‹‹ጦርነት የተደራጀ ግድያ እንጂ ሌላ አይደለም››
|
‹‹የዕብደት ውድመቱ የተጠነሰሰው በስመ አምባገነናዊ ስርዓትም ሆነ በስመ ቅዱሱ ነፃነት ወይም ዴሞክራሲ በጦርነቱ
ለሞተው፣ ወላጅ አልባ ለሆነውና ቤቱን ላጣው(ቤት አልባ ለሆነው) ምን ለውጥ ይኖሯል›› ማህተመ ጋንዲ
ህወሓት ደርግን ለማሸነፍ ጦርነት የጀመረበት 40ኛው ዓመት ከመቼውም ጊዜ በላይ በጣጣጣጣ...ጣጣጣም ጮክ ብሎ እያከበረ
ይገኛል፡፡በህይወቴ ጦርነት የተጀመረበት ቀን ይህን ያህል ከመጠን በላይ ተጋንኖ ሲከበር አይቼ አላውቅም፤ ለወደፊቱም ቢሆን ባላይ
እመርጣለሁ፡፡ይህ ቀን በሃገራችን፣ ብሎም በዓለማችን ጦርነት የቆመበት(ታሪክ የሆነበት) ቀን ቢሆን ኖሮ ‹‹እንኳን አደረሳችሁ››
ለማለት ማንም አይቀድመኝም ነበር፡፡ምን ዋጋለው! ቀኑ ጦርነት የተጀመረበት ነውና በጣም ለምወደው ህዝቤና ወገኔ የውድመት ቀን ለታወጀበት
ቀን ‹‹እንኳን አደረሰህ›› ለማለት ይከብደኛል፡፡
ለእኔ የካቲት 11 ቀን 1967 ዓ.ም ለትግራይ ህዝብ የምፅአት ቀን የታወጀበት ቀን ነው፡፡በእርግጥ፣ ለትግራይ ህዝብ
ብቻ አልነበረም፤ ለመላው ኢትዮጵያዊ እንጂ፡፡ጦርነቱን ማስቀረት ይቻል ነበር ወይ? ሌላ ጥያቄ ነው፡፡ያ ሃገር እንደ ሃገር የወደመችበት
ጦርነት የታወጀበት ቀንን ለማክበር ይህን ያህል ጨርቅን ጥሎ ማበድ ግን እንደ ቅጠል ለረገፋው የሰው ህይወትና ወደ አመድነት ለተቀየረው
የሃገር ንብረት ቅንጣትም አለመቆርቆር ነው፡፡በጣም የሚገርመው ደሞ፣ ‹‹የያኔው ጦርነት በሃገራችን እንዳይደገም ምን እናድርግ?››
አይደለም እየተባለ ያለው፡፡ይልቅስ፣ ‹‹ጦርነቱ አሁን ላለንበት ደረጃ አድርሶናልና እንኳን ደስ ያላችሁ›› ነው እየተባለ ያለው፡፡‹‹የት
ደረስን?›› ብሎ ለሚጠይቅ ዜጋ የሚሰጠው መልስ ግን ‹‹ፀረ ልማት፣ የድሮ ስርዓት ናፋቂ፣ ምንትስ ምንትስ…›› ነው የሚባለው፡፡ከዚሁ
የምንረዳው ቢኖር የትም አለመድረሳችን ነው፡፡
ጦርነቱ ያመጣው ድህነት፣ኋላ ቀርነትና ውርዴት ምን ያህል ነው? አይታወቅም! የማን ደፋርስ ነው እንዲህ ብሎ የሚጠይቀው?
