Wednesday, February 10, 2016

ኢቲቪ(ኢቢሲ) ከርሞ ጥጃ የሆነባቸው ምክንያቶች


1. በኢትዮጵያ የመደብ እንጂ የስርዓት ለውጥ
ስላልተከሰተባለፉት 50 ዓመታት መከታተል ኢትዮጰያን በሐይል ተቆጣጥረው ያስተዳደሩ ገዢዎች ከሞላ ጎደል ተቃራራቢ ናቸው፡፡ዘላለም ክብረት በቅርቡ ያደረገው ዳሰሳ የሚያመለክተው ሶስቱም ገዢዎች( ዘውዳዊው፣ ወታደራዊውና ኢህአዴግ) በአምባገነንነት እንደሚታወቁ ነው [1]፡፡ፅሑፎ የሚያመለክተው ከሶስቱም ገዢዎች በአፋኝነት የከፋው ደርግ ሲሆን ዘውዳዊውና የኢህአዴግ አገዛዝ በትንሹ ይሻላሉ፡፡ዘውዳዊው አገዛዝ ለመውደቅ ሲቃረብ ኢህአዴግ ደሞ በመጀመርያው አስር ዓመታት ደህና ነበሩ፡፡ያም ሆኖ ግን ልዩነታቸው እስከዚህም እንዳልነበር ነው፡፡ይህ ከሆነ ታድያ፣ አምባገነኖች ያለምንም ገደብ የፈለጉትን ይናገራሉ፣ ያደርጋሉ እንጂ የህዝብ ፍላጎት ብሎ ነገር አይውቁም፡፡ህዝቡ በኢቲቪ/ኢቢሲ ዝግጅቶች ደስተኛ ባይሆንም እንደ ኮሶ ቋቅ እስኪለው ድረስ ይግቱታል እንጂ የአቀራረብም ሆነ የይዘት ለውጥ ለማድረግ አይጨነቁም፡፡በለላ አነጋገር የኢቢሲ ኦዲቶርያል ፖሊሲ ከገዢው መደብ ጥቅምና ፍላጎት የሚመነጭ ነው፡፡
2. በጥናት ሳይሆን በትእዛዝ የሚመራ ስለሆነ

ከላይ እንደተጠቀሰው የኢቢሲ ግብ ሃገራዊ ሳይሆን የገዢው መደብ ጥቅምና ፍላጎት ማስጠበቅና ዓላማዎቹን ከግብ ማድረስ ነው፡፡ዋና ግቡ ቡዱናዊ ከሆነ እንግዲህ ድርጅቱ የሚመራው በጥናትና ምርምር ሳይሆን በትእዛዝ እንዲሆን ይገደዳል ማለት ነው፡፡ለዛውም ነው ባለፉት 50 ዓመታት ተመሳሳይ ተግባራት ሲፈፅም የሚስተዋለው፡፡በሌላ አገላለፅ የሃገራችን የፖለቲካ ሙቀት የሚለካው በኢቲቪ/ኢቢሲ ነው፡፡በጣም ሲግል ሌሎች ዝግጅቶች ዘግቶ የአዛዦቹን የደም ፍላት ሲንፈቀፈቅ ያሳያል፤አዛዦቹ አሁንም አሁንም በሞስኮቱ ብቅ እያሉ ሲደነፉና ሲገለፍጡ ያመለክታል፤ በጣም ሲቀዘቅዝ ደሞ ዜናውም ጭምር ድራማና ማስታወቅያ ይሆናል፡፡ኢቲቪ/ኢቢሲ በእነዚህ ጊዚያት ብቻ ነው ብዙ ተከታታዮች የሚያገኘው፡፡በአመፅ፣በጦርነትና ህዝቡ ተስፋ ሲቆርጥና አማራጭ ሲያጣ ተመልካች ይስባል፡፡

ህዝቡ አማራጭ ሲያጣ ጋዜጠኞቹም አማራጭ ስለሚያጡ ነው መሰለኝ አንድ ነገር ዓመት ሙሉ እየደጋገሙ ይዘግቡታል፡፡ለምሳሌ አንድ ዩኒቨርሲቲ ሊሰራ ሲታሰብ ስለመታሰቡ ይዘግባል፡፡በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ዩኒቨርሲቲ ሊሰራ ታስቧል ይባላል፡፡ከዛም የመሰረት ድንጋይ ሲቀመጥ ይዘገባል፡፡ቁፋሮ ሲጀመር ይዘግባል፣ ቁራሮው ሲያልቅ ይዘግባል፣ግንባታ ሲጀመር ግንባታ መጀመሩን ያበስራል፣ግንባታው 10 ከመቶ ሲደርስ ይህንኑ ያስውቃል፣ከርሞ ከርሞ 15 ፐርሰንት ተጠናቅቋል ይላል፣ደሞ ቆይቶ ቆይቶ ቆይቶ 20 ፐርሰንት ደርሷል ይላል፣ እንደገና ከተረሳ በኋላ 25 ፐርሰንት ደረሰ ይላል፣30 ፐርሰነት…እያለ እያለ እያለ ከስንት ዓመታት በኋላ 90 ፐርሰንት ሲደርስ ለምርቃት ይዘግባል፡፡ደሞ ለተማሪዎች ምዝገባ ይዘግባል…ለታማሪዎች ምርቃት ይዘግባል…የተመረቁ ተማሪዎች በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው ኮብል ስቶን ሲጠርቡ ያሳያል…

