Sunday, October 20, 2013

ጭፍን ደጋፊዎች፣ ጭፍን ተቃዋሚዎች፣ ለዘብተኞችና ገለልተኞች በኢትዮጵያ




ጭፍን ደጋፊዎች


‹‹ከተፈጠረች ጀምሮ ፀሐይ የሚወጣባትን አገር ጭፍን ደጋፊዎች ‘ኢሕአዴግ ባይኖር ኖር ፀሐይ አትወጣም ነበር’ ይላሉ፡፡ መንግሥት ልማታዊ ስለሆነ ‘ኦክስጅን በሽበሽ ነው’ ይሉናል፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እያለም ለነሱ በሽበሽ ነው፡፡ ቃላቶቻቸው ሁሉ ሁሌም ‘ተደነቀ ተሞገሰ’ ነው፡፡ ያለውን ተጨባጭ ችግርና ጉድለት እየገለጹ መንግሥትና ገዥው ፓርቲ እየታረሙ እንዲጠናከሩ ከማድረግ ይልቅ፣ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ እየሸፋፈኑና እየካዱ መንግሥትን ወደ ስህተትና ጥፋት ሲገፉት ይውላሉ፡፡››



የኢትዮጵያ ችግሮች፡- ድህነት፣የብሔር ብሔረሰቦች ብዛትና ልዩነት፣በተለያዩ ቋንቋዎች መፃፍና መናገር፣ሙስና፣የመልካም አስተዳደር እጦት፣ የዘርፍጅት መልካምነት የሚሰብኩ ጋዜጦችና  መዘጋትና የጋዜጠኝነት ስነ ምግባር የሚጥሱ ጋዜጠኞች መታሰር ወዘተ በገዢው ፓርቲ አማካኝነት የመጡና ለእርካሽ ፖለቲካ ሲባል የሚከናወኑ ናቸው፤ በጭፍን ተቃዋሚዎች እይታ፡፡በቃ፣ ኢህአዴግ ስልጣኑ በለቀቀ ማግስት ኢትዮጵያ ወደ ገነትነት ትቀየራለች ብለው ያስባሉ፡፡ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የሚታሰረው ኢህአዴግን ስለሚቃወም ብቻ ነው ይሉናል፡፡የገቢዎችና የጉምሩክ ባለስልጣናት የታሰሩ ሰሞን ሲያስተጋቧቸው የነበሩ የፖቲካ ዙርያ ጥምጥሞች እንስታውስ፡፡
 



ጭፍን ተቃዋሚዎች


‹‹በሚያሳዝንና በሚዘገንን ሁኔታም በአገራችን ጭፍን ተቃውሞ እየተሰማ ነው፡፡ በኢትዮጵያ እየታየ ባለው ልማትና መነሳሳት አፍሪካውያን ራሳቸው ኢትዮጵያን እንደ ተምሳሌት እየወሰዱ ባሉበት ጊዜ፣ ጭፍን ተቃዋሚዎች ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገሮች ኋላ ቀረች ይሉናል፡፡ ከጥላቻና ጭፍን ተቃውሞ በመነሳት መንገዱ የውሸት ነው፣ ሆስፒታሉ የውሸት ነው፣ ትምህርት ቤቱ የውሸት ነው ይሉናል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኢሕአዴግ ስለሆነ ኤሚሬትስ ይሻላችኋል፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ አትብረሩ ይላሉ፡፡ በዓባይ ወንዝ ላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ግድብ መገንባት የለበትም ይሉናል፡፡ ኢሳያስ አፈወርቂን የመሰለ ጀግና የለም ይላሉ፡፡ ከግብፅ አምስት መቶ ሺሕ ዶላር ተሰጠን እያሉ ይለፈልፋሉ፡፡ ኢሕአዴጎች ጤፍና እንጀራ ወደ ውጭ ስለሚልኩ እንጀራ አትብሉ፣ የጤፍ እንጀራ አትግዙ የሚሉ የተቃዋሚ ሬዲዮ ጣቢያዎችም ተደምጠዋል፡፡ ለዓለም ባንክ፣ ለአሜሪካና ለአውሮፓ ኢትዮጵያን አትርዱ፣ በኢትዮጵያ ኢንቨስት አታድርጉ የሚል ልመናና ተማፅኖ አድምጠናል፡፡ ››


