Sunday, December 29, 2013

የኢትዮጵያ ገዳይ ማን ነው?





ክንፍ አስወጥቶ የሚያስበርር ፍቅር በታዘብኩና በሰማሁ ቁጥር አንድ በጣም የቆዬ አባባል ሁሌም ትዝ ይለኛል፡፡ አባባሉ ‹‹የገደልኳት ስለወደድኳት ነው››(I killed here because I love her) የሚል ነው፡፡ይህ አባባል ለብዙ ዓመታት ከህሊ የማይጠፋ ቢሆንም ትርጓሜው እርሰበርሱ የሚጋጭ በመሆኑ ግን በቀላሉ ሊዋጥልኝ አልቻለም፡፡ምክንያቱም የሰው ልጅ የሚወደውን ከሞት ለማዳን ይሟሟታል እንጂ ለመግደል ይጨክናል ብዬ ስለማላምን ነው፡፡
እኔ እስከማውቀው ድረስ ጥላቻ ከቁጥጥር ውጪ ሲሆን ግድያን ያስከትላል፤ ለመግደል የሚያደርስ ጥላቻ መሸከም የጤና ነው ብዬ ባላምንም፡፡ፍቅር እየጎለበት ሲሄድም ደግሞ ራስን አሳልፎ እስከ መስጠት ያሰኬዳል፤ አማራጮች ሁሉ ተሟጥጠው ሲያልቁ ለሚወዱት ሰው ሲባል ራስን አሳልፎ መስጠት የነበረ፣ያለና ለወደፊትም የሚኖር ይመስለኛል፡፡
ይህ የሚሆነው ጠኔኛ አእምሮ ላላቸው ሰዎች ነው፡፡የሰው አእምሮ ሲቃወስ ግን ማፍቀርም ሆነ መግደል ልዩነት አይኖራቸውም፡፡ጨርቁን ጥሎ ያበደ ሰው ቫይረስ እንደ ተቆጣጠረው ኮምፒተር የሚያደርገው ሁሉ ግራ ያጋባል፡፡ደምር ስትለው ይቀንሳል፣ቀንስ ስትለው ይደምራል፤አባዛ ስትለው ያካፍላል፣ አካፍል ስትለውም ያባዛል፡፡የከፈትከው ነገር ይዘጋብሃል፣ያልከፈትከው ወይም ያልፈለግከው ነገር ይከፍትብሃል፡፡በአጠቃላይ የታዘዘው ሳይሆን ያልታዘዘው ነገር ያከናውናል፡፡
ከዚሁ አባባል ጋር ተመሳሳይ የሆነ የትርጉም፣የድርጊቶችና የአስተሳሰብ ግጭት ያለው የእንግሊዘኛ ግጥም ከኣንድ ዓመት በፊት በአንድ ድረ ገፅ ላይ ማንበብየን ትዝ ይለኛል፡፡ዛሬም ይኸው አባባል ትዝ ሲለኝ ጊዜ ግጥሙን ድጋሚ የማንበብ አምሮቴ ገፋፋኝና ግጥሙን እንዲፈልግልኝ ጎጉልን ተማፀንኩት፡፡ ጎጉል አላሳፈረኝም፤ጎልጉሎ አገኘው እና የኸው አለኝ፡፡ደጋግሜ እንዳነበብኩትም ይህችን ፅሑፍ ለማዘጋጀት ወሰንኩ፡፡
የግጥሙ ርእስ ‹‹የፖርፊርያ ወዳጅ››(Porphyria's Lover) ሲሆን ሮበርት ብሮውኒንግ በተባለ እንግሊዛዊ በ19ኛ ክፍለ ዘመን እንደ ፃፈው ይነገራል፡፡የግጥሙ መልእክት በጣም ግልፅና የተዋንያኖቹን አስተሳሰብና ድርጊት እንዲሁም ድርጊቱ የተፈፀመበት ቤትና አከባቢውን እንደ ፊልም ፍንተው አድርጎ ያሳያል፡፡ በሮውኒንግ ግጥሙን ሲጀምረው ወደ አንዲት በዛፎች የተከበበች በሃይቅ አጠገብ የምትገኝ ቤት በሃሳብ ይወስደናል፡፡አከባቢው ሃይለኛ ንፋስ በተቀላቀለው የዶፍ መዓት ሲወርድበት፣ሃይቁ በወጀብ ሲናወጥ ከዛም ፖርፊርያ ክፍት ወዳ ነበረችው ቤት በመግባት በሩን ስትዘጋው ንፋሱና ብርዱ ባንዴ ፀጥ ረጭ ሲል፣ቤቱም በወጀብና በብርድ መትክ በሙቀት ሲሞላ በዓይነ ህሊና ኮለል ብሎ ይታያል፡፡
ከዛም ፖርፊርያ ፍቅረኛዋን ተምበርክካ በመስገድ ሰላም ትለዋለች፡፡ ተነስታም በዝናብ የበሰበሱ የላይኛው ልብሶችዋን አወላልቃ ወደ ፍቅረኛዋ በመቅረብ ትጣራዋለች፡፡ መልስ ሳይሰጣት ሲቀርም ሄዳ ከአጠገቡ ትቀመጣለች፤እጆቹን በመሳብም በወገብዋ ታጋድማቸዋለች፡፡ አንገቱን ሰበር በማድረግም በትክሻዋና በለስላሳው ፀግሯ ዘምበል እንዲል በመጋበዝ እንዴት እንደምትወደው ታጉተመትማለች፡፡ፍቅረኛዋ ግን ይህን ሁሉ የሚታደርገው በጣም ስለምትወደው መሆኑን ቢያውቅም ለዝያ ሁሉ ውለታዋ ረዥሙ ፀጉሯን በአንገትዋ ሶስት ግዜ አክርሮ በማዞር አንቆ ይገድላታል፡፡
