Monday, April 15, 2013

አባትህ ማን ነው?





ድሮ ህፃን እያሎሁ ነበር እቺ ጥያቄ ጨቅላው አእምሮየን ማስጨነቅ የጀመረችው።ከዕለታት በአንዱ ቀን እኔ በለቅሶ ቤተሶቦቼ በደማቅ ዕልልታ በማጀብ ወደዚች ዓለም መምጣቴን አበሰርን።ለዕድሜ እረኝነት እንደደረከስኩኝ የሆነ ነገር አያቴን ማስጨነቅ ጀመረ።ከእኩዮቼን ተለይቼ የቤት እስረኛ ሆኜ መኖር እንደማልችል ብታምንም እውነታውን እንዴት አፍረጥርጣ ትንገረኝ? እንዳትነገረኝ ንፁህ አእሞሮየን ማቆሸሹን አልዋጥልሽ አላት።ምስጢሩን ደብቃ ዝም እንዳትለኝ ደሞ እንድያ ባለማድረጓ ሊደርስ የሚችለው አደጋ እስፈራት።ሁለት አስቀያሜ አማራጮች ግን ደሞ የግድ አንዱን መምረጥ ነበረባት።

ለብዙ ቀናት ብዙ ካሰበች በኋላ አንዱን ልትነግረኝ ወሰነች።እናም እረኝተነት ውዬ ቤት እንደገባሁ ሁሌም እንደምታደርገው መክሰሴን ሰጠችኝና ትኩር ብላ ዓይን ዓይኔን ታይን ጀመር።መክሰሴን በልቼ እንደጨረስኩ ከእኩዮቼ ጋር ለመጫወት ከቤት ልወጣ ስል ጠጋ ብላ ፆግሬን እያሻሸች አውነቱን ነገረችን።እንዴት? ለምን? እኔ ምን አጠፋሁ? በጥያቄዎች ወቅያኖስ ሰምጬ ፍርሃት አይሉት ጭንቀት  እንደ ዥዋዥዌ ወድያ ወዲህ ያላጋኝ ገባ።አያቴ ለጥያቄዎቼ መልስ ሳይሆን ሌላ ተጨማሪ ጥያቄ ነበር የሰጠችኝ።
«ይስፋው ወደይ፣ ድሕር ደጊም አቦኻ መን እዩ ተቢሎምኻ ቐሺ ብርሃኑ ኢኻ ልትብል።ትምሕል ተለኻለ ስጋ ቓሺ ኢኻ ልትብል።ወዲ ገዳሙ እየ ተቢልኻ ናቦኻ ፀለእቲ ክቐትሉኻ እዮም። ድሕሪ ደጊም ገዳሙ አቦኻ የኾነይ፤ተጠንቀቕ» አለቺኝ ።ትርጉሙም እንደሚከተለው ይመስላል።«ይስፋው ልጄ፣ ከአሁን በኋላ አባትህ ማን ነው ብለው ቢጠይቁህ ቄስ ብርሃኑ ነው መናገር ያለብህ።ስትምልም ቄስ ብርሃኑ ይሙት ማለት ይጠበቅብሃል። የገዳሙ ልጅ ነኝ ካልክ የሱ ጠላቶች ይገድሉሃል።ከአሁን ወድያ አባትህ አይደለም፣ ተጠንቀቅ»

የተባልኩት ሁሉ ተግባራዊ ባደርግም ከጭንቀትና ፍርሐት የሚገላግለኝ ግን አላገኘሁም።የምወዳት አያቴ ምክር አላባከንኩትም።በእውነተኛው አባቴ ስም የሚጠራኝ ሁሉ በድንጋይ ለመፈንከት ወደኋላ አልለም፤ ፆታ፣ዕድሜ፣ የሰውነት አቋም አያስጨንቀኝም።የሚያሽንፈኝ መሆኑን ካመንኩ በማይደርስብኝ ቦታ ሁኜ በወንጭፍ! ያተግባሬ ከእርግማንና ጥላቻ ውጪ ምንም አልፈየደልኝም።

