![]() |
| GERD |
ከሁለት ሳምንታት በፊት፣
በመስርያ ቤታችን ውስጥ በሚገኘው ክበብ ምሳ ለመብላት ከጓደኞቼ(የስራ ባለደረቦቼ) ጋር ተሰይሜያለሁ፡፡በመሐል አንዱ ጓደኛችን ‹‹ቤኒሻንጉል
ጉምዝ ከኢትዮጵያ ብትገነጠል የህዳሴው ግድብ ለማን ይሆናል?›› የሚል ድንገተኛ ጥያቄ አቀረበልኝ፡፡ይህን መሳይ ጥያቄ እጠየቃለሁ
የሚል ግምት ኖሮኝ አያውቅም፤ ጭራሽም አላሰብኩበትምና አግራሞትና ድንጋጤ
ፈጥሮብኛል፡፡
በመጀመርያ፣ የህዳሴው ግድብ ያረፈበት ቦታ የአማራ ክልል ግዛት ነው
ብለን ለራሳችን እናስቀረዋለን፤ የሚል መልስ ሰጠኋቸው፡፡ይህ መልስ ሊያሳምናቸው ስላልቻለ ግን ‹‹ቤኒሻንጉል ጉምዝ ከኢትዮጵያ እንድትገነጠል
አንፈቅድላትም›› ለማለት አሰበኩኝና በኢትዮጵያ ህገ መንግስት አንቀፅ
39 ቁጥር አንድ፣ የሰፈረው ‹‹የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች መብት ያለቅድመ ሁኔታ እስከ መገንጠል ድረስ›› የሚፈቅድ መሆኑን ትዝ
ስላለኝ ይህን ትቼ የሚከተለውን መልስ ሰጠኋቸው፡፡
‹‹ሲጀመር ከአሁን በኋላ ከኢትዮጵያ የሚገነጠል ክልል የሚኖር አይመስለኝም፡፡የቤኒሻንጉል
ጉምዝ ክልል የግድ ነፃነቴን ይሻለኛል ካለች ግን፣ አንድም ህዳሴው ግድብ ላረፈበት ቦታ በሊዝ መልክ ለኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ ማከራየት
ይጠበቅባታል፤ አልያም ግን የግድቡን የአዋጪነት ጥናት፣ለዲዛይን፣ ለግምባት የወጣበት ወጪ እንዲሁም ግንባታው ከተጠናቀቀ በኋላ ለዘመናት
የሚያመነጨውን የኤልክትሪክ ሐይል ዋጋ መክፈል ይጠበቅባታል›› አልኳቸው፡፡ሆኖም ግን፣ አሁንም መልሱ አጥጋቢ አልነበረም፤ ለእኔም
ለነርሱም፡፡ምክንያቱም፣ የህዳሴው ግድብ ከምጣኔ ሃብታዊ ፋይዳው ይለቅ ሃገራዊ ቅርስነቱና የኢትዮጵያውያን አርማነቱ በእጅጉ የሚልቅ
ነውና፡፡
ዞሮ ዞሮ ግን፣ የምሳ ሰዓት እረፍቱ አልቆ ወደ ስራ መመለስ ስለነበረብን
ጥያቄው በእንጥልጥል ቀረ፡፡ከዛ በኋላም፣ ለአንድ ሳምንት ያህል ትዝ አላለኝም ነበር፡፡ባለፈው ሳምንት የገብሩ አስራት መፅሐፍ(ሉዓላዊነትና
ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ) ገዝቼ ማንበብ ከጀመርኩ ወዲህ ግን ጥያቄው በህሊናየ እየተመላለሰ እረፍት ነሳኝ፡፡ገዢው መደብ ኢህአዴግ፣
በስልጣን ለመቆየት የሚያስችለው እስከሆነ ድረስ ይቅርና ለቤኒሻንጉል ጉምዝ(እንዲሁም ህዳሴው ግድብ) ኢትዮጵያም እንደ ሃገር አስይዞ
ቁማር አለመጫወቱም ማረጋገጫ ያለን አይመስለኝም፡፡በተለይ የኢትዮ-ኤርትራ ጉዳይ ሲነሳማ ጨርሶ ያልጠገገው ጠባሳችን እያመረቀዘ ውስጥ
ውስጡን የሚለበልብ የእግር እሳት ሆኖብናልና በሃገራችን ሉዓላዊነት ለመተማመን እጅግ አዳጋች ነው፡፡
ኤርትራ ከኢትዮጵያ የተገነጠለችበት
ዋናው ምክንያት ጣልያንና የዓረብ ሃገሮች ኢትዮጵያን በማዳከም በቁጥጥራቸው አስገብተው ለመግዛት ከነበራቸው ከፍተኛ ፍላጎት ቢሆንም
