ህወሓት የተመሰረተበት 40ኛው ዓመት የተከበረበት ቀንን ተንተርሰው የብአዴኑ አመራር አቶ በረከት
ስምኦንና የህወሓቱ ከፍተኛ አመራር አቦይ ስብሓት ነጋ ስለመለስ የሰጧቸው አስተያየቶች አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ፌስቡክን ጨምሮ የማሕበራዊ
ድረገፆች ተጠቃሚዎች ሲቀባበሏቸው ሰንብቷለ፤ የየራሳቸው አስተያየቶችም ሰጥተውባቸዋል፡፡ከፊሎቹ በረከት ነው ትክክል ሲሉ፣ ከፊሎቹ
ደሞ አይ አቦይ ስብሓት ናቸው ትክክል ሲሉም ተስተውሏል፡፡ለማስታወስ ያህል ሁለቱም የኢህአዴግ አመራሮች የሰጥዋቸው አስተያየቶች
እንሆ፡
አቶ በረከት ስምኦን‹‹
መለስ በክፍለ ዘመን አንዴ ከሚፈጠሩ ሰዎች የሚመደብ ነው›› ሲሉ፣ አቶ ስብሐት ነጋ
በበኩላቸው ‹‹የለም፣ አሁኑኑ ብዙ መለሶች መፈጠር ይችላሉ›› በማለት የአቶ በረከት አስተያየት እንደተቃወሙት ሪፖርተር ጋዜጣ ሳይቀር ዘግቦታል፡፡ለመሆኑ እነዚህ አስተያየቶች ልዩነት አላቸው? ካላቸው፣ ልዩነቱ ምንድን ነው? አንድነታቸውስ ምን ድን ነው? እስኪ የቻልነውን ያህል በጥልቀት እንመርምራቸውና ከአምልኮተ መለስ
ጋራ ያላቸው ዝምድና ለማየት እንሞክር፡፡
ሁለቱም አስተያየቶች በጥንቃቄ ስንመረምራቸው ያን ያህል የጎላ ልዩነት የላቸውም፡፡አቶ በረከት ያሉት መለስን የመሰለ መሪ ለማፍራት ብያንስ አንድ ክፍለ ዘመን ይወስዳል ሲሆን አቦይ ስብሓት ግን አሁኑኑ ብዙ መለሶች መፍጠር ይቻላል ነው ያሉት፡፡በመሆኑም በሁለቱም አስተያየቶች ያለው ልዩነት የጊዜው ማጠርና መርዘም ብቻ ነው፡፡
በተረፈ ግን፣ ሁለቱም መለስን ከማድነቅ አልፈው አምላኪዎች መሆናቸውን አሌ የሚባል አይደለም፡፡የሁለቱም ፍላጎትና ፀሎት መለስን የመሰለ ‹‹መሪ›› በማፍራት ላይ ያጠነጥናል፡፡ሁለቱም በመለስ ፍፁምነት ያምናሉ፤ እንደ ጣኦት ያመልካሉ፡፡መለስን በሌላ ‹‹መሪ›› መለወጥ ማለት ሃይማኖት የመለወጥ ያህል ይቆጥሩታል፡፡በመለስ ላይ ያላቸው እይታ
ምክንያታዊ ሳይሆን በጭፍን ስሜታዊነት የታወረ ነው፡፡ለዛም ነው መለስ የማይካዱ ጠንካራ ጎኖች እንደነበሩት ሁሉ፣ ማንም በቀላሉ
የማይረሳቸው የዘቀጡ ስራዎች ማከናወኑም ግልፅ ሆኖ ሳለ እነሱ ግን ማስተዋል የተሳናቸው፡፡
ከበጎ ምግባሮቹ ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል የአፍሪካ ህብረት ከአዲስ አበባ እንዳይነሳ ያደረገው ጠንካራ ክርክርና የአባይ
ግድብ እንዲጀመር ማድረጉ ሁሌም የሚወሱ ናቸው፡፡የሁለቱም በጎ ምግባሮች ሃገራዊ ፋይዳ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ሆኖም ግን፣ በስልጣን
ዘመኑ የፈፀማቸው እጅግ አስቀያሚ ተግባራትም መጥቀስ ይቻላል፡፡ዋነኞቹና ምናልባትም እንደ አንዳንዶቹ አባባል በሃገር ክህደት እስከማስጠየቅ
