የሰው ህይወትና ንብረት መጠበቅ፣
ሰላምና ፀጥታ ማስፈን፣ ህግና ስርዓት ማስከበር ጥቂቶቹ የፖሊስ ግዳጆች ናቸው፡፡ሰላምና ፀጥታ፣ህግና ስርዓት ለማስከበር ሲባልም
ከሰላም ወዳዱ ህዝብ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ ይሰራል፡፡ህግ ተላልፏል ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎችን ተከታትሎና በተጨባጭ ማስረጃዎችን
አስደግፎ በህግ ፊት ያቀርባል፡፡ ፎሬንሲክ ሳይንስና ፎሬንሲክ ሳይኮሎጂ ተጠቅሞ ወንጀሎችን ይመረምራል፣ ከበጎች መኃል የሸሸጉ ተኩላዎችን በመለየት
በህግ ያስዳኛል፡፡
በመሆኑም ፖሊስ ከሰላማዊው ህዝብ ጋር እጅና ጓንት ሲሆን ከወንጀለኞች ጋር ግን አይጥና ድመት ነው፡፡ፖሊስ ባለበት
ህግ ይከበራል፣ሰላምና ፀጥታ ይሰፍናል፣ በሰላም ወጥቶ የፈለጉትን አከናውኖ በሰላም መግባት ይቻላል፡፡አልፎ አልፎ ችግሮች ቢያጋጥሙም
ፖሊሶችን ያለምንም ስጋት በማማከርና እንደ መከታ በመጠቀም ከተለያዩ ዓይነት ስጋቶች ነፃ መሆን አይከብድም፡፡ በተለይ በበለፀጉ
አገሮች ፖሊስ ከአባትና እናት በላይ ይታመናል፣ ይከበራል፡፡
የስለዋ ከተማ በሆነችው ደላ እየሆነ ያለው ግን የዚሁ ተገላቢጦሽ ነው፡፡ ፖሊስና ሰላማዊው ህዝብ አይጥና ድመት ሲሆኑ ወንጀለኞችና ፖሊሶች ደሞ
ያውና አንድ ሆኗል፡፡ህዝቡን ያሰለቹና ደም ያነቡ ወረበሎች የፖሊሶች ሸሪክ ናቸው፡፡ወይም ደሞ ወሮ በሎቹ ፖሊሶች ናቸው፡፡ፖሊስ
ባለበት ሁሉ ግር ግር፣ትርምስ፣ ዱላና ጩቤ መማዘዝ፣ አንገት ለአንገት መተናነቅ ነገሷል፡፡በደላ የሚገኘው ፖሊስ ጣብያ በደርግ ዘመን
በማእከላዊ እስር ቤት ተፈፅሟል የሚባሉት የንፁሃን ማሰቃያ ዘድየዎች ተግባራዊ ይሆናሉ፡፡
ፖሊሶች ቁመናውን ያልወደዱት ሰው ሁሉ ከህዝብ መሃል በዱላ እየዠለጡ ወደ ፖሊስ ጣብያ ይወስዳሉ፣ዥለጣው ከደለቡ ቁንጫና
ቱሓኖች ጋር ውስጥም ይቀጥላል፡፡ማንኛውም ተጠርጣሪ እመን እየተባለ የፊጢኝ ታስሮ ይደበደባል፣ እስከ ስድስት ወር ድረስ ያለፍርድ
ይታሰራል፡፡
ይህ የስለዋ ህዝብና የመንግስት ቅልብ ፖሊሶች የአይጥና የድመት ጨዋታ ከመጥን በላይ መረን አየለቀቀ ሄዶ ሰኔ 6
ቀን 2006 ዓ.ም ሸማችና ሻጭ ለመገበያየት በዋጋ እየተደራደሩ ሳለ አንድ ሁሌም ድብን ብሎ ሰክሮ ከፊት ለፊቱ ያገኘውን ሁሉ በያዘው
ዱላ እየቀጠቀጠ ገበያተኛውን የሚያተራምስ ወመኔ ፖሊስ ስራውን ጀመረ፡፡ፖሊሱ በጣም ረዥምና ወፍራም ነው፡፡ሁሌም ይጠጣል ድብን ብሎ
ይሰክራል፡፡ ከዛም ዱላውን እያወጣወጠ ይገኘውን ሁሉ መነረት ነው፡፡ ህዝቡ ለበላይ አካላት አብየት ቢልም መፍትሔ አላገኘም - ፖሊሱ
ህዝብ ለማሸበር ሆን ተብሎ የተላከ በመሆኑ ከተግባሩ እንዲታቀብ አልተደረገም፡፡
እናም ባለፈው ሰኔ ስድስት እንደተለመደው ሰክሮ ወደ ገበያተኛው በመሄድ ፆታና ዕድሜ ሳይለይ ያገኘውን ሁሉ መደብደብ
ጀመረ፡፡በዚህ መሃል ፖሊሱ የአንድ ህፃን እጅ ይዞ መቀጥቀጥ ጀመረ፡፡ ልጁ ይንፈረፈራል ፖሊሱ ግን ሊለቀው አልቻለም፡፡ ይህን ክፉ
