Tuesday, September 24, 2013

‹‹Tower in the sky››ን እያነበብኩት ነው





በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ የታተመው ‹‹Tower in the sky›› በገበያ ላይ ተፈልጎ አይገኝም፡፡የትም አፈላልጌ ስላጣሁት ተስፋ ቆርጬ ልተወው ስወስን አንድ ምርጥ ጓደኛየና የስራ በለደረባየ መፅሐፉን ይዞ ደረሰልኝ፡፡ ዮናስ “My Best Friend is a person who will give me a book I have not read.” የሚለው የአብርሃም ሊንከን አባባል ታውቀው ነበር? ብታውቀውም ባታውቀውም በተግባር አውለኋልና ምስጋናየ ይድረስህ፡፡

በ1960ዎቹ  ከነበሩ አብዮተኞች አንድዋ የሆነችው ሂወት ተፈራ ‹‹Tower in the sky››ን ፅፋ ለህትመት ስታበቃልን ራሷን እንደ ፈጣሪ ምፁም አድርጋ ሌሎችን ለመኮነን፣አንዱን አጥቅታ ሌላኛውን ለመጥቀም፣የተወሰኑትን ለማሞገስ ወይም ለመኮነን አስባ አለመሆኑን መፅሐፉ ቋሚ ምስክር ነው፡፡ዓላማዋ ብዙ ስህተቶችና በጎ ነገሮች መፈፀማቸውን በማሳየት እንዳይደገሙ ለማስተማር ብቻ ይመስለኛል፡፡ብዙ የሃገራችን ፖለቲከኞች አንድና ከዛ በላይ መፃሕፍት ፅፈዋል፡፡የሂወት ተፈራ መፅሐፍ የሚተካከል መፅሐፍ ማንበቤ ግን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡
በሃገራችን ብዙ ነገሮች ተከናውኗል፤ እየተከናወኑም ነው፡፡ብዙ ነገሮች ተሰርቷል፤ እየተሰሩም ነው፡፡ብዙዎቹ እንኮራባቸዋለን፤በቀርስነት ታቅበው ለቀጣዩ ትውልድ የማስተላለፍ ግዴታ አለብን፡፡ብዙ የምናፍርባቸው ስሕተቶችም ተሰርተዋል፤ዛሬም ሲደገሙ እያየን ነው፤ አንድ ዓይነት ስሕተት ሲደጋገም ያሳፍራል ፤ያሸማቅቃል፡፡ይሁን እንጂ እነዚህም እንደወረደ ተዘግበው ለቀጣዩ ትውልድ መስተላለፍ አለባቸው፤ እንዳይ ደገሙ ለማስተማር፡፡
የሰው ልጅ ክፉና ደጉን የሚማረው ከህይወት ተመኩሮ ነው፡፡በማንኛውም ስራ ሲሰማራ መሳሳቱ አይቀርም፤ምክንያቱም ወደዚህ ዓለም ሲመጣ እንዴት መኖርና ስራውን መስራት እንዳለበት በግልፅ የሚያሳይ የመመርያ መፅሓፍ(manual/guide) አይሰጠውምና፡፡ሁሉም ሰው ከራሱና ከሌሎች  የህይወት ተመኩሮ የተሻለውን(የተሻለ ነው ብሎ ያሰበውን) እየወሰደ ነው ንሮውን የሚመራው፡፡ስለሆነም መሳሳቱ የሚያስኮንን ሃጥያት ሳይሆን ማስተማርያ ነው፡፡አንድ ዓይነት ስህተት ሲደጋገም ግን ያሳፍራልና ሊኮነን ይገባል፡፡
እስኪ በገፅ 158 ላይ ያሰፈረችውን ላስነብባችሁ፤‹‹…I often visualized in my mind the “shining city on the hill,” where justice prevailed. That was the “tower in the sky” we had set out to bring down to earth. I would have set the foundation for this “tower” with my blood,flesh and bones if need be. It did not matter if I did not live to see it…  
በተራራው ላይ ያለች ፍትህ የነገሰባት ደማቅ ከተማ በአእምሮየ ስቀርፅ ኑሬለሁ፡፡ያኛው ‹‹በሰማይ ያለው ማማ›› ወደ መሬት ለማውረድ ነበር የተነሳነው፡፡ ብያስፈልግ የማማው መሰረት በደሜ፣በስጋየና በአጥንቶቼ እገነባው ነበር፡፡ ያንኑ ለማይት በህይወት ባልኖርም ችግር አልነበረውም፡፡ ››
የ60ዎቹ የሃገራችን ፖለቲከኞች ዓላማና የለውጥ ናፍቆት በጣም የሚያስደምም ነበር፡፡የኢትዮጵያ ችግሮች እንዳለ በእርነሱ ትክሻ ላይ የወደቁ ያህል ሸክም የከበዳቸው ሸክሙ ለማቃለልም ህይወት እስከ መክፈል ድረስ ቆርጠው የተነሱ ጀግኖች ነበሩ፡፡ምን ዋጋ አለው! አካሄዳቸው ከድጡ ወደማጡ የሚመራ ነበር፡፡የህዝቡ ንሮ አሻሻልን ብለው የባሰውን አበላሹት፡፡አብዛኞቹ የ60ዎቹ ፖለቲከኞች ዛሬም ድረስ ስህተታቸውን መቀበል እንደሞት ያስፈራቸዋል፡፡በዓይናቸው የተሰነቀረው ግንድ ትተው በሌሎች ላይ ያለው ጉድፍ ሲጠቁሙ ነው የሚታየው፡፡የሂወት ግን ከሁሉም ትለያለች፤ ዛ ይሆን በፖለቲካው ዓለም የማትታየው?
አብዛኞቹ የሃገራችን ፖለቲከኞች ከአንዱ መንግስተ ጋር አብረው ሲፈተፍቱ ኖሮው ሌላ መንግስት ሲመጣ ከእርሱም ጋር ሌላ ነገር ለመፈትፈት ያምራቸዋል፡፡እንደ አውሮፓውያኑ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ከአንዱ የፖለቲካ ክለብ ወደ ሌላኛው ሲሽከረከሩ ይታያል(ከነበሩበት ፓርቲ ሲባረሩ ወደ ሌላኛው በነፃ ዘዋወራሉ)፡፡

