ዛሬ ጥዋት ወደ ስራ ስገባ አንድ ‹‹ትልቅ›› ባለስጣን በመስራቤታችን አጥር ግቢ ኢክስክዩቲቭ
መኪናውን አቁሞ በብዙ ነገሮች የታጨቀው ቦርሳውን አንጠልጥሎ ወደ ቢሮ ሲገባ ዘበኞቹ የሚሆኑት ሲያጡ ታዘብኩ፡፡ሁሉንም ዘበኞች ተስፈንጥረው
ተነሱና ኮፍያዎቻችውን አውልቀው አንዳንዶቹ ሽበታም ፀጉራቸውን እያሻሹ ሌሎቹ ደሞ መላጣቸውን እያከኩ ጎንበስ ቀና እያሉ ምንም ሳይፈትሹት
አሳለፉት፡፡እኔን ግን የማለብ ያህል ከላይ እስከ ታች ምጥጥ አድርገው ከመፈተሻቸውም በተጨማሪ ማስታወቅያየን እንዳሳያቸው ጠይቀውኛል፡፡የመስርያ
ቤቱ የጥበቃ ህግ ይሁን ምን ባላውቅም ትላልቅ ባለስልጣናትና የውጭ ሃገር ዜጎች አይፈተሹም፡፡
በመስርያ ቤታችን የቻይናውያን ቁጥር ከኢትዮጵያውያን ጋር ሊመጣጠን ትንሽ ነው የቀረው፡፡ከቻይናውያን
በተጨማሪ ግን የተለያዩ የውጭ ሃገር ዜጎችም ወደ መስርያ ቤታችን ይገባሉ ይወጣሉ፡፡ሆኖም ግን ማንም አይፈትሻቸውም፡፡አላስፈላጊ
እንግልቶችን ጨምሮ እጅግ የጠበቀ ቁጥጥርና ፍተሻ የሚደረግባቸው የበታች ሰራተኛ ኢትዮጵያውያን ብቻ ናቸው፡፡ነገርየው አዲስ ክስተት
ባይሆንም እንደ ዛሬ ግን በሁኔታው ተገርሜ አላውቅም ነበር፡፡ልክ ቢሮ እንደገባሁ በስራ ስለምጠመድ በቀላሉ እረሳዋለሁ ብየ ጠብቄ
ነበር፤ አልተሳካልኛም፡፡የፈለገው ያህል ስራ ቢበዛብኝም ስለሁኔታው መብሰልሰሌን አላቆምኩም፡፡
አለቆችስ ለምን አይፈተሹም?
መስርያ ቤቱ የማን ነው? የህዝብ ወይስ የአለቆች?
በሃገራችን እስከ አንገታቸው ድረስ በሙስና ውስጥ ተዘፍቀው የህዝብ ንብረት እየመዘበሩ ያሉት ትላልቅ ባለስልጣናት
ናቸው፡፡እነዚህ ጥያቄዎች በአእምሮየ እየተመላለሱ የህሊና እረፍት ስለነሱኝ ነው ለመፃፍ የወሰንኩት፡፡አብዛኞቹ የቴሌ ዘበኞች ከውትድርናው
ዓለም በጡረታ የተገለሉ ስለሆኑ ስለ ቴክኖሎጂ የሚያውቁት ነገር የለም፡፡ምናልባት የሚያውቁት ነገር ቢኖር የመሳርያዎች አጠቃቀም
ቢሆን ነው፡፡የቴክኖሎጂ ነገር ግን አይሆንላቸውም፡፡ሌላው ቀርቶ ላፕቶፕ እንደ ማለት እንኳን ላፍቶ ነው የሚሉት፡፡እናም ወደ ቢሮ
እንዳይገባ የሚከለክሉት ላፕቶፕና ካሜራ ብቻ ነው፡፡
እንደነ ታብሌት ፒሲዎች፣ የተለያዩ ዓይነት ዘመናዊ ቆፎዎችና ሌሎች የቴክኖሎጂ ውጤቶች ግን አይከለከሉም፡፡እንዚህ
