Thursday, April 10, 2014

‹‹በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብር ዥንጉርጉርነቱን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን?››


ኢትዮጵያዊነት በየዓይነት ነው፤ ዓይነት በተጨመረበት ቁጥር የሚጣፍጥ፡፡
ይህ ጥቅስ የእግዚአቢሔር ቃል እንደሆነ በሚነገርለት መፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ በትንቢተ ኤርምያስ ምዕራፍ 13፤ ቁጥር 23 ላይ ተከትቦ ይገኛል፡፡ብዙ ኢትዮጵያውያን ምሁራን ደጋግመው የሚጠቅሱት ጥቅስ ነው፤ በተለይም በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮችና ሰባኪዎች ተደጋግሞ የሚጠቀስ የፈጣሪ ቅዱስ ቃል ነው፡፡እኔም ኢትዮጵያዊ ነኝና ስለሃይማኖት ለመስበክ ሳይሆን ኢትዮጵያዊነትየን ለማስረዳትና አስረገጨ ለመሞገት ምርጫየን አድርጌዋለሁ፡፡በተለይ ደሞ ከሁለት ሳምንታት በፊት ‹‹ኢትዮጵያዊነትማንነት ሳይሆን ዜጎች በህግ የሚጎናጸፉት ማሊያ ነው!›› ብለው እንደ ፍካሬ እየሱስ በቀይ ቀለም ለፃፉት ዲያቆን ሙሉጌታ ወልደገብሪኤል በዚሁ የመፅሐፍ ቅዱስ ጥቅስና ሌሎች ምክንያቶች ልሞግታቸው እሻለሁ፡፡
ዲያቆን ሙሉጌታን በዚሁ ጥቅስ ልሞግታቸው የተነሳሁት ስለኢትዮጵያና ስለማንነት በመፃፋቸው ‹‹የኢትዮጵያን ክብር አቃልሏል››፤ በመሆኑም ‹‹ፀረ አንድነት›› ናቸው ብዬ ስለማምን ሳይሆን ‹‹ማንነትንና  ኢትዮጵያዊነትን እተረጉማለሁ›› ከሚል ቅንነት ቢነሱም የሁለቱም ቃላት ትርጉም አንድም ከእውቀት ማነስ ትርጉማቸውን አበላሽቷቿል፣ሁለትም አንድ አንድ ወገኖች ‹‹በኢትዮጵያዊነት ላይ የአንበሳ ድርሻ ያላቸው ያህል›› ስለኢትዮጵያዊነት ሲፃፍ በፀረ ኢትዮጵያዊነት እየፈረጁ እልህ ውስጥ ስለከተቷቸው እነሱን ለመበቀል በማሰብ የተሱበት ዓላማ ትተው(ረስተው) በመጠኑ የቆሸሸውን ‹‹ኢትዮጵያዊ መግባባት›› ለማደፍረስ ሞክሯል ብዬ ስለማምን ብቻ ነው፡፡

ታላቁ መፅሐፍ ቅዱስ ስለኢትዮጵያውየን ከላይ በጠቀስኩት ምዕራፍና ቁጥር በተለያዩ ቋንቋዎች እንዲህ ይላል ‹‹ይዌልጥኑ ኢትዮጵያዊ ማዕሶ ወነምር ሕንብርብሬሁ?››‹‹Can the Ethiopian change his skin Or the leopard his spots?›› (Jeremiah 13:23)… የሁለቱም ጥቅሶች ትርጉም ያው ነው፡ ‹‹በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብር ዥንጉርጉርነቱን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን?›› የዚሁ ጥቅስ ምስጢራዊና መንፈሳዊ ትርጉም ለሃይማኖት ልሂቃን እንተወውና ለጊዜው ‹‹ኢትዮጵያዊ መልክ››ንና የ‹‹ነብር ዥንጉርጉርነት››ን እንመልከት፡፡