ቀጥሎም  ስለ ሬሳው ያፈጠጡ ሰማያዊ ዓይኖች፣ ወርቃማና ረዥም ፀጉር እንዲሁም እርሷን በመግደሉ የተሰማው ደስታ ለራሱ ያነበንባል፡፡አንቆ ሲገድላት ምንም ዓይነት ተቃውሞ ባለማድረጓም እርሷን መግደሉን እንደወደደችለት ይመሰክራል፡፡ከዛም ሬሳዋን ታቅፎ ሌሊቱን ሙሉ ቁጭ ብሎ ማደሩንና ፈጣሪውም ምንም እንዳላለው ሲገልፅ ግጥሙ ያልቃል፡፡
የዚህኛው ግጥምና ከላይ ለማብራራት የሞከርኩት አባባል ባሰብኩ ቁጥር ታድያ ‹‹ኢትዮጵያን የገደልኳት ስለምወዳት ነው›› የሚሉት አጉል ፈሊጥ በህሊናየ ያንቃጭላል፡፡
ኢትዮጵያ ፍቅር ነች፤ የፍቅር ሃገር ነች፡፡በህዝቦችዋ ደግነት፣በመልክአ ምድራዊ አቀማመጧ፣ በአየር ፀባይዋ፣ በቁሳዊና መንፈሳዊ ቅርሶችዋ ከዓለም ቀደምት ሃገሮች ትመደባለች፡፡ይሁን እንጂ እቺ ምስኪን ሃገር በፍቅር አሳድጋ ያነገሰቻቸው መሪዎች አብዛኞቹ አምባገነኖች መሆናቸውን ነው የሚታወቀው፡፡አፄ ዮሃንስ አራተኛ እንደሉት ‹‹ኢትዮጵያ እናት፣እህት፣ ሚስት እንዲሁም ልጅ ነች››፡፡ይሁን እንጂ ለእናትና ለእህት ደግነት፣ርሕራሔና ቸርነት የሚሰጥ ፍቅርና አክብሮት፣ለሚስትና ለልጅ የሚከፈል መስዋእትነት የንሮ አጋርነት ያህል አልተከፈለላትም፡፡
በእርግጥ ብዙ ጀግኖች ደማቸውን አፍስሰውባታል፣አካላቸውን ጎድለውባታል ህይወታቸውም ገብረውላታል፡፡እነዝያ ጀግኖች መቃብር ውስጥ ከተውና ላአውሬ ሰጥተው በህይወት የተረፉት ግን ሃገሬ ሃገሬ እያሉ ደጋግመው ሾጧታል፡፡ከሃገር በታች እንድትሆን አድርጓታል፡፡እንደ መዥገር ተጣብቀው ደሟን በመምጠጥ አጥንት አትፏታል፡፡ሲናገሩ ግን ኢትዮጵያን እንደ እነሱ የሚወዳት ያለ አይመስልም፡፡
አብዛኞቹ ለኢትዮጵያ የነበራቸውና አሁንም ያላቸው ፍቅር በቃላት አሳምረው ይናገራሉ፡፡በተግባር ሲታይ ግን ደጋግመው ሲገድሏት፣ ገድለው ሲያበቁም በፍቅር እያንቆለጳጰሱ ወደ ማትወጣበት ድህነት፣የእርሰ በርስ መጠላለፍና የለየላቸው አውዳሚ ጦርነቶች ሲከቷት ነው የሚታየው፡፡በዚህ መክንያትም ሃገራችን እስከ ቅርብ ግዜ ድረስ የጦርነትና የድህነት ተምሳሌት ተደርጋ ትወሰድ እንደ ነበር ይታወቃል፡፡
ያ ሁሉ መከራና ስቃይ ሲያደርሱባትና በመጨረሻም አጥንት ብቻ አስቀርተው ሲገድሏት ግን በእነሱ ተግባር እንደ ተደሰተች ነው የሚገባቸው፡፡ልክ  የፖርፊርያ ፍቅረና እንዳደረገውና ኋላም ላይ ለራሱ እንዳነበነበው፡፡ አሁን አሁን ለዘመናት በእርሰ በርስ ጦርነትና ተደጋጋሚ ረሃቦች ስትጠበስ ኖራ ከእንቅልፏ እንደ ምትነቃ እያንሰራራች ትገኛለች፡፡ ይህ ግን ‹‹የኢትዮጵያ ከኛ ወድያ ወዳጅ ላሳር›› ብለው ለሚያምኑ ወገኖች የእብዶች ቅዠት ነው፡፡
‹‹ኢትዮጵያ ሃገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ
የደማልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ››

