Sunday, March 30, 2014

ቀሽም ፅሑፍ እየፃፉ ጊዜ ከማጥፋት ራስን ማጥፋት ይሻላል?




በእኔ ፅሑፎች በጣም የተሰላቸ የሚመስል አንድ አንባቢ እንደሚከተለው መክሮኛል፡፡‹‹ይህን የመሰሉ ቀሽም ፅሑፎች እየሞነጫጨርክ የራስህና የአንባቢዎችህ ወርቃማ ጊዜ ከምታጠፋ ለምን ራስህን አታጠፋም?››
አስቅኝና አስገራሚ ጥያቄ ነው፡፡አንድ አንድ ሰዎች እንዲሁ ተስፋ ለማስቆረጥና አጉል ለማሳቀቅ ሲሞክሩ ያስቃሉ፡፡ውድ አንባቢና የመረረው ተቺየ ሆይ፣ ጥያቄህን በጥያቄ ልመልስልህ ነው፡፡መቼም ይህ ፅሑፌም ቀስም እንደሚሆንብህ ይገባኛል፡፡ይሁን እንጂ ሌላ አማራጭ የለኝም፡፡

ራስን ማጥፋት ጊዜን እንደ ማጥፋት ቀላል ነው እንዴ? ራስን መግደል ጊዜን የመግደል ያህል ቀላል ቢሆን ንሮ በጠና ታመው በየሆስፒታሉ የሚማቅቁ ሰዎች፣ ወንጀል ፈፅመውም ይሁን የእንድ ጥጋበኛ ባለ ስልጣን ወይም ባለሃብት ፊት በማየታቸው ብቻ በዕድሜ ልክ እስራት ተፍርዶባቸው በየእስር ቤቱ ታሽገው የሚኖሩ ወገኖች ራሳቸው በማጥፋት አይገላገሉም ነበር ትላለህ? ራስን ማጥፋት መፍትሔ ቢሆን ንሮ በመቶ ሽዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ወደ ዓረብ ሃገሮች ይሰደቱ ነበር?

ውድ አንባቢ፣ ራስን ማጥፋት ወንጀል መሆኑን አታውቅም እንዴ? በምድር ብቻ ሳይሆን በሰማይም የሚያስጠይቅ ወንጀል ነው፡፡ደግሞስ ጊዜዋን ጠብቃ ራሷ ለምትጠፋው ህይወት ለማጥፋት ምን አስቸኮለኝ? ጊዜስ ቢሆን መጥፋቱ መቼ ይቀራል ብለህ ነው? ደሞ ለሐበሻ ጊዜ! ምድረ ሐበሻ የጊዜው ርዝመት አልገፋ ብሎት አይደለም እንዴ በየድድ መስጫው ተስጥቶ የሚውለው? ጓደኛየ፣ እኔ እኮ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው የምኖረው፤ ጊዜ እንደ ታክሲ ቆሞ ቢጠብቅህም ባይጠብቅህም ለውጥ በሌለው ሃገር፡፡


እናም የፈለገው ያህል ጊዜ ይጠፋታል እንጂ ቀሽም ፅሑፎች ከመፃፍም አልቆጠብም እራሴም አላጠፋም፡፡ምክንያቱም ገና ሕይወትን አጣጥሜ አጥሜ አልጠገብኩም፡፡ብዙ ነገሮች ስለሚያጓጉኝ መኖር እፈልጋለሁ፡፡መንኖረው በድህነትና በኋላ ቀርነትዋ ዓለም በወቃት ሃገር ነው፡፡የፈለግከውን ሁሉ በቀላሉ ማግኘት አትችልም፡፡ከምታውቀው የማታውቀው፣ከየኸው ያላየኸው፣ከሰማኸው ያልሰማኸው፣ከደረስክበት ያልደረስክበት በእጅጉ ይበልጣል፡፡በእጅህ ካለው ይልቅ በሌሎች እጅ ያለው ነገር በጣም ያጓጓል፡፡ብዙ ነገሮች የሚያጓጉህ ከሆነ ደሞ ምንም ሳታይ፣ምንም ሳታደርግ፣ምንም ሳይኖርህ፣ማንንም ሳትሆን፣የትም ሳትደርስ መሞት አትፈልግም፡፡