ያባቴ ጠላቶች በተግባር ባይፈፅሙትም እኔን ለመግደል እንደ አሞራ እያዣበቡብኝ መሆኑን ባማስነገር ሽብር ይለቁብኝ ጀመር።እኔ ባላውቃቸውም እነሱ ግን በዋልኩበት ባመሽሁበት ሁሉ እየተከታተሉኝ መሆኑን በዘመዶቼ አማካኝነት ያሳውቁኛል።ቀን ባይመጡብኝም ለሊት በሕልሜ ያሳድዱኛል።አያቴ በነገረችን ተረት ተረቶች ያሉ ጭራቆች ረዣዥምና ስለታም ገጀራዎች፣ትላልቅ መፍለጫዎች፣ ጎራዴ፣ቢላዋ፣ ማጭድ… አስፈሪ የሚባል ስለታም ነገር ሁሉ በእጃቸው የያዙ ሰዎች ያባርሩኛል።
በመጨረሻ ብዙ ሩጬ፣ሩጬ፣ ሩጬ በማላውቀው አካባቢ ስደርስ እገሮቼን ማንሳት ያቅተኛል። ደክሞኝ ተዝለፍለፌ ስወድቅ አንዱ በያዘው ትልቅ መፍለጫ ግንባሬን ሲፈነክተኝ «ኡ…ዪ!» በማለት የተኛሁበት ቤት በጭሆት ሳቀልጠውና ከእንቅልፌ ብንን ብዬ ስነቃ አንድ ይሆናል።የገጠር ንሮ ለሊት ለሊት ጭለማ ስለሆን ለተወሰነ ጊዜ መረጋጋት ያቅተኛል።ያኔ አያቴ በጭንቀት ልታብድ ትደርሳለች።በየፀበሉ ትወስደኛለች፤የአቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ፀበል፣የአቡነ ተክለሃይማኖት ፀበል፣የሚካኤል፣የገብሪኤል፣ የጊዮርጊስ… ብዙ ተጠመቅኩ።ፀበሉ ይሁን እያደግኩ ስለመጣሁ እንጃ ቅዠቱ እየለቀቀኝ መጣ።

ነገር ግን ጤናየ መታወክ ጀመረ።እምባላውም ሆነ እምጠጣው አይስማማኝም።አንዴ ቀርጠት፣በሌላ ጊዜ ፍልጠት፣ ራስምታት፣ተውካት፣ውጋት… የበሽታዎች ዓይነት መረማመጃ ሆንኩኝ። ሞት መዳከሜን ሲያውቅ እኔን ችላ ብሎ ሌሎችን እያሳደደ አፈር ያስግጣቸዋል።ብዙ ሰዎች ገደለ፤ አያቴ፣አክስቴ፣አጎቴ፣ታናሽ እህቴ… አረ ስንቶች! ከነዚህ ሁሉ በላይ የአያቴ ሞት ነበር በዚች ዓለም ተስፋ እንድቆርጥና ራሴን ለማጥፋት እንዳስብ ያደረገኝ። አላደረኩትም። ይህን ሁኔታየን የታዘበች እናቴ ከባሏ(የእንጀራ አባቴ) መፋጠጥ ጀመረች።ጧት ማታ ጭቅጭቅ ንትርክ ሆነ…በኔ ምክንያት።« እኔ በህይወት እያሎሁ ልጄ በጣም የሚወደው ትምህርቱን አቋርጦ ማይት አልፈልግም» በማለት የማይዛነፍ አቋሟን አሳወቀችው፤ እቅጩን ነገረችው።

ያኔ የስምንተኛ ብሔራዊ ፈተና ወስጀ ወደ ዘጠኛ አልፌሎሁ። ችግሩ ታድያ 35 ኪሎ ሜትሮችን አቋርጬ ሳልጓዝ መማር አልችልም ነበር።ስንቅ የሚልክልኝና የቤት ክራይ የሚከፍልልኝ ያስፈልገኛል።ጭንቅ ሆነ፤ እናቴ ከባሏ ልትፋታ አፋፍ ላይ ደረሰች። ይህን ስረዳ አንቺ ተፋተሽ የስደስት ሰዎች ህይወት ከሚመሰቃቀል እኔ ትምህርቱን አቁማሉሁ፤ እትቸገሪ አልኳት።በንዲህ ዓይነት አስጨናቂ ሁኔታ እያለን ነበር የትግራይ ማሕበር ልማት መቐለ በሚገኘው ቓላሚኖ የሚባል አዳሪ ትምህርት ቤት ልታስተምረኝ መሆኑን ያሳወቀቺኝ።ያ ዕድል በህይወቴ በጣም ወሳኝ ምዕራፍ ነበር።አዛ በኋላ ከመቃብር በላይ ትምህርት ማቋረጥ የማይታሰብ ሆነ።