እቺ ባለ ሁለት መስመር ግጥም ማን እንደ ቋጠራት አላውቅም፡፡ይሁን እንጂ ገጣሚው የኢትዮጵያ ታሪክ ከመጀመርያው እስከ መጨረሻው የሚያውቅ ይመስለኛል፡፡በሃገራችን የታሪክ እውቅና የሚያገኘው ታሪክ ሰሪውን ሳይሆን ታሪክ ፀሓፊውን ወይም እንዲፃፍ የዘዘውን ነው፡፡ታሪካችን ከሃዲዎችን በዘፈን፣ሀወልቶችን በማቆም፣ ፊልሞችን በመስራት ወዘተ ያሞግሳል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ለሃገራቸውና ለወገናቸው የቆሰሉትንና የሞቱትን ያ ስብእናቸውም ጭምር አብሯቸው ወደ መቃብር እንዲወርድ ይደረጋል፡፡
ለምሳሌ የድሮ ነገስታት ድንጋይና እንጨት መጥረብና ብረት መቀጥቀጥ ይቅርና የሚጠጡትን ውሃም በራሳቸው ቀድተው እንደማያውቁ ይታወቃል፡፡የእነሱ ስራ ተራራ የሚያክል ስም ተሸክሞ በሌሎች እጅ መብላትና መጠጣት ነበር፡፡የሁን እንጂ በሃገራችን ያሉ ታዋቂ ስነ ህንፃዎች በእነሱ ስም ነው የሚጠሩት፡፡የጎነደሩ ፋሲለደስ ቤተ መንግስት(በአፄ ፋሲለደስ)፣የላሊበላዎቹ ውቅር አብያተ ክርስትያናት( በንጉስ ላሊበላ)፣አብራሃ ወ አፅብሃ ውቅር ቤተ ክርስትያን(በአብራሃ ወ አፅበሃ) ወዘተ በዛኛው ዘመን በነገሱ ነገስታት የሚጠሩ ናቸው፡፡ይሁን እንጂ አንዲት ጠጠር አንስተው እንደማያውቁ ግን ግልፅ ነው፡፡የህንፃው መሃንዲስ ማን እንደሆነ፣እነማን ምን ዓይነት መሳርያ ተጠቅመው  እንዴት እንደገነቡት ግን አይታወቅም፡፡ምክንያቱም የሃገራችን ታሪክ ለተናገረው እንጂ ለሰራው አይዘገብማ፡፡
አሁን የአክሱም ሃወልቶችና የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያኖች ከአፈ ታሪክ በስተቀር ማን እንደ ሰራቸው፣እነዝያ ድንቃ ድንቅ ቅርሶች ምን ዓይነት መሳርያ ተጠቅመው እንደ ሰሯቸው ቢታወቅ ንሮ ሌሎች ብዙ ድንቃ ድንቆች መስራት ያቅተን ነበር? እነዝያ ከአንድ ወጥ ቋጥኞች የተሰሩት ሃወልቶችና አብያተ ክርስትያኖች የሰሩ ጥበበኞች ግን ለነገስታቱ ስሞች ሲባል መስዋእት ሁነው ቀርቷል፤ ከነ ጥበባቸው ጋር፡፡
በኛ ሃገር ሁሉም ነገር የተገላቢጦሽ ነው፡፡የሚናገረው ሲሰራ አይታይም፤ ስራው መናገር ብቻ ይመስሏል፡፡የሚሰራው ደግሞ አይናገርም፤ ለወሬ ጊዜ አይኖረውምና፡፡ታሪካችንም እንዲሁ የተገላቢጦሽ ነው፡፡ታሪካችን አናጢውን ግንበኛ!...ሞደሻ፣ማጭድ፣ማረሻ፣ገጀራ፣ብረት ድስት ወዘተ ሰሪው ቀጥቃጭ(ቡዳ)!... ጋቢ፣ነጠላ፣ቀሚስ፣መቀነት ወዘተ የሚሰራውን ሸማኔ(ክር በጣሽ)! … ነግዶ አድራፊውን መጫኛ ነካሽ!...አርሶ አደፋርሶ ጎተራ(ሆድ) የሚሞላውን አፈር ገፊ!... ለአገሩ ዘብ የሚቆመውና ህይወቱን የሚገብረውን ነፍጠኛ! በአጠቃላይ ለሃገሩ የሚኖረውን ሁሉ ይኮንናል፡፡

