Monday, April 15, 2013

ይድረስ ለዲያስፖራው ወዳጄ ባለህበት





የሀገሬ የወንዜ ልጅ፤ ሰሞኑን ከወትሮው በተለየ መልኩ አብዝተህ “ጤንነቴን” የጠየቅከኝ ያለ ምክንያት እንዳልሆነ አውቃለሁ፡፡ ያቀረብክልኝ ሠላምታ ሥጋት አለበት፡፡ መቼመ ሆነ የትም፣ ምንም ይሁን ምን፣ ኑሮ ቢሳካም ባይሳካልህም፣ ቢደላህም ባይደላህም ስለወገን እና ስለሃገርህ ማሰብህ ተገቢ ነው፡፡ ደግሞም አለማሰብም አይቻልህም፡፡ የማያስበው የሞተ ብቻ ነውና፡፡ 

ወዳጄ ልቤ፡- በአካል ከተለያየን ከብዙ ዓመታት በኋላ “ገፅ ለገፅ” ለመነጋገር የበቃነው በቅርቡ ነው፡፡ በ“ፌስ ቡክ” ከተጋመድን አንድ ዓመት እንኳ የሞላን አይመስለኝም፡፡ ከዚያ ጊዜ ወዲህ፤ በተለያየ ጊዜ፣ በተለያየ ሁኔታ፣ በተለያየ ምክንያት ሀገራቸውን ጥለው ለሥደት የተዳረጉ አንተን መሰል እህትና ወንድሞቼን ተጎዳኝቻለሁ፡፡ ከግል ጉዳይ አንስቶ እስከማህበራዊ፣ ከዚያም አልፎ ሃገራዊ እና ዓለማቀፋዊ ጉዳዮችን ስሰልቅም ከርሜያለሁ፡፡ በተለይ ከአንተ ጋር ያላወጋነው፣ ያልከረተፍነው፣ ያልሰነቅለው ጉዳይ የለም፡፡ 

2005 ዓም ከገባ ወዲህ ግን ከአንተ በኩል የሚሰደድልኝ መልዕክት በመጠይቅ ብቻ የታጀለ ሆነ፡፡ የኑሮ ውድነቱ፣ ሀሳብን የመግለፅ ነፃነት መታጣቱ፣ መንግስት በዜጎቹ ላይ መክፋቱ፣ ዲሞክራሲ የሚባል ከነአካቴው መጥፋቱ፣ ወዘተ ስለምን ነው ብለህ በጥያቄ ወጠርከኝ፡፡ እኔም እንዳንተው ቢጨንቅኝ፣ ይኸው ሃሳብ እያነጎለኝ አለሁ፡- መኖር ከተባለ፡፡

የሀገሬ ልጅ፡- እናልህ!... ሀሳብ እያነጎለኝ ለጥቂት ዘመናት ታሪክን የኋሊት እያስቃኘ አነፈረኝ፡፡ የሀገሬ ፖለቲካ አበሸቀኝ፡፡ ብሽቅ!! የምር ነው የምልህ የኛ ሀገር ፖለቲካ ብሽቅ ነው፡፡ የብሽቅ ብሽቅ!! ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ “ባህላችን” ነው፡፡እንደው በደፈናው የዛሬው የፖለቲካ ባህላችን “የእኛው ውጤት ነው” ወደሚል ድምዳሜ ደርሻለሁ፡፡ “የአንድ ሀገር እና ሕዝብ የሚሆነውና የሚያገኘው፣ መሆን ያለበትንና ማግኘት የፈለገውን ያህል ነው” ያለው ማን ነበር!? ረሳሁት እንጂ ይህንን ያለው የሆነ ሰው ነው፡- ፈነንጅ ነው መሰለኝ፡፡ ያው ፈረንጅ ያለው ሁሉ ትክክል ነው ብለን ስለምናምን እንጂ አስቀድመን ያልነው እኛ ኢትዮጵያኖች ሳንሆን አንቀርም፡፡
(ሣቅ በሣቅ) …
እየቀለድኩ እንዳይመስለህ!! ታሪካችን መመርመር አለበት፤ ባህላችን መመርመር አለበት፡፡ “የትኛውም ሕዝብ የሚያገኘው ወይም የሚኖረው የሚፈልገውን አይነት መሪ እና ኑሮ ነው” የተባለው ምንም ህፀፅ የለው፡፡


