Monday, April 18, 2016

ብዙ የተወራላቸው የኢትዮጵያ የሃገር የመከላከያ ሰራዊትና የድህንነት ተቋማት የት ገቡ?



የትግራይ ህዝብ ሲተርት ‹‹ጨጓርያ ከልብስ ኣሎ እናበልኻዮ ይመውት›› ይላል፡፡ፀጉራም ውሻ አለ እያሉት ይሞታል ማለት ነው፡፡ፀጉራም ውሻ መታመሙንና ምንኛ እንደከሳ ማወቁ አዳጋች ነው፤ ለተመልካቹ ሁሌም ገዝፎና ወፍሮ ስለየሚታየው፡፡እናም ሲሞት ድንገት የሞተ ያህል ምን ነካው? ያስብላል፡፡የሃገራችን መከላከያ ሰራዊት በተለያዩ የአፍሪካ ሃገሮች ስኬታማ የሚባሉ የሰላም ማስከበር ስራዎች በማከናወኑ በተደጋጋሚ ሲወደስና ሲሞገስ ይስተዋላል፡፡

በአሁኑ ሰዓት እንኳን ሁለቱም ሱዳኖች ባፋጠጠችው በአብዬ ግዛት ስላም በማስከበር ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡በሃገረ ሶማልያም አልሻባብን እየተፋለመ እንደሚገኝ የሚታወስ ነው፡፡በቴክኖሎጂ ዘርፍም ከፍተኛ የሆኑ እምርታዎች በማስመዝገብ ላይ መሆኑን በመንግስት ሚድያዎች ተዘግቧል፡፡ከተወሰኑ ዓመታት በፊት የሃገር መከላከያው ባዘጋጀው ዓውደ ርእይ ሰው አልባ በራሪ አካላት (ድሮንስ) እስከ ማምረት እንደ ደረሰ ተነግሮን ነበር፡፡

ሌላው የሃገር ድህንነት ተቋሙ በአወቃቀርም ሆነ በቴክኖሎጂ አጠቃቀሙ የተራቀቀ በመሆኑ የሃገራችን ሰላምና መረጋጋት ማረጋገጡን ሲለፈፍ ነበር፡፡ኬንያ የአልሻባብ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ለማስተናገድ ስትገደድ፣ ዩጋንዳና ጁብቲም የጥቃቱ ሰለባ ሲሆኑ ኢትዮጵያ ምንም ዓይነት ጥቃት ያልደረሰባት የድህንነትና የመከላከያ ሃይላችን አስተማማኝ ስለሆነ ነው የሚሉ ክርክሮች መስማትም አዲስ አይደለም፡፡

በቅርቡ ሙርሌ የተባሉ የደቡብ ሱዳን ጎሳ ታጣቂዎች በጋምቤላ ክልል ውስጥ በሚገኙ የኑዌር ተወላጆች ያደረሱት ጥቃትና አፈናን ጨምሮ በሃገራችን የተሰነዘሩት ተደጋጋሚ ጥቃቶች ስንመለከት ግን እውነታው ሌላ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡በኤርትራ አዋሳኝ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በሻዕብያ መንግስትና ኤርትራ በመሸጉ አማፂ ቡድኖች በተደጋጋሚ ይታፈናሉ ይገደላሉ፡፡

በሃገር ውስጥም ግጭት በተከሰተ ቁጥር በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ህይወት ማለፉንና ደም መፍሰሱ አልቀረም፡፡ፖሊስ፣ መከላከያና ድህንነት ዘመናዊ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅመው ግጭቶች ከመከሰታቸው በፊት ማክሸፍ፣ ግጭቶቹ ከተከሰቱም የሰው ህይወትና ንብረት ሳይወድም በቀላሉ መቆጣጠር ሲገባቸው በተደጋጋሚ ህይወትና ንብረት ሲወድም ይስተዋላል፡፡እናም እነዚህ ተቋማት የተሸከሙት ክብርና ዝና ከልሏዋቸው አሉ ብለን ስንኩራራ አሸልበው እንዳይሆን ያሰጋል፡፡የስጋቴ ምንጭ የሚከተሉት ናቸውና አንድ በአንድ እንያቸው፡፡

