ከአንድ ሳምንት በፊት ‹‹የኢንፎርሜሽንና ኮምኒኬሽን ሚኒስትር የጉንበት 20 ክብረ በዓልን
በድንምቀት ለማክበር በአዲስ አበባ የመሰብሰብያ አዳራሽ የውይይት መድርክ አዘጋጅቷልና እንድትገኙ ተጋብዛችኋል›› የሚል የኢሜል
መልእክት ደረሰኝ፡፡ትንሽ ወረድ ብሎ ደሞ ‹‹በውይይቱ መገኘት ግዴታ ነው…NB. Attendance is mandatory ›› የሚል በቀይ ቀለም ተፅፏል፡፡በመሆኑም ልክ የዛሬ ሳምንት (12/05/2014) በመሰብሰብያ
አደራሹ ተገኘሁ፡፡የስራ ባለደረቦቼም ግዴታቸው ነበርና በስብሰባው ላይ ተገኝቷል፡፡
‹‹የውይይቱ›› ርእስ ‹‹ባለፉት የGTP ዓመታት ያገኘናቸውን ድሎች በማስጠበቅ ሁለንተናዊ አቅማችንን
በቀጣይነት በመረባበር( በመረባረብ ለማለት ፈልገው
ይመስለኛል) የህዳሴ ጉዟችንን ይበልጥ እናፋጥናለን!›› የሚል ነበር፡፡እኔ ግን የውይይት መድርክ ሳይሆን የዲስኩር መድርክ ነበር
ባይ ነኝ፡፡አስገዳጅ ስብሰባና የውይይት መድርክ የሰማይና የምድር ያህል የተራራቁ ናቸው፡፡የውይይት መድርክ ህግና ስርዓት ኣለው፣
የውይይቱርእስና ጊዜ ይገድቡታል፣ በውይይቱ ርእስ(አጀንዳ) ላይ የግል ፍላጎት የሌለው የውይይት መሪ( ሞደሬቶር) ያስፈልጓል፡፡አወያይም
ሆነ የሚወያዩ ሰዎች በፍቃደኝነት ብቻ ነው በውይይት መድርኩ የሚገኙት፡፡ተሰብሳቢዎቹም
መቆየት የሚችሉት የውይይቱ ሙቀትና ድምቀት እንዲሁም ርእሰ ጉዳዩ እስከመሰጣቸው ድረስ ብቻ ነው፡፡
አስገዳጅ ስብሰባ ግን በአውጫጭ(
በአዋጅ) ትሰበሰባለህ፣ ተሰብሳቢዎቹ ወደዱም ጠሉም ዲስኩሩ እስኪያልቅ ድረስ የመጠበቅ ግዴታ አለባቸው፡፡ዲስኩሩን የሚነፋው ሰውየ
የጊዜም ሆነ የርእሰ ጉዳይ ገደብ የለበትም፡፡ከተሰብሳቢዎች ጥያቄ የመቀበል ግዴታም የለበትም፤ ሲፈልግ ዲስኩሩ ሲያልቅ (በ11ኛው
ሰዓት) ላይ ለይምሰል ‹‹ጥያቄ ወይም አስተያየት ካላችሁ፣ አጠር አጠር አድርጋችሁ መጠይቅ ወይም አስታይት መስጠት ትችላላችሁ…ያው
እንደምዩት ጊዜ አልቋል…ለሶስት ሰዎች ዕድል እሰጣለሁ›› ሊል ይችላል፡፡በዚሁ በአስገዳጅነት በተጠራነው የዲስኩር መድርክም የሆነው
እንዲሁ ነበር፡፡ከላይ እንደገለፅኩት፣ ወደ ስብሰባው የተጠራነው በአስገዳጅነት ነበር፡፡ዲስኩሩ እስክያልቅም እንደንጠብቅ ተገደድን
በመሰብሰብያ(ማጎርያ) አዳራሹ በሮች በተጠንቀቅ በቆሙ ጥበቆች፡፡
‹‹አወያዮቹ ›› የኢትዮ
ቴሌኮም የህዝብ ግንኙነት ሃላፊው አቶ አብድራሒምና ከመረጃና መገናኛ ሚኒስትር መጡ ያተባሉት አቶ ወልደገብሪኤል(መዓርጋቸው አላስታውሰውም፤
