Sunday, November 24, 2013

‹‹ሴኩላሪዝም››፡የአብሮ መኖር ቁልፍ(ክፍል ሁለት)



በበለፈው ፅሑፌ የሃይማኖትች መቻቻል ሳይሆን የሃይማኖት ገለልተኝነት ወይም ሴኩላሪዝም(መከባበር፣መፋቀር፣መዋደድ) የችግሮቻችን ሁነኛ መፍተሔ እንደሆነ በምሳሌዎች አስደግፌ ለማስረዳት ሞክሬ ነበር፡፡

ለመሆኑ ሴኩላሪዝም ወይም የሃይማኖት ገለልተኛነት ምንድንነው፤ምንስ አይደለም?

ብዙ ሰዎች ሴኩላሪዝም እንደነ ናዚዝም፣ማርክሲዝም-ለንኒዝም፣ሶሻሊዝም፣ፋሺዝም ወዘተ ሁሉ በመጨረሻ ላይ በ‹‹-ዝም›› ስለጨረሰ እንደ መጥፎ ነገር ይቆጥሩታል፡፡ይሁን እንጂ ሴኩላሪዝም በምንም መልኩ ከሌሎቹ መጥፎ ‹‹-ዝም››ኦች አይመሳሰልም፡፡ሴኩላሪዝም አሲዝም(እግዚሔር የለም ብሎ ማመንም) አይደለም፡፡

ሴኩላሪዝም ሁሉምን ሃይማኖቶች(በእግዚሔር አለማመንም ጨምሮ) በእኩል ዓይን ይመለከታል፤ያከብራልም፡፡የሁን እንጂ ሃይማኖቶች የእውቀት መጨረሻ ናቸው ብሎ አያምንም፡፡ሃይማኖቶች የሚመልሷቸው የሰው ልጅ መሰረታዊ ጥያቄዎች አሉ፤የማይመልሷቸውም አሉ፡፡ስለዚህ የሃይማኖቶች ዶግማና ቀኖና(ዶክትሪን) እንደ ገዢ አስተምህሮዎች አድርጎ አይቀበለም ማለት ነው፡፡በተለይም እነዚህ የሃይማኖቶች አስተምህሮዎች በመንግስት አሰራር ላይ ጥልቃ መግባት እንደ ሌለባቸው አበክሮ ይሰራል፤ይመክራልም፡፡


ይህን አስተሳሰብ በቀላሉ ለማስረዳት አንድ የህንዳውያን ጥንታዊ ተረት ማውሳት ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡ተረቱ ስለ አንድ ዝሆንና ስድስት ማየት የተሳናቸው ሰዎችን የሚተርት ሲሆን በሰው ልጅ የስሜት ህዋሳት ተጠቅመን የምንገነዘበው ነገር ፈፁም አለመሆኑን በደም የሚያስረዳ ነው፡፡አሁን በቀጥታ ወደ ተረቱ እናምራ…
በጥንታውያን ህንዶች ባህልና እምነት መሰረት ዓለማችን በዝሆኖች ጀርባ ላይ የቆመች ናት፡፡ዝሆኖቹም በትላልቅ ኤሊዎች ጀርባ ላይ የቆሙ ናቸው፡፡እናም እነዝያ በመተሳሰብ፣በመከባበርና በፍቅር አብረው የሚኖሩ ስድስት ማይት የተሳናቸው ህንዳውያን የዝሆኖች ገናናነት እያደነቁ ያወራሉ፡፡


ይሁን እንጂ ዝሆንን በአካል አይተውት ስለማያውቁ ብያገኙት ንሮ ደስታቸው ወደር ሊገኝለት እንደማይችል አንስተው በቁጭት ሲጨዋወቱ አንድ ዝሆኖች እያራባ የሚተዳደር ሰው በአጠገባቸው ሲያልፍ ይሰማና ሊያሳያቸው ቃል በመግባት ዝሆኑ ወዳለበት ቦታ አብረው ይሄዳሉ፡፡ዝሆኑ የቆመበት ስፍራ እንደደረሱም ‹‹ይኸውና ዝሆኑ እዚሁ ቆሞላችኋል፤አንድ በአንድ እየመጣችሁ በእጃችሁ በመዳበስ ምን እንደሚመስል ማወቅ ትችላላችሁ›› አላቸው፡፡
እነዝያ ማየት የተሳናቸው ሰዎች ሰውየው ስለዋለላቸው ውለታ በጣም እያመሰገኑ በዳበሳ ዝሆኑን መፈለግ ጀመሩ፡፡


የመጀመርያው ማየት የተሳነው ሰውየ የዝሆኑን ጎድንና ሆዱ አከባቢ በእጁ ዳበሰና‹‹ተመስገን አምላኬ! ዝሆንን አወቅኩት፤ልክ ግንብ ነው የሚመስለው›› አለ፡፡
ሁለተኛው ቀጠለና የዝሆኑን ጥርሶች በመዳበስ ‹‹ዋው! ዝሆን እጀታው ልሙጥ የሆነ ጦር ይመስላል፤ይህን ለማወቅ ያበቃኝ ልዑል ፈጣሪ የተባረከ ይሁን›› አለ፡፡