‹‹ኢትዮጵያዊ መልክ›› ድህነት፣ችጋር፣ስደት፣ማጣትና መራብ የማይቀይሩት፣የማያደበዝዙት በዓለም አቀፍ ደረጃ የምንለይበት ልዩ ተፈጥራዊ ስጦታችን ነው፡፡ልክ የ‹‹ነብር ዥንጉርጉርነት›› በተለያዩ ክፍላተ ዓለማት እንደማይቀየረውና እንደማይደበዝዘው ሁሉ ኢትዮጵያዊ መልክም በአፍሪካ፣በኤስያ፣በአውስትራልያ፣በአውሮፓ፣በሰሜንና በደቡብ አሜሪካ አይቀያየረም… በአንታርቲካና በጨረቃም ጭምር፡፡እንግዲህ ኢትዮጵያዊ መልክ እንዲሁ በቦታ፣በሃብት ደረጃ፣በፖለቲካና በጊዜ የማይቀየር ከሆነ ልዩ መለያችን ነው ማለት ነው፡፡ኢትዮጵያዊ መልካችን ፖለቲካችን በሞቀና በቀዘቀዘ ቁጥር የሚለዋወጥ ሳይሆን በማንኛውም ዓይነት ሁኔታ፣የትም ብንሄድና ምንጊዜም ቢሆን በፊታችን ታትሞ የሚኖርና ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ትውፊታችን ነው፡፡
ይህ ግን ‹‹ኢትዮጵያዊነትማንነት ሳይሆን ዜጎች በህግ የሚጎናጸፉት ማሊያ ነው!››  ብለው ሊሰብኩን ለሚቃጣቸው ወገኖቻችን በቂ አይደለምና በተቻለኝ መጠን ይበልጥ ለማብራራት እሞክራለሁ፡፡በዚሁም ‹‹ስለኢትዮጵያዊ ማንነት›› በተወራ ቁጥር ፀጉራቸው ለሚነጩና ራሳቸውን የ‹‹እውነተኛ›› ኢትዮጵያዊ ጥራትና ደረጃ መዳቢ አድርገው ለሾሙ ወገኖቻችን ቆም ብለው እንዲያስቡ ለማሳሰብ እወዳለሁ፡፡ምክንያቱም እየተከተሉት ያለው አስተሳሰብ ያረጀ ያፋጀ ኋላ ቀር ቅዠት ነውና፡፡ዩኒሴፍ ሳይቀር አለም አቀፋዊ ሰብአዊ ብዝሃነት(ማንነተ ብዙነት) ልክ እንደሌሎቹ ተፈጥራአዊ ብዝሃነት ለተፈጥሮ ወሳኝ መሆኑን አምኖ ተቀበሏል፡፡
የሪፖርተር ጋዜጠኛው የማነ ናግሽ ኢትዮጵያዊ ዝበሃል ማንነት የለን”  የሚል ርእስ ያለው የትግርኛ ፅሑፍ ከተወሰኑ ወራት በፊት በፌስቡክ ገፁ ላይ ከለጠፈ ወዲህ ስለኢትዮጵያዊ ማንነት ብዙ ወገኖች ፅፈዋል፡፡አንዳንዶቹም እንደልማዳቸው የስድብ አምሮታቸውን ተወጥተውበታል፡፡ፕሮፌስር መስፍን ወልደማርያምና መስፍን ነጋሽ “ኢትዮጵያዊ ዝበሃል ማንነት የለን” ለሚለው የየማነ ናግሽ ፅሑፍ ኢትዮጵያዊ የሚባል ማንነት የለም” ብለው ነበር የተረጎሙት፡፡የማነ ናግሽ ግን በዚሁ ትርጉም አይስማማም፡፡እሱ ለማለት የፈለገው “እንዲህ ብሎ ኢትዮጵያዊ መንነት የለም” ነው(ኋላ ለማብራራት እንደሞከረው)፡፡ምክንያቱን ሲገልፅ ደሞ ‹‹ለኢትዮጵያ አንድነት ሲባል ከኢትዮጵያዊ ማንነት ውጪ ያሉ ሌሎች ማንነቶች በውድም በግድም መስዋእት መሆን አለባቸው የሚሉት ኋላ ቀር ፈሊጥ እስካለ ድረስ ኢትዮጵያዊ ማንነት በተናጠል ሊኖር ስለማይችል ነው እንጂ ኢትዮጵያዊ ማንነት መኖሩን እየካድኩኝ አይደለም›› ይላል፡፡