ከአነጋገራቸው ብንገመግማቸው ግን ሃገሪቷ እንደለ ብእጃቸው የወደቀች ይመስላል፡፡)ኣቶ ኣብዱራሒም እንደተለመደው ለሁለት ሰዓታት
‹‹አበበ በሶ በላ…ጫላ ጩቤ ጨበጠ…›› እያሉ የምናውቀውን ተረት ተረት ነገሩን፡፡እንደኮሶ እየመረረን፣ከቄጋ እንደሰራ መኝታ እየቆረቆረን
ቢሆንም ግዴታችን ነበረና ሰማናቸው፡፡በገዛ ጆሯችን አስገድደው ተገላፈጡበት፡፡
የተከበሩ የአቶ ወልደገብሪኤል ደሞ ‹‹ጉንበት 20 በሃገራችን ለዘመናት ተንሰራፍቶ የኖረው
ጨቋኝ ስርዓት ተገርስሶ፣ የብሔር ብሔረ ሰቦችና ህዝቦች እኩልነት በህገመንግስቱ ሙሉ በሙሉ የተረጋገጠበት፣ ሁሉም ሰው እኩል የሆነበት፣የድህነትና
የኋላ ቀርነት ታሪካችን ተቀይሮ በ11 አሃዝ የእድገት ጎደናውን የተያያዝንበት፣ ዜጎች በማንነታቸው የሚኮሩበትና የሚከበሩበት ህገመንግስታዊ
መብታቸውን እውን ያደረግንበት፣ አስተማማኝ ፖሊሲና ስትራቴጂ ተቀርፆ የህዳሴው ጉዞ የተያያዝንበት፣ ባይዘወይ ፖሊሲና
ስተራቴጂ መቅረፅ ቀላል አይደለም፣ ለዜጎቼ ብሎ በራሱ ተነሳሽነት ስራ የሚፈጥር መንግስት እኮ ነው ማንግስታችን ብቻ ነው፣ ….›› እያሉ ደሰኮሩብን፡፡
ይህን ሁሉ የሚያደርጉት በላፕቶፓቸው ላይ ያለው ስልያድ ተደፍተው ነው፡፡ፊደሎቹን አንድ በኣንድ
እየቆጠሩና አጥብቀው እያነበቡ፡፡ከሚያነቧቸው ፊደሎችና ቃላት የመረረ ጥላቻ ያለባቸው ነው የሚመስለው፡፡ዲስኩረኛው ተሰምቶ የማያውቅ
ተአምር የሚናገሩ ሊመስላቸው ይችላል፡፡ለተሰብሳቢው ግን ልክ እንደ ‹‹አበበ በሶ በላ…ጫላ ጩቤ ጨበጠ›› ያህል አሰልቺና ተደጋጋሚ
ነበሩ፡፡ለአንድ ፕሮፌስር ‹‹አበበ በሶ በላ…ጫላ ጩቤ ጨበጠ…››እያሉ እንደ አዲስ የማስተማር ያህል፡፡ ምን ልበላችሁ፣ ግንዛቤ
ለማስጨበጥ ሳይሆን ለማስደበርና ለማስደንበር የታቀዱ ዲስኩሮች ነበሩ፡፡
የአንድ የውይይት መድርክ ወይም የአንድ ሰብሳቢ ውጤት የሚለካው ተሰብሳቢዎች ለመድርክ መሪውና
ለአጀንዳው በሚሰጡት ትኩረት ነው፡፡የመድርክ መሪው(አወያዩ)ና ተሰብሳቢዎቹ በአንድ ርእሰ ጉዳይ ላይ በተመስጦ ያሰላስላሉ፣ ይከራከራሉ፣
ይጠይቃሉ፣ጥያቄም ይመልሳሉ፡፡በአጠቃላይ ሰብሳቢውና ተሰብሳቢው ቢስማሙም ባይስማሙም ብያንስ ለውይይቱ አፅንኦት ይሰጣሉ፡፡በዚሁ ተሰብሳቢዎች
በጣም ተሰላችተው ‹‹ችጋራም ጉንበት 20!›› ብለው እስከመራገም የደረሱበት የዲስኩር መድርክ ግን ተሰብሳቢዎቹና ሰብሳቢዎቹ(አጋቾቹ)
