Friday, November 22, 2013

‹‹ሴኩላሪዝም››፡አብሮ የመኖር ቁልፍ





ከእለታት ባአንዱ ቀን አንድ የማላውቀው ሰውየ እመንገድ ላይ አስቆመኝና የሆነ ነገር ሊያነጋግረኝ እንደሚፈልግ ‹‹በታላቅ ትህትና›› ጠየቀኝ፡፡እሺ ብየ ቆምኩለት፡፡ከዛም የሆኑ በራሪ ወረቀቶች ሰጠኝና እንዳነባቸው ነገረኝ፡፡ትንሽ አየት አየት አድርጌ እንደማያስፈልጉኝ ነግሬው መልሼ ሰጠሁት፡፡
‹‹የእየሱስ መልእክ የያዙ ናቸው፤ እየሱስን መቀበልስ አትፈልግም?›› ጠየቀኝ፡፡
‹‹የት አለ?›› ጥያቄውን በጥያቄ መለስኩለት፡፡
‹‹አሱማ እየሱስ የትም አለ››
‹‹የትም ካለ ታድያ መቀበሉ ለምን አስፈለገ?››
‹‹እ… ምን መሰለህ…እ››
አላስጨረስኩትም፤ እዛው በቆመበት ትቼው ወደ ስራየ ሄድኩ፡፡ምክንያቱም እንደዚህ ዓይነቶቹ ‹‹የእየሱስ አከፋፋዮች›› እየሱሳቸውን እንድቀበልላቸው ብዙ ጊዜ ሊያግባቡኝ ሞክረው በተደጋጋሚ እንደማይሆን ነግሬያቸዋለሁ፤ ከነርሱ ጋር የምለመጥበት ትእግስቴ ተሟጦ አልቀዋል፡፡
ተከራይቼ እኖርበት በነበረው ግቢ ውስጥ ሁለት የድምፅ ማጉያዎች ያሉት ትልቅ ቴፕ እስከ መጨረሻው ድረስ ተከፍቶ ያጓራ ነበር፡፡የቴፑ ነጎድጓድ ድምፅ የጀሮ ታምቡር ይበሳል፤ አናት ይበረቅሳል፤ ያለ ማጋነን፡፡በቴፑ የሚደጋገሙት ዘፈኖች ተማሳሳይ ናቸው፤ በጎጃምኛ ዳንስ ታጀበው‹‹እየሱሴ… እየሱሴ…እየሱሴ…›› ይላሉ፡፡‹‹እየሱስ ጀግና ነው፤ እየሱስ ሃይለኛ ነው፤ የኔ ጌታ አሃ አሃ፤ የኔ ጌታ አሃ አሃ…›› የእየሱስ ሰርግ ወይም እየሱስ ድል የተቀዳጀበት ቀን ነበር የሚመስለው፡፡
ይህኛው እየሱስ ያ ‹‹የአዳም ልጆችን ሃጠያት ለመደምሰስ›› በጎለጎታ ተሰቅሎ የሞተው ሳይሆን እንደነ በላይ ዘለቀ፣አብዲሳ አጋ፣አሉላ አባነጋ ወዘተ የባዕድ ወራሪዎችን ታግሎ ያሸነፈ ነው የሚመስለው፡፡ እየሱስን የሚያሞካሹ ዘፈኖች በላይ ዘለቀን ለሟሞካሸት ከሚዘፈኑ በላይ በላይ የሚሉ ዘፈኖች መለየት ይከብዳል፡፡
ይህን ያህል የሚዘፈንለት ሰውየ በመፅሓፍ ‹‹ቅዱስ›› ካለው እየሱስ ጋር በምንም መልኩ አይመሳሰሉም፡፡የመፅሓፍ ‹‹ቅድሱ›› እየሱስ ዘፈን እንደማይወድ መፅሐፉ ይነናገራል፤ይህኛው ግን እንደ ‹‹አባባ ታምራት›› እያንጓለለ ይባልለታል፡፡‹‹እየሱስ ያድናል…እየሱስ ጌታ ነው…›› የሚሉ መፈክሮች በየፌስቡኩና በየጎዳናው ይስተጋቡለታል፡፡ተከታዮቹ የ60ዎቹ አብዮተኞች ይመስላሉ፡፡