ወዳጄ ልቤ፡- ይኼንን አባባል በምሳሌ ባስረዳህ ነው የሚሻለው፡፡ ለወጋችን ያህል የእኔና የአንተን ዕድሜ አስላውማ!!? 40 ዓመት ደፈንን፡፡ ዕድሜን ለመቁጠር እንጂ ለመኖር አልታደልንም መቼም፡፡ በእነዚህ ዓመታት ሁለት መንግስታት አይተናል፡፡ ኢህአዴግን እና ደርግን፡፡ የአጼውም መንግስት ብዙም አልራቀንም፡፡ ከቀደምት የሀገራችን መንግስታት በተሻለ የአፄውን ዘመን ታሪክ እናውቀዋለን፡፡ ሶስቱም መንግስታት አንድ አይነት ናቸው፡፡ አፄ ኃይለስላሴ አምባገነን ነበሩ፡፡ ደርግ አምባገነን ነበረ፡፡ ኢህአዴግ አምባገነን ነው፡፡ የሚለያቸው ዘመን እና አምባገነንነታቸው የተገለፀበት (የሚገለፅበት) ሁኔታ ነው፡፡ የሚለያቸው የሚከተሉት የአምባነንነት ስልት ነው፡፡ የሆነ ሆኖ ሶስቱም የእኛው ውጤቶች ናቸው፡፡ የባህላችን ስሪቶች ናቸው፡፡ 
 ምን ለማለት ፈልጌ መሰለህ?! አሁን ላይ ሆኜ ያለፍነውን እና ያለንበትን ዘመን ሁኔታ በጥሞና ሳብሰለስለው፤ የመናገርን ወይም ሀሳብን በነፃነት መብታችንን የተነፈግነው በሕፃንነት ዘመናችን ነው ብዬ ወደማመን ደርሻለሁ፡፡ ገና በጨቅላነታችን ነው የመናገር ነፃነታችንን የተነፈግነውና ያጣነው፡፡ በአስተዳደግ “ባሕላችንን” ክፋት የተነሳ፡፡ 

ወዳጄ ልቤ፡- እዚችጋ በትውስታ ወደህፃንነት ዘመን ልመልስህ፡፡ ያኔ ጨቅላ ሳለን፣ ሕፃን ሳለን፣ እንቦቀቅላ ሳለን፣ ገና አንድ ፍሬ ልጅ ሳለን፣ ክፉና ደጉን ለይተን በማናውቅበት ጮርቃነታችን ዘመን፣ እኔም ሆንን አንተ እየተገረፍን፣ እየተቀጣን ነው ያደግነው፡፡ አንዳንዴ አጥፍተን፣ አንዳንዴ ደግሞ ሳናጠፋ ነበር የምንቀጣው፡፡ ታዲያ ይኼ ከጉዳያችን ጋር ምን ያገናኘዋል? ትለኝ ይሆናል፡፡ ወላጆች ልጆቻቸውን ያርቁ ዘንድ ግድ ነው ትለኝ ይሆናል፡፡ በእርግጥም ወላጆች ልጆቻቸውን ከስህተታቸው ሊያርሙ ይገባል፡፡ ሊቀጡም ሊቆጣል ይገባል፡፡ ነገር ግን ከቀጡህ እና ከተቆጡህ በኋላስ?!....ታለቅሳለህ፡፡ ስታልቅስ ይብስባቸዋል፡፡ “አፍህን ያዝ!!” እያሉ ግርፊያቸውን ይቀጥላሉ፡፡ እንዳታለቅስ እንኳ ይከለክሉሃል፡፡ ይኼ አታልቅስ ማለትታቸው እኮ በራሱ ያስለቅሳል፡፡

ትዝ ይለሃል ያኔ ሀ፣ሁ ስንማር? ፊደል ስንስት ስንሳሳት? መምሬ አያሌው አንተን እንዴት እንደበጠበጠቡህ? ሰውነትህ እስኪጉረበረብ ዠልጠውህ፣ ዠልጠውህ ሲያበቁ “ፀጥ በል፣ ትንፍሽ እንዳትል፣ ድምጥህን (“ጥ” እንጂ “ፅ” የሚል ድምፀት አይችሉም ነበር) እንዳልሰማ” እያሉ አሳርህን ያስቆጠሩህ!?፡፡ ከዚያች ቀን በኋላ አይደል እሳቸው ጋ ፊደል መቁጠር ያቆምከው!? እስከአፍላነት እድሜ ድረስ እንዴት ትጠላቸው እንደነበር ታወሰህ? ይኸውልህ እንግዲህ ወላጆቻችንም፣ የጨቅላነት መምህሮቻችን በጨቅላነታችን የቀረፁን በዚህ አይነት ባህል ነው፡፡ የእኛ ሀገር መሪዎችም በዚህ ክፉ ባህል ውስጥ ነው ያለፉት፡፡

