Saturday, April 19, 2014

ታስሮ የከረመው ውሻ ሲለቀቅ…



ነገ የፋሲካ በዓል ነው፤ በዓሉን በጉጉት ስትጠባበቁ ለነበራችሁ ምእመናን በሙሉ እንኳን አደረሳችሁ ማለት እወዳለሁ፡፡በእርግጥ፣ እንኳን አደረሳችሁ መባል አለባችሁ፤ ይገባችኋል፡፡ቃሊቲ ባትወርዱም ታስራችሁ ከረማችኋልና… እንኳን ልጓመ ፆሙን ፈታላችሁ፡፡ለአርባ ምናምን ቀናት ስጋ የለ፣ እንቁላል የለ፣ወተት የለ … ነጋ ጠባ የፈረደባት ሽሮሮሮ… የሁዳዴው ፆም የበሬ፣የበግ፣የፍየልና የደሮ የእፎይታ ወቅት ነበር፡፡ስንት ስጋ ቤት ነው ተዘግቶ የከረመው?


አዲስ አበባ ጎዳናዎች የበሬና የበግ መንጋ ሲነዳ ካየሁ ወራት አልፏል…የሾላ ገበያ የቅርጫት ጎጆዎችም ባዷቸውን ነበሩ፡፡ዛሬ ግን መተላለፍያም የለም…በየጎደናው መኪና ሳይሆን የበሬና የበግ መንጋ ይነዳል…ዶሮና እንቁላል ያንጠለጠሉ የገጠር ሰዎች አዲስ አበባን አጥለቅልቀዋታል፡፡ነገ በሽዎች የሚቆጠሩ እንስሳት መስዋእት ይሆናሉ…እንደ እየሱስ ክርስቶስ ግን በሶስተኛው ቀን አይነሱም፡፡ይቀቀላሉ፣ይጠበሳሉ፣ይከተፋሉ፣ይቆረጣሉ… ይዘለዘላሉ…ይበላሉ፡፡የሁዳዴ ፆም አስሮት የከረመው ውሻ ዋጥ ስልቅጥ ያደርጋቸዋል፡፡ሁዳዴ… (ሆድ ታሰሮ በዳዴ ሄደ ማለት ይሆን?)….ሐበሻና ሆድ…የፕሮፌስር መስፍን መጣጥፍ ትዝ አለችኝ፡፡

‹‹ሐበሻ ቢሰራ ለሆዱ፣ቢያስብ ለሆዱ…ቢተርት ለሆዱ…ብያፈቅር ለሆዱ…ቢቆጣና ቢያዝን ለሆዱ…ቢራራ ለሆዱ…ቆርጦ ቢጨክን ለሆዱ..ሐበሻና ሆድ…›› ሐበሻ ከሌሎች የሚለየው በሆዱ ላይ ያለው ልዩ ፍቅር ሳይሆን ይቀራል? የሐበሻ ሆድ ሽንቁር ጋን ነው፡፡እናም ታስሮ የከረመው ውሻ ነገ በመጠጥና በስጋ ዘር ይወተፋል… ዳሩ አይሞላም፡፡ኤድያ! እኔ ግን የስጋ ዘር ባልቀምስ ይሻለኛል፤ ከቤቴም ባልወጣ እመርጣለሁ፡፡ ምክንያቱም በዚህ ዓለም በጣም እንደ መራብና በጣም እንደ መጥገብ የሚያስጠላኝ ነገር የለም፡፡ቤት ከዋልኩ ስጋ አልቀምስም…የመጠጥ ዓይነት ሲያልፍ አይነካኝም… ከውሃ በስተቀር፡፡ግን ደሞ ወቀሳው አይጣል ነው…‹‹ትዕቢተኛ…ዓመት በዓል እንኳን ብትጠይቀን ምናለበት? ጨካኝ አረመኔ ነህ…የሆንክ ዝጋታም ነገር…›› የስድብ ናዳ ይወርድብኛል፡፡ ቤተሰብ ጥየቃ ከዞርኩ ደሞ እዚህም እዚያም ጠላ፣የለስላሳ ዓይነት፣ዱለት…ቀይ ወጥ…የደሮ ወጥ…ጥብስ…መቀማመሴን ሰለማይቀር የቁንጣን ሰለባ መሆኔ ነው፡፡ነገ ያው እሁድ ነው… ብናርፍበት ምናለበት?