ብቻ ግን ከ60 ሺ በላይ ወገኖች ህይወታቸውን እንዳጡና ከ100 ሺ የሚልቁ ደሞ አካላቸውን እንዳጡ ይነገራል፡፡እንግዲህ፣ ‹‹60
ሺ ወገኖች እንደ ቅጠል ረገፉ፤ 100 ሺ አካላቸው ጎደሉ›› ሲባል ከቁጥር በስተቀር ምንም ነገር ትዝ የማያላቸው ‹‹ሰዎች›› መኖራቸውን
አንርሳ፡፡ለአንድ በቢልዮኖች የሚቆጠር ብር ተቀብሎ በባንክ አካውንት የሚያስቀምጥ የሒሳብ ሰራተኛ ያብር ምኑም አያደለም፤ ቁጥር
ብቻ ነው፡፡ለእነዚህ ወገኖችም 60 ሺ ሙትና 100 ሺ አካል ጉዳተኛ ሲባል ከቁጥር ውጪ ሌላ አይታያቸውም፡፡ምን ያህል ቤተ ሰብ
ልቡ በሃዘን ተሰበረ? ምን ያህል የዕድሜ ባለፀጎች ያለ ጧሪና ቀባሪ ቀሩ? ምን ያህል እናቶች አባት የሌላቸው ልጆች ብቻቸውን ለማሳደግ
ተገደዱ? ምን ያህል ልጆች ያለ አባት ወይም ያለ እናት ወይም ያለ አባትና እናት ቀሩ? ወዘተ የመሳሰሉ ጥያቄዎች ማንም አይጠይቅም፡፡
እንደ ኢትዮጵያዊና እንደ ማንኛውም ሰብአዊ ፍጡር እናስብ ቢባል ደሞ ያ ጦርነት የታወጀበት ቀን በጭፈራና በሆታ ማክበራችን
‹‹ለመሆኑ ሰዎች ነን?›› የሚያስብሉ እውነታዎች መኖራቸውን እናስተውላለን፡፡ህወሓቶች ‹‹በትጥቅ ትግሉ ወቅት 60 ሺ ተሰውተዋል፣
100 ሺ ደሞ አካል ጉዳተኛ ሆኗል›› ሲሉ የህወሓት ታጋዮችን ብቻ ስለሚቆጥሩ ነው፡፡በየቤቱ የተገደለውስ ማን ነው የሚቆጥረው?
በ1977ቱ ድርቅ እንደ ቅጠል የረገፈው የትግራይ ህዝብስ? ጦርነቱ ባይኖር ኖሮ ያን ያህል ህዝብ ያልቅ ነበር? እያሉ መጠየቅ ስሜት
አይሰጣቸውም፡፡
‹‹የጦርነት ልዕለ ጥበብ ሳይታገሉ ጠላትን ማንበርከክ ነው›› ሳን ዙ
አንድም ጊዜ እንኳን ሲያነሱት ሰምቻቸው የማላውቀው ጉዳይ ግን ከደርግ ጋር ተሰልፎ እየተዋጋ ስላለቀውና ስለቆሰለው
ወገን ነው፡፡ብያንስ ብያንስ 60 ሺ ሳይሞትና 100 ሺም ሳይቆስል እንደማይቅር እርግጠኛ መሆን የሚቻል ይመስለኛል፡፡ በአጠቃላይ
ከ120 ሺ በላይ ኢትዮጵያዊ ህይወቱን አጥቷል፤ ከ200 ሺ በላይ ደሞ ለአካል ጉዳት ተዳርጓል፡፡ ምን ያህል ንብረትስ ወድሞ ይሆን?
ኢትዮጵያ እንዳለች ተቃጥላ ወደ አመድነት ተቀየረች ማለት ሳይቀል ይቀራል?መቸስ የደርግ ወታደር ቢሆንም ኢትዮጵያዊ ነውና ኪሳራው
ለመላው ኢትዮጵያውያን ነው፡፡
‹‹የጦርነት መጨረሻ ያዩት የሞቱ ሰዎች ብቻ ናቸው›› ፕሌቶ
እሺ፣ ይህንንስ ሆነና ጦርነቱ ካለቀ በኋላስ ጦርነትን ታሪክ የሚያደርጉ ሁኔታዎች ተፈጥሯል ወይ? ብለን ብንጠይቅስ?
