Sunday, June 1, 2014

‹‹በአንድ ሌሊት የወለድኳቸው ይመስል፤ በአንድ ሌሊት ፈጇቸው!!!››



የካቲት 28 ቀን 2002 ዓ.ም
ወ/ሮ ከበቡሽ አድማሱ
(አራት ልጆቻቸው የተገደሉባቸው)
ከደርግ ማህደር ገፅ 360
የወ/ሮ ከበቡሽ አድማሱ ልጆች፡-
 1.  ደምሴ ብርሀኑ ዕድሜ 18 ዓመት
 2.  ተፈራ ብርሀኑ ዕድሜ 16 ዓመት
 3.  ግርማ ብርሀኑ ዕድሜ 14 ዓመት
 4.  ሞገስ ብርሀኑ ዕድሜ 12 ዓመት
እንዲሁም የአክስታቸው ልጅ የሆነው ተስፋየ መኮነን(የ17 ዓመት ወጣት) በአሰቃቂ ሁኔታ በአንድ ሌሊት በፋሽስቶች ተፈጃችሁ እኔ ለዚህ ምስክር ነኝ፡፡እግዚአቢሔር ነፍሳችሁን በገነት ያኑረው፡፡ ሁሌ አስባችኋለሁ እወዳችኋለሁ፡፡
ከሞት/ከመረሸን ያመለጥኩ ጓደኛችሁ/ወንድማችሁ
ኤልያስ ተሾመ ወይም ገንፎ፤ 19/1/2005
ከደርግ ማህደር ገፅ 253ና 380

ከላይ የተጠቀሱት አሳዛኝና ሰቅጣጭ ፅሑፎች ከማህደር ደርግ ከተባለው መፅሐፍ ሲሆን አራት ለጋ ልጆቻቸውን በአንዲት ሌሊት ያጡ ወይዘሮ ከበቡሽ አድማሱና ሊገደሉ ተወስደው ከመለጡ አንዱ የሆነው አልስ ተሾመ በተጠቀሱት ቀንና አመተ ምህረቶች የቀይሽብር ሰማእታት ሀወልት ከጎበኙ በኋላ ካሰፈሩት አስተያየት የተወሰዱ ናቸው፡፡አራቴ ለዘጠኝ ወራት በሆዳቸው ተሸክመው፣ ለዓመታት አዝለውና አጥብተውና ተንከባክበው ያሳደጓቸው ልጆቻቸውን ደርጎች(ጭራቆች) በአንዲት ሌሊት የጥይት እራት ሲያደርጉባቸው ልባቸው ምንኛ ተጎድቶና ደምቶ ይሆን? የሰው ልጅ የማይችለውን የምታሸክም ዓለም ምንኛ ጨካኝ ነች!!


‹‹እነዚህ ፀረ ህዝብ የሆኑ የታሪክ አተላዎች ባለፉት ጊዜያት አያሌ ታጋዮችንና የህዝብ ወገኖችን ጥለውብናል፡፡ስለሆነም የተጀመረው ቀይሽብር ማዕከላዊ አመራር ባለው ዲሲፕሊን የተሞላበት ሁኔታ ያለማቋረጥ መቀጠል አለበት፡፡በየከተማው፣በየገጠሩ፣በየመንደሩም እነኝህ የታሪክ አተላዎች እስኪጠፉ ድረስም ምንጠራው መቀጠል አለበት፡፡››
ሌ/ኮ መንግስቱ ሃይለማርያም
(አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ጥር 25 ቀን 1970 ዓ.ም፣የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ጥር 27 ቀን 1970 ዓ.ም )
ከደርግ ማህደር ገፅ 320