የዕለት ቁርስና ልብስ አጥቶ የሚወዳት ሃገሩን የኋሊት ትቶ በሚሰደድባትና መጠለያ አጥቶ በየበረንዳው ወድቆ በሚያድርባት ሃገረ ኢትዮጵያ እየኖሩኩ በቁንጣን ከመጨናነቅ የከፋ ሐጥያት ይኖር ይሆን? ነገ ታስሮ የከረመው ውሻ ይህንንም ያንንም እንደ ጉድ ይውጣል …ሳያላምጥ፡፡ይበላል…ይጠጣል…ይሰክራል…እንደ ጉድ ያስታውካል… ወደታች ወደላይ!!! እኔ ግን ሁዳዴን አልፆምኩምና ነገ ስጋ ባለመብላት፣ መጣ መጠጥ ባለ መቅመስ እፆማለሁ፡፡ቸር አይደለሁ? የታረዙ፣የተጠሙና የተራቡ ወገኖቼን ነገ አስባቸዋለሁ…ማንም ሳያዘኝ በፍቃዴ በመፆም፡፡ቢሆንም ግን ማስታወቅያ አልሰራባቸውም…‹‹እንትና የተባለ ‹ምግባረ ሰናይ ድርጅት› ወይም የሰንበቴ ማሕበር፣ የምናምን ተቋም በዓሉን ምክንያት በማድረግ ምንዱባንን ሲያበላና ሲያጠጣ ዋለ›› የሚል ዜና እንዲሰራልኝ አልሻም፡፡ሆድ ዓመት በዓልን አይጠብቅም…ገና፣ፋሲካ፣እንቁጣጣሽ… ሰኞ፣ማክሰኞ…እሁድ ሁሉም እኩል ናቸው…ለተራበው ለተጠማው ሆድ፡፡

ሆድ ያው ሆድ ነው… ዓመት በዓል በመሆኑ አይሰፋም…አዘቦት ቀን በመሆኑም አይጠብም፡፡ግን አመል ነውና በድግስ ሰበብ ‹‹በሞቴ…አፍር ስሆን…እችን ብቻ…›› እየተባለ ቋቅ እስኪልህ ድረስ ትወተፋለህ፡፡ሆድህ ሞልቶ እያየ ‹‹በሞቴ …››እያለ ከሚያጎርስ ይጠብቃችሁ፡፡እኔ ስጠግብ የሚያጎርሰኝ ሰው በጣም ያስጨንቀኛል…ጉሮሮየን ያነቀኝ ያህል፡፡በቃኝ ጠገብኩ…እያልከው የማይረዳልህ ሰው ገዳይ ነው…ወዳጅ መሳይ ጠላት፡፡ነገ ከቤት እንዳልወጣ ከሚያደርጉኝ ነገሮች አንዱ የኸው ነው…ነፃነቴን ላለማስደፈር…ጤንነቴን ላለማቃወስ…

እናም ሃይማኖት በሚሉት አምባገነን ተቸንክሮ የከረመው የአዳም ዘር ነገ አለ የተባለውን መጠጥ እንደ ጉድ ይጠጣል፣ አለ የሚባለውን የስጋ ዓይነት እንደጉድ ይሰለቅጣል፡፡ይህ ታድያ፣ ታስሮ ከተፈታው ውሻ በምን ይለያል? በአይሁዶች ባዕዳዊ ባህል ተሸብቦ የሚኖረው ህዝብ …‹‹ሃገሬ በቀኝ ገዢዎች አልተገዛችም›› ይለኛል፤ በኩራት! ኤድያልኝ፡፡ብላ ስትባል ትበላለህ… አትብላ ስትባል ታቆማለህ…ጨፍር ስትባል ትጨፍራለህ…አልቅስ ስትባል ታለቅሳለህ... ወዲህ በል ስትባል እየተስገበገብ ትቀርባለህ…ሂድ ስትባል ጭራህን ወሽቀህ እብስ ትላለህ፡፡እናም ደረትህ ነፍተህ ‹‹አልታሰርኩም ነፃ ነኝ›› እያልክ ትቀባጥራለህ… ቆይ ግን ትንሽ አይደብርህም? በትእዛዝ የምትኖር ታዛዥ ወገኔ ሆይ… ለመሆኑ ነፃነት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ታውቃለህ? ዛሬ(የፋሲካ ዋዜማ) በአዲስ አበባ ተዘዋውረህ ከሆነ ከየአቅጣጫው የሚነዱ የበግና የበሬ መንጋዎችን ሳታይ አትቀርም፡፡ ነፃ ናቸው?