ድሮ ከአንዱ ፓርቲ ጋር ሆነው ብዙ ነገር ሲበሉ ሲጠጡ፤ሲገድሉ፣ሲጨቁኑ፣በህዝቡ ላይ ሲረማመዱ እንዳል ነበር እንደ ጲላጦስ ‹‹እጄ ንፁህ ነው›› ብለው አፋቸው ሞልተው ሌላኛውን ሲኮንኑ መታዘብ የተለመደ ነው፡፡እነዚህ ፖለቲከኞች እጅና እግራቸውን አጣምረው የኖሩ ካልኖሩ በስተቀር ስህተት መስራታቸው አይቀሬ ነው፡፡ነገር ግን የራሳቸው ስህተት አያምኑም የሌሎች ስህተት ብቻ ያብጠለጥላሉ፡፡
ግን ለምንድነው ስህተታቸውን የማያምኑት?የትናንት ማንነታቸው ከዛሬው ጋር እኩል ስለሆነ ነው፡፡ለውጥ ቢኖር እንኳን ሽበታቸው ብቻ ነው፤ትናንት አፍሮ የነበረው ፀጉራቸው ድራሹ ይጠፋል፤የወጣትነት ወዘናቸው ጠፍቶ አመድ ላይ ሲንከባለል የዋለ አህያ ይመስላሉ፤ ፊታቸው ይጨማደዳል፡፡ከነዚህ ውጪ ምንም ዓይነት ለውጥ ስለማያመጡ ነው፡፡ያለውፍን ስህተታቸው ስህተት መሆኑን ለማመን ከትናንቱ ስብእናቸው የተሻሉ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡
አመለካከታቸው፣እይታቸውና ነገሮችን የመገንዘብ ብቃታቸው ልክ እንደ ትናንቱ ከሆነ ግን የትናንቱ ስህተት ይደጋግሙት እንደሆነ እንጂ ስህተት መኖሩን አይገነዘቡም፡፡ስለሆነም ከ40 ዓመታት በፊት የሰሩት ስህተት ዛሬም ይደጋግሙታል፡፡ለዛም ሁል ጊዜ እነሱ ትክክል ሌሎች ግን የተሳሳቱ መስለው የሚታዩዋቸው፡፡
 


ይቀጥላል…

No comments:

Post a Comment