ሁሌም ነው በተለያዩ የምድያ ቶቋማት ሲደጋገም የምሰማው።የኢትዮጵያ ህዝብ ሰው አክባሪ፣እንግዳ ተቀባይ ነው ይባላል።የገጠር
ልጅ ነኝና አዲስ አበባ ከመምጣቴ በፊት አባባሉ ለአፍታም ቢሆን አልጠራጠረውም ነበር።ይባላል ብቻ ሳይሆን በእርግጠኝነት «ነው»
ማለት እችላለሁ።«ደጉ ባላገሩ» ይባል የለም?ዘፈን ብቻ እንዳይመስልህ እውነት ነው።ካላመንከኝ ምናልባ የአዲስ አበባ ልጅ ነህ እና
ወደ ክፍለ ሃገር ጎራ ብለህ ማረጋገጥ ትችላለህ። የባላገር ንሮ የጋራ ነው፤በጋራ ይሰራል፣በጋራ የበላል፣በጋራ ይኖራል።በቃ!በሐዝንም
ሆነ በደስታ ንሮው በጋራ ነው።
በክፍለ ሃገር የሰው ልጅ ያው ሰው ነው…ለማዳና አውሬ ወይም የቤትና የበረሐ፣ ፋራና አራዳ ተብሎ አይከፋፈልም፤ እንግዳም
ቢሆን።የንሮ ልዩነቱም ብትል ተመሳሳይ ሁኖ ነው የሚጠብቅህ።ብያንስ ብያንስ በክፍለ ሃገር ጎደና አደሮች አታገኝም፤ሁሉም ሰው ቤት
ውስጥ ይኖራል፤አለቀ።የቤቶች ልዩነት ቢኖር ቢበዛ ጣርያቸው በሳር ወይም በቆርቆሮ የተከደነ መሆኑን ብቻ ነው። ሃብታሙ ብዙ የቤት
እንስሳትና ላቅ ቢልም ወፍጮቤት ወይም አይሱዝ መኪና ሊኖረው ይችላል።ነገር ግን የቤቱ አጥር «Denger! አደገኛ» የሚል ፅሑፍ የተንጠርለጠለበት የኤሌትሪክ ሽቦ የታጠረና በብረት መዝግያ የተቸነከረ አይደለም።ለጎረቤት፣ለወገን ዘመድ
እንዲሁም ለእንግዳ ሁሌም ክፍት ነው።
አዲስ አበባ መኖር ከጀመርኩ ወዲህ ግን የሰዎች ልዩነት
የሰማይና የመሬት ያህል የተራራቀ መሆኑን ተገንዚቤለሁ፤ጥርሱን ያገጠጠ፣ዓይኑን ያፈጠጠ ሰፊ ልዩነት።የሰው ልጅ በእምነት(ሃይማኖት)፣በፖለቲካ፣በዘር፣በሃብት፣በብሔር፣በሰፈር፣በፆታ
ወዘተ የተቆራረጠ ይመስላል።ሰው አክባሪነትና እንግዳ ተቀባይነት የሚሉቃላት
በወሬ እንጂ በተግባር አላጋጠሙኝም።ስለሆነም «ይባላል» እንጂ «ነው» ለማለት አልደፍርም።ምክንያቱም ሲባል ከመስማት በስተቀር ሲደረግ
አላየሁም።
አዲስ አበቤዎች ለውጭ ሃገር ዜጎች እንጂ ለሐበሾች ሲበዛ ክፉ ናቸው።ፈረንጆች ወይም ከንፈራቸው ወፈር፣ፊታቸው ጠቆር
ያሉ አፍሪካውያን ካዩ ሳይላኩ ወድየት፣ ሳይጠሩም አቤት ይላሉ።ተጨማሪ ክፍያ ልያገኙም ላያገኙም ይችላሉ።ግን አለ አይደል፣ እንዲሁ
አመል ሆኖባቸው ነው መሰለኝ ማሽቃበጥ ያበዛሉ፤ሲበዛ ይሽቆጠቆጣሉ።ሐበሻ ከሆነስ? አይጣል ነው። ለማንኛውም አገልግሎት እንግልት
ይደርስበታል፤ይጉላላል፣ይዋከባል።ድርጅቱ የመንግስትም ሆነ የግለሰብ ለውጥ የለውም።
