ሃገራችን ኢትዮጵያ ለዘመናት በዘውዳዊ አገዛዝ ስትረገጥ
ኖራለች፡፡የ60ዎቹ አብዮት በመጥለፍ ህዝቡን አንደ ብረት አቅልጦ እንደ ዱቄት ፈጭቶ ‹‹በኢትዮጵያ ትቅደም›› ስም የአንድ ትውልድ
ወጣቶች በግፍ የጨፈጨፈውና ሃገሪቱ ወደማትወጣው ድህነት የከተተው ደርግም ዘውዳዊው አገዛዝ በወታደራዊ አምባገነናዊ አዛዝ ነበር
የቀየረው፡፡ሃገራችን ከደርግ ያተረፈችው ነገር ቢኖር ድህነት ነው፤የልጆቿ ያለ ፍርድ መጨፍጨፍ ነው፤ ስርዓት አልባነት ነው፤ ከሁሉም
በላይ ደግሞ እነዚህን ተከትሎ የመጣው ‹‹ፖለቲካና ኮረንቲ በሩቁ›› የሚሉት አባዜ ነው፡፡
በንጉሱ አስተዳደር (ከዛ በፊት በነበሩ ኋላ ቀር
ነገስታትም ጭምር) ብዙ አፍራሽ
ነገሮች ተከስተዋል፡፡በፊውዳሉ የአገዛዝ ዘመን ኢትዮጵያን ‹‹አንድ ሃይማኖት፣ባህልና ቋንቋ ያላት አንዲት ብሔር›› ለማድረግ ሲባል
ከ80 በላይ የሆኑ ብሔር ብሔረሰቦች በሃይል ሲደፈጠጡ ንሯል፡፡የባሌ፣የጎዣምና የትግራይ አርሶ አደሮች የመብት ጥያቄዎች የእንግሊዝ
አውሮፕላኖች በሚያዘንቡት የቦምብ ናዳ ነበር መልስ የተሰጣቸው፡፡ የኤርትራ ፌደሬሽን ቀርቶ እንደ ሌሎቹ ጠቅላይ ግዛቶች የንጉሱ
የግል ንብረት ለማድረግ በተደረገው የመብት መደፍጠጥ ኋላ ላይ እንድናጣት ምክንያት ሆኗል፡፡ የትግራይና ወሎ ጠቅላይ ግዛቶች ረሃብ
በንጉሱ የ80ኛ በዓል ምክንያት ተረስተው ብዙ ህዝብ እንደ ቅጠል ረግፈዋል፡፡
በወታደራዊው የአገዛዝ ዘመን የዘውዳዊው ስርዓት ጨፍጫፎችና የመብት ረገጣዎች በሽዎች ተባዝተው ምሊዮኖች ህይወታቸውን
አጥተውበታል፤ ሃገሪትዋም የድህነት የረሃብ ተምሳሌት እንድትሆን አድርጓታል፡፡የወሎና የትግራይ ድርቅ ብሶበታል፤ መፍትሔውም ህዝቡ
በሃይ ቀየውን እንዲለቅ በማድረግ በየሰፈራ ጣብያው ረግፎ እንዲቀር ነበር ያደረጉት፡፡ንጉሱን ጨምሮ 60 ትላልቅ ባለስልጣኖች ያለ
ምንም ፍርድ በመግደል ስልጣኑን የጀመረው የመንግስቱ ጭራቃዊ አገዛዝ ቀይ ሽብሩ ሲጋጋል በቀን እስከ 54 ሽህ ወጣቶች በመጨፍጨፍ
ለተገደሉበት እያንዳንዱ ጥይት ወላጆቻቸው 120 ብር እንዲከፍሉ ተገድዷል፡፡በጎንደርና በትግራይ ‹‹አሳውን ለማጥፋት ባህሩን ማድረቅ››
በሚሉት ፍፁም እንስሳዊ አስተሳሰብ ህዝቡ በገበያ ቀኖች፣በክብረ በዓላትና ስርዓተ ቀብር በሚካሄድባቸው ጊዚያቶች በተደጋጋሚ በሚጎች
ተደብደቧል፡፡
እነዚህ ሁሉ ግፎች ታሪክ ሆኖው ኢህአዴግ ደርግን ድባቅ
በመምታት ስልጣን ሲጨብጥ የብሔር ብሔረ ሰቦችና ህዝቦች መብት የሚያስከብር ህገ መንግስት ተረቆ ሃገራችን በፌዴራላዊ ስርዓት ትስተዳደር ጀመር፡፡ህገ