የአየር ክልላችን ክፍተት ያጋለጡ ክስተቶች


ቀኑ አርብ ነበር፤ ከሰዓት በኋላ፡፡የዓይደር አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ህፃናት በትምህርት ቤቱ ቅፅር ግቢ በሚገኘው ሜዳ ይቦርቃሉ፡፡ድንገት አንድ መቶ ፓውንድ የሚመዘን ክላስተር ቦምብ የጫነ የኤርትራ የጦር አውሮፕላን ወደ ትምህርት ቤቱ ዝቅ ብሎ በረረና በህፃናቱ ላይ አወረደው፡፡ሲጫወቱ የነበሩ ህፃናት ከአፈር ጋር ተቀላቅለው ወደ አመድነት ተለወጡ፡፡ሳቅና ጨዋታ ወደ ዋይታና ማጣጣር ተቀየሩ፡፡በዛች ቅፅበት የ15 ህፃናትና አስተማሪዎች ህይወት ተቀጠፈ፤ ከአስር በላይ የሚቆጠሩ ደሞ ኩፍኛ ቆሰሉ፡፡ይህን መርዶ የሰሙ የመቐለ ኗሪዎች፣ የአደጋ ሰራተኞችና የተማሪዎቹ ወላጆች በአስር ደቂቃ ወስጥ ተምህርት ቤቱን ወረሩት፡፡

ከአንድ ሰዓት በኋላ የጦር አውሮፕላኑ ሌላ ክላስተር ቦምብ ጭኖ ተመለሰና በትምህርት ቤቱ በሚርመሰመሰው ህዝብ ላይ አዘነበው፡፡ሌላ ጭኾት፣ ሌላ ዋይታ፣ ሌላ ሲቃና ማጣጣር ሆነ፡፡የኤርትራ የጦር አውሮፕላን አስር ህፃናትን ጨምሮ የ48 ንፁሃን ዜጎች ህይወት ቀጠፈ፡፡150 ንፁሃን ዜጎች ኩፍኛ ተጎዱ፡፡ይህ ምንጊዜም በቁጭት የሚያንገበገብ ዘግናኝ ጥቃት የደረሰው ግንቦት 28 ቀን 1990 ዓ.ም. ሲሆን ጥቃቱ የተፈፀመው ደሞ የትግራይ መናገሻ በሆነችው በመቐለ ከተማ ነው፡፡

ያኔ የኢህአደግ መንግስት ኢትዮጵያን ከተቆጣጠረ በ15 ዓመቱ ነበር፡፡የኢትዮጵያ አየር ሃይል የት እንደነበረ አይታወቅም፡፡ የጦር ጄቶችን በአርፒጂ ሳይቀር ከሰማይ ያረግፋሉ የሚባልላቸው የህወሓት ታጋዮች ወሬውን ከህዝቡ እኩል ሰምተው በቁጭት ከመቃጠል ውጪ ሌላ አማራጭ አልነበራቸውም፡፡
ጥያቄው ዛሬስ ምን ዋስትና አለን፤ ከተመሳሳይ ጥቃቶች ነፃ ነን ወይ የሚል ይሆናል፡፡

ወደ 1997 ዓ.ም. እናምራ፡፡ ድህረ ምርጫ 97ን ተከትሎ በተነሳው ግርግር ምክንያት ሻምበል አብዮት እና ሻምበል በኃይሉ የተባሉ የኢትዮጵያ አየር ኃይል አብራሪዎች አንድ ኤምአይ 35 ሔሊኮፕተር ይዘው ወደ ጐረቤት አገር ጂቡቲ ኮብልለው እንደነበር ይታወሳል፡፡ ዳሩ ግን፣ የጂቡቲ መንግሥት አብራሪዎቹንና ሔሊኮፕተሩን ለኢትዮጵያ መንግሥት አሳልፎ በመስጠቱ ቡዙም ሳይቆዩ ነበር የተመለሱት፡፡ አብራሪዎቹ የጦር ፍርድ ቤት ቀርበው ስለተፈረደባቸው በአሁኑ ወቅት በእስር እንደሚገኙ ይነገራል፡፡ኤምአይ 35 ሔሊኮፕተር ይዞ ወደ ሌላ ሃገር መኮብለሉ ግን በሻምበል አብዮት እና በሻምበል በኃይሉ መታሰር አላቆመም፡፡ልክ ከ10 ዓመት በኋላ ሌላ ተመሳሳይ ሔሊኮፕተር ተጠልፏል፡፡