ነገር ግን የጤናየ ጉዳይ ከመሻሻል ይልቅ አሳሳቢ እየሆነ መጣ።ወደ ክልኒክ መመላለስ አበዛሁ፣ ብዙ የመድሃኒት እንክብሎች እንደ ጉድ ዋጥኩኝ።የሽሮፕ ዓይነቶች ጠጣሁኝ።በመጨረሻ የበላሁት ሁሉ እንደ እሳት ሆዴን ያቃጥለኝ ጀመር።የመረመሩኝ ሐኪሞች ጨጓራ ነው አሉኝ።በቃ፣ ወጥ የነካው ምግም መብላት ጭራሹን አቆምኩ።ምግቤ ዳቦ ብቻ ሆኑ።በጣም ከሳሁ፤ ግልበት አጣሁ።እንዳልበላ ያመኛል፤ዝም እንዳልል ይርበኛል… ሌላ የህይወት ፈተና።

በዚህ ግዚ ነበር «አባትህ ማን ነው?» የሚለው ህፃን እያሎሁ የተጠየኩት ጥያቄ መልሼ ራሴን መጠየቅ የጀመርኩት።ቀኑን ባላስታውሰውም በ1990 ዎቹ መጨረሻ የፃፍኳት ትንሽየ መጣጥር ይህችትና።
ውድ አንባቢሆይ ፣ የልደት ቀንህን በትክክል ታወቀዋለህ? መልስህ አዎ ነው? እርግጠኛ ነህ? እንድያማ ከሆነ ስትወለድ ታውቅ ነበር ማለት ነዋ።እንድም «ጂኔስ» ነህ አልያም ዕድለኛ። ታድለህ፣ በየዓመቱ የልደት ቀንህን ታከብራለህ ማለት እኮ ነው።እኔ ግን እንኳንስ ላከብረው ጭራሹንም ትዝ አይለኝም።

ዓመተ ምህረቱን ባታውቀውም ዕለተ ቀዳሜ፣ ጥር 23 ቀን እንደ ተወለድኩኝ እናቴ ነግራኛለች።የተወለድኩበት ዓመተ ምህረት ባማወቅዋ ቅር አይለኝም።ምክንያቱም እናቴ እንደኔ ተምራ ማንበብና መፃፍ የምትችልበት ዕድል አላገኘችም። ብያንስ በኩር ልጇን ለመገላገል ያማጠችበትን ቀን አልረሳችም።አባቴ መሆኑን አስራ ምናምን ዓመት ሲሞላኝ ሰዎች ያስተዋወቁኝ ሰውዬ ቀኑም ሆነ ዓመተ ምህረቱን አያውቀውም።ግንኮ ፊደል የቆጠረ ሊቅ ነው እየተባለ የሚወራለት ከባላባቶች የሚወለድ ቀጭን ጌታ ነው።የቀኛዝማች ልጅ ስለኔ ምንም ነገር አያውቅም።

አበራሽ የምትባል ታናሽ እህት ነበረችኝ።ነገር ግን የዚህ ዓለም ፈተና ማለፍ ስላልቻለች በትክክል መናገር እንኳን ሳትችል ነበር ዳግም ላትነሳ ያንቀላፋችው።በጣም ውብ ነበርች።እግዚሔር ቀናተኛ ነው ይባል የለ? ውበቷ አማልሎት እንደ እምቡጥ ፅጌ ረዳ ሙሉ በሙሉ ሳታብብ ቀጥፏት ይሆናል። እኔን ግን አይወደኝም፤ እንዲወስደኝ ብዙ ጊዜ አባብየው አሻፈረኝ ብሎኛል።

