Thursday, April 16, 2015

የኢትዮጵያውያን አሳፋሪ ስቃይ መቼ ይሆን የሚያበቃው?



የእኛው፣ የኢትዮጵያውያን ሰቆቃ ተነግሮ አያልቅም፡፡ቢፃፍ…ቢፃፍ…ቢፃፍ…መቋጫ የለውም፡፡ደሞ መግለፅ ከምችለው በላይ አሳፋሪ ነው፤ቅስም የሚሰብር አሳዛኝም ነው፡፡ክፉኛ የተሰበረው ልባችን፣እርር…ድብን ብሎ የተቃጠለው አንጀታችን፣ውጋ! ንቀል! ውጋ! ንቀል!እያሉ ያቆሰሉት ገላችን ሳይድን መልሰው መላልሰው እየወጉት… እንሆ ዛሬም በደም እየታጠበ ይገኛል፡፡

የጦርነትና የርሃብ ተምሳሌት ነን፡፡ዓለምን ጉድ ባሰኘ ድህነትና ኋላ ቀርነት እንታወቃለን፡፡የለየላቸው አምባገነኖች በማፍራትና እርሰ በርሳችን በመገዳደል ታሪካችን አናፍርም፡፡እንዳውም፣ አንዱ ጥጋበኛ መጥቶ በሌላ የእርሰ በርስ የመገዳደል በዓል እስኪተካው ድረስ በየዓመቱ በድምቀት እናከብራለን፡፡‹‹ገዳይ ዬ…ገዳይ ዬ…›› የሚለው ሐረግ ከዘፈኖቻችን አይጠፋም፡፡ገዳዮችን የምንክብበት መለያ መዝሙራችን ነው፡፡

ሴራ፣ተንኮል፣ምቀኝነት የእኛ መገለጫዎች ናቸው፡፡ብንተባበር እንደ ዝንጀሮ መንጋ የተከመረውን እናፈርሳለን እንጂ የፈረሰውን አንገነባም፡፡የክፋት መለያዎቻችን ከቀን ወደ ቀን በብዛትም በጥራትም እየጨመሩ ይገኛሉ፡፡በገፍ ከሃገር መሰደድና የውርዴት ሰለባዎች መሆን መታወቅያችን ከሆነ ሰነባብቷል፡፡

2004 ዓመተ ምህረት(ዓመተ ፍዳ ወይስ ዓመተ ምህረት?)

አዎ፤ለማሳጠር ያህል ከ2004 ዓ.ም ልጀምር፡፡ወሩ የካቲት ነበር፤ ዓመተ ምህረቱ 2004፡፡ሶስት ወይም አራት የሚሆኑ ዓረብኛ ተናጋሪ ጎልማሶች በሆነ ዛፍ ላይ ጥለው ከዚህም ከዚያም ሲጎነታትሏት ይታያል፡፡ልጅትዋ በወደቀችው ሆና ‹‹አይ!አይ…››እያለች ታቃስታለች፤ ታለቅሳለች፡፡በመጨረሻ ላይ፣ በሐይል ጎትተው ወደ መኪና ሊያስገቧት ሲታገሉ ‹‹ኖ…ኖ…ኖ! ወይኔ…››እያለች ስትጮህ ይሰማል፡፡ሃገሯ ኢትዮጵያ የመኖር ተስፋዋን የነፈገቻት ወጣት ዓለም ደቻሳ ነበረች፡፡ዓለም እንደ በግ በአደባባይ ስትጎተት፣ ሰብአዊ መብትዋ በጠራራ ፀሐይ ሲገሰስ፣ ጭኾትዋ ሰሚ አጥቶ ስታቃስት የሚያሳይ ቪድዮ ታዋቂ መገናኛ ብዙሓን ሲቀባበሉት አይተናል፡፡ይህ አሳዛኝ ትዕይንት የተከሰተው ሊባኖስ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ አጠገብ ነው፡፡

ከአንድ ሳምንት በኋላ ዓለም ደቻሳ ዓለም በቃኝ ብላ ራሷን እንዳጠፋች ተሰማ፡፡አንጀት የሚያቃጥል፣ ልብ የሚሰብር ክስተት ነበር፡፡