በየራሳቸው ዓለም ነበሩ፡፡ ሰውየው ‹‹ሁሉም ሰው እኩል የሆነበት…›› ሲል እኔ ደሞ ‹‹ሁሉም ሰው እኩል ከሆነ
ታድያ አንተ በምን መስፈርት ነው አወያይ(አጋች) የሆንከው?›› እያልኩ እጠይቀዋለሁ…በውስጤ፡፡ኋላ ላይ ዲስኩሩ በጣም ሲደብረኝ
ግን ዓይኖቼን በአደራሹ ሰንከራትታቸው የአደራሹ ዙርያ መለሽ በመፈክሮች
መወረሩን ታዘብኩ፡፡መፈክሮቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡
1. ‹‹በስራ
ላይ ነን፣ ለወሬ ጊዜ የለንም!››
ይህንን መፈክር ሳነብ በጣም ነበር የገረመኝ፡፡ቁጭት ኣይሉት ምሬት መላው እኔነቴን ተቆጣጥሮታል፡፡እናም
እንደሚከተለው በውስጤ መጎትኳቸው፡፡በርግጥ ጊዜያቸውን የሚያጠፉት በወሬ ነው፡፡የትኛው የኢህአዴግ ባለስልጣን ነው በተፈለገው የስራ
ሰዓት በስራው ላይ የሚገኘው? እንተዋወቅ የለም እንዴ? ‹‹ዕንጉለን ቆርበትን እናተፋለጡ ይማለጡ›› አሉ የትግራይ ሊቃውንት፡፡‹‹በስብሰባ
ላይ ነኝ ወይም ናቸው›› የማያስብሉ ባለስልጣናት ከቶ እነማን ናቸው?የኢህአዴግ ባለስልጣናት ከሚሰሩት ይልቅ የሚያወሩት በሚሊዮኖች
እጥፍ እንደሚበልጥ እምዬ ኢትዮጵያ በደንብ ታውቃለች፡፡መቼስ ‹‹ምስ ደገዝማቲ መን ተሟጋቲ›› እንዲሉ ከእነሩስ ጋር ማን ይከራከራል፡፡
2. ‹‹የግንቦት
20 ድሎች በሕዳሴው መንፈስ ማዕበል ይበልጥ ይደምቃሉ!!››
3. ‹‹ሩቅ
አስባ ሩቅ ለማደር እየተጋች ያለች ሃገር!!››
4. ‹‹እዚህ
ደርሰናል፤ቀሪውንም በጥረታችን ሙሉዕ እናደርጋለን!››
5. ‹‹የጉንበት 20 ድል በህዝቦች መስዋዕትነት የተገኘ በመሆኑ በቀጣይነት የሚጠበቀውም በህዝቡ ነው!!››
እያንዳንዱ መፈክር ሳነብ የሆኑ የመልስ
ምቶች ከእረፍት አልባው ጭንቅላቴ እንደ ጅረት ይንፎለፎሉ ነበር፡፡አብዛኞቹ ለድህንነቴ ስል እዚሁ አልፅፋቸውም፡፡በኣንዳንዶቹ ላይ
ግን እንዲህ እላለሁ፡- በዚህች መፈክር የሚያምኑ ቢሆን ንሮ ከህዝቡ ጋር እጅና ጓንት ሆነው መስራት በቻሉ ነበር፡፡ግን የህዝቡ
ሮሮ መቼ ሰምተው ያውቃሉ?ህዝቡ እስከ መቼ እንዲሞኝላቸው ነው የሚፈልጉት? ከልባቸው የማያምኑበት መፈክር ለምን እንደሚጠቀሙ አይገባኝም፡፡
6. ‹‹የተጀመሩትን
የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት በማጠናከር የሃገራችን የህዳሴ ጉዞ እናፋጥናለን!!›› ልማቱም የመልካም አስተዳደሩም ከ23
ዓመታት በኋላም በጀምር ላይ ናቸው፡፡እስከ መቼ ነው ‹‹የተጀመሩትን›› እያሉ የሚኖሩት?