ይህ ነገር ወሬ ብቻ እንዳይ መስልህ እመነኝ! እውነት ነው።ካላመንከ ፈረንጆችና ሐበሾች ወደ ሚስተናገዱባቸው ሆቴሎች፣ኤርፖርቶች(የኤርፖርቶች
ደምበኛ አይደለሁም ግን ለሐበሾች አስቸጋሪ መሆኑን ይታወቃል) ፣የዜግነትና የስደተኞች ጉዳይ ምኒስተር መስራ ቤት ጎራ በል።ጉድ
ታያለህ። ፓስፖርት ለማውጣት ብያንስ ለሶስት ወራት ትንከራተታለህ።ፈረንጅ ከሆንክ ግን አንድ ቀንም አይፈጅብህም።ሆቴሎች ሐበሻ ለመስተናገድ
ብያንስ ግማሽ ሰዓት ይፈጅባቸዋል።ለፈረንጅስ?ቢበዛ በአንድ ደቂቃ!እናም በቀላሉ አንድ ሐበሻ የሚስተናገደው ከርሱ በኋላ የመጡ
27 ፈረንጆች ከተስተናገዱ በኋለ ነው።በመንግስት ድርጅቶች፣በተለይ በቴሌ ፈረንጆች አይፈተሹም፤ምስኪን ሐበሻ ግን በደምብ ይታሻል…
ከላይ እስከታች።
በአከራይና ተከራይ መካከል ያለው ግንኙነት እግዚኦ! የሚያስብል ነው፤በተለይ ለሴቶችና ለባለ ትዳሮች(ለወለዱ በጣም ይከፋል)።ሽንት
ቤት ቢቆሽሽ፣ ውሃ ቢፈስ፣መብራት ከሶስት ሰዓት በኋላ ከበራ ወዘተ መዓት ይወርድብሃል…ድርጅቱ የተፈፀመው ባንተ ላይሆን ይችላል፤
የሆነ ሁኖ ግን ተጠያቂ ነህ።
እዚች ጋ አንዲት ቀልድ ትዝ አለችኝ።ድሮ ነው አሉ(«አሉ ነው እንግዲህ» አለ የፌስ ቡክ ፀሐፊ) የሆነ ሰው በእንግድነት
ወደ አንዱ ቤት ይሄዳል።ወሩ ጥቅምት ነበር።ወርሐ ጥቅምት ደሞ የእሸት ወር መሆኑን ይታወቃል።እንደ አጋጣሚ ሁኖ የቤተሰቡ እራት
የተለያዩ ዓይነት ሰብሎች እሸት ነበር፤ የበቆሎ፣የአተር፣የአኩሪ አተር እሸት እንደጉድ የጠበሳል፣የቀቀላል…ይበላል ። እራት ከተበላ
በኋለ የእያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ሆድ እንደ ባሉን ተነፋ።ትንሽ ቆይቶ ቤቱ በፈስ ድምፅ የጦር አውድማ መስሎ ቁጭ አለ።መጀመርያ
አከባቢ የቤቱ አባወራና እማወራ ለድምፅ ብክለቱ በሳቅ ያለፉት ነበር።እየቆየ ሲመጣ ግን እየሆነ ያለው ነገር አሜን በለው ለመቀበል
የሚያስቸግር ሆነባቸው።
አባወራ አከታትለው ለቀቁት፤ቀደድ፣ቀደደድ፣ቡም።ተንሰተው ሂደው ትንሹኝ ልጃቸው «ይድፋህ»በማለት በጥፊ አጮሉት።
እማወራ ቀጠሉ፤ቀደድ፣ቦጭ፤ቦጨጭ፤ቦጨጨጭ።እናትም ተነሱና «ምናባቱ ይህ ባለጌ ሰዳቢ እንደ አህያ ይለቀዋልሳ» ብለው ለልጁ
በጥፊ ደረገሙበት።ልጁ አንዴ ፈርዶበታልና ምንም አላለም፤ጭጭ፣ዝም።
በመጨረሻ እንግዳው፤ስጢጥ፣ስ…ጢ…ጥ፣ኡቭ፣ቋ…ቅ(በጣም የታፈነ የፈስ ድምፅ አሰሙ)።ማን ይቀራል ታድያ? እንግዳም ተነሳ።
አባወራ ጠየቁ፤ወዴት ነው ጌታየ?
