ዓርብ ማታ
ከአከራዮቼ ልጆች አንዷ ጴንጤ ነች።የሰላሳዎቹ
የዕድሜ ክልል አጠናቅቃ ወደ አርባዎቹ የተጠጋች ትመስላለች።ነገር ግን ልጅም ሆነ ባል የላትም።ፀገሯ ልክ እንደ ቁመቷ አጭርና ሳሳ
ያለ ነው።በዊግ ቀጣጥላ ረዥምና ብዙ ለማስመሰል ብትጣጣርም የባሰ ያስጠላባታል።አሻንጉሊት ያስመስላታል።ገፅታዋ«ጠይም ዓሳ መሳይ»
ነገር ነው፤ቢሆንም ግን በኮስሞቲክስ ብዛት ሳይሆን አይቀርም ወዘናው ጠፍቷል።አብዛኛው ጊዜ ደግና ርህሩህ ብጤ ነች፤አመለ ሸጋና
ሆደ ባሻ ነገር።
ቤተ ክርስትያን ( እርሷ church ነው የምትለው) ሂዳ «የእየሱስ ቃል»
ሰምታ ስትመጣ ግን የተለየ ባህሪ ታመጣለች።የእየሱስ ስም ደጋግማ በማንሳት አንዱን እያነሳች ሌላው እየጣለች፣ራሷ ጠይቃ ራሷ እየመለሰች፣አንዱ
የጴንጤ ሞዝሙር ክፍታ የቴፑ ድምፅ ሙሉ በሙሉ እየለቀቀች፣ ደግሞ ያኛው ሳያልቅ በሌላ እየቀየረች…በቃ የምትሆነው ታጣለች።ወደ ቤቷ
ትገባና መልሳ ደግሞ አፍታኳን ሳትቆይ ትወጣለች።ሽንት ቤት ትገባና በመስታወቱ ፊት ለፊት ተገትራ ራሷን ስታይ ቆይታ ስለ ሽንት
ቤቱ መቆሸሽ፣ ማን ገብቶ እንደወጣ፣ «ምን ዓይነት እንስሳ ነው በየሱስ ስም» በማለት ትጠይቃለች፣ደጋግማ ትምላለች፣ እንዲሁም ትገዝታለች።ያኔ
ማንም ተከራይም ሆነ ሌላ ትንፍሽ አይልም፤ እናቷም ጭምር። ዓለም በአንድ እግሯ የቆመች ነው የሚመስለው።ዓርብ ማታ እንዲሁ ነበር
ስትሆን ያመሸችው።
መጀመርያ በነሱ ግቢ ተከራይቼ ስገባ
አንድ ታላቅ ወንደሟ ስለነበረ አንዲት ቃል አትተነፍስም ነበር።ጭራዋን በሁለት እግሮቿ መሃል ሽሽጋ የምትሸሽ ውሻ ነበር የምትመስለው።«
አንቺ ጴንጤ!» ይላታል፤በወጣ በገባ ቁጥር።ያን ጊዜ እምትገባበት ታጣ ነበር።እርሱ ተከራይቶ ይሁን ወደራሱ ቤት ከወጣ ወዲህ ግን
እናትና ልጅ እየተፈራረቁ ግቢው ሰላም አሳጥተውታል።በግቢው ውስጥ አንድ ወንድና ስድስት ሴቶች ይኖራሉ፤ ከሶስት ተከራዮች ጋር።የቤቱ
ፈላጭ ቆራጮች ግን እማወራዋና ጴንጠዋ ናቸው።ሌሎቹ ሰዎች ሲወጡና ሲገቡ እንጂ አንዳችም ቃል ሲተነፍሱ አይሰማም።
ቅዳሜ ጧት
የቤቱ እማወራ ሁል ጊዜ እንደሚያደርጉት
በ200 ሜትር ርቀት የሚገኘው የዮሐንስ ቤተ ክርስትያን ተሳልመው መጥቷል።እርሳቸውም ልክ እንደ ጴንጠዋ ልጃቸው ዓይነት ባህሪ ነው
ያላቸው።በመልክ፣በቁመናና በሴትነት መዓርግ ግን የትም አይገናኙም።በርሷ ዕድሜ እያሉ ይቅርና ሽማግሌ በሚባል ዕድሜ ሁነውም በጣም