መንግስቱ የግለሰብ መብት ብቻ ሳይሆን ለዘመናት ተረግጠው የኖሩ የብዱን መብቶችም እንዲከበሩ በመፍቀዱ የተለያዩ ዓይነት ባህሎች፣
ቋንቋዎችና ልምዶች ማደግ ጀመረዋል፡፡ለምሳሌ ‹‹የትግራይ ህዝብ ታሪክ ይሰራል እንጂ ታሪክ አዘግብም›› የሚባለው አባባል ታሪክ
ለመሆን የበቃው በቋንቋችን እንድንማር ስለተፈቀደልን ነው፡፡በአሁን ጊዜ የትግራይ ህዝብ ታሪክ በራሱ ተወላጆች በትግርኛ እየተፃፈ
ይገኛል፡፡ ድሮ ግን አንድ አንድ የታሪክ ምሁራን ነን ባዮች በምርቃና የፃፉትን ነበር ስንማር የኖርነው፡፡ሌሎቹ ብሔሮችም እንዲሁ
ባህላቸውና ታሪካቸው በራሳቸው ቋንቋ በመፃፍ ይገኛሉ፡፡
ይህ ለውጥ ግን በህዝቡ ክንድ ተቀጥቅጠው ከስልጣን ለተባረሩ የድሮ ስርዓት ርዝራዦች ራስ ምታት ሆኖባቸዋል፡፡የፌደራል
ስርዓት መዋቅሩና የብሔር ብሔረሰቦች መብት መከበር የአንድ ትውልድ ዕድሜ(23) ያህል በመቆየቱ የሚይዙት የሚጨብጡት አሳጥቷቿል፡፡ከጥቂቶች
በስተቀር የሁሉም ተቃዋሚዎች ለማለት በሚቻል መልኩ ዓላማቸው የድሮው ጨቋኝ ስርዓት ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊና
ሰብአዊ መብቶች፣ የመብት እኩልነት፣የፕረስ ነፃነት ወዘተ እያሉ የሚለፍፉት የስልጣን ጥማቸውን እስኪያረኩ ነው እንጂ ስለነዚህ ነገሮች
ተቆርቁረው አለመሆኑን አካሄዳቸውን በማጤን ብቻ ማወቅ ይቻላል፡፡አብዛኞቹ የፓርቲዎች አመራሮች ከሶስት ጊዜ በላይ ፓርቲዎች ቀያይሯል፤
እስካሁን ግን በአንዱም አልተሳካላቸውም፡፡የተቀሩት ደግሞ ሲመቻቸው ብረት አንስተን እንዋጋለን ይላሉ ካልተመቻቸውም በሰላማዊ መንገድ
እንታገላለን በማለት የሚገለባበጡት ስለሃገርና ስለህዝቦቿ አስበው ሳይሆን የግል ጥቅማቸው የተነካባቸው መስሎ ስለሚሰማቸው ነው፡፡
ከእነዚህ የከሰሩ ፖለቲከኞች ስብስብ አንዱ የሆነው የግንፍሌው ሰማያዊ ፓርቲ ሲሆን ከመቶ በላይ አባላት ሳይኖሩት
የኢትዮጵያ አማራጭ ህገ መንግስት ማርቀቁን አስታውቋል፡፡እንደ ሌሎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በምክንያት ሳይሆን በጭፍን ጥላቻና በስሜታዊነት
የሚንቀሳቀሰው የፓርቲው ስብስብ የፌዴራል ስርዓት አወቃቀሩ በአሀዳዊ ለመቀየር እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ይህ የሰማያዊ ፓርቲ ዓይነቱ
ህገ መንግስት ግን አዲስ አይደለም፤ በደርግና በዘውዳዊው ስርዓቶች የነበረና የህዝብ ተቀባይነት አጥቶ የፈረሰ ነው፡፡
ከፌዴራላዊ የመንግሥት አወቃቀር ይልቅ አሀዳዊ የመንግሥት አወቃቀር?
