Tuesday, January 1, 2013

መውደድ ከራስ ይጀምራል



ብዙ ሰዎች ‹‹ራስ ወዳድ አትሁን›› ሲሉ ይሰማል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ‹‹ ከራስ በላይ ንፋስ››ብለው ይመስላሉ፡፡ የትኛው ነው ትክክለኛ አባባል? እስኪ አንድ ምሳሌ ልጨምርና ወደ መነሻ ሃሰቤ ልግባ፡፡‹‹ራስ ሳይጠና ጉተና›› ይላል አማራ  ሲተርት፡፡እውነት ግን ራስ ከሌለ ጉተና ይታሰባል?ለራሳችን ሳንኖርስ ለሌሎች መሆንና መኖር እንችላለን? እንደኔ እንደኔ ማናችንም ቢሆን የወደቀውን ለማንሳት አንድ ነገር ግዴታ ያስፈልገናል፤ ራሳችንን ችለን መቆም፡፡

ሌሎችን ለመርዳት ዓላማ ካለን መጀመርያ ራሳችን መርዳት አለብን፡፡ ሌሎችን ማክበር ከፈለግን ራሳችንን አክብረን መገኘት ይኖርብናል፡፡ሌሎችን ለመውደድም ራሳችን መውደድ አለብን፡፡ካልሆነ ግን አንዱ ክብረ ቢስ‹‹ሰለወደድኳት ገድልኳት››እንዳለው ነው የሚሆነው፡፡

እንደዚህ ዓይነት ሰው ማንንም አይወድም፤ እራሱም ጭምር፡፡አስመሳይ፣ውሸታምና ከዳተኛ ነው፡፡ ለሚወዱት ሰው መግደል ይቅርና በመጠኑ ማስቀየምም በጣም ይከብዳል፡፡ምናልባት የሚወዱትን ሰው ከሞት ለመታደግ ራስን አሳልፎ መስጥት የመውደድ ምልክት ሊሆን ይችላል፡፡በትክክል መባል ያለበትም‹‹ሰለወደድኳት ራሴን አሳልፌ ሰጠኋት››ነው፡፡

ነገር ግን ለሌሎች ሲባል ራስን አሳልፎ መስጠት በራሱ በሌላው ፅንፍ ላይ ያለ ራስ ወዳድነት ነው፡፡ለምን ቢባል የሚወዱትን ሰው ማጣት ሁሉንም ነገር እንደ ማጣት የሚሆንበት ጊዜ አለና ነው፡፡በጣም ከሚወዱት ሰው ተለይቶ ከመኖር ሺ ጊዜ መሞት የሚሻልበት ጊዜ አለ፡፡ልክ እንደ ራስ የሚወዱትን ማጣት ሰላም ይነሳል፤እንቅልፍ ያሳጣል፡፡ቀንና ሌሊት በእውንና በሕልም እየተከሰተ ያስቸግራል፡፡ከዚ በላይ የቁም ስቃይ የለምና ይለይለት ብሎ መወስን ይቀላል፡፡

ይህ ዓይነት መውደድ ግን ምክንያታዊ ሳይሆን ግብታዊነት ነው፡፡አያድርገውና በፍቅር የሚንሰፈሰፉለት ሰው ባሕር ውስጥ እየሰጠመ ነው እንበል፡፡እርሶ መዋኘት አይችሉም፤በአጠገብዎም የሂይወት አድን ዋናተኛ የለም፡፡የወዳጅዎ ሂይወት ከሞት ማትረፍ  አያችሉም፡፡ ምን ብያደርጉ ይሻላል?ዘሎ መግባትና ከሚወዱት ጋራ ባሕር ውስጥ ሰጥሞ መሞት?ይህ ዓይነት ውሳኔ ግን አደጋውን እጥፍ ያደርጓል እንጂ አይቀንሰውም፡፡ለርሶም ለወዳጅዎም አንዳች የሚፈይደው ነገር የለም፡፡ ስለዚህ ትክክለኛው መፍተሔ ለክፉም ለደጉም ዋናተኛ ሆኖ መገኘት ነው፡፡