ይበልጧታል።በአብዛኛው ጊዜ በግ ነገር ናቸው።ነጭ በነጭ በሆነ የሐበሻ ባህላዊ አለባበስ አሸብርቀውና ነጭ እርግብ መስለው ወደ ቤተ
ክርስትያን ይበራሉ።
አንዳንዴ ግን የጂኒ ፈረስ ይመስላሉ።ቀንድ
ያበቅላሉ።በሆነው ባልሆው ይጮሐሉ፣ያራገማሉ፣ ይገለፍጣሉ።እርሳቸውም ልክ እንደ ልጃቸው የሽብር ክፍለ ጊዜው አዘጋጅና አቅራቢ ይሆኑና
መሬት ቆውጢ ያደርጓታል።
የርሳቸው የቁጣ መዓት ተጠቂ የቤት ሰራተኛቸው ነች።ሆድ ሲብስባቸው ከምንም ተነስተው እንጀራው አያምርም፤ዓይን
የለውም፣ቀጠነ፣ወፈረ፣ አረረ ምናም፤ ወጡ አይጣፍጥም፣ጨው የለውም ወይም በዛበት… እያሉ የእርግማንና የስድብ እያሪኮ ያወርዱባታል።ሰራተኛዋ
ግን ትንፍሽ አትልም።ሰምታ እንዳል ሰማች ዝም ጭጭ።ድሮ በየሳምንቱ ነበር የቤት ሰራተኛ የሚቀያይሩት፤እንዲህ አንዳቸው ሲጮሁባቸው
ቤቱን ጥለው ይወጣሉ።የአሁኗ ግን ገራገር ነገር ነች፤በመጣባቸው ቁጥር ልጅና እናት በሚያቀጣጥሉት የእሳት ወላፈን እየተጠበሰች እንደ
አመጣጡ እየቻለች ወራት ብቻ ሳይሆን ዓመትም ሳታስቆጥር አትቀርም።ዓርብ ማታና ቅዳሜ ጥዋት ከልጅና ከእናት የተወረወሩት የቃላት
ቦምቦች ብታስተናግድም ይሀው ዛሬም አለች።
ቅዳሜ ከስዓት
በፌስቡክ እየተናፈሱ ያሉ «የበሬ
ወለደ» ወሬዎች ከልክ በላይ ተሰላችቼሎህ።ፖለቲከኞችና ደጋፊዎቻቸው ቁንጫውን በሬ፣በሬውም ተራራ በማስመሰል የቀሽሞች ፕሮፖጋንዳ
ይነፋሉ።ጉንበት ሰባቶች ኢህወዴግ-ዲ ተመስረቷል ይላሉ።ኢህወዴጎች ደግሞ ጉንበት ሰባት-ዲ ተፈጥሯል በማለት የመልስ ምት ይሰጣሉ።ተቃዋሚዎችና
የመንግስት ደጋፊዎች ሁለቱም እንደ በዶ ቤርሜሎች ትንሽ በተነኩ ቁጥር ከፅናፍ እስከ አፅናፍ ያስተጋባሉ።የገደል ማሚቶው ከአንዱ
ፅንፈኛ ወደ ሌላው ፅንፈኛ ሲያስተጋባ በአከባቢው የሚገኙ ሰላማዊ ዜጎችን ሰላም ይነሳል፤ ያቅለሸልሻል።
«ሃይማኖተኞቹ» «ከአንዱ ጫፍ የእምነት
ነፃነታችን ተነጠቅን» በማለት ይጮሃሉ።በሌላው ጫፍ ደሞ «ነብዪ አልያስ አራት ኪሎ ይገኛል።ቡና ሲጠጣ አግንቼው ለምእመኑ እንዲህ
ብዬ እንደናገር አዞኛል።» የሚል ጭሆት ያስተጋባል።ጭሆቱ አሁንም ይቀጥልና « በዓሉ ግርማ በህይወት አለ፤ዓለም በቀኝ ብሎ በጣና
ሃይቅ በሚገኝ አንድ ገዳም በምናኔ ይኖራል።ዴርቶ ጋዳ፣ራማቶራ፣ዣንቶዣራ፣ተልሚድና ሌሎቹም መፃሕፍት ፅፎ በይስመዓከ ወርቁ ስም አማከኝት
እንዲ ወጡ ያደረገው እርሱ ነው።» ይላል።
ፖለቲከኞችና ሃይማኖተኞች እንደ