መልሱ አይደለም ነው፡፡(በኢቢሲ የሚወራውን ትተን)ትናንት የፍትህ ያለህ ሲባል እንደ ነበረው ሁሉ ዛሬም የፍትህ ያለህ የሚስብሉ
ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ሰርቶ አደሩ የአከራዮች ጭሰኛ ነው፡፡የውሃ፣ የመብራት፣ የትራንስፖርት እጥረቶች ዛሬም አልተፈቱም፡፡ ዲሞክራሲ
ህልም ነው፤ ሰብአዊ መብቶች ይረገጣሉ፣ እንደ ኑግ ይወቀጣሉ፡፡በአጠቃላይ፣ ኢትዮጵያውያን ጎራ ለይተን እርሰ በራሳችን እንደ ባላንጣ
መተያየቱን ትተን ክርና ማግ ሆነን እንደንኖር የሚያስችሉ ሁኔታዎች አልተፈጠሩም፡፡ጦርነቱ ዛሬም እየቀጠለ ነው፡፡
የክፋቱ ክፋት፣ ጦርነት የተጀመረበት ቀን ይህን ያህል ተጋንኖ ከተሞካሸ፣ ጦርነት ጀማሪዎቹ ከፈጣሪ በላይ እንዲመለኩ
አለ የሚባለው ጊዜ፣ ገንዘብና ስልጣን መስዋእት ከተደረገ፣ ጦርነቱን ‹‹ያሸነፉ›› ሰዎች ሃገሪቷን እንዳሻቸው ማድረግ የሚችሉበት
ደረጃ የሚያደርስ ከሆነ ለወደፊቱስ ጦርነትን እርም የምንልበት ምክንያት ይኖራል ወይ? እኔ ግን ይቅርታ ይደረግልኝና አይመስለኝም፡፡ጦርነት
ይህን ያህል ክብር፣ ዝና፣ መጠን የለሽ ሃብትና ስልጣን የሚሰጥ ከሆነ ሌሎችም እንደ አማራጭ የማይጠቀሙበት ምክንያት አይኖርም፡፡ብያንስ፣
የጥቂቶች ልብ ሊሰልብ ይችላል፤ ኋላ ጦርነቱን የጀመሩት በብሶት ይሁን በምኞት አይታወቅምና፡፡ እንግዲህ፣ የካቲት 11ን ሳስብ ትዝ
የሚለኝ ይህን ሁሉ ስለሆነ ነው ‹‹እንኳን ደስ ያላችሁ›› ለማለት የማልደፍረው፡፡
ይህን በማለቴ ብዙዎች ቅር ሊላቸው እንደሚችል አውቃለሁ፡፡ከቅሬታ አልፈው የፍረጃ፣ የውግዘትና የእርግማን መዓት የሚያወርዱብኝ
ወገኖች እንደሚኖሩም ከልምድ ተምሬላሁ፡፡ ቢሆንም ግን የእምነትና የአመለካከት ጉዳይ ነውና የተሰጠኝን ከመቀበል ውጪ ሌላ አማራጭ
የለኝም፤ ሁልንም በፀጋ እቀበላለሁ፡፡ምናልባት ግን፣ የጦርነት ትርጉምና ማንነት፣ በሰው ህይወትና በሃገር ንብረት የሚያስከትለው
አደገኛ ውድመት በትክክል አውቀው ሲረዱት ድንፋታውን ይተውት ይሆናል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ደርግና ህወሓት የስልጣን ኮርቻን ለመቆናጠጥ የጨበጣ ውግያ በሚያካሂዱበት ወቅት የትግራይ ህዝብ ኑሮውን ከተለመደው
ውጪ ለመምራት ተገድዶ ነበር፡፡ለምሳሌ፣ ያፈራውን ለመሸጥና የፈለገውን ለመሸመት ወደ ገበያ መሄድ የተለመደ ተግባር ነው፡፡የትግራይ
ህዝብ ግን ያኔ በጠራራ ፀሐይ መገበያየት አይችልም ነበር፤ የደርግ ጭካኔ ምን ድረስ እንደነበር በሐውዜን ከተማ ለመገበያየት በተሰበሰበው