በወርሐ ሰኔ 2004 ዓ.ም ደሞ፣ በሕገ ወጥ መንገድ በኮንቴነር ታሽገው ከተንዛንያ ወደ ማላዊ በመጓዝ ላይ የነበሩ 45 ኢትዮጵያውያን የሚተነፍሱት ኦክስጅን አጥተው ለህልፈት እንደተዳረጉና 72 የሚሆኑ ደሞ አሳሳቢ የጤና እከል እንደደረሰባቸው ሰምተን ከልባችን አዝነናል፡፡

መስከረም 2005 ዓመተ ምህረት

ሶስት ኢትዮጵያውያን በጭካኔ የተገድለዋል ፡፡ብዙ ሴቶች የአስገድዶ መደፈር ጥቃት ደርሶባቸዋል፡፡ወጣት ሴቶችና ወንዶች ጀለብያ በለበሱ ዓረቦች ታስረው ሲገረፉ አይተናል፡፡በፖሊሶች ቆመጥ ሲዠለጡ ተመልክተናል፡፡የመኪና ጎማ አንስተው በአናታቸው ላይ ሲጥሉባቸው የሚያሳዩ ቪድዮዎች ፌስቡክን አጥለቀልቀውት ነበር፡፡ብዙዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡

ውሎ አድሮ ግን ከ150 ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን ለዓመታት ሰርተው ያፈሩት ንብረት ተዘርፈው፣ከሳውዲ ዓረብያ ታፍሰው ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ ተገድዷል፡፡እምባ እየተናነቀን፣ በእልህና በቁጭት እየተቃጠልን መርዶውን የተከታትለነዋል፡፡ሆኖም ግን፣ መቋጫ አላበጀንበትም፡፡

ሐምለ 2005 ዓመተ ምህረት፡- ቢቢሲ ከየመን በሰፊው የዘገበው የኢትዮጵያውያንሰቆቃ አንብበናል፡፡ኢትዮጵያውያኑ በህገ ወጥ ደላሎች አማካኝነት ቀይ ባሕርን በትናንሽ ጀልባዎች ከተሻገሩ በኋላ የመን ሲደርሱ የሚደርስባቸው ግድያ፣ግርፋትና የአስገድዶ መደፈር መከራ ማንበብ አሳፋሪ፣አሰቃቂና አሳዛኝ ነበር፡፡

በጥቅምት ወር፣ 2006 ዓመተ ምህረት፡- ስደተኞች ጭና ወደ የመን በማቅናት ላይ ነበረች ጀልባ ሰምጣ የ70 ኢትዮጵያውያን ህይወት ማለፉን ቢቢሲ መዘገቡ አይረሳም፡፡ 

2007 ዓመተ ምህረት፡- ባሳለፍነው የመጋቢት ወር የሳውዲ ዓረብያ የጦር አውሮፕላኖች የመንን ሲደበድቡ ከአስር በላይ ኢትዮጵያውያን መገደላቸውን ሰምተናል፡፡ 

በዚህ ሳምንት ደሞ በደቡብ አፍሪካ የስደት ኑሮ እየገፉ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን አሰቃቂ ግድያ፣ድብደባና ዝርፍያ እየደረሰባቸው ይገኛል፡፡አስከሁን ድረስ ሶስት ኢትዮጵያውያን መገደላቸውን ሰምተናል፡፡ጥረው ግረው ያፈሩት ንብረት ተዘርፈው በመጠልያ ታጉረው የሚገኙት ብዙ ናቸው፡፡ ብዙዎችም ከአሁን አሁን ይዘርፉናል፣ይገድሉናል እያሉ በመሳቀቅ ላይ ይገኛሉ፡፡

ከእነዚህ ሁሉ አሰቃቂና አሳፋሪ ክስተቶች የምንረዳው ምንድን ነው? ወይ በሃገራችን ሰርተን አያልፍልን፣ ወይ ተሰድተን አልቀናን በሄድንበት ሁሉ መከራና ስቃይ ይፈራረቁብናል፡፡መቼ ይሆን ከዚህ ሁሉ ሰቆቃ ተገላግለን፣ እፎይይይ…ብለን በሃገራችን በኩራት የምንኖረው?


No comments:

Post a Comment