ወሬው በማሕበራዊ ሚድያ ሲሰራጭ ከሰነበት በኋላም ሪፖርተር ጋዜጣ በታኅሳስ 15 ቀን 2007 ዓ.ም. ሰፋ አድርጎ እንደዘገበው ይታወሳል፡፡ዘገባው ‹‹የኢትዮጵያ አየር ኃይል ንብረት የሆነ ተዋጊ ሔሊኮፕተር ባለፈው ዓርብ ተጠልፎ ኤርትራ ግዛት አሰብ ማረፉ ተረጋገጠ፡፡›› ይላል፡፡ባለቤትነቱ የኢትዮጵያ አየር ኃይል የሆነውና ሩሲያ ሠራሽ ኤምአይ 35 ተዋጊ ሔሊኮፕተር ይዞ ወደ ኤርትራ የኮበለለው ዋና አብራሪ ሻምበል ሳሙኤል ግደይ፣ከረዳት አብራሪው መቶ አለቃ ቢልልኝ ደሳለኝና የበረራ ቴክኒሺያን ፀጋ ብርሃን ግደይ ጋር የዘወትር የልምምድ በረራ ለማድረግ ከጠዋቱ 2፡35 ሰዓት ድሬዳዋ ከሚገኘው የአየር ኃይል ቤዝ ተነስተው የዓፋር ክልልን አቋርጠው ዓሰብ እስኪ ደርሱ ድረስ ማነህ ያላቸው አካል አልነበረም፡፡

ይህ ክስተት የአየር ክልላችን በምን ሁኔታ እንደሚገኝ የሚጠቁም ነበር፡፡ሔሊኮፕተሩ ከድሬዳዋ ተነስቶ አፋር አቋርጦ ዓሰብ እስኪደርስ ድረስ የሃገር መከላከያ ሃይላችን በተለይም የአይር ሃይላችን ከእንቅልፉ አልነቃም ነበር፡፡ዜናውን ቀድመን የሰማነውም ከማሕበራዊ ምድያዎች ነው፡፡

የሚያስገርመው ደሞ የኢትዮጵያ አይር ሃይል ሰዎች ‹‹ረዳት አብራሪው ጀማሪ ነው፡፡ የበረራ ቴክኒሺያኑ ቴክኒካዊ ጉዳዮችን መከታተል ነው፡፡ ዋና አብራሪው ረዳት አብራሪውና ቴክኒሺያኑ እያወቁም ወይም ያለነሱ ዕውቅና የፈለገበት ወስዶ ሊያሳርፍ ይችላል፤›› ከማለት ውጪ ስለረዳት አብራሪውና ስለተክንሻኑ ሁኔታ ምንም አለማለታቸው ነው፡፡መቸስ እነዚህ ዜጎች ያለፍቃዳቸው ከሆነ ዓሰብ እንዲያርፉ የተገደዱት አየር ሃይላችንም ሆነ መንግስት ሊደርሱላቸው ይገባ ነበር፡፡ሆኖም ግን እነርሱም እንደ ኮለኔል በዛብህ ጴጥሮስ የገቡበት አይታወቅም፡፡ሔሊኮፕተሩም ለሻዕብያ በስጦታ መልክ የተበረከተ ይመስል ተረስቶ ቀረ፡፡ኤምአይ 35 ሔሊኮፕተር መትረየስና ተወንጫፊ ሮኬቶች የተገጠሙለት ዘመናዊ ተዋጊ ሔሊኮፕተር ስለሆነ እንዲሁ ችላ ሊባል አይገባም ነበር፡፡