የሆነው ሁኖ ግን የየማነ ናግሽ የትግርኛው ፅሑፍ ተከትሎ ስለኢትዮጵያዊ ማንነት ከተፃፉ ፅሑፎች ሁሉ የተመቸኝ የመስፍን ነጋሽ ፅሑፍ ነው፤በስነ ፅሑፋዊ ፍሰቱ፣በይዘቱና በጥልቀቱ፡፡ሌሎቹን ከሞላ ጎደል እየተከታተልኩ አንቢቤያቸዋለሁ፤  ለመግባባት ሳይሆን ለፀጉር ስንጠቃና ሆን ብሎ ነገሮችን ለማካረር የተፃፉ ይመስላሉ፡፡በተለይም የፕሮፌሰር መስፍንና ለዚሁ ፅሑፍ መነሻ የሆነኝ ፅሑፍ የፃፉት ድያቆን ሙሉጌታ ወልደገብሪኤል የመኖርና ያለመኖር ያህል በተራራቁ ፅንፎች ይመደባሉ፡፡እነዚህ ሰዎች በኢትዮጵያዊ ማንነት ላይ ያላቸው አረዳድና ትርጓሜ ተቃራኒ ቢሆንም በጣም የተሳሳተ ነው፡፡ፕሮፌስር መስፍንና መሰሎቻቸው(ሰማያዊ ፓርቲና ጭፍሮቹ) ከ‹‹ኢትዮጵያዊ ማንነት ውጪ ሌላ ማንነት የለም›› ብለው በጭፍን ይደመድማሉ፡፡ያሉትንም ‹‹ጎሳ፣ዘውግ፣ጠባብ ብሐየሮች›› ወዘተ እያሉ ማንነታቸውን ያጣጥላሉ፣ያጥላላሉ፡፡ ድያቆን ሙሉጌታና መሰሎቻቸው(የትግራይ ኦንላይን ድረ ገፅ ኤዲተሮች ጭምር…ባይሆኑ ንሮ ፅሑፉ በድረገፃቸው ላይ አይለጥፉትም ነበር) ደሞ በአንፃሩ ኢትዮጵያዊ ማንነት የለም እስከማለትና ወደ ማሊያ(ህጋዊ ጨርቅነት) ለማውረድ ይሞክራሉ፡፡ዳሩ ግን የማሊያና የማንነት ትርጉም ባይገባቸው ነው እንጂ እንድያ አይሉም ነበር፡፡
ለመሆኑ ማንነት ምድን ነው? ኢትዮጵያዊነትስ?
ማንነት ጠቅለል ባለ መልኩ ሲተረጎም አንድ ነገር(ሰው/ሰዎች፣ብሔር/ብሔሮች፣ሃገር/ሃገሮች ወዘተ) ከሌሎች ጋር የሚለይባቸውና የሚመሳሰልባቸው ልዩ ባህርያቶች(ሰው ሰራሽና ተፈጥራዊ መዋቅሮች) የሚያጠቃልል ፅንሰ ሐሳብ ነው፡፡ልብ እንበል፣ ማንነት ማለት አንድ ሰው(የሆነ ነገር) ከሌሎች የሚለይበት ብቻ ሳይሆን የሚመሳሰልበትም ነው፡፡መመሳሰሉ ሌሎች አለኝታችን መሆናቸውን እንድናምንና ሳንሸማቀቅ ከእነሱ ጋር ተቀላቅለን እንድንኖር የሚያስችለን ሲሆን ልዩነቱ ደግሞ አንዳችን ከሌላችን ለይቶ ለማወቅ ይጠቅመናል፡፡ለምሳሌ ማሊያን እንውሰድ፡፡ማሊያ የማንነት መገለጫ ነው፤እንድ ክለብ ከሌላኛው ጋር የሚመሳሰልበትና የሚለያይበት፡፡የደደቢት እግር ኳስ ክለብ ከጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ ጋር ሲጫወት አንድ ተጫዋች የየትኛው ክለብ አባል መሆኑን የምናውቀው በለበሰው ማሊያ ነው፡፡ከአንዱ ክለብ ጋር ሲመሳሰል ከሌላኛው ደግሞ ይለያል፡፡ሆኖም ግን የእግር ኳስ ተጫዋቾች ብቸኛው መለያ(ማመሳሰልያ) መንገድ ማሊያ ብቻ አይደለም፡፡የተጫዋቹ ስም፣ቁመና፣የአጨዋወት ጥበብና ብቃት፣የሚጫወትበት ቦታ ወዘተም ሌሎቹ መለያዎች ናቸው፡፡በመሆኑም ማንኛውም ነገር ብዙ ዓይነት መለያዎች(ማንነቶች) አሉት ማለት ነው፡፡