ጭፍን ደጋፊዎችና ጭፍን ተቃዋሚዎችን የሚተቹ፣የገዢው ፓርቲና የተቃዋሚ ፓረቲዎች አፍራሽ ተግባራት ነቅሰው በማውጣት ከስህተቶቻቸው እንዲታረሙ የሚመክሩና የሚገስፁ ወገኖች ደግሞ የቡርኩታ ዕጣ ፈንታ እያጋጠማቸው ይገኛል፡፡ቡርኩታ የሚጠበሰው(የሚሰራው) በተድቦለቦለው የገብስ ቡኽእ ውስጥ እንደ ብረት ግሎ የቀላ የድንጋይ አለሎ ይጨመርበትና ተድቦልቡሎ ወደ እሳት ማገዶ ይገባል፡፡እናም ከውስጥም ከውጭም ይጠበሳል፡፡የሚዛናዊ ተቺዎች ዕጣም እንዲሁ ነው፡፡ የመንግስት ችግሮች ከነቀፉ ጭፍን ደጋፊዎች ይዘምቱባቸዋል፤ ከተቃዋሚው ጎራ እንደተሰለፉ አድርገው ይፈርጅዋቸዋል፡፡የተቃዋሚዎች አፍራሽ አካሄዶች ከዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታዎችና የታሪክ ክስተቶች ተመስርተው ሲተቹም እንዲሁ የጭፍን ተቃዋማች ሰለባ ይሆናሉ፤ የገዢው ፓርቲ ደጋፊዎች ናቸው ይባላሉ፡፡

በነዚህ ምክንያቶች አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ‹‹ፖለቲካና ኮረንት በሩቁ ነው›› የሚል አባባል በመተግበር ላይ ይገኛሉ፡፡ፖለቲካ ተንከፍ ውይይቶች በተነሱ ቁጥር ራሳቸው ገሸሽ ያደርጋሉ፤ ከማንኛውም ሃገራዊና ዓለም አቀፋዊ የፖለቲካ ሁነቶች ለመራቅ ሲሉ ይሞክራሉ፡፡የፖለቲካ ፅሑፎች በሩቁ የማግለል አዝማምያ ይታይባቸዋል፡፡ለዚህም ነው አብዛኞቹ የሃገራችን የተቃዋሚ ፓርቲዎች በአፄው ዘውዳዊ አገዛዝ አንቱ የተባሉ ቱባ ባለስልጣናት፣ የወታደራዊው አምባገነን አማካሪዎችና ‹‹አወንታዊ ተቺዎች›› በነበሩና ውሃ እንደነካው ሳሙና በሚምለጨለጭ ባህርያቸው አማካኝነት ከኢህአዴግ ጋርም ስልጣን ተጋርተው ህዝቡን እኩል ሲረግጡ ኖረው በ11ኛው ሰዓት ከስልጣን በተባረሩ እስስቶች እየተመሩ ያሉት፡፡ሁሉም ለማለት በሚቻል መልኩ የ60ዎቹ ነውጠኛ ትውልድ ውጤቶች ናቸው፤ በኢህአዴግም በተቃዋሚውም ጎራ ተሰልፈው ይህ ትውልድ እንዳሻቸው እያሽከረከሩት ያሉት፡፡መድርክና በመድርክ ስር የተሰባሰቡ ፓርቲዎች ለዚህ አባባል በግንባር ቀደም የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ለምሳሌ ዓረናን እንውሰድ፤ በጳጉሜ የማእከላይ ኮምቴና የስራስፈፃሚ አባል ሆኖ የተመረጠው አብራሃ ደስታ ‹‹ ዓረና ከህወሓት ተገንጥለው በወጡ የድሮ ፖለቲከኞች ስለሚመራ ከህወሓት በምንም መልኩ አይለይምና በአዲስ ትውልድ ይምትለው ሊቀ ምንበራችሁ ሳይቀር የህወሓት አባል የነበረ አይደለም ወይ? በአዲስ ትውልድ ለምን አልተካችሁትም?›› ብየ ጠይቄው ነበር፡፡ህወሓት ያልነበረ በሳል መሪ ስላጣን ሲል ነበር የመለሰልኝ፡፡አውነታው ግን ዓረናን መምራት የሚችል በሳል መሪ ስለጠፋ ሳይሆን በፖለቲካ ውስጥ እጁ ለማስገባት የሚፈልግ የትግራይ ተወላጅ ስለጠፋ ነው፡፡እንጂ ብዙ እጅግ በጣም ብዙ ምሁራን አለ፤ ከተቃዋሚውም ከህወሓትም ጎራ ያልተሰለፉ፡፡