የእንዚህ አላስፈላጊ ድምፆች ፍቱን መከላከያ አለኝ፤ሁለቱም ጆሮዎቼ ጥርቅም አድርጎ የሚዘጋ ‹‹ሄድ ፎን›› አድርጌ ሙዚቃ ወይም በድምፅ የተቀነባበረ መፅሐፍ ማዳመጥ፡፡ያኔ ሃገር የሚበጠብጠው ውዳሴ እየሱስ ‹‹ጃም›› ይደረጋል፡፡አሁን አሁን ደግሞ የጋሼ አበራ ሞላ ‹‹ያምራል አገሬ›› አልበም ለ‹‹ጃሚንግ››ና ለመዝናናት እየተገለገልኩበት እገኛለሁ፡፡እዛ ጋ ‹‹እየሱሴ…እየሱሴ…እየሱሴ…›› ይባላል፡፡እዚ ጋ ደግሞ ‹‹ያምራል ሃገሬ….ኸረ ያምራል ሃገሬ…ያምራል ሃገሬ…››
አላስፈላጊ ድምፆች ጃም በማድረግ መከላከል ችየ ነበር፡፡ነገር ግን መከላከል የማይቻል ሌላ ችግር ገጠመኝ፤ አከራዮቼ በአዲስ አበባ የሚደጋገመው የውሃ መጥፋትን አስታክከው ለራሳቸው እንደ ፈለጉ እየተጠቀሙ እኔንን ግን ሊያስጠቅሙኝ አልፈቀዱም፡፡እነሱ ከቀዱና ገላቸውን ከታጠቡ በኋላ ቆጣሪውን ያጠፉታል፡፡ከዛም ‹‹ውሃ የለም›› ማለት ልሙድ አደረጉት፤ እኔም ውሃ እየገዛሁ መጠቀም ግዴታየ ሆነ፡፡ይህ ነገር ለሁለት ወራት ቀጠለ፡፡የኋላ ኋላ ሲመረኝ ግን የአከራዮቼ ጎረቤቶችን በመጠየቅ እውነታውን ማወቅ ቻልኩ፡፡
ይህ አውነታ በጣም አስከፋኝ፡፡ከአከራዮቼ ጋር የነበረው የእገዚሔር ሰላምታ ተቋረጠ፤ እነሱም ከአንድ ወር በኋላ ቤታቸውን ለቅቄ እንድወጣ አዘዙኝ፡፡እናም ሌላ የሚከራይ ቤት ፍለጋ ወጣሁ፤ ደላሎች እንደ ኳስ ተቀባበሉብኝ፡፡‹‹አዛ ጋ ቤት አለ›› ይሉኛል፤ ቤቱን እንዲያሳዩኝ ጠይቄያቸው አብረን እንደሄዳለን፡፡ቤቱ የተከራየው ሰውየ ግን ገና አልወጣም፤ ወይም ቤቱ ለሰው ልጅ ቀርቶ ለበጎች ጉሮኖነት የማይበቃ ሁኖ አገኘዋለሁ፡፡በመጨረሻ ግን የወር ደሞዜን ግማሽ በየወሩ እየከፍልኩ እንድኖር ግዴታየ ሆነና አንድ ቤት ተከራየሁ፡፡
የአዲስ አበባ ቤት አከራዮች መቸም የማይረካ የብር ፍላጎት እንጂ የሰው ክብርና ፍቅር የላቸውም፡፡የብር ‹‹ሸውሃታቸው?›› ምንጊዜም እንደ ጨረር በጨመረ ቁጥር ሰብአዊነታቸው ወደ ዜሮ እየተጠጋ ይሄዳል፡፡የህ አካሄዳቸው በዚሁ ከቀጠለ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ የከተማ ጅቦች መሆናቸው አይቀርም፡፡ጅቦች ደግሞ እርሰ በርሳቸው ስለማይተማመኑ አብረው መኖር አይችሉም፡፡ጋሼ አበራ ሞላ እንዲህ ይመክረናል፡
መከባበር… መተሳሰብ… መፋቀር
መዋደድ… ያስፈልጋል የሰው ልጅ… ሲኖር ባንድ አገር
አልያግን
አኔም የለሁ… አንተም የለህ
እሱም የለም …አንችም የለሽ
ማንም የለም
የሃይማኖት መቻቻል፡ ማን ይቻል?