ሃይለኛ ጠጪ ፊኛ በውሸት ተወጥረዋል።በዚህም በዚያም በየቀኑ የሚቃዠው ቁጥር እንደ አሸን ፈልቷል።አንዱ የቃዠው ሌላው ቅዠታም በማጋነን
ያስተጋባዋል።ውሸታሞችና ቅዠታሞች ለትልቅ ሽልማት የሚፎካከሩ ነው የሚመስለው።ጨዋታው ማን ደግ ሰራ ማንስ ተሳሳተ አይደለም፤ የማን
ቀደዳ ከአድማስ አድማስ አስተጋባ ነው።በዚህ ምክንያት በፌስቡክ የማጠፋው ጊዜ ከቀን ወደ ቀን እየተመናመነ ይገኛል።እንደውም ራሴን
ሳላጠፋ አልቀርም።ታድያ ከዚች ዓለም አለመሆኑን ይታወቅለኝ፤ራሴን እማጠፋው ከፌስቡክ ብቻ ነው።
ቅዳሜ ጧት በነዚህና በሌሎች የሐሳቦች
ማዕበሎች ግራና ቀኝ ስናጥ አርፍጄ ከሰዓት ለመማር ወደ ክፍል («ክላስ») አመራሁ።አንደኛው ክፍለ ጊዜ የተማሪዎች «ፕረዘንቴሽን»
ነበር።አንዷ ተማሪ አሮንጓዴ ሱሪ፣አሮንጓዴ የጥፍር ቀለምና በግራና ቀኝ ክንፍያለው የሚመስል ግራጫ ሸሚዝ አድርጋ ዊግ ምናም ስትል
ደረስኩ።መጀመርያ ትንሽ ግር ብሎኝ ነበር፤የፀጉር አሰራር ዓይነቶች ያምታወራ መስሎኝ።
ሁለተኛው ክፍለ ጊዜ ከአስር የሚያዝ
ፈተና ተፈተንን።ምን ዓይነት ፈተና? ሌላ ጊዜ እመለስበታሎሁ።
በሶስተኛው ክፍለ ጊዜ አስተማሪው
ላፕቶፑን አየጎረጎረ ትንሽ ጊዜ ስለወሰደ አንዱ ተማሪ ከምፒተሩ አስክት ከፍት ድረስ የሆነ ነገር እናውራ ብሎ ስለተማፀነ የሰሙኑን
የፌስቡክ በሬ ወለደ ተነሳ።የበዓሉ ግርማ በጣና ሐይቅ ከሚገኙ ገዳሞች በአንዱ ሞንክሶ መኖር ለማሳመን ሰንካላ የሆኑ ምክንያቶች
ተነሱ።ልክ እንደ ፌስቡክ አንዱ እውነት ነው ወይም ሊሆን ይችላል ይላል ሌላው መሰረተ ቢስ ውሸት ነው በማለት ይሞግታል።ነገር ግን
ስምምነት ላይ ሳይደረስ ወደ መደበኛው የትምህርቱ ርእስ ተገባ።
በዕለቱ የተወያየንባቸው ርእሶች
እውነት ስለመናገር፣ማንኛውም ነገር በትክክል ስለመግለፅ፣ራስን ችሎ በራስ አቋም ስለመመራት፣ስለተጠያቂነት፣ስለፍትሐዊነት ወዘተ የሚያወሱ
ነበሩ።
በጣም ያስገረመኝ ግን በፌስቡክ
ስለሚናፈሱ አልቧልታዎች ብያኔ መስጠትና አቋም መያዝ አቅቶን ስለእውነት፣ፍትሕና እኩልነት ምንነት መዘባረቀችን ነው።አንዱን በጭፍን
እየተቃወሙና ሌላውን በጭፍን እየደገፉ እንዴት ነው እውነት መናገር የሚቻለው?ፍትሕና እኩልነትስ ከየት ይመጡ? አንዱ ከመሬት ተነስቶ
ሲገላፍጥ ሌላውም ያንኑን የሚያስተጋባ ከሆነ መማራችን ምን ዋጋ አለው?ለዝያውማ ተራሮች አሉ አይደል? «አረ ጉድ ነው፣ጉድ ነው፣ጉድ
ነው…» ያለው ማን ነበር?
ቅዳሜ
ማታ፣ መጋቢት 5 ቀን 2005 ዓ.ም
No comments:
Post a Comment