እንግዳ መለሰ፤ ወደፈረደበት ልጅ።
የአዲስ አበባ ተከራይም እንዲህ ነው፤የማንም ፈሳም ማሳበብያ።
ወንደ ላጤ ሁነ በዕድሜ ገፋ ያሉ ሴቶች ያሉበት ግቢ ውስጥ ከተከራየህ ግን ያን ያህል አትቸገርም።እንደውም ቡና ጠጣ
ምናምን ትባላለህ።በሰበብ አስባቡ ከሴቶቹ ጋር እንደትተዋወቅ ጥረት ይደረጋል፤ያው በአረዶች አባባል «ጠበሳ» መሆኑን ነው።
ባንዱ ቤት ያጋጠመኝ ግን የተለየ ነበር።የአክስቴ ልጅ በሳሪስ አቦ አከባቢ ተከራይቶ ይኖራል።እናም ባለቤቱ ስለወደች
ለመጠየቅ ሄድኩኝ።ቤቷ በጣም ጠባብ ነች፤ቆርቆሮ በቆርቆሮ።ለይመሰል በውስጥ በኩል በፕላሰቲክና በመዳበርያ ተሸፋፍኛለች።ቢሆንም ግን
እጅግ በጣም ትሞቃለች፤እንግዶቹም ሆነ የቤቷ ተከራዮች ላብ በላብ ሁኗል።ይባስ ብሎ ግን ዓይን የሚያስለቅስ፣አፍንጫ እየሰረሰረ አሁንም
አሁንም የሚያስነጥስ ነገር በቤቷ በር በኩል መግባት ጀመረ።እሁድ ቢሆንም አከራይዋ ሴትዮ በቤቷ አጠገብ(ወደ በር ተጠግታ) በርበሬ እየወቀጠች ነው። አንዱ «እጥሾ!» ይላል፤እንባው መንታ መንታ ቦይ
ሰርቶ ፊቱን እያጠበ ይወርዳል።ሌላውም እንዲሁ ይከተላል።ሰባት ሰዎች!ንጥሻ በንጥሻ፣እንባ በእንባ ሁኗል።አይኖች ቀልቷል፤ያለ ማቋረጥ
እንባ ያፈሳሉ።አፍንጮች አብጧል፤ደጋግመው ይናፈጣሉ።
ሴትዮዋ ግን ስራውን አለቆመችም።አይን የለም፣ጆሮ የለም …ርህራሄ አይታሰብም።አንድ በአንድ እየተናፈጥን፣አያነባን ቤቷን
እየለቀቅን ወደየመጣንበት።ይገርማል! የአዲስ አበባ መስተንግዶ በርበሬ ማጠንም ይጨምራል።በዚህ ምክንያት የኢትዮጵያ እንግዳ ተቀባይነት
አዲስ አበባን ሳይጨምር መሆን አለበት።ምክንያቱም አዲስ አበቤዎች በእንግድነት ቀርቶ በተከራይነትም መኖር ይህን ያህል አስቸጋሪ
ነው።በተከራየህበት ቤት እንግዶች መቀበል በርበሬ እስከማጠን ደረስ እያስቀጣ ነው።"ወይ ዘንድሮ" አለ ዘፋኙ?
No comments:
Post a Comment