የደርጉን ኮ/ል መንግስቱን ውሰድ፡፡ የለየላቸው አምባገነን ነበሩ፡፡ የሚመሩት ሥርዓት የለየለት አፋኝ ነበረ፡፡ ጨካኝ፡፡ እንኳንስ ማልቀስ፣ ትንፍሽ ማለት አይቻልም ነበረ፡፡ እሳቸውን የተኩት የኢህአዲጉ አቶ መለስም አምባገነን ነበሩ፡፡ (ነፍስ ይማር) እነዚህ መሪዎች በሕፃንነታቸው አጥፍተውም ሆነ ሳያጠፉ ተገርፈው (ተቀጥተው) ሲያለቅሱ፤ “አታልቅሱ፤ አፋችሁን ያዙ” በሚል ባህል ውስጥ ያደጉ ናቸው፡፡ ለዚህ ነው የሀገር መሪ ሲሆኑ፣ ብሶታችንን መናገር እንኳ የነፈጉን፡፡ ማልቀስ እንኳ የከለከሉን፡፡
እነዚህ መሪዎች በስልጣን ዘመናቸው የሚመሩትን ሕዝብ “አፍህን ያዝ አልልም” አለማለት አይችሉም፡፡ ምክንያቱም በሥልጣን መንበራቸው ዙሪያ ያሰባሰባቸው ሹሞቻቸው “አፍህን ያዝ” ተብለው የታነፁ ናቸው፡፡ ቁንጮዎቹ መሪዎች ሕዝቡ “አፍህን ያዝ” ማለት ባይፈልጉ እንኳ፣ “አፉን ይያዝ እንጂ” ብለው የሚመክሩ ናቸው፡፡ ቁንጮው መሪ፣ ካለ ሹሞቹ ምንም ኃይል ስለማይኖረው “አፉን ይያዝ” ከማለት ውጪ ምንም ምርጫ የለው፡፡ ሕዝቡም አፉን ከመያዝ በቀር ምንም ነገር ለማድረግ የማይደፍረው፣ አሳዳጊዎቹ ወይም አሳዳሪዎቹ ያነፁት በዚያው መጠን ስለሆነ ነው፡፡
እንደው በአጭሩ የመናገር ነፃነታችንን የተነፈግነው “በባህላችን ክፋት” የተነሳ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ የደረስኩት ለዚህ ነው፡፡ ስለዚህ ነው መሪዎቻችንን የፈጠርነው እኛው ነን የምልህ፡፡ (ቤተሰብ የሕብረተሰብ መሠረት ነው የሚለውን ሀቅ እንዳትዘነጋብኝ)… የሆነ ሆኖ በሀገራችን ያየነው፣ የኖርነው፣ የምንኖረው ዕውነት ይኸው ነው፡- “አታልቅስ አፍህን ያዝ” እየተባልን፡፡ ይኸው እኔም አታልቅስ የሚሉት ፈሊጥ እያስለቀሰኝ እንዳለሁ አለሁ፡፡


የሀገሬ ልጅ፡- በል እንግዲህ ይህን ያህል ካልኩህ ይበቃል፡፡ የቀረውን ሃሳቤን ሌላ ጊዜ አወጋሀለሁ፡፡ እስከዚያው ባለህበት ቦታ ሁሉ ሠላምና ጤና ካንተ ጋር ይሆን ዘንድ እመኛለሁ፡፡ በተረፈ ካንተው ጋር ላሉ ለሃገሬን ልጆች ሁሉ (ለሴቱም ለወንዱም፣ ለታናናሾችም ለታላላቆችም፣ ለሊቆቹም ለደቂቆቹም) የከበረ ሠላምታ አድርስልኝ፡፡ “እኔ እንዳለሁ አለሁ፤ እናንተ እንዴት ናችሁ” በልልኝ፡፡


ተፃፈ፡- በ2005 ዓ.ም፤
ከዓመቱም በስምንተኛው ወር (ሚያዝያ)
ከወሩም በመጀመሪያው ቀን፡፡


ወዳጅህ ወሰንሰገድ ገ/ኪዳን

አዲስ አበባ፡፡ 

No comments:

Post a Comment