ለምን ቢባል ደግሞ ከላይ ለመግለፅ እንደሞከርኩት ለዘብተኛና ሚዛናዊ የሆነ ፖለቲካ የሚያራምዱ ወገኖች የቡርኩታ ዕጣ ፈንታ ስለሚገጠማቸው ተስፋ ቆርጠው ራሳቸው ስለሚያገሉ ነው፡፡ይህ አካሄድ ግን በፖለቲካውም በምጣኔ ህብቱም የበለፀገች ኢትዮጵያ የማየት ህልማችን መና ሊያደርግ የሚችል ውጤት ስላለው ከወዲሁ መቅረት ያለበት ይመስለኛል፡፡ጭፍን ተቃዋሚዎችና ጭፍን ደጋፊዎች በአካል ተገናኝተው በሰለጠነ ውይይት ችግራቸውን ለመፍታት አይችሉም፡፡መሰዳደብ፣መፈራረጅ፣ጣት መቀሳሰር ነው የሚቀናቸው፡፡በሁለቱም ፅንፎች ያሉ ወገኖቻችን አንዱ ሌላኛውን ካለጠፋ በስተቀር አብረው መኖር የሚችሉ ዓይነት አይደሉም፡፡የ60ዎቹ አክራሪዎች ያስከተለው የነጭና የቀይ ሽብሮች እልቂት ምንጊዜም መርሳት የለብንም፡፡
እንዚያ አዝማምያዎች ዛሬም ድረስ አብረውን አሉ፤ ጭፍን ተቃዋሚዎች ገዢው ፓርቲ የፈለገው በጎ ነገር ይስራ የሚያጣጥሉበት መንገድ ይፈልጋሉ እንጂ እውቅና ለመስጠት ብቃቱም ወኔውም የላቸውም፡፡ኢያጎአዊ ‹‹ኢጎአቸው›› ጠፍሮ ይዞ አላላውስ አላንቀሳቅስ ብሏቸው ይገኛል፡፡ገዢው ፓርቲም ለሃገር ቅድሚያ በስጠት የግላቸው የስልጣን ጥማት ገሸሽ አድርገው ለዘብተኛ በሆነ መልኩ የሚቃወሙትን ከፅንፈኞቹ ጋር ሲፈርጃቸው ይታያል፡፡ሁለቱም ግን ለሃገራችን ቀጣይነት ስለማይበጁ በለዘብተኛውና አርቆ አሳቢው መተካት አለባቸው፡፡ይህ እውን የሚሆነው ደግሞ ‹‹ፖለቲካና ኮረንቲ ብሩቁ›› እያሉ በመሸሽ ሳይሆን የሃገር ጉዳይ መሆኑን አውቆ የመጣው ይምጣ፤ የተባለው ይባል ብሎ ቆርጦ በመነሳት ብቻ ነው፡፡ካልሆነ ግን እንደ ‹‹ኢነርት››ብረቶች የአሲዶች ማሸግያና መሸሸግያ እንዲሁም ማጓጓዣ ሆኖ መቅረት ነው፡፡

ግን እስከ መቸ ነው አብዛኛው ሰላማዊና ለዘብተኛው ወገን የጥቂት ፅንፈኞች መጫወቻ ሆኖ የሚኖረው?እነዚህ ፅንፈኞች(የፖቲካና የሃይማኖት) መነሻና መድረሻቸው የግል ጥቅማቸውን ማሳካት ብቻ ነው፡፡ለዛም ነው እነሱ ካሉትና ካከናወኑት በስተቀር የሌሎች አስተሳሰብና አስራር(ሃገራዊ ጥቅማቸው የተራጋገጡም ቢሆን) በጭፍን ሲቃወሙ የሚታየው፡፡በጭፍን መቃወምና መደግፍ እንዲሁም ‹‹ፖለቲካና ኮረንቲ ብሩቁ›› እያሉ ከሃገራዊ ጉዳዮች ራስን ማግለል መቆም አለባቸው፡፡



ደጋፊውም ተቃዋሚውም ሚዛን አልባ እየሆነ ነው:ethiopianreporter.com




No comments:

Post a Comment