ኢትዮጵያዊነት ደሞ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ብሔር ብሔረ ሰቦች የአንዱ አባል ከሆኑ ቤተሰቦች የተወለዱ ኢትዮጵያውያን የጋራ መለያ ነው፡፡ከእነ ከንያ፣ሱዳን፣ጁብቲ፣ሶማልያ፣ሩዋንዳ ወዘተ የሚለያቸውና የሚያመሳስላቸው መገለጫ ነው፡፡ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ከኢትዮጵያ ውጪ እያለ(ለጉብኝት፣ለስራ፣ለስደት ከሃገሩ ከወጣ) ከየት እንደመጣ ቢጠየቅ ‹‹ከኢትዮጵያ›› እንጂ ከትግራይ፣ከኦረምያ፣ከአማራ ወዘተ ቢል የሚረዳው አይኖርም፡፡በመሆኑም ‹‹ትግራይ የት ነው፣ኦረምያ የት ነው፣አማራ የት አከባቢ ይገኛል… ወዘተ›› የሚሉ ጥያቄዎች መመለስ ይጠበቅበታል፡፡ያኔ ወደደም ጠላም በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ክልሎች አንድ መሆኗን ለመግፅ ይገደዳል ማለት ነው፡፡ዜግነቱ የቀየረ እንደሆነም ተውልደ ኢትዮጵያዊ ነው ይባላል…አሁንም ‹‹ኢትዮጵያዊነት›› መለያው ነች(ማንነቱን ፍቆ ሊጥለው አልቻለም)፡፡በተለይ ድያቆን ሙሉጌታ በሚኖሩበት ሃገረ አሜሪካ ዜጎች ከሚለዩባቸው ማንነቶች አንዱ ‹‹የመጣበት ሃገር…National Origion›› የሚል ይገኝበታል፡፡እናም ኢትዮ- አሜሪካውያኖቹ የመጣበት ሃገር የሚሉት መለያቸው ላይ የሚሞሉት ‹‹ኢትዮጵያ›› የሚል ሆናል ማለት ነው፡፡‹‹በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብር ዥንጉርጉርነቱን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን?›› ይሉሃል የሄ ነው፡፡
ዝሮ ዝሮ ግን ማንነት ፈርጀ ብዙ(ብዙ ዓይነት) ቢሆንም በተፈጥሮ(Ascribed)፣በምርጫ የሚገኝና(Aquired)  ሌሎች ነው ብለው ባመኑልን(Assumed) የሚገኝ በመሆኑ አንደኛው ከሌሎቹ በበለጠ መልኩ ሊገልፀን ይችላል፡፡በመጀመርያ የሚመደበው የግል ማንነት ነው፣ከዛም ዘር ነው፣ከዛም ባህላዊ ማንነት፣ማህበራዊ ማንነት፣ፖለቲካዊ ማንነት ወዘተ እያለ ይቀጥላል፡፡
ለምሳሌ የሰው ልጅን ብንወስድ የግል ማንነት አለው፡ ስራ፣ሙያ፣ልዩ ችሎታ፣ባህሪ፣መልክ፣የቤተ ሰብ ማንነት፣የተወለደበት አከባቢ፣የዘር፣የቋንቋ፣ቁመና፣ዕድሜ፣ፆታ፣እምነት፣ሃይማኖት፣የሃብት ደረጃ፣የሚከተለው ፍልስፍና፣ የሚወደውና የሚጠላው ነገር ወዘተ…ከሌሎች ጋር የሚለዩትና የሚያመሳስሉት ነገሮች ናቸው፡፡በመሆኑም በመጀመርያ ደረጃ የሚመደበው ማንነት የግል ማንነት ሲሆን፣ቀጥሎ የቤተሰብ ማንነት ይከተላል፣ከዛም የዘመድ አዝማድ፣ከዛም የአከባቢ ማንነት፣ብሔራዊ ማንነት፣ሃገራዊ ማንነት፣አህጉራዊ ማንነት፣በመጨረሻም ዓለም አቀፋዊ ማንነት ይከተላል፡፡በአጭሩ ለመግለፅ ያህል ማንነት እንደ ቀይ ሽንኩርት አንዱ ከሌላኛው ላይ የተደራረበ ነው፡፡የላይኛው ሲላጥ የውስጠኛው ብቅ ይላል፡፡እንደዛ እያለም ይቀጥላል፡፡የዚሁ ፅንሰ ሐሳብ ጠንሳሽና አቀንቃኝ በሁለተኛው ክፍለ ዘመን በግሪክ ይኖር የነበረው ሄሮክለስ የተባለ የስቶይክ ፍልስፍና ተከታይ ነው፡፡ይህ ፍልስፍና ከሌሎች ክልሰ ሐሳቦች ይበልጥ አሳማኝነት አለው፡፡