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ፓይለቶች መኮብለል በእነዚህ ሁለት ክስተቶች አልተጀመረም፡፡በድህረ ምርጫ 97 ዓ.ም. በቤላሩስ በሥልጠና ላይ የነበሩ ሰባት የኢትዮጵያ አየር ኃይል የኤስዩ 27 ተዋጊ ጀት አብራሪዎች ከድተው ጥገኝነት መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡ አብራሪዎቹ በተለያዩ የምዕራብ አገሮች ጥገኝነት ማግኘታቸው ይነገራል፡፡ቀደም ሲል ሻምበል ተሾመ ተንኮሉ የተባለ የአየር ኃይል ባልደረባ በ1995 ዓ.ም. ኤል 39 የተሰኘ የመለማመጃና ቀላል የውጊያ አውሮፕላን ለልምምድ በረራ ከመቀሌ ቤዝ ይዞ እንደተነሳ ወደ ኤርትራ ኮብልሎ ነበር፡፡

እነዚህ ተከታታይ ክስተቶች በቅርቡ በጋምቤላ ውስጥ ከተፈፀመውና 208 የሚሆኑ ዜጎች የፈጀው ዘግናኝ ጭፍጨፋ ጋር አያይዘን ስንመዝናቸው ከተከታይ ጥቃቶችና ስጋቶች የሚታደገን አካል አለመኖሩን ይጠቁማሉ፡፡አንቱ የተባሉት የአየር ኃይል አብራሪዎች የሃገር ድህንነት መጠበቅ ሲገባቸው የሚኮበልሉ ከሆነ ትልቅ አደጋ አለ ማለት ነው፡፡ይህ አደጋ ለሃገር ድህንነት ተቋሙ አልታየውም ወይም ቀድሞ ሊደርስበት አልቻለም፡፡

‹‹እያንዳንዱን የድንበር ወሰን ወታደር አስቁሞ መጠበቅ አይቻልም፤››አቶ ጌታቸው ረዳ


ፅርግያ ግርማይ በትግራይ ክልል ውስጥ በካፍታ ሁመራ ወረዳ ይገኛል፡፡ከተለያዩ የትግራይ አከባቢዎች የተሰባሰቡ ወጣቶች በባህላዊ መንገድ ወርቅ የሚያወጡበት አከባቢ ነው፡፡ጥር 27 ቀን 2008 ዓ.ም. ከንጋቱ 12 ሰዓት ላይ 85 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን እንደተለመደው በባህላዊ መንገድ ወርቅ በማውጣት ላይ ተሰማርቷል፡፡ድንገት የሃገራችን ደንበር ጥሰው የገቡና ከኤርትራ በመጡ ታጣቂዎች ተከበቡ፡፡የተወሰኑ ወጣቶች ለማምለጥ ሙከራ ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም፤ ከበባው ሁሉንም አቅጣጫዎች የሚያካልል ነበር፡፡ታጣቂዎቹ ‹‹ከአሁኗ ሰዓት ጀምሮ ከእኛ ትእዛዝ ውጪ ስንዝር እንኳን መንቀሳቀስ አትችሉም›› የሚል ቀጭን ትእዛዝ ሰጧቸው፡፡ከዛም በጠብ መንጃ አፈሙዝ አስገድደው ወደ ኤርትራ ወሰዷቸውና የለበሱት ልብስና በእጃቸው የያዙት ንብረት እንዳለ ገፈው በምትኩ ወታደራዊ ልብስ እንዲለብሱ ተደረገ፡፡