ለነመንግስቱ ስለሃገሩ የሚቆረቆሩ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የታሪክ አተላዎች ናቸው፡፡ አተላ ደሞ መደፋት አለበት፡፡ ለዛም ነበር ከፊት ለፊታቸው ቆሞ የተመለከቱት ኢትዮጵያዊ ሁሉ ፆታና ዕድሜ ሳይለዩ ይደፉት የነበረው፡፡በሌላ አባባል ደሞ መንግስቱንና ሸሪኮቹን የሚቃወም ሁሉ ፀረ አብዮት ነው፡፡ፀረ አብዮት የእርሻ ማሳውን ሸፍኖ አላሳርስ አሰራ ያለ ቁጥቋጦ ወይም ጫካ ማለት ነበር፡፡ለዛም ነበር ጫካው ተመንጥሮ እስኪያልቅ ደረስ ቀይሽብሩ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ያለው፡፡ባአጠቃላይ ለመንግስቱና ሸሪኮቹ ተቃዋሚ ማለት ሰው ሳይሆን አተላ( መደፋት ያለበት) ወይም ጫካ(መመንጠር ያለበት) ይመስላቸው ነበር፡፡

ደርግ እንደ መንግስት በህግና ደምብ ሃገር የሚያስተዳደር፣አእምሮ ባላቸው ሰዎች የሚመራ ድርጅት ሳይሆን ሰደድ እሳት ነበር፡፡እሳቱን ሎክሶ ያቀጣጠለው ደሞ የ1966 ዓ.ም አብዮት ነበር፡፡ያእሳት እንደ እሳተ ጎመራ ገንፍሎ ሃገራችንን እንዲያዳርስና እንዳልነበረች እንዲያደርጋት ጭራሮና ጋዝ በመጨመር ካባባሱት አቀጣጣዮች ደሞ ኢህአፓና መኢሶን ነበሩበ፡፡እሳት ተረባርበው እስካላጠፉትና የሚቀጣጠል ነገር እስካላጣ ድረስ እፊቱ ያገኘውን ሁሉ ወደ አመድነት እየቀየረና በአውሎ ንፋስ እየተነዳ ሃገርን ያካልላል፡፡ደርግም ያው ነበር፡፡እናም የበላውን በልቶ በኢህዴግ ታጋዮች እስኪ ከስም ድረስ ህፃን፣ወጣት፣ሽማግሌ፣ሴትና ወንድ ሳይል ሁሉንም ኢትዮጵያውያንን ዶግ አመድ አድርጓል፡፡

ህፃን እያለሁ ስለ ደርግ ሲወራ እሰማ ነበር፡፡ወሬው ግን ስለአንዲት ለዓላዊት ሃገር የሚያስተዳደር መንግስት ሳይሆን የገኘውን ሁሉ በግፍ እየገደለ ሃገሪቱን ወደ በረሃነት ለመቀየር ስለተነሳ ጭራቅ ነበር የሚመስለው፡፡እንትና በተባለ አከባቢ ደረግ የህን ያህል ወጣቶች፣አርሶ አደሮች፣አስተማሪዎች፣እናቶች፣እረኞች ገደለ፤ ይህን ያህል ቤቶች አቃጠለ፤ ይህን ያህል ከብትና ፍየሎች ዘረፈ ወዘተ የመሳሰሉ ነበሩ፡፡እናም ደርግ ሲባል የሰው አምሳል ያለው፣እንደ ሰው ሟች የሆነና እንደ ሰው የሚያስብ ፍጡር ሳይሆን የሆነ ታይቶ የማያውቅ አውሬ ይመስለኝ ነበር፡፡አልተሳሳትኩም! ደርግ እውነትም በሃገራችን ታይቶም ሆነ ተሰምቶ የማያውቅ አዲስ መጤ አውሬ ነበር፡፡ይህን እውነታ ካረጋገጡልኝ ታሪኮች አንዱ በቅርቡ በግርማይ አብርሃ ተፅፎ ለሕትመት የበቃው ‹‹ከደርግ ማህደር›› የሚባል መፅሐፍ ነው፡፡