እግዚሔር ሁሉም አዋቂ፣ሁሉም ቻይ፣ ጊዜና ቦታ እንደማይወስነው ይነገራል።ደሞ ቀናተኛና በቀለኛ ነውም ይበላል።ታድያ ከኔው በምን ይሻላል? ያለጥፋቴ፣ ያለሐጥያቴ ሲያሳድዱኝ ከነበሩ ሰዎችስ በምን ይለያል? እኔስ ቅናት፣ንዴትና ቂም አይደሉም ቆሽቴን የሚያቃጥሉት? አባቴ ባጠፋው ጥፋት እኔን ለመግደል ሲያሴሩ የኖሩት በቀለኞች ስለሆኑ አይደለም?

 ቀናተኛ፣ምቀኛ፣ቁጡ፣ርህሩህ ወዘተ እያሉ የሚሽቆጠቆጡለት አምላክ የኔ አምላክ ሊሆን አይችልም።ምክንያቱም ከልክ በላይ ስሜታዊና ግልፍተኛ ነገር ነው።በስሜት እንጂ በምክንያት አያምንም።ድስ ላሰኘው፣ «በኢጎው» ለተጫወተበት የሾማል፣ ባለሃብትና ጥበበኛ ያደርጋል…እስራኤን ያወርሳል፤ከዛም ወደ ገነት። ላስቀየመው ግን ያሳድዳል፣ያሰቃያል፣ባርያ ያደርጋል።ይበቀላል፤ ወደ ግሃንመ እሳት በመወርወር።በቀሉ እስከ ሰባት ትልዶች ያቀጥላል።

ስማ አንተ፣ ከዛሬ ጀምሮ አላመልክህም፤ ከፈለግክ አሁንኑ ፈንግለኝ።ችሎታህ ይህ ነውና።ዘላለማዊ ህይወት ትሰጣለህ ሲባል ብሰማም እህቴን ዓይኖቿን ሳትገልጥ፣አፍዋን ሳትከፍት ነበር የቀጨሀት።እንኳንስ ዘላለማዊነት የአንድ ሰው ዕድሜ ለመስጠትም በፍጥረታት ደም የተጨማለቁ እጆችህ አልተፈቱም።

የኔ አምላክ ፍፁም ነው።ቁጣ፣ቅናት፣ምቀኝንት ወዘተ የሚባሉ የደካሞች ባህርያት አይገልፁትም።ደግሞ«አባትና እናትህን እክብር» ትለኛለህ፤ ከአስርቱ ትእዘዛትህ በአራተኛው።ቆይ አባቴ የት አውቀዋሎሁና ነው እማከብረው?እናቴስ? አሳዳጊዎችህ ለማለት ፈልገህ ከሆነ ንገረኝ።አለዚያ ወልደው ለአሳዳጊዎች የሚያስረክቡ በጣም ብዙ መሆናቸውን ታውቅ የለ?ሰዎች ይሀውና አባትህ ይህ ነው ስላሉኝ ብቻ አሜን ብዬ መቀበል አለብኝ? በምን እርግጠኛ እሆናለሁ?

ወይጉድ! ደሞ «ዲኤንኤ» ምርመራ ምናም ልትለኝ ይሆናል።ታድያ የመመርመርያ መሳርያው ሳትፈጥር ለምን በሰባተኛው ቀን ተኛህ ጃል?ይህን ግኝትስ ውሸት መሆኑን የሚያረጋግጥ ሌላ ግኝት አለመኖሩን እንዴ እርግጠኛ መሆን እንችላለን?«እናትና አባትህ በሚያደርጉልህ ልዩ እንክብካቤ ወላጆችህ መሆናቸውን ማወቅ ትችላለህ» ያልከኝ መሰለኝ።ታድያ ሁሉም የጉዲፊቻ አሳዳጊዎች መጥፎናቸው ያለህ ማን ይሆን? በመስተንግዶ በጣም የተወራላቸው ሐበሾች ይቅርና በቀለም የማይመሳሰሉን ፈርንጆች በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ህፃናት በጉዲፊቻ ለማሳደግ እየተሻሙ መሆኑን አታውቅም?