ራሱን በሚገባ የሚወድ ሰው ሌሎችን ያለቅድመ ሁኔታ የመውደድ ብቃት አለው፡፡ እስከ ቻለው ድረስ ለማንኛውም ነገር ቅድመ ዝግጅት ያደርጋል፤ ሳይደርስበት ደርሶ ለማክሸፍ ሁሌም እንደ ወታደር ለራሱም ለወገኖቹም በተጠንቀቅ ዘብ ይቆማል፡፡ራስን መውደድ ሰዶ ማሳደድ አይደልም፡፡ራስን መውደድ ሌሎችን ገድሎ መኖር አይደለም፡፡ ራስን መውደድ የሚወዱት ሲኖር መኖር፤ካልኖረ ደግሞ ራስን ማጥፋት ሳይሆን ሌሎች እንዲኖሩ መኖር ነው፡፡ የሌሎችን ሂይወት ወይም ንሮ ለማሻሻል የተሻለ ሁኖ መገኘት ነው፡፡ትርፍ ገንዘብ ሊኖር ይችላል፤ትርፍ ሂይወትና ትርፍ ጊዜ ግን አይታሰብም፡፡

ስለዚህ ራስን መውደድ ማለት የተሻለ ሰው ለመሆን ያለውን የሂይወትና የጊዜ እንጥፍጣፊ አሟጦ መጠቀም ነው፡፡ልክ እንደ ሻማ እየበሩ መቅለጥ፡፡ሻማ በእሳት ነዶ ካልቀለጠ ብርሃን እንደማይሰጠው ሁሉ የሰው ልጅም በሮ እሳት ካልነደደ ብርሃንም ሆነ ሙቀት ሊሰጥ አይችልም፡፡ ነገር ግን ብርሃን ቢሰጥም ባይሰጥም እንደ ሻማ መቅለጡ አይቀርለትም፡፡ሰለሆነም ጉድጓድ ውስጥ ተደብቆ ከመቅለጥ ይልቅ ተራራ ላይ ወጥቶ እየቀለጡ ዓለምን ማብራት ይመረጣል፡፡

ይህ ለራስ ሲባል የሚከፈል መስዋእትነት ነው፡፡ ስለራሱ ደንታ የሌለው ሰው ግን ዓይንን የሚያቃጥል ጭስ እንጂ ብርሃን አይሰጥም፡፡እንደ ተዳፈነ ክሰል ውስጥ ውስጡን ነዶ በከንቱ ያልቃል፡፡

ማሕተመ ጋንዲ ራሱን ባይወድ ሮ ራሱን በፍቅር አሸንፎ በፍቅረ ንዋይ ራሳቸውን የረሱ አውረፓውያን በቅር በማሸነፍ ለሕንዳውያን፣ለደቡብ አፍሪካውያና ለጥቁር አመሪካውያን ነፃነትና እኩልነት ራሱን አሳልፎ አይሰጥም ነበር፤ኔልሰን ማንዴላና ማርቲን ሉተር ኪንግም የሱን አርአያ በልተከተሉ ነበር፡፡ራሱን ባይወድ ሮ አጉል ጦር በመማዘዝ ራሱን ጨምሮ የሚልዬኖችን ደም መፍሰስና ሂይወት መጥፋት ምክንያት በሆነ ነበር፤ ልክ እንደ ሂትለር፡፡

ሂትለር በሂይወት ዘመኑ ማንንም መውደድ ቀርቶ አያምንም ነበር ይባላል፤ራሱንም ጭምር፡፡ራሱን የሚወድ ሰው ራሱንም ሆነ ሌሎችም በአሰቃቂ ሁኔታ አይገድልም፡፡በሂይወት ዘመኑ ሙሉ ሌሎችን ሲያወግዝ እንደሮው ሁሉ ስሙ ከመቃብር በላይ እየተወገዘ ይገኛል፡፡

እንዚያ ለሌሎች ሲሉ በቁማቸው እንደ ሻማ የቀለጡት ማሕተመ ጋንዲና ዶክተር ማርቲን ሉተር ኪነግ ግን እስካሁን ድረስ በመልካም ተምሳሌትነት እየተወሱ ይገኛሉ፡፡‹‹ሂይወት እንደ ገደል ማሚቶ ናት›› የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ጥላቻ ዘርቶ ፈቅር ማጨድ አይቻልም፡፡ፈቅር ለመስጠት ፍቅር መሆን ግድ ይላል፡፡

  



No comments:

Post a Comment