በደርግ ግዜ ሬሳ ንግድ መጧጧፉን፣እናቶች ልጆቻቸው ለተገደሉበት ጥይት ዋጋ መክፈላቸው፣ በልጆቻቸው ሬሳ ላይ እየተረማመዱ እንዲጨፍሩ መገደዳቸው ስሰማ ፕሮፓጋንዳ ይመስለኝ ነበር፡፡እንዚህ ዘግናኝ ግፎች ብዙ አሳማኝ ምንጮች በታጨቁባቸው የህትመት ውጤቶች ሳነባቸው ግን ሃገራችን ‹‹ያለ ምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም›› እያሉ ህዝቦቿን ያለ ምንም ርህራሄ በሚፈጁ አውሬዎች ትተዳደር እንደነበር አምኛለሁ፡፡እናት፣አባትና እህት የልጅጆቻቸው፣ወይም የእህቶቻቸው ወይም የወንድሞቻቸው ሬሳ ከሬሳዎች መካከል ፈልገው ለማግኘት የሚያደርጉት ውጣ ውረድ፣ የሚመለከቱት ዘግናኝ ትእይንት፣ ልጆቻቸውን በግፍ ተገድለው በጠራራ ፀሓይ ተጠለው አላፊ አግዳሚውን አጮልቆ እያያቸው ሲመላልስ፣ በዚህ መሃል የሬሳው እናቶች፣አባቶች፣ወንድም እህቶች ይህንን ተአምር ሲመለከቱ ሳነብ የምሆነውን አጥቻለሁ፡፡

ከደርግ ማህደር በአብዛኛው የኢህአፓ መስራችና ክፍተኛ አመራር የነበረው ብርሃነ መስቀል ረዳ የፃፈው ፅሑፍ የያዘ ሲሆን ሌሎች አያሌ መረጃዎችን አጭቆ ይዟል፡፡መፅሐፎች፣ጋዜጦች፣መፂሔቶችና የቀይሽብር ሰማእታት ሀወልት ከጎበኙ በኋላ በሐሳብ መስጫ መፅሐፍ ላይ ሃሳባቸውን ከከተቡት ላይም የተወሰኑትን ቀንጭቦ ይዟል፡፡የመፅሐፉ የግማሽ ይህሉን በብርነ መስቀል ረዳ ፅሑፍ የተሞላ ከመሆኑ አንፃር ሲታይ መፅሐፉ እንዳለ የብርሃነ መስቀል ሊመስል ይችላል፡፡ወደ ማሃል አከባቢ ሲደርሱ ግን ሌሎች ብዙ ታሪኮች ይገኙበታል፡፡በተላይ እኔን ያስገረሙኝና በጣሙን ያሳዘኑኝ ክስተቶች ግን ስለ ነጭ ሽብርና ቀይሽብር የሚያወሱ ታሪኮች ናቸው፡፡ከእነዚህ አንዱ ፅሑፌ እንደርእስ የተጠቀምኩበትን ዝርዝር ታሪክ እንደወረደ ላስነብባችሁና ምን እንደሚሰማችሁ አስተያየታችሁን ስጡኝ፡፡

አምስት ልጆች ከአንድ ቤት (የታሪኩ ርእስ ነው)

‹‹ በ1969 ዓ.ም በሚያዝያ ወር ላይ ሊነጋጋ አከባቢ የውጪው በር በሃይል ተንኳኳ፡፡በር ከፍቼ ስወጣ የአጥራችን ዙሪያ በበርካታ አብዮት ጥበቃዎች ተከቧል፡፡በሩን ከፈትኩላቸው፡፡ ‹ልጆቹን እንፈልጋለን› አሉኝ፡፡ለምን አልኳቸው፡፡ ለምስክርነት ነው ወዲያው ይመለሳሉ ቀስቅሷቸው አሉኝ፡፡እኔም ልጆቼን ከተኙበት ቀሰቀስኳቸው፡፡

እናታቸው አይሄዱም ብላ ስትከራከር የቀበሌው ሊቀመንበር የመሳርያውን አፈሙዝ አዙሮባት ሊተኩስ አቀባበለ፡፡ኧረ በሽተኛ ናት ተዋት ብዬ ተመፅኜ አዳንኳት፡፡ወጣት ተስፋዬ መኮነን የተባለውን የእህቴ ልጅ በህመም ምክንያት ለአንድ ወር ያህል ከተኛበት አልጋ ላይ ያለርህራሄ ነው አስነስተው የወሰዱት፤ በሽተኛ ነው ብንልም ሰሚ አላገኘንም፡፡