እነዚህን ሁሉ ሲያሽሟሟጥጡና ሲያጣጥሉ እንዲሁም እንደ የግል እቃዎቻቸው ቆጥረው ሲኮፈሱባቸው የኖሩትን ግን እንደ መላእክት ተአምራት ሰሪዎች አድርጎ ይስላቸውል፡፡በተረት ተረትና በልበ ወለዶች ይክባቸዋል፤ የኛ ታሪክ፡፡ብዙ ለማመን የሚያዳግቱ ሰይጣናዊ በደሎች ቢፈፅሙም ‹‹ሃገራቸው ስለሚወዱ ነበር እንደዝያ ያደረጉት›› ይባልላቸዋል፡፡ዕድሜ ልካቸው በገባሩ ጫንቃ የኖሩ ቢሆንም ‹‹አባ ሰጠው፣ ቸሩና ፀሐዩ ንጉሳችን›› እያለ ያሞካሻል፡፡ ሞካንንት፣ተወለጄ፣ባላባት፣መሳፍንት፣ምርጥ ዘር(ጭዋ) ወዘተበቅምጣቸው ደግሞ ቀኝና ግራ አዝማች! ፊተ አውራሪ አፍተራሪ፣ቢትወደድ ወዘተ እያለ ያንቆለጳጵሳል፡፡ይህ ነገር ዛሬም ድረስ ጨርሶ አልጠፋም፡፡ በሙስና፣በክራይ ሰብሳቢነትና በቤተሰባዊ መድሎ መልኩ ቀጥሏል፡፡