ስለዚህ ከዛሬ ጀምሮ የኔ እምነት ሰው የዘራውን ያጭዳል የሚል ይሆናል።አዎ! የፈለግከውን ማድረግ ትችላለህ፤እስላሙ፣ክርስትያኑ፣ቡድሂስቱ፣የሁንዲዝም ተከታዩ፣የአይሁድ አማኙ፣ ኢአማኙ ሁሉም እኩል ናቸው።የተረገመ ወይም ተባረከ ዘር ብሎ ነገር የለም።ባርያ፣ቡዳ፣ጭዋ … ወዘተ የሚሉ ኋለ ቀር ታርጋዎች በሰው ልጆች ላይ መለጠፍ ጅልነት ነው። ሰዎች ያው ሰዎች ናቸው፤ የዘሩትን ያጭዳሉ በቀጥታም ሆነ በዘወርዋራ።አለዚያ ላንዱ አንግሰህ ሌላውን ባርያ ማለትህ አምባገንነት ነው፤አጥብቄ እቀወመዋለሁ።ስለዚህ አባትና እናቴን እማከብረው ሲያከብሩኝ ብቻ ነው።ካልሆነ ግን እንሱ እንደጎዱኝ እኔም ባልጎዳቸውም ያልዘሩትን እንዲያጭዱ አልፈቅድላቸውም።

ማንኛውም ሰው ወልዶ ማሳደግ የማይችል ከሆነ መውለድ የለበትም።እግዚሔር ያውቅል፣በዕድሉ ይደግ ብሎ ነገር መቆም አለበት።ከወለደ አፈር ልሶ ስራስር ምሶም ቢሆን ማሳደግ አለበት፤ ግዴታ ነው።እኔ ፈጣሪ ብሆን ንሮ ወልደው የማያሳድጉትን ሁሉ ብልቶታቸውን ሽባ አደርግባቸው ነበር።ወለደው የሚያሳድጉትንም በተቃራኒው የማይደበዝዝ ዘላለማዊ ፍቅር እሰጣቸው ነበር።

«የጀነቲክስ» ወይም ዘረ መል ባለሞያዎች ፍቅር የጅኖች የተፅዕኖ ውጤት ነው ይላሉ።አንዲት እናት የእርግዝናን ድካም ለዘጠኝ ወራት ችላ፣ የምጥ ስቀይ ተቋቁማ ወልዳ፣ጡቶቿን አጥብታ እንድታሳድግ የሚያስገድዳት የጅኖች ዘርን የመተካት ጫና ነው በማለት ይሞግታሉ።ምክንያቱም የዘረመሎች(ጅኖች) ተፈጥራዊ ልዩ ባህሪ ራስን መተካት ነው።ይህ ራስን የመተካት ግብታዊ ሀይል ነው እንግዲህ ወንድና ሴት በፍቅር አማካኝነት አጣምሮ፣ ወልደው ከብደውና የሞቀ ቤተሰብ መስርተው እንዲያልፉ የሚያስገድደው።

ሳይንሱ የፈለገው ማለት ይችላል፤ እውነትም ይሁን ውሸት ግድየለኝም።ይህን ሁሉ ምሬቴን በፅሑፍ የዘከዘኩት ከአስር ዓመታት በፊት ነው።ከምችለው በላይ ከፍቶኝ በንበረበት ጊዜ ስለነበር ከአሁኑ እምነቴ ጋር በጠኑም ቢሆን የሚጋጩ ሐሳቦች አሉ።ሆኖ ግን እንደዚያ እንዳስብ ያደረገኝ የቤተሰብ የፍቅር እጦት ስለነበር እንናንተ ልጆቻችሁ በፍቅርና በእንክብካቤ ያሳደጋችሁና በማሳደግ ላይ ያላችሁ፣ እንዲሁም ወልዳችሁ በቻላችሁት መጠን አቀማጥላችሁ ለማሳደግ የቆረጣችሁ ሁሉ በልጆቻችሁ ስም እጅግ በጣም አድርጌ አመስግናቿሎሁ።በልጆቻችሁ አማካኝነት ፍቅር የዘራችሁ ሁሉ የፍቅር አዝመራ ይበርክትላችሁ።

                                                                            
                                                                            
                               እለተ እሁድ፣ ማዝያ 6 ቀን 2005 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment