Monday, April 14, 2014

ተመስገን ደሳለኝና የዓመፅ ጥሪዎቹ



የሃገራችን ፖለቲካ በሁለት የማይታረቁ፣ ማዶ ለማዶ ሆነው በጎሪጥ በየሚተያዩ፣ አንዱ ካልጠፋ በቀር ሌላኛው ይኖራል ተብሎ በማይታሰቡ ፅንፎች መከፋፈሉን ይታወቅል፡፡በአንደኛው ፅንፍ ኢህአዴግ አለ … የስልጣን ዘመኑን ለማራዘም በራሱ ይሁንታ ያፀደቀው ህገ መንግስት ሳይቀር ለመጣስ ወደ ኋላ የማይል፣ህዝቡን የምኞት ህብስት የሚመግብ፣ ለፈርጀ ብዙ ኢኮነሚያዊና ማሕበራዊ ቀውሶች አፋጣኝ መፍትሔ ሳይሆን ተደጋጋሚና አሰልቺ ተልካሻ ምክንያቶችን የሚደረድር፣ ጀሮውን ቢቆርጡት የህዝብ ሮሮ የማይሰማ የግብዞች ስብስብ ነው፡፡


በሌላኛው ፅንፍ በ1960 ዎቹና 70ዎቹ በውስጣዊ ችግራቸውና ከኢህአዴግ ጋር በገጠሙት ጦርነት ተሸንፈው ከጥቅም ውጪ የሆኑት ነገር ግን ከዚህም ከዚያም ተሰባስበው ያ በጦር ሜዳ ያሸነፋቸው ኢህአዴግን ለመበቀልና በተገኘው አጋጣሚ የስልጣን ባለቤት ለመሆን በተቃዋሚነት ስም የሚንቀሳቀሱ አሉላችሁ፡፡እነዚህ ‹‹ሰዎች›› ትናንት በኢህአፓ፣ መኢሶን፣ ደርግ ወዘተ ስም ተሰባስበው ህዝቡን ሲገድሉና ሲያጋድሉ፣ ሃገሪቷን ሲያፈራርሱ የነበሩ የስርዓት አልበኝነት፣የክህደትና የፈላጭ ቆራጭነት ተምሳሌት ናቸው፡፡ከዚሁ የሚመደቡ ተቃዋሚዎች ከተቻለ በምርጫ፣ ምርጫው ካልተሳካ ደሞ ‹‹በሰላማዊ ህዝባዊ ዓመፅ›› የስልጣን ኮርቻ መቆናጠጥ ብቸኛው ዓላማቸው ነው፡፡ስለ ሃገር ግንባታ፣ ስለ ሶሼዮ ኢኮነሚያዊና ፖለቲካዊ ልዕልና የሚያስጨንቃቸውም ሆነ የሚያውቁት ነገር የለም፡፡በቃ፣ ሃገሪቷ ከፈለገች እንጠረጦስ ትጋባ… ብቻ እነሱ የስልጣን ባለቤቶች ይሁኑ፡፡

ከላይ ተገለፁት ሁለት ፅንፎች እንዳሻቸው የሚያጦዟቸው መስሎ አዳሪ የመገናኛ ብዙሓን ተቋሞች ባለቤት ናቸው፡፡በሁለቱም ፅንፎች ሙያቸውን አፈር ድሜ ያስጋጡ ፅንፈኛ ጋዜጠኞችና ትንቢት ተናጋሪ፣ ከኮብ ቆጣሪ ፃፎች ተሰልፈው የታዘዙትን ያለማመንታት በማከናውን ላይ ይገኛሉ፡፡በአንዱ ፅንፍ የተሰለፉት፣ ‹‹በማንኛውም መንገድ ይህን መንግስት አስወግዳችሁ ተቃዋሚዎችን የስልጣን ባለቤት ካላደረጋችሁ አለቀላችሁ›› እያሉ ይጮሐሉ፤ ህዝቡን ያሸብራሉ… የ‹‹አትነሳም ወይ›› አታሞ ይመታሉ፡፡በሌላው ፅንፍ ደሞ ‹‹መንግስታችን ሕብስተ መና ማከፋፈል ሊጀምር ነውና እንኳን ደስ ያላችሁ›› እያሉ ቆሽታችንን ያሳርሩታል፡፡

የኢህአዴግ መራሹ የመገናኛ ብዙሓን ተቋሞች ኢትዮጵያ ከገሐንምነት ተስፈንጥራ ወደ ገነትነት እየገሰገሰች እንደሆነች ብቻ ነው የሚዘግቡት፡፡ህዝባችን በንሮ ውድነት፣በውሃ፣ በመብራትና በስልክ መቆራረጥ እንዲሁም በትራንስፖርት እጥረት፣በፍትሕ መጓደልና በመልካም አስተዳደር እጦት እያማረረ ይገኛል፡፡የመንግስት ሚድያዎች ግን እንዚህ ችግሮች ለምን ተከሰቱ፣ለምንስ መፍትሔ አይበጅላቸውም? ብለው አይጠይቁም፡፡የእነሱ ስራ ‹‹በልማታዊ ጋዜጠኝነት መርህ›› በሃገራችን በመገንባት ላይ ያሉ ‹‹መጠነ ሰፊ መሰረተ ልማቶች›› ጧት ማታ መለፈፍ እንጂ ፀረ ልማት የሆኑ ችግሮችም መኖራቸውን አምነው መፍትሔ እንዲፈለግላቸው የማሳወቅ ግዴታ እንዳላቸውም አያውቁም ወይም ሆን ብለው ዘለውታል፡፡እናም ሃገራችን በእንከን የለሽ መሪዎች የምትተዳደር ምድረ ገነት እንደሆነች ለማሳመን ጧት ማታ ያደነቁሩናል፡፡

ከፅንፈኛ ተቃዋሚዎች ጋር የተሰለፉ ፃፎችና ጋዜጠኞች ሃገራችን ከድጡ ወደ ማጡ፣ከሲኦልነት ወደ ግሐንምነት፣ከመኖር ወደ አለመኖር እየተለወጠች መሆኗን ይሰብካሉ፡፡የአርማገዴዮንና የመቅሰፍት ወራቶች መቃረብ ይተነብያሉ፤ ይተነትናሉ፡፡በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ‹‹የአርበኝነት›› መፈክሮችና የወንድ ያለህ ጥሪዎችን ያስተጋባሉ፡፡የ2007ቱን ቅድመና ድህረ ምርጫ ውጤቱ ምንም ይሁን ምን በ‹‹ሰላማዊ ህዝባዊ ዓመፅ›› መታጀብ እንዳለበት ይመክራሉ፡፡ሃይማኖታዊና ሃገራዊ ክብረ ብዓሎችም በ‹‹ሃይማኖታችን ተደፈረ›› ስም የፀሎት፣የሞንዙማ፣የቅዳሴና የውዳሴ ሳይሆን የዓመፅ ማስነሻና የእርሰበርስ መከታከቻ እንዲሆኑ የተለያዩ የስጋት ትርክቶችን በመፈብረክ ያራግባሉ፡፡

ተመስገን ደሳለኝ ከዚህ ጎራ የተሰለፈና ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ መፂሔቶችና ጋዜጦች ለ‹‹ህዝባዊ ሰላማዊ ዓመፅ›› ሲቀሰቅስ የኖረ የአብዮት ጥሩምባ ነፊ ነው፡፡ከቱንዝያ ተነስቶ የዓረብ ሃገራትን ያተረማመሰው የዓረቡ ፀደይ ተሞክሮዎችና ስኬቶችን በማጥናት በመስቀል አደባባይ እንዲደገም ከ‹‹በቃ››ና ‹‹ድምፃችን ይሰማ›› አርበኞች ጋር በመሰለፍ የተለያዩ የስብከት ፅሑፎችና የአትነሳም ወይ ጥሪዎችን አስተጋብቷል፡፡ተመስገንና ቃፊሮቹን እንዳሻቸው የሚያሾሯቸው በተደጋጋሚ ሽንፈቶች ያበዱና የሃገርና የህዝብ ጉዳይ አሳስቧቸው ሳይሆን ሽንፈቶቻቸውን ለመበቀል በሌላኛው ፅንፍ የተሰለፉ በመሆናቸው የምፅአትና የዓመፅ ጥሪ ከማስተላለፍ ውጪ ሌላ ስራ የላቸውም፡፡