ሻዕብያና ህወሓት ውጥኑ በማስፈፀሙ በኩል ወደር የለሽ ሚና ተጫውቷል፡፡ህወሓት፣ በሻዕብያ አስራፂነት ‹‹የኤርትራ ጥያቄ የቀኝ ግዛት
ጥያቄ ነው፤ መፍትሔውም ነፃነት ነው›› የሚል አቋም ወስዶና በድርጅቱ የአቋም
መግለጫ አስፍሮ ለተግባራዊነቱም ‹‹የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረ ሰቦችና ህዝቦች መብት ያለቅድመ ሁኔታ እስከ መገንጠል ድረስ የሚያጠቃልል
ነው›› ብሎ ሲያውጅ በሻዕብያ በኩል የቀረበለት ኢትዮጵያን የመከፋፈልና የማዳከም ሚና መጫወቱን ነበር፡፡
ሁለቱም የቀድሞ አማፅያን ድርጅቶች ተቀናቃኞቻቸውን በጦርነት በማምበርከክ
ለመንበረ ንግስና ሲበቁምና ኤርትራ ከኢትዮጵያ
ስትገነጠል ዓሰብና ቀይ ባሕር ወደቦቻችንን ጠቅልላ ስትሄድ ያለ ባሕር በር መቅረታችን ይታወሳል፡፡
የኤርትራና ኤርትራውያን
ጉዳይ ከእንግዲህ ወዲህ ያለቀለት ይመስላል፡፡የህወሓት መሪዎች ዛሬም ‹‹ኤትራውያንን እንጂ የኤርትራን መሬት እንደማይፈልጉ›› ይናገራሉ፡፡ይህ
አቋማቸው አደገኛ የሚሆነው ግን ‹‹እኛ የምንፈልገው የቤኒሻንጉል ጉምዝ ህዝብ እንጂ የቤኒሻንጉል መሬት አንፈልግም›› ያሉ እንደሆነ
ነው፡፡ምክንያቱም፣ ህዳሴው ግድባችን በቤኒሻንጉል መሬት ነውና የሚገኘው፡፡
ራሱን የቤኒሻንጉል ሕዝቦች ነፃ አውጭ ንቅናቄ (ቤሕነን) የተባለው ዓማፂ ቡድን ደሞ ቤኒሳንጉል ጉምዝን
የማስገንጠል ዓላማ አንግቦ የትጥቅ ትግል ከጀመረ 18 ዓመት ገደማ ሆኖታል፡፡ሆኖም ግን አልፎ አልፎ ከሚያደርሳቸው የሽምቅ ጥቃቶች
ውጪ ጠንካራ እንቅስቃሴ አከናውኖ አያውቅም፡፡እንዳውም ከሁለት
ዓመታት በፊት ይኸው ዓማጺ ቡድን ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር አርቀሰላም አውርዶ ትጥቁን ፈትተዋል የሚል አስደሳች ዜና አንብቤ ነበር፡፡አሁን አሁን ግን፣ የህዳሴው ግድብ እየተፋጠነ ባለበት ወቅት ይህን ዓማጺ ቡድን ሊያጠናክሩ
የሚችሉ ብዙ አስጊ ክስተቶች ብቅ ብቅ እያሉ ይገኛሉ፡፡
የመጀመርያው አስጊ ሁኔታ የደቡብ
ሱዳን ፖለቲከኞች መከፋፈል ነው፡፡እንደሚታወቀው፣ ዶክተር ሪክ ማቻርና ፕረዚደንት ሳልቫ ኪር ጎሳ ለይተው ጦር ከተማዘዙ ዓመታት
አስቆጥረዋል፡፡ኤርትራ፣ዩጓንዳና ግብፅ የሳልቫ ኪር ደጋፊዎች ናቸው ይባላል፡፡በተለይ ዩጓንዳ የሳልቫ ኪርን አገዛዝ በሪክ ማቻር
ይደርስበት ከነበረው ሽንፈት በመታደግ የማይተካ ሚና ተጫውታለች፡፡ወታደሮችዋን በመላክ ሪክ ማቻርን ታድጋቸዋለች፡፡
ሪፖርተ ጋዜጣ ደሞ ‹‹ከግብፅ ጋር አንዳንድ ወታደራዊ ስምምነት ሲያደርጉ የሚስተዋሉት ፕሬዚዳንት ሳል ቫኪር፣ ኢትዮጵያ ዶ/ር ማቻርን ውስጥ ለውስጥ ትደገፋለች የሚል ሥጋት ያላቸው ይመስላል፡፡ ቀደም ሲል የመንግሥታቸው ማስታወቂያ ሚኒስትር ለዓለም አቀፍ ሚዲያ ይህንን በግላጭ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡›› በማለት ግብፅ ሳልቫ ኪርን እንደምትደግፍ ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡በተጨማሪ ግን የደቡብ ሱዳኑ ቀውስ የኤርትራ