ሊለጠጡ የሚችሉት በኤርትራ ጉዳይ ያስተላለፋቸው ውሳኔዎች ናቸው፡፡
ኤርትራ ኢትዮጵያን ከመውረሯ በፊት(በስድስት ወር ቀደም ብለው) የትግራይ ክልል ፕረዚደንት የነበረት አቶ ገብሩ አስራትና
የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት አቶ አውዓሎም ወልዱ የኤርትራ አካሄድ በትክክል ተገንዝበው ቅድመ ዝግጅት እንዲደረግ ሲጠይቁ አቶ
መለስ ‹‹ሻዕብያ ዕብድ አይደለም፤ አይወረንም›› ብለው ከመከራከርም አልፈው በድምፅ ብልጫ አፋቸውን እንዳስያዟቸው በአቶ ገብሩ
መፅሐፍ ማንበብ እንችላለን፡፡ሻዕብያ ይወረናል የሚል ድምፅ የሰጡት ገብሩ፣ተወልደ፣አውዓሎምና አባይ ሲሆኑ፤ ስብሐት፣ስዬ፣ክንፈ፣
ስዩምና መለስ ደሞ አይወረንም በማለት ድምፃቸውን ሰጥቷል፡፡እናም የመለስ ድምፅ የፖሊት ቢሮው ውሳኔ የመቀልበስ ስልጣን ነበራትና
የሆነውን እንዲሆን አድርጋለች፡፡
የሚገርመው ግን በዚህ ብቻ ሳይገታ፣ ኤርትራ ሃገራችን በሐይል ከወረረች በኋላም ‹‹ዝም እንበላቸው፣ አንተንክፋቸው››
እያለ መከራከሩ ነው፡፡ሻዕብያ መቐለን በጄት አስደብድቧል፤ ዓድ ግራትና አጎራባች ከተሞችም ረዥም ርቀት በሚያዳርሱ ከባድ መሳርያዎች
ሲያስጨንቅ ‹‹እጅና እግራችሁ አሳስራችሁ ዝም በሉ›› ነበር የአቶ መለስ ክርክር፡፡
ኋላ ላይ አቶ መለስ በድምፅ ብልጫ ተሸንፎ ደምበር የማስከበሩ ጦርነት ሲጀመር የሻዕብያ እብሪት ወድያው እንደ ፊኛ ፈንድቶ
ድራሹ ሲጠፋና እግሬን አውጭኝ ብሎ ሲሸሽ ሻዕብያን ከጥፋት የታደጉት አቶ መለስ ናቸው፤የ24 ሰዓት የተኩስ አቁም አዋጅ በግላቸው
ፍቃድ በማወጅ፡፡ይህ አልበቃ ብሏቸውም፣ ሻዕብያ ተገድዶ ወደ ዕርቀ ሰላም ሲመለስም ለሃገራቸውን በመወገን ጠንክረው ከመከራከር ይልቅ
የአልጀርስና የጄነቫ ስምምነቶችን በመፈረም በሃገር ልጆች ደም የተመለሰው ባድሜን ለሻዕብያ ሸልመውታል፡፡በመሆኑም በአቶ ስዩም መስፍን
አማካኝነት ያስረዱን መርዶ ‹‹ባድሜ ለሻዕብያ ተሰጥታለችና እርማችሁን አውጡ›› የሚል ነበር( ‹‹ባድሜ የእኛ መሆኗን ተረጋገጠ››
ብሎ ሲያስጨፍረን ‹‹እኛ›› የሚለው ቃል ሻዕብያን እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብን ሊወክል እንደማይችል ከጥቂት ቀናት በኋላ እውን ሆኗል)፡፡
እነዚህ ጥቂት ምሳሌዎች ለማስታወስ የተገደድኩት ሰውዬውን ለመውቀስ ሳይሆን እንከን የለሽ ‹‹መሪ›› እንዳልነበረ ለማስረገጥ
ብቻ ነው፡፡በመሆኑም፣ እኔ ለሃገሬ ያለኝ ምኞት አቶ በረከትና አቦይ ስብሓት እንደሚመኙትና ለማስረገጥ እንደፈለጉት መለስን የመሰለ
አገረ ገዢ ሳይሆን ከመለስ በእጅጉ የተሻለ መሪ ነው፡፡የህዝብ ጥያቄዎችን በማሰርና በማስፈራራት ጭጭ ለማሰኘት የሚተጋ፤ በማንኛውም
መንገድ በስልጣን ላይ ለመቆየት ቆርጦ የተነሳ ሳይሆን አስተዳደራዊ ጉድለቶችን እየዘረዘሩ የሚተቹትን የሚሸልም መሪ ያስፈልገናል፡፡