በጠቅላላ አምስት ልጆች ከቤት ሲወሰዱ ልብሳቸውን እንኳ አስተካክለው አልለበሱም፡፡ጫማ ሳያደርጉ በባዶ እግራቸው ነው እያጣደፉ ወደ ቀበሌ 23 የወሰዷቸው፡፡ በማግስቱ ስድስተኛ ፖሊስ ጣብያ መታሰራቸውን ሰማን፡፡ ምሽት ራት ልናደርስ ስንሄድ ደርግ ፅሕፈት ቤጽ ሄዷል ተባለ፡፡ በዙም ሳይቆይ ከደርግ ፅሕፈት ቤት አውጥተው ከቀበሌው በርካታ ወጣቶች ጋር ገፈርሳ ጫካ ውስጥ እንደገደሏቸው በስልክ ተነገረን፡፡

መኖርያ ቤታችን ባላሰብነው ሰዓት ስልክ ተደወለ፡፡ የእህቴ ልጅ ነበር ልጆቹ አልቀዋል፤ እኔ ከመኪና ላይ ሳመልጥ በሶስት ጥይት ተመትቼ አንድ ቤት በእንፉቅቅ ገብቼ ደብቀውኛል፡፡ ብትጠየቁ ሞቷል አስከሬኑ ያልተገኘው አውሬ በልቶት ይሆናል ብላችሁ ተናገሩ፡፡ አብዮት ጥበቃዎች መኖሬን ከሰሙ ተከታትለው መጥተው ይወስዱኛል አለ፡፡

የልጆቼንና የእህቴን ልጅ መሞት ከሰማን በኋላ አስከሬን የያዘ መኪና ወደ ዳግማዊ ሚኒሊክ ሆስፒታል ሲመላለስ መዋሉን ሰማን፡፡ እኛም እርማችንን ለማውጣት አስከሬን ቤት ገባን፡፡ እውነት ለመናገር 500 የሚገመቱ አስከሬኖች ተጋደመዋል፡፡ ከዛ ውስጥ የ18 ዓመቱ ወጣት ደምሴ ብርሃኑ፣ የ12 ዓመቱ ህፃን ሞገስ ብርሃኑ እና የ14 ዓመቱ ህፃን ግርማ ብርሃኑ አስከሬን ሚኒሊክ ሆስፒታል ሲገኝ የ16 ዓመቱ ተፈራ ብርሃኑ አስከሬን ጠፋ፣ አውሬ ይብላው የት ይውደቅ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ የ17 ዓመት ዕደሜ የነበረው የእህቴ ልጅ ተስፋዬ መኮነን ደግሞ አስከሬኑን አባቱ ቀደም ሲል ወስዶ አስቀብሮታል፡፡

የልጆቼ አስከሬን ቢገኝም የመቅበርም ሆነ የማልቀስ ዕድል አላገኘሁም፡፡ እናታቸው ልጆቼን የሌሉበት ቤት አልኖርም ብላ ከዘመድ ጋር ነው የምትኖረው፤ ልጆቼን ከገደሏቸው በኋላ ሊሸፍት ነው መትረየስ አለው በሚል ከቀበሌና ከደርግ ፅሕፈት ቤት የመጡ ታጣቂዎች ቤቴ ገብተው ፈተሹ፤ ልጆቼን ገደላችሁ አኔን ለምን ግራ ታጋቡኛላችሁ ብዬ ስጠይቃቸው መትረየስ አለህ ተብሏል በሚል የቤቴ እቃ አንድ ሳይቀራቸው ገለባብጠው ፈተሹ ይህ ሆኖም ምንም ነገር ባለማግኘታቸው ሄዱ፡፡››
ከደርግ ማህደር ገፅ 253

(ይህ ታሪኩ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ ግንቦት 17 ቀን 1999 ዓ.ም፤ ኮሎኔል ብርሃኔ መሸሻ(የልጆቹ አባት) የሰጡት ቃለ መጠይቅ የተወሰደ መሆኑን በህዳግ ተጠቅሷል፡፡)


No comments:

Post a Comment