እንደተለመደው፣ ዜናው የተሰማው በማሕበራዊ ምድያ ተጠቃሚዎችና በአሜሪካ ድምፅ ሬድዮ የትግርኛው ክፍለ ግዜ ብቻ ነበር፡፡ሁሌም በምስጢራዊነቱ የሚታወቀው የኢትዮጵያ መንግስት ለሁለት ሳምንታት ያህል አንዲት ቃል ትንፍሽ አላለም፡፡ወደ ኤርትራ ታፍነው የተወሰዱት ዜጎች ግን በአስገዳጅ የጉልበት ስራ ተሰማረተው ሌት ተቀን የባርነት ህይወት ለማሳለፍ ተገድዷል፡፡

መንግስት ዜጎቹ ድህንነታቸውን የመጠበቅና እንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ሲፈጠሩም የሕዝቡ መረጃን የማግኘትና ስለሃገሩ ወቅታዊ ጉዳዮቸ የማወቅ መብት ዋጥ አድርጎት ዝም ነበር ያለው፡፡ከሁለት ሳምንታት በኋላ ከመንግስት ባለስልጣናት ጋራ የቀረበ ግንኙነት ያላቸው የግል ሚድያዎች በሻዕቢያ መንግስት የተጠለፉት ኢትዮጵያውያን 32 ብቻ እንደሆኑና በሱዳን አደራዳሪነት ወደ ሃገራቸው እንደተመለሱ ሰምተናል፡፡የአሜሪካው ድምፅ ሬድዮ ጨምሮ ቡዙ ወገኖች በዚህ ቁጥር አይስማሙም፡፡
በሱዳን አደራዳሪነት ከሻዕብያ አፈና ነፃ ወጥተው ወደ ሃገራቸው የተመለሱት ኢትዮጵያውያን ታድያ
ያለ ክፍያ ተገደው የእርሻ ሥራ በሚሠሩበት አካባቢ እንደነሱ ተጠልፈው የተወሰዱ ቁጥራቸው ከ30 በላይ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ቀን ቀን በዚሁ ተመሳሳይ የጉልበት ሥራ ተገደው ሲሠሩ፣ ሌሊት ሌሊት ደግሞ በአሰቃቂ ሁኔታ ታስረው እንደሚያድሩ መመልከታቸውን፤ አብዛኞቹ ለማምለጥ ሲሞክሩ በጥይት የተገደሉ፣ ተመትተው አካላቸው ላይ ጉዳት ደርሶባቸው በሕይወት የተረፉ መኖራቸውን፣ እንዲሁም በርካቶች ተገደው ወታደራዊ ሥልጠና ወስደው በተለይ ግንቦት ሰባት አርበኞች ግንባር የተባለውን ድርጅት እንዲቀላቀሉ መደረጋቸውን በይፋ ሲናገሩ ተሰምቷል፡፡
በኤርትራ አዋሳኝ አካባቢ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የኤርትራ ወታደሮችና ደምሒትን ጨምሮ በኤርትራ መሽገው የሚገኙ የኢትዮጵያ አማፂ ኃይሎች ሁሌም ወጣቶችን እያፈኑ እንደሚወስዱ ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡የሚገርመው ግን የኢትዮጵያ መንግስትም ስለሁኔታው በደምብ ቢያውቅም በአፈ ቀላጤው አማካኝነት እንደማያስደንቀው መናገሩን ነው፡፡

የኤርትራ መንግስትና በኤርትራ የሚገኙት የኢትዮጵያ አማፅያን ስለፈፅሟቸው ተደጋጋሚ አፈናዎች ጥያቄ የቀረበላቸው የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ‹‹እያንዳንዱን የድንበር ወሰን ወታደር አስቁሞ መጠበቅ አይቻልም፤የኤርትራ መንግሥት ኃላፊነት የጎደለው የሽፍትነት ተግባር ላይ የተሰማራ በመሆኑ በተፈጸመው ጠለፋ እምብዛም አለመገረማቸውን›› ነበር ያሉት፡፡

