በ1980ዎቹ ገደማ አንድ ሴትዮ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስተር አቶ መለስ ዜናዊን የኢትዮጵያ ህዝብ
ከአስር ዓመታት በኋላ ምን ዓይነት ኑሮ እንዲኖር እንደሚመኙለት ጠይቀዋቸው ነበር፡፡ሰውየው ሲመለሱ ‹‹የዛሬዓስር ዓመት ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ በቀን ሶስት ጊዜ ምግብ ያገኛል››አሉ፡፡ያ ምኞት የቀን ቅዠት ነበር መሰለኝ ከአስር ዓመታት በኋላ ቀርቶ ከ24
ዓመታት በኋላም እውን አልሆነም፡፡በእርግጥ በኢቢሲ የምንመለከታት ኢትዮጵያ የቅር በአፍሪካ በአውሮፓም ተወዳዳሪ የሚገኝላት አትመስልም፡፡
የኢቢሲዋን
ኢትዮጵያ ለኢቢሲዎች እንተዋትና እኛ ስለምንኖርባት ኢትዮጵያን እንጨዋወት፡፡
ከሶስት ዓመታት በፊት የአዲስ አበባ ህዝብን ስለሚፈታተኑ አምስት አንኳር ችግሮችን አስመልክቸ
ትንሽየ መጣጠፍ ፅፌ ነበር፡፡እነዝያ
ችግሮች ለብዙ ዓመታት አብሯችን ከመኖራቸው የተነሳ ነው መሰለኝ በምሬት ስንነጋገርባቸው አይስተዋልም፡፡ውሃ ለሳምንታት ይጠፋል፤መብራት
በየጊዜው ይሄዳል ይመጣል፤የኑሮ ውድነቱ…የሱኳር፣የዘይትና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች መጥፋት፣የትራንስፖርት እጥረት፣የቤት ክራይ ዋጋ
ጣራ መንካት ወዘተ ዛሬም ህዝቡን ከመጠን በላይ እየተፈታተኑት ይገኛሉ፡፡ ህዝቡ ግን ምሬቱን ሲገልፅ አይታይም፡፡ የመገናኛ ብዙሓን
ስለእነዚህ ችግሮች መዘገብ አቁሟል…በጣም ከመደጋገማቸው የተነሳ ሳይሰለቻቸው አልቀረም፡፡
በአሁኑ ጊዜ ውሃና መብራት የሚጠፋው እንደ ድሮው ሳት እያለ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ እንደሚናፈቅ አድርጎ ነው፡፡ለሳምንታት
እልም ብሎ ይጠፋል፡፡መብራት ሲጠፋ ስልክ ይጠፋል…ኔትወርክ ይጠፋል…ባንኮች አገልግሎት መስጠት ያቆማሉ…ከተማው የለመደው እንዳጣ
ሱሰኛ አፉን ከፍቶ ያዛጋል፡፡ማንም አይናገርም…አይጋገረም፡፡ሁሉም ዝም…ጭጭ፡፡ያው አምርሮ የሚናገር እጣው ምን እንደሚሆን ያውቃታል…እስር
ቤት ወይም ስደት ነው፡፡ስለዚህ፣ የባሰ አታምጣ እያለ እንዳላየና እንዳልሰማ መስሎ ዝም ነው፡፡ህዝቡ ቢርበው ጉልበቱን አጥፎ ዝም
ነው፤ቢጠማው ዝም…ኑሮው ቢከፋው ዝም…ዝም ከማለት ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌለው ከልምድ ተምሯልና፡፡
ኢህአዴግ በበኩሉ፣ እንደተለመደው ‹‹አበበ በሶ በላ›› እያለ ይለፍፋል፤ ‹‹መጭው ጊዜ ከኢህአዴግ ጋር ብሩህ ነው››
ይላል፡፡እንደዚህ ዓይነቱ ‹‹ካፈርኩ አይመልሰኝ›› ዓይነ ደረቅነት ይኖር ይሆን?ኢህአዴግ ከሚያቀርባቸው ለኑሮ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች
መቼም ቢሆን እንደልብ እንደማይገኙ ይታወቃል፡፡ህዝቡ ውሃ ፍለጋ ይሰለፋል…ታክሲ ፍለጋ ይሰለፋል…የኮንደምኔም እጣ ፍለጋ ይሰለፋል…ምሬቱን