መፍትሔው፡

የኢትዮጵያ ታሪክ በእውነት ከተፃፈ የድህነት፣ የህዝቦች ጭቆና፣የእርሰ በርስ መጠላለፍ፣የክህደት ወዘተ ሁኖ ነው የምናገኘው፡፡‹‹ኢትዮጵያ ሃገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ
የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ›› የኢትዮጵያ ታሪክ ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡የዚች በለ ሁለት መስመር ግጥም የቋጠረ ሰው የኢትዮጵያ ታሪክ ከመጀመርያው እስከ መጨረሻው እንደ ፊልም በዓይኑ የተመለከተ ነው የሚመስለው፡፡ዝምብሎ የተገጠመና የተዘፈነ አይደለም፡፡
ይሁን እንጂ ያለፈውን ታሪክ ወደኋላ ተመልሰን ማስተካከል አንችልም፤ ብንችልም ፋይዳ የለውም፡፡ስለዚህ ደግም ይሁን መጥፎ(ለእኔ በአብዛኛው መጥፎ ነበር) ያለፈውን አልፏል፤ እንርሳውና እንደ አዲስ እንጀምር፤የዛሬዎቹን የጋራ ችግሮቻች አብረን መፍትሔ እናበጅላቸው፡፡ሌሎችን በፈጠራ ታረክ እያጣጣልንና ስማቸውን እያጠፋን የእንትና ጦርነት ‹‹ቅዱስ ጦርነት ነበር›› ማለቱን እናቁም፡፡ የትናንቱን ቁርሾ እያነሱ መሸለል፣ቡራ ከረዩ ማለት፣ ያዙኝ ልቀቁኝ እያሉ ማስቸገር ለሁላችንም አይጠቅምም፡፡
እንዲህ ብለን ለማሰብና የአሁኑ አካሄዳችን በማጤን ለማስተካከል የሚከተሉት የዓለም የጥፋት መንገዶች አውቆ አቅጣጫ መቀየስ የግድ ይላል፡፡ 

 ‹‹ሰለወደደኳት ገደልኳት››…አንድ


 ጅርመናውያን በፈጣሪ የተመረጥን የኤርያን ዝርያዎች ነን ብለው ያምኑ ነበር
የአዶልፍ ሂትለር የቀኝ እጅ ጆሴፍ ጎብልስ ነበር፡፡የጆሴፍ ጎብልስ የፕሮፖጋንዳ መልእክቶች በጀርመናውያን ሰርፀው ለጥፋት እንዲነሳሱ ደግሞ የጁሌስ ስትሬሸር የጋዜጠኝነት ሙያ በጣም አስፈላጊ ነበር፡፡ስትሬሸር የDer Sturmer(The stormer) ጋዜጣ መስራችና ዋና ኤዲር የነበረ ሲሆን የጋዜጣው ዋና ዓላማ ደግሞ አይሁዳውያንን መርዘኛ እንጉዳይ፣ ቀበሮ አያለ በማጥላላት ከሰውነት  ማድረግ ነበር፡፡የዝያኛው ውጤት ደግሞ ሆለኳስ!!!

‹‹ሰለወደደኳት ገደልኳት››…ሁለት


 ሩዋንዳውያኖቹ ሁቱዎች ቱትሲዎችን በረሮዎች ይሏቸው ነበር
ይኸው የስምና ዘር ማጥፋት ዘመቻ አንድ ሚሊዮን ቱትሲዎችን ሊፈጅ የቻለው ደግሞ የዴንማርክ ቄሶችና የኢንተር ሃምዎይ ሬድዮ ጋዜጠኞች ባቀጣጠሉት ሰደድ እሳት ላይ ጋዝ በማርከፍከፍ ከቁጥጥር ውጪ እንዲሆን ስላደረጉት ነበር፡፡ብዙ ፕሮፓጋንዳዎች ከተለፈፉ በኋላ ሁቱዎች ቱትሲዎችን በሮሮዎች ናቸው ብለው ስላመኑ በመፍለጫ፣በገጀራና በጦር ወግተው ከመግደል ወደኋላ አላሉም፡፡በሁቱዎች እሳቤ ቱትሲዎችን በመጨፍጨፋቸው ለሃገራቸው ውለታ ከፍሏል፡፡