ይህን መሳይ አፈናዎች ግን የመጀመርያም የመጨረሻም አይደሉም፡፡ፀሎታችን ሆነ ምኞታችን ለወደፊት እንዳይከሰቱ ነው፤ ፀሎትና ምኞት ዋስትና ባይሰጡም ዳሩ፡፡ከአራት ዓመት በፊት፣ በ2004 ዓ.ም. በተመሳሳይ በባህላዊ መንገድ ወርቅ በማውጣት ላይ ከነበሩት ኢትዮጵያውያን 140 የሚሆኑት ዜጎች ታፍነው የተወሰዱ ቢሆንም እስከ ዛሬ ድረስ ግን እነሱን የበላው ጅብ ሲጮኽ አልተሰማም፡፡

የኢህአዴግ ባለስልጣናትም ከማስፈራራት አልፈው የወሰዱት እርምጃ የለም፡፡
The Irob Rights Advocacy Association (IRAA) የተባለ ተቋም በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት በኤርትራ መንግስት ተፍነው የተወሰዱ የ96 ዜጎች ስም ዝርዘር ለትግራይ ክልል መንግሥትና ለፌደራል መንግሥት አሳውቀዋቸው ነበር፡፡የክልሉም ሆነ የፌደራል ባለስልጣናቱ ግን ሰምተው እንዳልሰሙ ነበር ጭጭ ያሉት፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት በሻዕቢያ ላይ የአፀፋ እርምጃ የወሰደው የአውሮፓ ቱሪስቶችና ኢትዮጵያውያን ከአፋር ክልል አፍኖ በወሰደበት ወቅት ነበር፡፡ያኔም ቢሆን ግን የተወሰኑ የሻዕቢያ ወታደራዊ ካምፖችን ከማጥቃት የዘለለ አልነበረም፡፡ በአጠቃላይ ሻዕቢያ ለፈጸማቸው ተደጋጋሚ ትንኮሳዎች ‹‹በአንድአንድ ወሳኝ ሥፍራዎች ላይ የአውሮፕላን ጥቃት ፈፅመናል›› ይላሉ እንጂ የማያዳግም የተበለለት እርምጃ ተወስዶ አያውቅም፡፡
የኢህአዴግ ባለስልጣናት አቋም በሚከተለው የአለማ ተስፋይ ጥቅስ ሊጠቃለል ይችላል፡፡
The Ethiopian government never fights for its own citizens’ rights; instead it fights hard to make sure that it stays in power long.
For the Ethiopian government officials, to follow individuals who are suspected of some minor demeanors related to their power equation is more important than to search for the whereabouts of over a hundred abducted civilians of their own citizens.
እንሆ ዛሬም የሃገራችን ድምበር ዘልቀው በገቡ የደቡብ ሱዳን የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ባደረሱት ዘግናኝ ጥቃት የ208 ንፁሃን ዜጎች ህይወት አልፏል፤ 108 ህፃናት ታፍነው ተወስዷል፣ 75 ዜጎች ለአካል ጉዳት ተዳርጓል፣ 2000 የቀንድ ከብቶች ተዘርፈዋል፣ እንዲሁም ሃብትና ንብረት ወድሟል፡፡አስደንጋጭና የሚቆጭ ጥቃቱ ተከትሎም ብዙ ዜጎች ‹‹ይህን ሁሉ ሲሆን የፌደራል ፖሊስ፣ የሃገር መከላከያና የሃገር ድህንነት ተቋማት የት ነበሩ?›› በማለት እየጠየቁ ይገኛሉ፡፡

የኢትዮጵያ ተከታታይ ገዢዎች ከቀደምቶቻቸው ተምረው ሊያርሙት ያልቻሉት አንደ መጥፎ አመል አለ፡፡ገዢዎቹ አንድ ጉዳይ ትኩረት የሚሰጡትና አርምጃ የሚወስዱበት ከሃገር ሉዓላዊነት፣ ከዜጎች መብትና ድህንነት ጋራ ካለው አንድምታ መዝነው ሳይሆን የግል ጥቅማቸው ያማከለ ነው፡፡ምንጊዜም ቢሆን ቀጣይነት ካላቸው ሃገራዊ ጥቅሞች ለስልጣናቸው ቅድሚያ ይሰጣሉ፡፡


Origionally posted on: www.ethiopianaffairs.com

No comments:

Post a Comment