ለመግለፅ ብቻ ነው እንዲሰለፍ የማይፈቀድለት፡፡ምሬቱን ለመግለፅ እንዳይሰለፍ ምን የሚያካክሉ ወጠምሾች ዱላ ይዘው ይጠባበቃሉ፡፡ሰልፍ
ለመውጣት የሞከሩ እስኪያስመልሳቸው ድረስ ተጠብጥቧል፡፡መብቴ ተደፍሯል ብትል ሰሚ የለም፤ ውሃ ጠፋ ብትል ሰሚ የለም፤ፍትሕ አጣሁ
ብትል ሰሚ የለም፡፡ የኢህአዴጎች የተለመደው መልስ ‹‹ እንድ አንድ ትምክህተኞች…አንድ አንድ ፀረ ሰላም ሃይሎች…አንድ አንድ ጨለምተኞች
የሚያወሩት ውሸት ነው››ይላል፡፡
ቢሆንም ግን ‹‹ምርጫ›› በደረሰ ቁጥር ‹‹መጭው ጊዜ ከኤህአዴግ ጋራ ብሩህ ነው›› ይለናል፡፡ብሩህ የሆነው ምኑን
ነው? መቼስ ፀሐይ የምትወጣው ኢህአዴግ ስላዘዛት ነው ማለት አይቻልም፡፡የዓይኖቻችን ብርሃን ያልጠፉት ኢህአዴግ በስልጣን ስላለ
ነው ማለትም አንችልም፡፡ህዝቡ ኦክስጅን የሚተነፍሰው ኢህአዴግ እየቆነጠረለት አይደለም፡፡አንድ አንድ የአዲስ አበባ ኗሪዎች በኢቢሲ
አለፋላፊነት ደስታቸው ስለገለፁ ብቻ ህዝቡ ደስተኛ ነው፤ ደልቶታል…ቁጭ ቢል ሶፋ ላይ…ቢተኛ ስፕንጅ ፍራሽ ላይ…ቢራመድ በቀይ ምንጣፍ
ላይ አይደለም፡፡በእግሩ ቢራመድ ቀይ ሽብር ይገጨዋል(ሲኖትራክም ይሉታል፤ ቻይና በኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት ተማርራ የላከችብን መዓት?)…ቢሰለፍ
ሰልፉ ማለቅያ የለውም፡፡ሰልፉን እንደምንም አልቆ ታክሲ ተሳፍሮ ሲጓዝ የትራፊክ መጨናነቁ አይጣል ነው፡፡ብሩህ የሆነው የቱ ጋር
ነው?
‹‹በምርጫ›› 2002 ዓ.ም ወቅት አንገብጋቢ የነበሩ ህዝቡ እረሮዎች ዛሬም እንዳሉ ናቸው፡፡ውሃ…መብራት…ስልክ…የኑሮ
ውድነት…የቤት ክራይ መናር…ሱኳር…ዘይት… እያሉ ችግሮችን መዘርዘር ይቻላል፡፡አምስት ዓመት ቀላል አይደለም…በአምስት ዓመታት ውስጥ
ግን አንዳቸውም አልተፈቱም፡፡የፕረስ መፃነት ታሪክ እየሆነ ነው…መታሰር፣ መንገላታት…ነበሩ አሉ፡፡ሞባሌ ተዘረፍኩ ማለት ተራ ወሬ
ሆኗል፤ላፕቶፕ…መኪና…ሌሎች ትላልቅ ንብረቶች መዘረፍ እየተዘወተሩ ነውና፡፡ዘራፌዎች…ማጅራት መቼዎች…ታሰሩ ቢባል ስድስት ወር…እስከ
ሶስት ዓመት ነው፡፡መብቱ ጠይቆ የሚታሰረው ግን ፍርድ ሳያገኝም ለዓመታት ይታሰራል፡፡ፀሐይ በጠለቀች ቁጥር ህዝቡ የሚሸማቀቅ ከሆነ
ብርሃኑ የቱ ጋር ነው? እንደ ልብ ገብቶ መውጣት ካልተቻለ ፖሊሶቹ እንደአሸን ቢፈሱ ምን ይፈይዳሉ?
የህግ ስርዓቱ ግለ ሰዎች ለፈልጉት ጥቅም የሚያውሉት ከሆነ ህግነቱ ምኑ ላይ ነው?ዘራፊዎች፣ ማጅራት መቺዎች፣ሙሰኞች
በኩራት ተንቀባርረው የሚኖሩባት ሃገር ይዘን፤ ድህነት በቁማችን ሊቀብረን የተቃረበባት ሃገር እየመሩ ስለጭው ጊዜ ብሩህነት መለፈፍ
‹‹ከሞትክ በኋላ ገነት ትገባለህ›› ከሚሉት ስብከት በምን ይለያል?ከአምስት ዓመታት በፊት የነበሩ ችግሮች ዛሬም ብሶባቸው ኑሯችን
ከድጡ ወደ ማጡ የሚያደርጉት ከሆነ መጪው ጊዜም ከኢህአዴግ ጋራ ያው እንደ ድሮው ነው፡፡

No comments:
Post a Comment