ነገር ግን ይህ አስተሳሰብ ለሌላው ግሪካዊ ፈላስፋ ዲያጀንስ(400-325 ቅድሚ ልደተ ክርስቶስ) አይሰራም፡፡ዲያጀንስ በ412 ቅ.ል.ክ ከየት እንደመጣ ሲጠየቅ በዛን ዘመን ልሙድ እንደነበረው ከግሪክ(ሄለንስ) ወይም የመጣበት ልዩ ከተማ ከመጥቀስ ይልቅ ‹‹እኔ የዓለም ዜጋ ነኝ›› ብሎ ነበር የመለሰው፡፡ያኔ ዓለም አቀፋዊ ዜግነት አይታወቅም ነበርና ዲያጀንስ እንደነውረኛ(አፈንጋጭ) አስቆጥሮት ነበር፡፡የኋላ ኋላ ግን እነ ሶቅራጠስም(‹‹እኔ ዓለም አቀፋዊ ዜጋ እንጂ ግሪካዊወይም አቴኒሳዊ አይደለሁም›› ይል ነበር) የእርሱ ፍልስፍና ተከታዮች ሆኖዋል፡፡ኤንስታይንም  እስከ ህልፈተ ሞቱ ዓለም አቀፋዊ ዜግነት(ማንነት) ሲያቀነቅን  ነበር፡፡
ከዚህ የምንረዳው ነገር ቢኖር ማንነት ፈርጀ ብዙ ቢሆንም አንዳንዴ በፍላጎታችን ልንቀይረው ወይም ልናሳደገው(ልናስወግደው) እንደምንችል ነው፡፡ሃይማኖት፣ሃገር፣ዜግነት፣የቆዳ ቀለም(ማይክል ጃክሰን) ወዘተ መቀየር ይቻላል፡፡ቢሆንም ግን ያ ማንነታችን ጭራሽ አልነበረም(የለም) ማለት አንችልም፡፡የድያቆን ሙሉጌታ ማከራከርያ ሐሳብ የትናንቱና የዛሬው የኤርትራውያን ዜግነት ነው፡፡ትናንት ኢትዮጵያውያን ነበሩ ዛሬ ግን አይደሉም፡፡
በመሆኑም ‹‹ኢትዮጵያዊነትማንነት ሳይሆን ዜጎች በህግ የሚጎናጸፉት ማሊያ ነው!›› … የድያቆኑ ማጠንጠኛ ናት፡፡ሆኖም ግን እዚጋ ያለው የተሳሳተ አመለካከት የዜግነት ምንጭ ህግ እንደሆነ ተደርጎ መወሰዱን ነው፡፡የህጉ ምንጭ ዜጎች ናቸው… መጀመርያ ዜግነት ለማን ይገባል፣ለማንስ አይገባም ብለው የሚወስኑት ራሳቸው ናቸው፡፡ብሔራዊ ሞዝሙራቸው፣ብሔራዊ አርማቸው፣ብሔራዊ በዓላቸውና እሴቶቻቸውን የሚመርጡት እነሱ ናቸው፡፡ህጉ እንደ ህግ እንዲቀጥል የሚፈቅዱት ዜጎች ናቸው፡፡ ነገር ግን ‹‹በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብር ዥንጉርጉርነቱን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን?›› እደተባለው ሁሉ ማንነት በዜግነት ብቻ የሚደረት አይደለም፡፡ኤርትራውያን ትናንት ኢትዮጵያውያን ነበሩ፤ዛሬ አይደሉም፡፡ሆኖም ግን ኢትዮጵያዊ መልካቸው ዛሬም ድረስ አልተቀየረም፡፡ያ ጠይም ገፅታቸው ከሌሎቹ የዓለም ህዝቦች ይልቅ ከኢትዮጵያውያን ጋር በእጅጉ ያመሳስላቸዋል፡፡የተቀየረው የተቀየረው ባንዴራቸው፣የመገበያያ ገንዘባቸው እንዲሁም መታወቅያቸው ነው፡፡ይህ ግን ፖለቲካዊ ለውጥ ያመጣው ነውና በፖለቲካ ሊቀየር ይችላል፡፡ልክ እንደ ክርምያ ኤርትራውያንም አንድ ቀን 96.7 ከመቶ ኢትዮጵያዊነታቸውን በማስበለጥ ወደ እናት ሃገራቸው ይመለሱ ይሆናል፡፡

ያምሆነ ይህ ግን ኢትዮጵያዊ ማንነት ነበረ፣አለ ለወደፊትም ይኖራል፡፡

No comments:

Post a Comment