ሰሶስተኛው የዝሆኑን ኩምቢ(ሸውጣጣው አፉንና አፍንጫውን) በእጆቹን በመዳበስ‹‹የፈጣሪ ያለህ! ዝሆን ትልቅ ዘንዶን የሚመስለው›› አለ፤ በጣም እየተገረመ፡፡


የአራተኛው ተራ ደረሰና የዝሆኑን እግሮች ዳበሰ፡፡እናም‹‹አሃ! ለካ ይህ ተአምረኛ አውሬ የዛፍ ግንድ የሚመስል ነበር?››አለና፣ዝሆን ምን እንደሚመስለ በማወቁ ተደሰተ፡፡


አምስተኛው ደግሞ የዝሆኑን ጀሮ ዳበሰና‹‹እንዴ! ለካ ዝሆን ማለት መሽረፈት የሚመስል አውሬ ነው?ይገርማል›› አለ፡


በመጨረሻም ስድስተኛው ሰውየ ወደ ዝሆኑ ተጠጋና ጅራቱን ከዳበሰው በኋላ ‹‹ፐ…ፐ…ፐ! ለካ ዝሆን ሆየ፣ ልክ ወፍራም ገመድ  የሚመስል ንረሯል?›› በማለት ትእዝብቱን ገለፀ፡፡


እንሆ ዝሆንን የመሰለ ድንቅ አውሬ ለመጀመርያ ጊዜ ብእጆቻቸው በመዳበስ ያወቁ ስድስቱ ማይት ተሳናቸው ሰዎች ባገኙት እውቀት እየተደሰቱ በአንድ ላይ ተሰባስበው ወደ መኖርያቸው የመልስ ጉዞውን ተያያዙት፡፡በመጓዝ ላይ እያሉም ዝሆን ምን እንደሚመስል በአግራሞት መወያየት ጀመሩ፡፡


ይሁን እንጂ ዝሆንን ለማውቅ እኩል የጓጉትን ያህል ለመጀመርያ ጊዜ ስላወቁት ዝሆን መነጋገር እንደጀመሩ ሊግባቡ አልቻሉም፡፡
አንደኛው ‹‹ዝሆን ግንብ ነው የሚመስለው›› ሲል፤ ሁለተኛው ደግሞ፣‹‹ እንዴ! ምን ነካህ ወዳጄ? ዝሆን እማ ጦር ነው የሚመስለው›› ይላል፡፡

ሶስተኛውም የጓደኞቹን አለማወቅ እያስደነቀው፤‹‹ጓዶች ምን ነካችሁ? ዝሆን እኮ ዘንዶ ነው የሚመስለው››በማለት ያምባርቃል፡፡

አራተኛው በማስከተል፣‹‹እናነተ ሰዎች አብዳችኋል ልበል? ዝሆን እኮ የዛፍ ግንድ ነው የሚመስለው!››በማለት በእርገጠኝነት ተናገረ፡፡

አምስተኛው ሰውየ ጓደኞቹ በሚናገሩት ነገር እየተገረመ፤‹‹ ወዳጆቼ ሆይ፤ዝሆኑን አላገኛችሁትም ልበል? ዝሆን እኮ ቁርጥ መሽረፈት ነው የሚመስለው›› አለ፤ሃይለቃል በተሞላበት አነጋገር፡፡

በመጨረሻም ስድስተኛው ሰውየ‹‹ጓዶች! ሁላችሁም ዝሆንን አላወቃችሁትምና እኔ ልንገራችሁ፤ዝሆን ወፍራም ገመድ ነው የሚመስለው››ብሎ ሳይጨርስ፣ ሌሎች ጓደኞቹ እጆቻቸውን በማወናጨፍ በአንድ ድምፅ ‹‹አይደለም፣ተሳስተሃል፣እንዴት?...››በማለት እርሱም እንደተሳሳተ ነገሩት፡፡


አንዱ ሌላኛው የሚናገረውን እያጣጣለ እንደወፎች ተንጫጩ፡፡ በመሃከላቸው መደማመጥ ጠፋ፤ባለመደማመጣቸውም እርባና የለሽ ክርክራቸው እየናረ፣እየናረ… ቀጠለና ወደ ጥላቻ አደገ፡፡አሁን በሃሳብ ሊግባቡ አልቻሉምና የድሮ መከባበር፣መተሳሰብና መፋቀር በጥላቻ፣ባለመተማነንና በመናናቅ ተተካ፡፡በመጨረሻም አብረው ላለመኖር ወሰኑና ተለያዩ፡፡


ውድ አንባቢ ሆይ፣ ይህንኑ አለመግባባት የተከሰተው ለምን ይመስሎታል?