‹‹ሰለወደደኳት ገደልኳት››…ሶስት  

ከንያውያኖቹ የካለንጂን  ጎሳዎች ኪኩዩ ለሚባሉት ጎሳዎችን ‹‹አረሞች›› ይሏቸው ነበር
እናም በእነሱ አቆጣጠር በ2007/2008 ዓ.ም በተካሄደው ሃገራዊ ምርጫ ተከትሎ የተነሳው የእርሰ በርስ መጨራረስ ካለንጂኖች ኪኩዩ የሚባሉ አረሞችን ነቅለው ለማጥፋት ሆ ብለው ተነስተው ነበር፡፡በዚሁ ምክንያትም ከ1000 በላይ ከንያውያን ለሞት ሲዳረጉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ የስደትና የምጣኔ ሃብታዊ ዝቅጠት ሰለባ ሆኗል፡፡ለካለንጂን ጎሳ ተወላጆች ኪኩዩ የሚባሉ አረሞች ከስረ መሰረታቸው በነቃቅሮ ማጥፋት ሃገራዊ ግዴታ ነበር፡፡
 ‹‹ሰለወደደኳት ገደልኳት››…አራት
በእኛ ሃገርም በ97 ዓ.ም የትግራይ ተወላጆችን ነቀርሳዎች ተብሏል
የትግራይ ህዝብ ‹‹ነቀርሳ›› በመሆኑ ህዝቡን በማስወገድ ኢትዮጵያን ከበሽታ ለማዳን ያልተሞከረ ጥረት አልነበረም፡፡‹‹ትግሬ ወደ መቀሌ ንብረት ወደ ቀበሌ›› የ‹‹ሰላማዊ ሰልፈኞች›› መፈክር ለመሆን በቅቶ ነበር፡፡እንደህ በማለት ህዝቡን ለማታለል የሞከሩት ደግም ‹‹ከኢትዮጵያውያን በላይ ኢትዮጵያውያን ነን›› ባዮችና ‹‹ከሌሎች ኢትዮጵያውያን በበለጠ ኢትዮጵያን እንወዳታለን›› እያሉ የሚመፃደቁ ግብዞች ሲሆኑ የፖለቲካ መርሃቸውም በ‹‹የእኛና የእነሱ›› ፅንፎች የሚያጠነጥን ነበር፡

ጀርመናውያን የአይሁዳውያን እልቂት በይፋ አውግዟል፡፡የናዚዎች ምልክት ይዞ የተገኘ ማንኛውም ጀርመናዊ የህግ ቅጣት ይጠብቀዋል፡፡ያ ከድሮ ስህተታቸው በመማርም ዛሬ ከዓለም ቁንጮዎች ለመሰለፍ በቅቷል፡፡እኛስ???
እንደ ውሾች ከተጣለ ዓመታት ባስቀጠረ ዓጥንት መናከስም ሆነ ከትናንቶቹ መጥፎና በጎ ትውስታወች እኩል ተምረን ወደፊት መራመድ በእጃችን ናቸው፡፡


3 comments:


  1. ‘ስለወደድኳት ገደልኳት’…እውነት ብለሃል አስፋው…ሲገድለን የኖረ…እየገደለን ለመኖር ያደፈጠ የህሊናችን አስተሳሰብ ዝግመት…የራእያችን ጉዞ ጽልመት ነው….’ስለወደድኳት ገደልኳት’ !!

    ReplyDelete
  2. ‘ስለወደድኳት ገደልኳት’…እውነት ብለሃል አስፋው…ሲገድለን የኖረ…እየገደለን ለመኖር ያደፈጠ የህሊናችን አስተሳሰብ ዝግመት…የራእያችን ጉዞ ጽልመት ነው….’ስለወደድኳት ገደልኳት’ !!

    ReplyDelete
  3. "ሲገድለን የኖረ…እየገደለን ለመኖር ያደፈጠ የህሊናችን አስተሳሰብ ዝግመት…የራእያችን ጉዞ ጽልመት ነው….’ስለወደድኳት ገደልኳት’ !"

    ምርጥ የማጠቃለያ አስተያየት፡፡ምን ለማለት እንደፈለግኩ ስለተረዳህልኝ በጣም አመሰግናሃለሁ Kibrom Sabian!!!

    ReplyDelete