በጥናት የሚመራ ቢሆን ኖሮ ግን የቁጥጥር፣የይዘት፣ሚዲያው የሚጠቀምበት ቴክኖሎጂ፣የተመልካች፣የዓላማ(ግብ)ና የሁኔታ ትንታኔዎችና ግምገማዎችን በየጊዜው በማድረግ፣ዳስሳዎችንና ጥልቅ ጥናቶችን በማካሄድ ከዘመኑ ጋራ መራመድ ይችል ነበር፡፡በኢቲቪ/ኢቢሲ እምነት ከ50 ዓመታት በፊት የነበረው የኢትዮጵያ ህዝብ ዛሬም ያውና እኩል ነው፡፡የቴሌቪዥን መስኮቶች ከለር እንኳን ጥቁር ሁሉም ዓይነት ከለሮች(ቀለሞች) እስከሟሟላት፣ ከድቡልቡልና ጠፍጣፋ ወደ ፍላት ስክሪን ማደጉን ልብ ያለ አይመስልም፡፡በጣም የሚገርመው ግን ህዝቡ ከምሳና እራቱን ቆጥቦ ዲሽ መግዛቱ በኢቲቪ/ኢቢሲ መሰላቸቱ ሳይሆን ሃገሪቱ ያስመዘገበችው ፈጣን እድገት ማሳያ ነው ብለው ማሰባቸውን ነው፡፡

ኢቲቪ/ኢቢሲ ይህ በመሆኑ በጣም በተደጋጋሚ የተጎዳው ኢህአዴግ ብቻ ነው፡፡ለምን?@Andualem Buketo Geda ን ጠይቁት፤ እንዲህ ይላል…
‹‹…እኔ እስከምረዳዉ እንደ ኢቲቪ ዋና የወያኔ ጥላት የለም …..እንግዲህ አብዛኛዎቻችን ወያኔን ጠልተን የቀረነዉ በፌስቡክ ተነግሮን አልነበረም መቼም….. እንደ ኢቲቪ ስለወያኔ አስከፊነት በመንገር ሆዳችንን የሞላን ነበረ እንዴ?!….በነገራችን ላይ ኢቲቪ ያኔ ወያኔ ጫካ እያለች እንድትጠላ ሲሰራ የነበረዉ ፕሮፓጋንዳ የተሳካ ሲሆን አሁን ደግሞ ስልጣን ከያዘች በኋላ ስለልማትም ይሁን ስለጥፋት በሚያቀርባቸዉ አሰልቺ ፕሮፓጋንዳዎች ወያኔ ተጠልታ እንድትቀር አሌ የሚባል አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል፡፡ቴንክ ዩ ኢቲቪ የትግላችን አጋር ነህ…..›› [2]
ኢቲቪ/ኢቢሰ በጣም ተሸወደው ግን…
3. የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ አንድ የአዲስ አበባ ኗሪዎች ስለሚመስለው ነው

አንድ አንድ የአዲስ አበባ
ኗሪዎች ሁሉ ጊዜ ኢቲቪ/ኢቢሲ ይከታተላሉ፡፡ምክንያቱም፣ ተናገሩ እያለ ስለሚወተውታቸውና ያልተናገሩት ነገር ተናግሯል ብሎ ካስተላለፈ ሰፈር ለመቀየር ወይም ሃገር ጥለው ለመሸሽ እንዲዘጋጁ ነው፡፡ለዛም ነው አንድ አንድ የአዲስ አበባ ኗሪዎች ሰፈራቸው የት እንደሆነ የማይታወቁት፡፡ስለዚህ ኢቲቪ/ኢቢሲ ምን እንደሚዘግብ፣ለምን ምክንያት እንደሚዘግብ፣በምን ሁኔታ ተመስርቶ እንደሚዘግብ፣እንዴት እንደሚያሰራጨው፣መቼና ለማን እንደሚያቀርበው፣ የዘገባው ውጤት ምን እንደሆነ አያውቅም ማለት ነው፡፡በርግጥ መገመቱ አይቀርም…ግምቱ ግን የጥንቆላ ያህል ነው፡፡ልክ በአየር ሁኔታ(ሜትሮሎጂ) ስዓት እንደሚያቀርበው ግምት ማለት ነው፡፡

[1] Zelalem Kibret, ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ፡ የግማሽ ምዕተ ዓመት ጉዞhttps://www.facebook.com/notes/zone9/%E1%8B%B4%E1%88%9E%E1%8A%AD%E1%88%AB%E1%88%B2-%E1%89%A0%E1%8A%A2%E1%89%B5%E1%8B%AE%E1%8C%B5%E1%8B%AB-%E1%8B%A8%E1%8C%8D%E1%88%9B%E1%88%BD-%E1%88%9D%E1%8B%95%E1%89%B0-%E1%8B%93%E1%88%98%E1%89%B5-%E1%8C%89%E1%8B%9E/935633566525136[2] Andualem Buketo, ሶልሻየር,https://www.facebook.com/andualem.geda/posts/10153581859854915

No comments:

Post a Comment