶስተኛ አማራጮች አይታሰቡም፡፡ሲጀምርም በእነሱ እይታ የጋራ ብሎ ነገር የለም፡፡አይናቸው ያረፈበት ሁሉ ካላገኙ ከሞት በስተቀር የሚያግዳቸው ያለ አይመስላቸውም፡፡ጩቤ እስከ ጨበጡ ድረሰ ቀልባቸውን የከጀለው ሁሉ በማስፈራራት ካልሆነም በመግደል የራሳቸው ያደርጋሉ፡፡ለምሳሌ የሃገራችን ፖለቲከኞችን ብንወስድ ስልጣን በሰላማዊ መንገድ የሚገኝ አይመስላቸውም… በጩቤ፣ በሳንጃ፣ በነፍጥ ወዘት ብቻ እንጂ ፡፡እናም የሄ ጫላነታችንን ጠንቅቀው ስለሚያውቁ በበሶም በሌላም በመደለል ብዙ ጫላዎችን ከጎናቸው በማሰለፍ እርሰ በርሳችን ያጨፋጭፉናል፡፡አሁን አሁን ደሞ ተቃዋሚዎች ‹‹ህዝባዊ ዓመፅ›› የሚሉት ነገር እንደ ጩቤ ተጠቅመው ስልጣን ለመመንጨቅ ይፍጨረጨራሉ፡፡ሆኖም ግን ገዢው ፓርቲም የስልጣን ባለቤት የሆነው ከነፍሰ በላው ደርግ በጩቤ ነጥቆ ነበርና ሌሎችን ላለማስጠጋት በጩቤ እያስፈራራ ለዘላለም ለመንገስ ይፈልጋል፡፡
ኢህአዴግ ስለ ሰጥቶ መቀበል የሚቀባጥረው የባድመ ጉዳይ ሲነሳ ብቻ ነው፡፡ዲሞክራሲ ማለትም የብሔር ብሔረ ሰቦችና ህዝቦች መብዛት እንጂ የተለያዩ ሐሳቦች መንሸራሸር አይመስለውም፡፡ለዛም ሳይሆን አይቀርም በፓርላማ የተሰባሰቡት ‹‹የህዝብ ተወካዮች›› ድምፅ ለመስጠት የሚመዘዙ እጆች እንጂ የሚያስብ ጭንቅላትና የሚናገር አፍ ያላቸው ሰዎች የማይመስሉት፡፡ተቃዋሚዎች ደሞ (ከጥቂቶች በስተቀር) መነሻና መድረሻቸው በሃገራችን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲነግስ ሳይሆን ስልጣን ለማግኘት ነውና በማንኛውም መንገድ ተጠቅመው ‹‹የተከበሩ ባለስልጣን›› ለመሆን ጩቤ ይጨብጣሉ…ጩቤ ይረግጣሉ…ያስረግጣሉ፡፡በዚህ መሐል የህግ የበላይነት ተረት ተረት ይሆንና ኢህኤዴጋችን አይነገብ ያልሆኑትን ለማጎር ይጠቀምበታል፡፡ተቃዋሚዎች ደሞ በስመ ‹‹ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት›› በነፃነት ፅንሰ ሐሳብ ላይ ይረማመዳሉ፡፡ተቃዋሚዎችን በሚያማምሩ ቃላት የሚሸነግል ከሆነ ወንጀል ይስራ አይስራ መታሰር የለበትም፡፡ዘሮ ዘሮ ግን ሁለቱም ያው ናቸው…‹‹ጫላ ጩቤ ጨበጠ››፡፡

እናም የአማርኛ አርፍተ ነገር አመሰራረት የተማሩ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን (በሃገር ቤትም ይኑሩ ከሃገር ውጪ) አንድም ለበሶ የሚኳትኑ አበበዎች ናቸው አልያም ጩቤ የጨበጡ ጫላዎች፡፡ለዚህም ነው ከድህነት፣ከጦርነትና ከኋላ ቀርነት ውጪ የማንታወቀው፡፡ከእነዚህ ሃገራዊ በሽታዎች ለመላቀቅ በጋራ መክሮ በጋራ መስራት የግድ ይላል፡፡እኛ ግን ጫላ ወይም አበበ በመሆናችን ከመተባበር ይልቅ መሰባበርን ነው የመረጥነው፡፡

No comments:

Post a Comment