መንግስት እጅም ሳይኖርበት አይቀርም፡፡
የኤርትራ መንግስት በደቡብ ሱዳን
ቀውስ ላይ ቤንዚን ከማርከፍከፍ አልፎ የቤሕነን
ታጣቂዎችን በማሰልጠንና በማስታጠቅም ገፍቶበታል፡፡ሪፖርተር ‹‹በኤርትራ መንግሥት ድጋፍ ኤርትራ ውስጥ የተለያዩ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ሥልጠናዎችን በመውሰድ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሽብርተኝነት ድርጊት ለመፈጸም በማቀድና በመዘጋጀት፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን ለመገንጠል የሽብርተኝነት ድርጊት ፈጽመዋል በሚል በተጠረጠሩ አሥር የክልሉ ነዋሪዎች ላይ ታኅሳስ 7 ቀን 2007 ዓ.ም. ክስ ተመሠረተ፡፡›› በማለት እንደዘገበው ከሆነ ሻዕብያ የህዳሴው ግድብ ግንባታን ለማደናቀፍ የቻለውን
ሁሉ እያደረገ ይገኛል፡፡
በተጨማሪ ግን ኢትዮጵያና ግብፅ በህዳሴው ግድብ ላይ ሲያድርጉት የነበረው ውይይትስምምነት ላይ ሳይደርሱ ማቋረጣቸውን ወርልድ ቡሉተን የተባለ ድረ ገፅ በቅርቡ ይፋ አድርጓል፡፡ይህ ማለት ደሞ፣ ግብፅ በሻዕብያ አማካኝነት የቤሕነን
ታጣቂዎችን ማሰልጠንና ማስታጠቋ አይቀሬ ነው ማለት ነው፡፡በተለይ ግን በቀድሞው የኢትዮጵያ ውጪ ጉዳይ
ሚኒስትር(የአሁኑ አምባሳደር) ስዩም መስፍን አደራዳሪነት ለአንድ
ዓመት ሙሉ ሲካሄድ የነበረው ፕረዚደንት ሳልቫ ኪርና ዶክተር ሪክ ማቻርን የማስታረቁ ጥረት ውጤት አልባ መሆኑን ሲታይ ሁኔታው ውስብስብ
ያደርጓል፡፡
ሪፖርተር የአምባሳደር ስዩም ተስፋ እንደሚከተለው ዘግቦታል ‹‹አምባሳደር ሥዩም ሐዘን በተሞላበት አኳኋን፣ ‹‹የተደረጉ ጥረቶች የሉም ማለት አይደለም፡፡ የፈለግነውን ያህል ለመሮጥ ብንሞክርም መሬት ላይ ያለው ሀቅ ምን ይመስላል ብሎ መጠየቅ ግን ያስፈልጋል፤›› ይላሉ፡፡ ጥረታቸው መና እንደቀረ በሚያሳይ ሁኔታ፡፡›› እንግዲህ ድርድሩ ፍሬ አልባ ከሆነ፣ ፕረዚደንት
ሳልቫ ኪር ከግብፅና ኤርትራ ጋር በመወገን ኢትዮጵያን ለመፈታተን ጥረት ማደረጋቸው አይቀሬ ይሆናል ማለት ነው፡፡ከዚሁ ጋር ተያይዞም
የቤኒሻንጉል ሕዝቦች ነፃ አውጭ ንቅናቄ(ቤሕነንን) የማጠናከር ጉልህ ሚና ይኖሮዋል፡፡
በመሆኑም፣ ቤሕነን የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልልን
ለማስገንጠል የሚያስችል ጫና ለመፍጠር ዕድል ይኖረዋል ማለት ነው፡፡
ለመሆኑ ውድ አንባቢስ
‹‹ቤኒሻንጉል ጉምዝ ከኢትዮጵያ ብትገነጠል የህዳሴው ግድብ ለማን ይሆናል?›› የሚል ጥያቄ በቀርብሎ እንዴት ይመልሱታል?

No comments:
Post a Comment