የነገው ጉጉት፣የነገው ምኞት፣የነገው ተስፋ፣ ያ ከቁመቴ በላይ የተሰቀለው እጅግ አጓጒ ነገር ራሴን ከማጥፋት ይልቅ ቀሽም ፅሑፎችን እየሞነጫጨርኩ መኖር ይሻለኛል፡፡ለመኖር ደሞ መተንፈስ ያስፈልገኛል፡፡አተነፋፈሴ ከተመቸህ እሰዮ፤ ካልተመቸህ ግን ምንም ማድረግ አልችልም፡፡እፎይይየ! ብዬ ከምተነፍስባቸው መንገዶች አንዱ መፃፍ(መሞነጫጨር) ነው፡፡ቀሽም ፅሑፍ የምፅፈው ግን አፍ የሚያስከፍቱና ልብን የሚያንጠለጥሉ ቀሽት ፅሑፎች መፃፍ ስለማልፈልግ አይደለም፡፡ስላልተሳካልኝ ብቻ ነው፡፡ይሁን እንጂ ከሽም ዝምታ(መታፈን) ቀሽም ፅሑፍ መፃፍ ይሻለኛል፡፡

አስኪ አንድ እውነት ልንገርህ፡፡ከፌስቡክ አድራሻህ እንደተረዳሁት ከሆነ የከተማ ኗሪ ነህ፡፡ከተሞች ከተሞች ከመሆናቸው በፊት ምን እንደ ነበሩ ታውቃለህ? ትናንሽ የገጠር መንደሮች ነበሩ፡፡መንደሮቹ ከመቋቋማቸው በፊት ደሞ ያ አከባቢ አውሬዎች እንዳሻቸው የሚፈንጩበት ጫካ ነበረ፡፡የዛሬዋ አዲስ አበባ ስሟን ያገኘችው በኢተገ ጣይቱ ነበረ፤ከዛ በፊት ምን ትመስል እደነበር መረጃ ባይኖረንም የጭቃ ቤቶችና የኮረኮንች መንገዶች ባለቤት እንደ ነበረች ግን የሚያጠራጥር አይደለም፡፡እንዝያ መንገዶች ለመኪኖች ቀርቶ ለዳልጋ ከብቶችና ለሰው ልጆች የማይመቹ ነበሩ፡፡

ቀስ በቀስ ግን ወደ አስፓልትነት እየተቀየሩ ነው፡፡ዛሬም ድረስ ደረጃቸው የጠበቁ አስፓልቶች በመሰራት ላይ ናቸው፡፡የመኪኖቹ ፍሰትም በአየር ላይ የመንሳፍፍ ያህል ነው፡፡ምቾቱም ፍሰቱም ስጥ ባለ ሜዳ ላይ የሚፈስ ውሃ ነው የሚመስለው፡፡እነዚህ አስፓልቶች ከመሰራታቸው በፊት ግን መኪኖች ሳይንገራገጩ መጓዝ አይችሉም ነበር፡፡

የውሃ ቦዮችና ትላልቅ ወንዞችም ወራጅ ውሃ አቅጣጫውን ጠብቆ የሚፈስባቸው ሸለቆዎች ከመሆናቸው በፊት ለውሃው ፍሰት የማይመቹ ኮረኮንች ነበሩ፡፡በመሆኑም ደራሽ ውሃ በመጣ ቁጥር አቅጣጫውን በመሳት አከባቢውን አጥለቅልቆ፣ ብዙ ነገሮችን አጨማልቆ ያልፍ ነበር፡፡ከጊዜ በኋላ ግን ቦዮች ሆኑና የውሃው ፍሰት የተቃና ሆነ፡፡

የእኔው ፅሑፍም ዛሬ የፍሰት አቅጣጫው የማይታወቅ ቀሽም ቢሆንም ከብዙ ልምምድ በኋላ ሊቃና ይችላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ልክ የተለያዩ ዓይነት መኪኖች ያለ ምንም መንገራገጭ እንደሚንፈላሰሱበት አስፓልት፣ ደራሽ ውሃ አቅጣጫው ሳይስት እንደሚፋስባቸው ወንዞች የእኔ ፅሑፍም የአንባቢ ምቾት የማያሳጣ፣የማይጎረብጥ፣ የፍሰት አቅጣጫውና ጭብጡ ጥርት ያለ ሊሆን ስለሚችል ተስፋ አልቆርጥም፡፡

ውድ አንባቢ ሐሳቤን ሳልገልፅ መኖር የመታፈን ያህል ያስጨንቀኛል፡፡ፅሑፌ ቀሽም ቢሆንም ለእኔ የመተንፈስ ያህል ያስፈልገኛል፤ሰብአዊና ዲሞክራስያዊ መብቴም ነው፡፡ሳልተነፍስ መኖር አልችልም፡፡ራሴን ማጥፋትም አለሻም፡፡በመሆኑም የሌሎች መብቶች እስካልተጋፋሁ ድረስ የሐሳቤን በነፃነት የመግለፅ መብቴን ልትደፈጥጥብኝ ባትሞክር ይሻላል፡፡


No comments:

Post a Comment