Monday, October 7, 2013

የኢትዮ ቴሌኮም ሰራተኞች የጋራ ዓመታዊ በዓል ፋይዳው ምንድነው?





 የኢትዮ ቴሌኮም ሠራተኞች የጋራ በዓል(GET TOGETHER) ብየዓመቱ ይዘጋጃል፡፡በዚህ መሰረት የዘንድሮ ዓመት  የጋራ በዓሉ የተካሄደው መስከረም 25 ቀን 2006 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ ነበር፡፡የኣዲስ ኣበባ ሰራተኞች ብቻ በሰባት የተለያዩ ቦታዎች ተከፋፍለው ነበር በዓሉን ያከበሩት፡፡በሳባቱ ኣዳራሾች ሰባት ዲጄዮች ከተወዝዋዦች ጋር በዓሉን ሲያደምቁ ውለዋል፡፡ምግብና መጠጥ ከልክ በላይ ተትረፍርፎ ሰራተኛው ሲጫወትበት ኣምሽቷል፡፡በተለይ የመጠጦች ዓይነት ተምሯል ለሚባልለት የቴሌኮም ሰራተኛ ክብር የሚመጥን ኣልነበረም፡፡ከለስላሳ እስከ ሻምፓኝ ያልተንቆረቆረ፣ያልተረጨ ኣለነበረም፡፡
ብዙ ሰራተኞች ገና ከጅምሩ ዓይኖቻቸው ፈጧል፤ የፊታቸው ደምስሮች ተገታትሯል፡፡መላቅጡ የጠፋበት ዳንኪራ እዚህም እዚያም ይጨፈራል፤ ለቅሶ ይሁን ዘፈን በውሉ ያልተወቀ የስርዓት ኣልበኞች ዓይነት ጭሆት እዚህም እዚያም ያስተጋባል፡፡እኔ በዓሉ ለምን ተከበረ የሚል ተቃውሞ የለኝም፡፡አከባበሩ ግን ስነ ስርዓት የለቀቀ መስሎ ተሰምቶኛል፤ ተምሯል ተብሎ የሚታመነው ማሕበረሰባችን እንዲያ ከስብእና በታች ሆኖ እንደማየት ያለ አስቀያሚና ተስፋ አስቆራጭ ነገር ምንናለ?
ለመላው የኢትዮ ቴሌኮም ስራተኞች የጋራ ዓመታዊ በዓል 3 ሚሊዮን ብር መውጣቱን ከአዘጋጅ ኮምቴ አባላት ስሰማ እማ በጣም ነበር ያዘንኩት፡፡እሺ እኛ የኢትዮ ቴሌኮም ሰራተኞች በ3 ሚሊዮን ብር በላን ጠጣን ከዛም ሸናነው፣ እና ምን አተረፍን? ሃገራችን የህን ያህል ብር በዛባት እንዴ? እኛ እኮ ከድህነት ለመላቀቅ ገና በመፍጨርጨር ላይ ያለን ህዝቦች ነን፡፡ይህ ሁሉ መዓት ብር ለቁም ነገር የማናውለው ለምንድነው? 3 ሚሊዮን ብር እኮ ብያንስ አንድ ደረጃውን የጠበቀ ጤና ጣብያ ከነ ሙሉ እቃው ጋር ያስገነባል፡፡ወይም ደግሞ አንድ ከፍተኛ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ማስገንባት ይችላል፡፡
በኢትዮ ቴሌኮም ሰራተኞች ስም በየዓመቱ አንድ ትልቅ ጤና ጣብያ ወይም አንድ ከፍተኛ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መገንባት ማለት ለሃገራችን ምንያህል እንደሚረዳ ተገንዝበኗል? ባአስር ዓመት ውስጥ አስር ጤና ጣብያዎች! ወይም አስር ከፍተኛ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች! የስንት ዜጎች ህይወት ይታደጋል? ስንት ልጆች ያስተምራል? በዳሶች ውስጥ ከንፋስ ጋር እየተታገሉ የሚማሩ ልጆች ባሉባት ሃገር፣ ልጆችና አረጋውያን የሚበሉት፣የሚጠጡትና የሚለብሱት አጥተው ያለ ተንከባካቢ በየጎዳናው በሚኖሩባት ሃገር፣ አስፈላጊ የህክምና አጥተው ዜጎች በቀላል በሽታዎች ህይወታቸው በሚያጡባት ሃገር፣ በ3 ሚሊዮን ብር ቁንጣን እስኪይዘን ድራስ መብላት፣ በስካር ህሊናችን እስክንስት ደረስ መጠጣት ከዛም ማስታወክ፤ ራስንና አከባቢን መበከል ምን ይሉታል?
ነገሩ በጣም አሳዛኝ የምያደርገው ደግሞ ይህን የሚያክል ብር ለመጠጥ፣ለምግብና ለጭፈራ በየዓመቱ የሚባክነው በኢትዮ ቴሌኮም ብቻ አለመሆኑን ስናውቅ ነው፡፡ሁሉም ልማታዊ የመንግስት መስራቤቶች( መብራት ሃይል፣ኢትዮጵያ አየር መንገድ፣የአየር ፖርቶች ድርጅት፣ የቤቶች ልማት ድርጅት ወዘተ.) እያንዳንዳቸው በአማካይ በየዓመቱ 3 ሚሊዮን ብር ያባክናሉ፡፡ብያንስ አስር ልማታዊ የመንግስት መስራቤቶች ቢኖሩንና ለምግብ፣ለመጠጥና ለጭፈራ የምናባክነው ገንዘብ ቢጠራቀም(ብያንስ 30 ሚሊዮን ብር ይሆናል) በየዓመቱ አስር ጤና ጣብያዎች መገንባት እንችል ነበር፡፡አሁን እያደረግን ያለነው ግን በየዓመቱ በአንድ ቀን ብቻ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ወደ ሽንት ቤት መሸኘት ነው፤ የስካርና የቁንጣን ወራሽ መፀዳጃ ቤት ብቻ ይሆናል፡፡ታድያ ለእኛ ድህነት ያንስብናል?
እንደኔ እምነት ግን የሚሻለው በኢትዮ ቴሌኮም ሰራተኞች ስም በየዓመቱ አንድ ተቋም ቢገነባ ነው፡፡እንዲህ ሲሆን እንደ ምሁራንና እንደ የአንድ ድርጅት ሰራተኞች በጣም የምንደሰተው፡፡በእኛ ስም የተገነባው ተቋም ፍርያማነቱን ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ መለስ ብለን ስናየው ሁሌም ያስደስተናል፡፡ስለሆነም የኢትዮ ቴሌኮም ሰራተኞች ዓመታዊ የጋራ በዓል
 ለዋናው ዝግጅት ኮሚቴ አባላት በሙሉ እንድታስቡበት በትህትና እጠይቃለሁ፡፡እባካችሁ አርቀን እናስብ፡፡

No comments:

Post a Comment