ህዝብ ላይ በፈፀመው እጅግ ዘግናኝ ጭፍጨፋ አስመስከሯል፡፡ በመሆኑም፣ የትግራይ ህዝብ በቀን መገበያየቱን አቁሞ በለሌት፣ለዛውም
ጫካ ባለበት ለመገበያየት ተገድዶ ነበር፡፡
ሌላ ምሳሌ ልጨምር፤ ደርግ የትግራይ ህዝብ በተኛበት ቤቱ ውስጥ እያለ ከነልጆቹ እሳት ይለቅበት፣ ለመሸሽ ቢሞክርም
በመትረየስ ይለቅመው ስለነበር ቤቱ ውስጥ መተኛት አቁሞ ነበር፡፡ማለትም እህሉን ጉድጓድ ውስጥ ቀብሮ፣ የቤት እንስሶቹን ይዞ ቤቱን
ትቶ አሉ በሚባሉት ገለልተኛ ዋሻዎች ውስጥ ለመኖር ተገድዶ ነበር፡፡ይህን ስል ተረት ተረት የሚመለስለው ሊኖር ይችላል፤ በፍፁም
አይደለም፡፡በተግባር አይቸዋለሁ፤ ያኔ ትርጉሙ ባይገባኝም ህፃን ቤተሰቦቼ ሌሊት ወደ ገበያ ሲሄዱ አስታውሳለሁ፣ ዋሻ ውስጥ ስንኖርም
አውቃለሁ፡፡በአጠቃላይ፣ ቤት ማቃጠል፣ የቤት እንስሶችን ዘርፎ መሄድ፣ ዕድሜና ፆታ ሳይለዩ መረሸን የተለመዱ ተግባራት ነበሩ፡፡
ተጠያቄው ማን ነው? የደርግና የህወሓት ባለስልጣናት! ለምን? ጦርነት እንደ ሁነኛው መፍተሔ ቆጥረው የህዝብ ልጆችን
በሁለት እሳትና ጭድ የሆኑ ጎራዎች ከፋፍለው ደም በማቀባባታቸው፡፡ጦርነት ከሚያስከትለው የሰውና የንብረት ውድመት ይልቅ ጥሎት የሚያልፈው
መቼም የማይሽር ጥቁር ጠባሳ በጣም የከፋ ይመስለኛል፡፡ምክንያቱም፣ ጠባሳውን ለማከም መሞከር ማለት በሰውነታችን የተሰካው ጦር በሐይል
መዝዞ ለማስወጣጥ እንደመሞከር ነው፡፡ስቃዩ አይጣል ነው፤ ልብን ያስወልቃል፡፡በጦርነት የወደመች ሃገር መልሶ መገንባትም ልክ እንደዛው
ነው፡፡
ሲጀመር፣ የሰው ልጅ ወደ ጦርነት አመራ ማለት እንደ ሰው ማሰብ ተስኖታል ማለት ነው፡፡በመሆኑም የጦርነት አሸናፊም
ተሸናፊም አይኖርም፡፡የጦርነቱ ጠባሳ ሙሉ በሙሉ እንዲድን ከተፈለገ ታድያ በጦርነቱ የተሳተፉ ሁሉ እኩል እንደተሳሳቱ በማመንና ከእነርሱ
ለመማር ዝግጁ በመሆን ነው፡፡እንዱን እያሞካሸን ሌላኛውን የምናወግዝ ከሆነ ግን ጊዜው ይረዝም እንደሆነ እንጂ አንዱ ሌላኛውን እንዲበቀል
እየገፋፋን መሆኑን ማወቅ ይኖርብናል፡፡
ለማጠቃልል ያህል፣ እስካሁን ድረስ እርሰ በርሳችን ተጨፋጭፈናል፣ ተጋድለናል፣ ደም ተቃብተናል፡፡የእኛ ነገር በእጭሩ፣
‹‹የገደለው ወንድምሽ፣ የሞተው ባልሽ
ሐዘንሽ ቅጥ አጣ፣ ከቤትሽ ላይወጣ›› ያስብላልና እርሰ
በርስ የተገዳደልንበት ቀን ማክበሩን ትተን ጦርነት ታሪክ ያደረግንበት ቀን ለማክበር ያብቃን፡፡
No comments:
Post a Comment