ነፃነት ማለት ራስህንና ሌሎችን ሳትጎዳ…የራስንና የሌሎችን መብት ሳትነካ የፈለግከውን ማድረግ ማለት ነው(ህሊናን ማደንዘዝና ራስን መግደል ከሽንፈት እንጂ ከነፃነት አይቆጠሩም)፡፡ከዚህ ውጪ የሚከናወነው ሁሉ ባርነት ነው… የእስር ቤት ንሮ ነው፡፡ልክ ዛሬ ሲነዱ እንዳየሃቸው የበግና የበሬ መንጋዎች በሌሎች መነዳት ነው፡፡መድረሻህን አታውቅም… ቄራ ደርሰህ ከመታረድህ በፊት ወዴት እየተነዳህ መሆኑን አታውቅም… ቄራ ደረስክ ማለት አለቀ…ገነት ይደርሳል የተባለው ምንትስ በምንትስ ይገኛል፡፡ ‹‹ሃይማኖተኛ ነኝ›› እያሉ የሚመፃደቁ ሰዎችም ባያውቁት ነው እንጂ ወደማያውቁት አቅጣጫ በሌሎች የሚነዱ መንጋዎች ናቸው፡፡ሃይማኖት የሰው ልጅን ወደ መንጋነት ከቀየሩ ጥንታዊ ተቋሞች አንደኛው ነው፡፡መቼ ምን መበላትና ማድረግ እንዳለብህ የሚያዝህ ሃይሞኖት ነው፡፡የኸው ከመንጋዎቹ አንዱ ከሆንክ ታስረህ ከርመሃልና ነገ ልትፈታ ነው…ያለፉትን 50 ቀናት የስጋ ዘር እንዳትቀምስ የታሰርከውን ያህል የሚቀጥሉት 50 ቀናትም አርበ ሮብ ሳትል ስጋ ልትበላ ተፈቅዶልሃል፡፡ታስረህ ከረምክና ነገ ትፈታለህ… እንኳን ደስ ያለህ… ምስኪን፡፡አሳዛኝ ሐበሻ…ለባለስልጣናት ይሰግዳል…ለሃይማኖት መሪዎች ይሰግዳል…ሆዱን ለሞምላት ጎምበስ ቀና ይላል…

የሐበሻ ‹‹ነፃነት›› በነፃነት አይገኝም፡፡የፈለግከውን ለማድረግና ለመሆን ሰክረህ ወይም አብደህ ህሊናህን መሳት ይጠበቅብሃል፡፡ልብ አድርግ፣ ሃይማኖታችሁንና መንጋችሁን አልፈልግም ማለት እንደ እብደት ይቆጠራል…በሐበሻ ምድር፡፡እናም የመንጋን ንሮ አልፈልገም ብሎ ራሱን ያገለለ ሐበሻ ቢያጋጥምህ ‹‹በእጀ ሱስ ስም!››፣ ‹‹በስማም!››፣‹‹ያአላሕ›› ወዘተ ትል ይሆናል…ዳሩ ግን ነፃ ሰው ማለት ያ መሆኑን እወቅ፡፡እሱ በይሉኝታ እጅና እግሮቹን አልታሰረም…አይኖቹን አልታወረም…አፉን አልተለጎመም…በስካርና በእብደት ሳያሳብብ በፈለገው ጊዜና ቦታ ያሻውን ያደርጋል፡፡

በደብተራ፣በቡዳ፣በባህል፣በሃይማኖት፣በመተት፣በጠንቋይ ወዘተ ያልታሰረ ነፃ ሰው ነውና፡፡አይ፣ እኔም ነፃ ሰው ንኝ የምትል ከሆነ በነገው ዕለት ራስህን ከቁንጣን ጠብቅ፡፡የሚቀርብህ ነገር ቢኖር ቅዘንና ተውካት ብቻ ነው፡፡ታመምኩ ምናምን ብለህ ወደ ጤና ተቋሞች ከመመላለስም ራስህን ተታደጋለህ፡፡ለማንኛውም ይህን ያህል ታግሰህ ‹‹አፈንጋጭ›› ፅሑፌን ማንበብህ የሚደነቅ ነውና ለዛሬው ያደረሰህ ፈጣሪ ለቀጣዩ ዓመትም በሰላም ያድርስህ፡፡
በማንኛውም ሃገር ነፃነት በነፃ አይከፋፈልም…ሃይማኖት ነፃነት ያሳጣል፣ባህል ነፃነት ያሳጣል፣ፖለቲካ ነፃነት ያሳጣል…ብያንስ ግን ከፖለቲካ በስተቀር ከሌሎቹን ነፃ መሆን ይቻላል፡፡ለዚህም ነው ይህ አፈንጋጭ ፅሑፍ ለመፃፍ የተነሳሁትና ካስቀየምኩህ ‹‹የሚያደርጉትን አያውቁምና…›› ብለህ አፉን በለኝ፡፡

መልካም በዓል



No comments:

Post a Comment