ተመስገን ደሳለኝና ቃፊሮቹ በፍት ጋዜጣ ፍትሕና ርትዕ ሳይሆን ፅልመትና ውድመቶችን ሰብኳል፡፡የኢትዮጵያ ህዝብን ለዘረኝነት፣ለእርሰ በርስ መካካድና መጨፋጨፍ አንሳስቷል፡፡ፍትሕ ብለው በሰየሟት ጋዜጣ ችሎት ተሰይመው ‹‹እንእንትና ነፃ ይለቀቁ እንትና ደሞ ይታሰሩ፣ ከሃገር ይባሩ›› በማለት ፈርዷል አስፈርዷል፡፡ዳሩ ግን መንግስት የፕረስ ሕጉ በሚያዘው መሰረት ጋዜጣዋን በሕግ ፊት አቅርቦ በሕጉ መሰረት ከመፋረድ ይልቅ በፍቃዱ እንዳዘጋት ነው የሚነገረው፡፡የጋዜጣዋ ዋና አዘጋጅ የነበረው ተመስገን ደሳለኝም ‹‹የሕገ መንግስቱን ለመናድ ቅስቀሳ በማድረግ››፣ ‹‹የመንግስትን ስም በማጥፋት››ና ‹‹የህዝብን አስተሳሰብ በማናወፅ›› በሚሉ ክሶች ተከሶ ወደ 16ኛው ወንጀል ችሎት እየተመላለሰ ይገኛል፡፡

ከፍትሕ መዘጋት በኋላ የተቋቋመችው አዲስ ታይምስ መፅሔትም ከስም በስተቀር የይዘት ለውጥ አልታየባትም፡፡በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮምኒኬሽን ተመራቂዎች ተጠንታም የጋዜጠኝነት ስነ ምግባርና ሙያ እንደማትከተል ተረጋግጧል፡፡በመሆኑም ልቅነቷ ለመዘጋቷ ምክንያት ሆነና ተዘጋች፡፡ የአዲስ ታይምስ መፂሔት መፎረሽን ተከትሎ ልዕልና የተባለች ገዜጣ ብቅ ብላ ነበር፤ አልቆየችም ወድያው ጠፋች፡፡

አቶ ተመስገን ግን ተልእኮውን አላሳካምና ዛሬም በቀይ ቀለም ባሸበረቀችው ፋክት መፂሔት የአመፅና የጋጋታ ጥሪዎቹን እያስተጋባ ይገኛል፡፡እርሱና ጋዜጠኛ ተብየ ቃፊሮቹ ለዓመፅ ቆርጠው ተነስቷል፡፡ቃፊሮቹ ‹‹የአመፁ አይቀሬነት›› ይሰብካሉ፤ የአዲስ አበባ ጎደናዎች እንደ ታሕሪር አደባባይ በህዝብ ይጥለቀለቃሉ፣ህንፃዎችዋና ህዝቦችዋ እንደ ዩክሬን ይተረማመሳሉ፡፡ ያሉ በእርግጠኝነት ይፅፋሉ፡፡ ተመስገን ደሞ የሃገራችን ፈርጀ ብዙ ችግሮችን በመተንተን ህዝባዊ አመፅ አማራጭ የሌለው ብቸኛው መፍትሔ መሆኑን ይደመድምና  ‹‹የፈራ ይመለስ›› እያለ ‹‹ፈሪዎችም›› ያነሳሳል፡፡
‹‹የፈራ ይመለስ›› በቅፅ 2 ቁጥር 35 የካቲት 2006 ዓ.ም በተመስገን ተፅፎ በፋክት መፂሔት ላይ ለሕትመት የበቃ ሲሆን ቀጣይ ክፍሎች አሉት፡፡በዚሁ ቅፅ ላይ ካነሳቸው አንኳር ጭብጦች የሚከተሉትን ይገኙበታል፡፡