ከላይ ተዘረዘሩት መፈክሮች ልክ እንደ ፀጉር አስተካካይ ወንበሮች አንገቴን
እያሽከረከርኩ በማንበብ ላይ እያለሁ ዲስኩሩ እስኪያልቅ ድረስ ያገተን ሰውየ ‹‹ንብረት የማፍራትና ያለመወረስ መብት ሙሉ
ለሙሉ ተከበሯል…›› ሲል ሰማሁት፡፡ሲጀመር ግን ንብረት የማፍራት ሙሉ መብት አለን እንዴ? የሃገራችን ታላቁና ቁጥር አንዱ አንጡራ
ሃብታችን መሬት ነው፡፡መሬት ደሞ የኛ ሳይሆን የመሪዎቻችን ብቻ ነው፡፡መሪዎቻችን ለባለሃብቶች መሸጥ ይችላሉ፡፡እኛ ግን የመግዥያ
ገንዘብም የለንም፣ ሰርተን ከምናገኛትም 50 ከመቶ ታክሲ እንድንከፍል ስለምንገደድ ንብረት እናፈራለን? ሃገሪቷን እንዳለ እንደፈለገው የሚያደርግ
መንግስት እያለ እንዴት ነው የንበረት ባለቤት መሆን የምንችለው? ሙሉ ስልጣን ያለው በባለ ሃብቶችና በባለስልጣኖች ብቻ መሆኑን
እየታወቀ ይህን የመሰሉ ስላቆች መደርደር በጣም ያሳዝናል፡፡እንዲህ ከራሴ ጋር ስብሰለሰል ቆይቸ መፈክሮቹን ወደ ማንበቡን ተመለስኩ፡፡
7. ‹‹አገራችን
በሁሉም መስኮች እየተለወጠች ነው፡፡ የለውጡ ምንጭና ተጠቃሚዎች እኛው ነን!!›› እዚች ጋ እውነት ብሏል፤ በተለይም ‹‹የለውጡ
ተጠቃሚዎች እኛው ነን›› ማለታቸው ተስማምቶኞል፡፡አዎ ተጠቃሚዎቹ እነርሱና ቤተሰቦቻቸው ናቸው፡፡‹‹የለውጡ ተጠቃሚ ህዝቡ ነው››
ቢሉ ንሮ እቀየማቸው ነበር፡፡የእነርሱና የቤተሰቦቻቸው ልጆች(የልጅ ልጆችም ጭምር) የሚማሩት በዶላሮች እየተከፈላቸው በውጭ ሃገር
በሚገኙ የሃብታም ልጆች ብቻ በሚማሩባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ነው፡፡እናም ጌቶቻችን የለውጡ ምንጭ ባይሆኑም ‹‹የለውጡ ተጠቃሚዎች››
ናቸው፡፡
እንዲህ እንዲህ እያልኩ ከራሴ ጋር ብዙ ስነታረክ ቆይሁና ሰዓቱ ከቀኑ 6፡30 በመሆኑ እገታው
‹‹በድል›› መጠናቀቁ የድምፅ ማጉልያዎች አበሰሩኝ፡፡በእርግጥ ከድምፅ ማጉልያዎቹ የሚሰማው ድምፅ ባለስጣኖቻችን ሪከርድ ያደረጓቸው መቅረፀ ድምፅ መሳይ
ሰዎች ናቸው፡፡‹‹ሰው መሳይ›› ያልኩበት ምክንያትም ከቀኑ 6፡30 የቁርስ ይሁን የምሳ ሰዓት ለይተው ባለማወቃቸው ነው፡፡ልክ ስድስት
ሰዓት ተኩል ሲሆን ‹‹የቁርስ ሰዓት ደርሷልና ሻይ ቡና እንድትሉ ተጋብዛችኋል›› የሚል ድምፅ ከማጉልያው በኩል ሲያስተጋባ ሰማሁ፡፡‹‹እንዴ!
የሞባይሌ ስዓት ወይስ እኔ? ማናችን ነው የተሳሳትነው?›› እያልኩ ለትንሽ ጊዜ መወዛገቤን አልቀረም፡፡
ኋላ ግን ወዝጋቦቹ የተቀረፁ ድምፆች መሆናቸውን አስተዋልኩና ‹‹ከሰዓት በየስራ ክፍላችሁ እንድትገኙ›› የሚለውን
ጥብቅ ትእዛዝ አስታውሼ መኪኖች ወዳሉበት ተንደረደርኩ፡፡ከስትር በምትባለው መኪና ወደ ስራ ስንመለስ ነበር እንግዲህ አንዱ የመረረው
ተሰብሳቢ(ታጋች) ‹‹ችጋራም ጉንበት 20!›› ብሎ ሲራገም የሰማሁት፡፡እኔም እርግማኗ ሁኔታውን በደምብ የምትገልፅ ሆና ስላገኘኋት
ሰውየውን በሆዴ አመስግኜ የፁሑፌ ርእስ አድርግያታለሁ፡፡
መልካም የቅዳሜና እሁድ ዕረፍት ይሁንላችሁ!
No comments:
Post a Comment