ትእይንት ሲመለከት ነበረው አባት ‹‹ ምን ብያድረግህ ነው እንዲሁ የምትደበድበው? ህግ ከተላለፈ ለምን ወደ ፖሊስ ጣብያ አትወስደውም?››
ብሎ ይጠይቋል፡፡ ያ ከዱላው የማይሻል ፖሊስ ‹‹ እንታይ ዴኻ ኣእቲውካ ወዲ ሰበይቲ!›› በማለት ለኣባትየውም ሊመታው ቃጣው፡፡
በአከባቢያችን ወንድ ልጅን ‹‹ ወዲ ሰበይቲ›› ብሎ መስደብ እስከ መጋደል ያደርሳል፡፡ አባትየው ግን የህግ መጣስ
ከሚያንገበግባቸው ሰላም ወዳዶች አንዱ ነበረና ስድቡን ከቁብ ሳይቆጥር ‹‹ስነ ስርዓት አድርግ! ዱላህንም ሰብስብ፣ ዓላማህ ህግ
ማስከበር ከሆነ ወደ ፖሊስ ጣብያ እንሂድና በህግ ፊት እንወያይ›› ብሎት ወደ ፖሊስ ጣብያ አመሩ፡፡ወደ ፖሊስ ጣብያ እያመሩ ሳለ
ግን የፖሊሱ ድብደባ አላባራም፤ ህፃኑን ልጅ ከአባቱ ፊት የባሰውን ይቀጠቅጧል፡፡አባትየው ‹‹ስነ ስርዓት›› እያለ ይከተላል፡፡
ፖሊስ ጣብያ ግቢ እንደደረሱ ልጁ ይዘረራል፡፡ አባት አሁንም ‹‹ ስነ ስርዓት›› ብሎ ፖሊሱን ያዘው፡፡ የፖሊሱ ዱላ
ወደ አባትየው ሲዞር የአባት ትእግስት ስላለቀ አንገት ለአንገት ሲተናነቁ እዛው የነበረው ፖሊስ አባትየውን መደብደብ ጀመረ፡፡ አባትየው
ግን በቀላሉ ሊበገር አልቻለም፡፡ የፖሊሱን አንገት ይዞ አልቅም አለ - ፖሊሱ ሰክሮ ስለነበረ ዥዋ ብሎ ወደቀ፡፡ ሁለተኛው ፖሊስ
የአባትየውን ትከሻ በጩቤ ወግቶ ጣለው፡፡የህን ትዕይንት በመከታተል የነበረው ህዝብ ከቁጥጥር ውጪ ሆኖ ወደ ፖሊስ ጣብያ ዘልቆ በመግባት
ከፖሊሶቹ ጋር መተናነቅ ጀመረ፡፡ ሰካራሙ ፖሊስ ማን እንደ ወረወረው በማይታወቅ ድንጋይ ግንባሩ ተበርቅሶ ወደቀና መላው ሰውነቱ
በደም ታጠበ፡፡እዛው የነበረው ፖሊስ እየሸሸ ወደ ሰማይ ጥይት ይተኩሳል፡፡ገበያው ተተረማመሰ፤ ማልሻዎችና ሽማግሌዎች ተሰባሰቡ፡፡
ፖሊሶች አምባ ጓሮውን ሊቆጣጠሩት አልቻሉም፡፡ ህዝቡ እርሰ በርስ ተው ጋላ መባባል ጀመረ፡፡ የአከባቢው ማልሻዎች፣ቄሶችና
ሽማግሌዎች በፖሊሶቹና ብህዝቡ መሃል ገብተው ማረጋጋት ጀመሩ፡፡ ከዛም በጩቤ የተወጋው አባት፣ ልጁና በድንጋይ ተፈነከተው ፖሊስ
ወደ ጤና ጣብያ ተወሰዱ፡፡ግር ግሩ አልፎ መረጋጋት ሰፈነ፡፡
ፖሊሶች ህዝቡን እንዳለ መወንጀል እንደማያዋጣቸው ስለተረዱ ሽማግሌዎች፣ቄሶችና ተሰሚነት ያላቸው የአከባቢው ሰዎች
ሰብስበው ‹‹ይህዝቡ ስርዓት ዓልበኝነት እንዴት እንግራው?›› ብለው ውይይት ጀመሩ፡፡ ሽማግሌዎቹ ግን ‹‹ስርዓት አልበኞቹ እናንተ
እንጂ ህዝቡ አይደለም፡፡ መጀመርያውኑ ህግ እየጣሳችሁ ያላችሁት እናንተው ራሳችሁ ናችሁ፡፡ ያለፍርድ ታስራላችሁ፣ የተጠረጠረው ሁሉ
በግፍ እያሰቃያችሁ መሆኑን እናውቃለን፡፡ከዚህ ተግባራችሁ ከታቀባችሁ ችግሩ ይፈታል›› ብለው ከህዝቡ ጋር ቆሙ፡፡ይህን የታዘቡ የፖሊስ
አዛዦች ነገርየው ወደ ራሳቸው ሊዞር መሆኑን ስላወቁ ችግራቸው በከፊል በመቀበል ከሽማግሌዎቹ ጋር ተስማሙ፡፡የፖሊሶቹ መጥፎ ስነ
ምግባር ተስተካክሎ ከህዝቡ ጋር ይስማሙ ይሆን?
No comments:
Post a Comment