‹‹ለከተማ አብዮት መፈንዳት ወሳኝ ሆነው ከሚጠቀሱ ጭብጦች ብዙዎቹን የእኛይቷም ምድር እነደምታሟላ ከዚህ በፊትም ለማስታወስ ሞክሬያለሁ፡፡›› በማለት ለአራት ዓመታት የሰበከውን ስብከት ያስታወሰው አቶ(ጋዜጠኛ የሚሉትም አሉ ኮሜርስ ጋዜጠኞች ማፍራት መጀመሩን ባላውቅም) ተመስገን በመቀጠልም ‹‹በተለይም ስራ አጥ የተማሩ የከተሜ ወጣቶች አለቅጥ መብዛት እና ወጣቶች በአጠቃላዩ ሕዝብ ወደ 37 ከመቶ የሚጠጉ መሆናቸውን ከአረቡ ፀደይ መንገስ አኳያ ስንቃኘው አብዮቱን አይቀሬ ያደርገዋል፡፡›› ሲል ስራ አጦቹን ወጣቶች የአብዮት መቀጣጠያ ጭራሮ በማድረግ ሃገራችንን በነውጥ ለማጋየት ይመክራል፡፡አሪፍ የስራ ፈጠራ ነው መቸስ፡፡የትግራይ ቀደምቶች እንደ ተመስገን ደሳለኝ በትላልቅ ሆቴሎች ቁጭ ብሎ ሆዱን እየሞላ እንዲህ ሁን፣እንደዝያ አድርግ ለሚል ብልጣ ብልጥ ‹‹ብኢድ እንዳማትኻ ተመን ሓዝ›› በማለት ይተርቱበታል፡፡በግርድፉ ስተረጎም ‹‹በሌሎች እጅ እባብ ጨብጥበት›› እንደማለት ነው፡፡
  

‹‹በአናቱም›› በማለት ይቀጥላል ትንታኔው‹‹የሁለቱ ሓይማኖት ተከታዮች በመንግሰት ላይ የያዙት ቅራኔ ልክ፣ የተቋጠረ ምሬት ፅንስ ስለመኖሩ በድፍረት ለመናገር ያስችላል፡፡›› በማለት የአብዮቱን አይቀሬነት ያስረግጥልናል፡፡

ወረድ ብሎም ‹‹በተጨማሪ ዛሬም እየተነሱ ካሉት የማንነት ጥያቄዎች አልፎ፣ በቅርምቱ ከአያቶቻቸው መሬት ከተፈናቀሉ ወጣቶች ምሬት ጋር የኢኮኖሚውን ድቀት አዛምደን ስንመለከት፣ ፍርሃትን አቸንፈው ወደኋላ ላለመመለስ የደፈሩ ወጣቶች ስርዓቱን እንደሚንዱት ለመመልከት ጥቂት ወራትን ብቻ መታግስ ይበቃል፡፡›› በማለት የኢኮነሚ ድቀቱን በአመፅና በእርሰ በርስ መፈጀት እንዲቀለበስ ይሰብካል፡፡አብዮት ሲነሳ ቼ ጉቬራም አብሮው ከሚነሱ አብዮተኞች አንዱ ነው፡፡ እናም አቶ ተመስገን ‹‹አብዮት የወይን ዘለላ ነው፤እስኪበስል እንጂ መሬት እስኪወድቅ አትታገሰውም›› በማለት የቼን ጥቅስ ለአብዮት መቀስቀሻነት ተጠቅሞ ‹‹ያረገዘውን አብዮት ከማዋለድ ያለፈ ምርጫ የለም፡፡›› ብሎ ይደመድማል፡፡

የተመስገን የአመፅ ጭሆቶች መቋጫ የላቸውም፡፡አመፁ ተቀጣጥሎ፣ ያወደመውን አውድሞና ኢህአዴግን አስወግዶ ፅንፈኞቹ ተቃዋሚዎችን አራት ኪሎ ካላደረሰ በቀር ጭሆቱ አይቆምም፤ ይቀጥላል፡፡ ታድያ በቀጣዩ ክፍል እስክንገናኝ ድረስ ቸር ያቀየንና በዚሁ ላብቃ፡፡


No comments:

Post a Comment