ቴክኖሎጂ ያፈራቸው ዘመናዊ እቃዎች ግን ካሚራና ላፕቶፕ መስራት ከሚችሉት በላይ የተለያዩ ነገሮች ለማድረግ ያስችላሉ፡፡የሚገርመው
ደሞ እጅግ በጣም የላቁ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የሚጠቀሙት(ለመያዝ ኢኮኖሚ የማይገድባቸው) ትላልቅ ባለስልጣናትና የውጭ ሃገር ዜጎች
ናቸው፡፡ሳይፈተሹ የሚገቡና የሚወጡት ደሞ እንርሱ፡፡እንግዲህ ምኑን ነው የተጠበቀው?እንደ
ቴሌ ዓይነቶቹ ልማታዊ ድርጅቶች የህዝብ ናቸው፡፡የጥበቃ ሰራተኞች የህዝብ ንብረት ለመጠበቅ የተቀጠሩ የማሕበረሰባችን ክፋል ናቸው፡፡አሁን
እያደሩጉት ያለው ነገር ግን የሚያስተዛዝብ ነው፡፡ድርጅቱን ባንዴ ማሽመድመድ የሚያስችል መሳርያ ይዘው የሚገቡትን ትተው ባዷቸውን
የሚገቡት የበታች ሰራተኞች ላይ ይረባረባሉ፡፡
አለቆችና ፈረንጆች ወደ መስርያ ቤታችን ሲገቡ ወደ ቤታቸው የሚገቡት ያህል ነው ዝው ብለው
የሚገቡት፡፡ላዛውም በብዙ ጎንበስ ቀናዎች ታጅበው፡፡እናም የጥበቃ ሰራተኞች ዋናው ስራ የአለቆች ምቾትና ድህንነት ማረጋገጥ ብቻ
እያስመሰለባቸው ነው፡፡አለቆች ሲገቡና ሲወጡ ሃይለኛ ማዕበል እንደሚያገላብጠው ዛፍ እጥፍ ዘርጋ፣ ጎምበስ ቀና፣ ኮፍያቸውን አውልቀው
መላጣቸውን እያከኩ መሽቆጥቆጥ አረስንቱን እቴ፡፡እንደኔ ከሆነ ግን በጣም መፈተሸ የነበረባቸው ትላልቆቹ አለቆችና
የውጭ ዜጎች ናቸው፡፡
አሁን እየሆነ ያለው ግን የተገላቢጦሽ ነው፡፡ይዘርፋሉ ተብለው የሚገመቱት አይፈተሹም፤ ቅንጣት
ታህል ችግር ይፈጥራሉ ተብለው የማይታሰቡትን ደሞ ቆዳቸው እስኪሞሸለቅ ድረስ ሞረድ በሚመስሉ እጆች የሞረዳሉ፡፡ይህ ታድያ ‹‹ላም
ባልዋለበት ኩበት ለቀማ›› አይስብልም? ይህን መሳዩ ዘራፊዎች እንዳሻቸው የሚፈንጩበት አስተዳደር ክለፕቶክራሲ ይሉታል፡፡ የሌቦች
አስተዳደር ማለት ነው፡፡ እና ሌቦች የመዝረፍያ መሳርያዎች ይዘው ሲገቡም ሆን ዘርፈው ሲወጡ የማይፈተሹት እነርሱ የሚቆጣጠሩት ስርዓት
ስለሆነ ነው፡፡ምናልባት የሌብነት ዶሴያቸው ሊፈተሸ የሚችለው (ተቃዋሚዎች እንደሚሉት) የፖለቲካ አለመግባባት ሲፈጠር ነው፡፡እስከዛው
ድረስ ግን የቻሉትን ያህል መዝረፍ ይችላሉ፡፡
No comments:
Post a Comment