አዎ፤ እንዝያ ማየት የተሳናቸው ሰዎች የዝሆኑን አንድ አካል እንጂ ሙሉውን ዝሆን ለማወቅ አልታደሉም፡፡የሁሉንም እውቀት ከዝሆኑን አንድ አካል የማያልፍ ነበር፡፡እያንዳንዳቸው ስላወቁት አንድ አካል ግን ትክክል ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ አንደኛው የሚያውቀው ሌላኛው አያውቀውም ነበር፡፡ይህ የእውቀት ልዩነትና ድሩትነት ግን በራሱ ችግር አልነበረም፤ችግሩ የመነጨው አንዱ የሚያውቀው ሌላኛው እንደማያውቅ ካለማወቃቸው ነበር፡፡

የዓለም ሃይማኖቶችም በዚህ መልኩ ነው የተፈጠሩት፡፡የሰው ልጅ ከጥንት ጀምሮ ከየት እንደ መጣ፣ማን እንደ ፈጠረው፣ለምን እንደ ፈጠረው ወዘተ ለማወቅ በሚኖርበት አከባቢና በነበረት ዘመነ አመጣጡን ለማወቅ ሲባዝን ነሯል፤እስከ አሁን ድረስም በመፈለግ ላይ ነው፡፡ይሁን እንጂ የሰው ልጅ የግንዛቤው ደረጃና አመለለካከቱ የተለያየ ከመሆኑም በተጨማሪ በቦታና በዕድሜም የተደረተ በመሆኑ እስከ አሁን ድረስ የዓለማችን ስንክሳሮች ሙሉ በምሉ ማወቅ አልቻለም፡፡


አንዱ የዓለማችን እሚንት ምስጢር ይገነዘብና ‹‹ዓለም እንዲህ ነች፤በዚህ መልኩ ተፈጥረናል መኖር ያለብንም እንዲህ መሆን አለበት..፣››እያለ ይሰብካል፡፡ፈጣሪ ነው ያሉትን ከባህላቸው፣ ከአኗኗራቸው፣ነገሮችን የመገንዘብ አቅማቸውና የህይወት መርሃቸው በመነሳት የየራሳቸው ሃይማኖት ይፈጥራሉ፡፡ያ ሃይማኖት ከተቻለ ሌሎችን በማግባባት ካልሆነም በማስፈራራትና በማስገደድ በየስፍራው ይስፋፋል፡፡አንዱ ራሱ ስለሚያውቀው እንጂ ሌላኛው ስለሚያውቀው ስማያውቅ መግባባት ካልቻሉ ወደ ጦርነት ያመራሉ፡፡በዓለም የምናውቃቸው የአውሮፓውያኖቹ ክሩሳደሮችና የዓረቦቹ ጂሃዲስቶች የዚህ ተምሳሌት ናቸው፡፡


በዚህ አለም የሚኖሩ ሰዎችም እንዲሁ ናቸው፤አንዱ የሚያውቀው ሌላኛው ላያውቀው ይችላል፡፡አንዱ ሃኪም ይሆናል፤ሌላኛው መሃንዲስ፡፡አንዱ አናፂ ሲሆን፤ሌላኛው ለአናፂው ድንጋይ ወይም ብሎኬት ያቀባብላል፡፡አንደኛው መኪና ነጂ ይሆናል፤ሌላኛው አውሮፕላን አብራሪ፡፡አንዱ የሃይማኖት መሪ ነኝ ይላል፤ሌላኛው የሃገር መሪ ይሆናል ወይም ይሾማል፡፡


ለሴኩላሪዝም አቀንቃኞችና ነፃ አስተሳሰብ አራማጆች ይህ ልዩነት የወለደው የሃይማኖቶቹ ስህተት ሳይሆን የእውቀት ጎዶሎነት ስለሆነ እንደ ክፋት አይቆጠርም፡፡ክፋት የሚሆነው አንዱ ሌላኛው ለማስገደድ ሲሞክር ብቻ ነው፡፡አንዱ የሌላኛው እምነትና ሃይማኖት እስካስከበረ ድረስ መኖራቸው በራሱ ችግር የለውም ይላሉ፡፡


የሃይማኖት ገለልተኛነት አስፈላጊነት



  1.  መንግስትና ሃይማኖት መለያየት 
  2.  የሃይማኖተኞችና ሃይማኖተኞች ያልሆኑትን መብት መጠ
  3.  የመናገርና የፃፍ(ሌሎችን ሳይጎዱ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ) ነፃነት ማረጋገጥ
  4.  የሃይማኖት ነፃነት መጠበቅ፣ ዴሞክራሲ ማስፈን፣ የህዝብ ግልጋሎት እኩል የማግኘት ወዘተ ያራምዳል፡፡

በሃገራችን የአውራምባ ማሕበረሰብ የሃይማኖት ገለልተኛነትን በማራመድ የመጀመርያው ሳይሆን አይቀርም፡፡በአውራምባ ማህበረሰብ እምነት የግል ሲሆን ሁሉም ሰው እኩል ነው፤ ከተፈጥራዊ ልዩነቶች በስተቀር በፆታ፣በዕድሜና በሃብት አይለያዩም፡፡የማህበረሰቡ መስራች የክብር ዶክተር ዙምራ ከሌሎቹ የማህበረሰብ አባላት ራሱን አያስበልጥም፡፡እናም አውራምባ የስልጣኔ አምባ ነች፡፡





ክፍል አንድን ለማንበብ እዚሁ ይጫኑ

No comments:

Post a Comment