ጠንካራ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በተለያዩ ዘድየዎች የሚያሽመደምድ ሳይሆን ልፍስፍስ ፓርቲዎችን በሞራልና በገንዘብ እየደገፈ
ጠንክረው እንዲወጡ የሚያደርግ መሪ ያስፈልገናል፡፡ለአንድ ፓርቲ የቆመ ፖሊስ፣ፍርድ ቤት፣የሚድያ ተቋም፣ ጥረት፣ወንዶ፣ቶምሳና ትእምት
የምሳሰሉ ትላልቅ የንግድ ድርጅቶች አቋቁሞ ሃገር የግለሰቦች እንዲመስል የሚያደርግ ሳይሆን ነፃና ገለልተኛ የምርጫ ቦር፣ ፖሊስ፣ፍርድ
ቤት፣ ፓርላማ፣ የግብይት ስርዓት ወዘተ የሚገነባ መሪ ነው የሚያስፈልገን፡፡በመሆኑም፣ ሃገራችን ኢትዮጵያ ለአሁኑኑም ሆነ ለወደፊቱ
የመለስን የመሰለ ስብእና ያለው ገዢ አያስፈልጋትም፡፡
ለማጠቃለል ያህል፣ አቶ መለስን ከማድነቅ አልፈው ወደ ማምለክ የተሸጋገሩ ወገኖች በሚከተሉት ነጥቦች ልዩነት የላቸውም፡፡አንድ፣
እስካሁን ድረስ መለስ እንደማንኛውም ሰው ሞቶ መቀበሩን አልካዱም፡፡ሰውዬውን ከልክ በላይ ቢያመልኩትም እንደ እየሱስ ክርስቶስ
‹‹የነበረ፣ ያለ፣ የሚኖር፤ አልፋና ኦሜጋ›› እያሉ ከማወደስ የተቆጠቡ ይመስለኛል፡፡
ቢሆንም ግን ለእነርሱ አቶ መለስ በትግሉ ወቅትም ሆነ ከትግሉ በኋላ ከተሰው ታጋዮች ሁሉ በእጥፍ እንደሚበልጥ ያምናሉ(በመቐለ ከተማ፣ ከሁሉም አቅጣጫ በሚታየው ቦታ የተሰራው ሐወልት አንዱ ምስክር ሲሆን ድሮ ከተሰውት ታጋዮችን ከሚያመለክተው ፈቶ መካከል የአቶ መለስ ፎቶ ከሁሉም በላይ በትልቁ መሰቀሉ ሌላው ምሳሌ ነው) ፤ በህይወት ካሉ መሪዎች በላይ መሆኑንም ያለልዩነት ይስማማሉ(‹‹የመለሰ ራዕይ›› የሚያጠነጥነው ይህንኑን ነው) ፤ በጣም የሚገርመውና የሚያሳዝነው ግን አቶ መለስ የሚመጣውን ትውልድም አይስተካከለውም ብለው ማመናቸውን ነው (የአቶ በረከት አስተያየትና አስተያየቱን የደገፉ ወገኖች አቋም የሚያስረግጠውም ይህንን ነው)፡፡
|
በመጠናቀቅ ላይ ባለው የመቐለ ስተድዮም በትልቁ
የተሰቀለው የመለስ ፎቶ ህያው መሪ ብቻ ሳይሆን የህያዋን ህያው መሆኑን ይገልፃል፡፡
|
ቢሆንም ግን ለእነርሱ አቶ መለስ በትግሉ ወቅትም ሆነ ከትግሉ በኋላ ከተሰው ታጋዮች ሁሉ በእጥፍ እንደሚበልጥ ያምናሉ(በመቐለ ከተማ፣ ከሁሉም አቅጣጫ በሚታየው ቦታ የተሰራው ሐወልት አንዱ ምስክር ሲሆን ድሮ ከተሰውት ታጋዮችን ከሚያመለክተው ፈቶ መካከል የአቶ መለስ ፎቶ ከሁሉም በላይ በትልቁ መሰቀሉ ሌላው ምሳሌ ነው) ፤ በህይወት ካሉ መሪዎች በላይ መሆኑንም ያለልዩነት ይስማማሉ(‹‹የመለሰ ራዕይ›› የሚያጠነጥነው ይህንኑን ነው) ፤ በጣም የሚገርመውና የሚያሳዝነው ግን አቶ መለስ የሚመጣውን ትውልድም አይስተካከለውም ብለው ማመናቸውን ነው (የአቶ በረከት አስተያየትና አስተያየቱን የደገፉ ወገኖች አቋም የሚያስረግጠውም ይህንን ነው)፡፡
No comments:
Post a Comment