‹‹የሃይማኖት መቻቻል›› በመገናኛ ብዙሐን ተደጋግሞ ሲወራ ይደመጣል፡፡በተለያዩ የህትመት ውጤቶች ብዙ ጊዜ ተፅፏል፤አንብበናል፡፡ይሁን እንጂ አለመቻቻሉ እየተባባሰ ሲቀጥል እንጂ መሻሻል አላሳየም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ መቻቻል መፍትሔ ሊሆን ስለማይችል ነው፡፡መቻቻል፡ አንዱ ፅንፈኛ ጉልቤ ‹‹እኔ ያልኩህ የማትቀበል ከሆነ ክንዴን አሳይሃለሁ›› እያለ ሲፎክርብህ፣ ዝም ብሎ ማሳለፍ፤ ስሜቱን መቆጣጠር አቅቶት ቡጢ ሲያቀምስህ፣ ዋጥ አድርገህ ጭጭ ማለትን ያመለክታል፡፡
ሆኖም ግን ብዙ በታገስክ ቁጥር ፅንፈኛውም እልህ ውስጥ ስለሚገባ የባሰ ጉዳት ለማድረስ(የመደባደብ ስሜቱን ለማርካት) ያለ የሌለ ጉልበቱና ችሎታው መጠቀሙ አይቀርም፡፡ይህ ሲሆን ግን የተጠቂው ትእግስት ተሟጥጦ ስለሚያልቅ ከመታገስ ወደ መከላከል፣ ከምከላከልም ወደ ማጥቃት መሸጋገሩ የግድ ይሆናል፡፡ይህ ማለት ደግሞ መቻቻሉ ወደ ጦርነት አደገ ማለት ነው፡፡
ስለዚህ እኛ የሚያስፈልገን የሃይማኖት መቻቻል ሳይሆን መከባበር፣መተሳሰብና መፋቀር ነው፤ ጋሼ አበራ ሞላ እንዳለው፡፡እነዚህ ነገሮች ሲኖሩ ነው በማሃከላችን ሰላም ሊሰፍን የሚችለው፡፡ሰላም ደግሞ አብሮ የመኖር ቁልፍ ነው፡፡በአንፃሩ ደግሞ መከባበር ሳይኖር መተሳሰብ ሊመጣ አይችልም፤ መተሳሰብ በሌለበት መፋቅር አይኖርም፤ ፍቅር ከሌለም ሰላም አይታሰብም፡፡ሰላም የሌለው ማሕበረሰብ ደግሞ የበረሃ አውሬ ማለት ነው፤ አንዱ ሌላውን እየበላ ይኖራል፡፡
ባለፈው ሳምንት ‹‹ሴኩላሪዝምና መልካም አስተዳደር በማስፈን የሲቪል ሰርቪሱ ሚና›› በሚል ርእስ የተጠናቀረ ፅሑፍ ለኢትዮቴሌኮም ሰራተኞች የ‹‹ኢንፎርሜሽን ሲስተም ዲቪዥን ---information system division›› በኢሜል ተልኮልን ተወያይተንበታል፡፡የፅሑፉ ዋና ዓለማ የሚያጠነጥነው የመንግስት ሰራተኞች በሚሰሩበት መስራቤት ከሃይማኖት ገለልተኛ በሞሆን ተገልጋዩን(ህዝብ) በእኩልነት እንዲያስተናግዱ የሚመክር ነው፡፡በተጨማሪም ሃይማኖታዊ የሆኑ ነገሮች በየመስራቤቱ እንዳይንፀባረቁ በማድረግ መልካም አስተዳደር ለማስፈን ያለመ ነው፡፡
በመስራቤት ውስጥና መስራቤቱ ስራ ለማቀላጠፍ በሚያቀርባቸው መኪኖች መዝሙርና መንዙማ ማዳመጥ አይቻልም፤ሃይማኖታዊ ስእሎችና ቅርፃ ቅርፆች፣የሰንበቴና የበዓለ ማርያም እንዲሁም የበዓለ ወልድ ዝክሮች ተቀባይነት እንደማይኖራቸው ያትታል፤ ፅሑፉ፡፡
በውይይቱ ላይ ‹‹CRBT…color ring back tone›› ስለሚባል የቴሌ ደምበኞች ሲደወልላቸው ለደዋዩ የሚያሰሙት የድምፅ አገልግሎት ተነስቷል፡፡አገልግሎቱ ለኢትዮ ቴሌኮም ብዙ ገቢ የሚያስገኝ ቢሆንም የተወሰኑ ደምበኞች ለሚደውሉላቸው ደምበኞች የሚለቁት ድምፅ ግን አላስፈላጊ መሆኑን ተገልፀዋል፡፡
ለምሳሌ፡ በስራ ምክንያት ወይም ሰላም ለማለት የደወልክለት ሰው‹‹ ቻው! ቻው…››፣ ‹‹ሂድልኝ ሃዘኝ ጭንቀቴ…››ና ‹‹ጠላቴሆይ ደስ አይበልህ…›› የሚሉ ዘፈኖች ወይም መዝሙራች ብያስደምጥህ በድጋሚ እንድትደውልለት አያበረታቱም፤ አድማጩን ተስፋ የሚያስቆርጡ ብሎም የሚያበሳጩ ስለሆኑ፡፡
ፅሑፉ የተፃፈበት ምክንያት ግን ግልፅና ወቅታዊ ነው፡፡በአሁኑ ጊዜ በሃገራችን እየታዩ ያሉ የሃይማኖት አክራሪነት ዝንባሌዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ በመባባስ ላይ ስለሆኑ ፅሑፉ ወቅታዊ ያደረገዋል፡፡እንዚህ ዝንባሌዎች በየመስራቤቱና በማንኛውም የህዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋሞች መንፀባረቃቻውም ግልፅ ነው፡፡
እናም የሃይማኖት ገለልተኝነት(‹‹ሴኩላሪዝም››) ከላይ የተጠቀሱት ችግሮችን የሚያስወግድ ቁልፍ መሆኑን ታምኖበት ለውይይት ቀርበዋል፡፡




No comments:

Post a Comment