ፌዴራላዊ የመንግስት አወቃቀር ብዙ ብሔር ብሔረ
ሰቦችና ህዝቦች ባለት ሃገር የሚመረጥና አዋጪ መሆኑን የተረጋገጠ የመንግስት አወቃቀር ነው፡፡ከቻይና በስተቀር በጣም ሰፋፊና ብዙ
ብሄር ብሔረ ሶቦች የሚኖሩባቸው ሃገሮች ፌዴራላዊ የመንግስት አወቃቀር ይከተላሉ፡፡አሜሪካ፣ራሽያ፣አውስትራልያ፣ብራዚል፣ህንድ
ወዘተ የዚህ ዓይነት አወቃቀር ተከታዮች ናቸው፡፡በዚህ ምክንያት ነበር ሃገራችን ኢትዮጵያም የፌዴራል ስርዓት ተከታይ እንድትሆን
የተወሰነው፡፡አሃዳዊ የምንግስት አወቃቀር ግን አንድ ብሔር (አናሳ ብሔሮች) በሚኖርባቸው ትናንሽ
ሃገሮች ነው ውጤታማ መሆኑን የሚነገረው፡፡የተማከለ ስልጣን ስለሚከተል ደግሞ ወደ አምባገነንነትና ፈላጭቆራጭነት የሚያመራ የመንግስት
አወቃቀር ነው፡፡ለነ እንጂኔር ይልቃል ግን ይህ ጉዳይ ወሳኝ ነው፤ ህዝቡን እንደፈለጉ ለመርገጥ በር የሚከፍት ነውና፡፡ስለሆነም
ነው ወደ አሃዳዊ ስርዓት የሚመልስ ህገ ይልቃሎች የቀረፁት፡፡
ከቡድን መብት ይልቅ የግለሰብ መብቶች?
ከቡድን
መብት ይልቅ የግለሰብ መብት የሚያስቀድሙት ክላሲካል ሊበርታርያኖች ነበሩ፡፡ቡድን የግለሰቦች ስብስብ ሰለሆነ የግለሰቦች መብት ከተከበረ
የቡድኑም ይከበራል በማለት ይከራከራሉ፡፡አሁን ግን ጊዜው ተቀይሯል፤የቡድንና የግለሰብ መብቶች እኩል መካተት አለባቸው፡፡የሰው ልጅ በተፈጥረው
ማህበራዊ ነው፤ በማህበር ይኖራል፡፡በማህበር ሲኖር ለማህበሩ የሚመቹ ባህሎች፣ ቋንቋዎች፣ ልምዶችና እምነቶችን ያዳብራል፡፡እነዚህ
ነገሮች ከተነኩበት ወይም በነፃነት እንዲያከናውን ከተከለከለ ማመፁ አይቀርም፡፡ስለሆነም ከግለሰብ መብቶች በተጨማሪ የቡድን መብቶችም
ሊከበሩለት ይገባል፡፡
የእኛ ሃገር ተቃዋሚዎች በተለይም ሰማያዊ ፓርቲ ግን የግለሰብ መብት
የቡድን መብትን መቅደም አለበት ባያች ናቸው፡፡ይህ ዓይነት አካሄድ ግን ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ከታሪክ መማር እንችላለን፡፡የሃገራችን
ህዝቦች ከአማርኛ በስተቀር በቋንቋቸው እንዲማሩና እንዲፅፉ አይፈቀድላቸውም ነበር፡፡በመሆኑም ባህላቸው ወደ መጥፋት ተቃርቦ ነበር(ከሞቱ
ቋንቋዎች የጠፋም ይኖራል)፡፡
ከብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሉዓላዊነት ይልቅ የሕዝቦች ሉዓላዊነት?
የኢፌዴሪ ህገ መንግስት የብሔር፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች
ሉዓላዊነት ካስፈለገም እስከ መገንጠል ድረስ ይፈቅዳል፡፡አብዛኞቹ የሃገራችን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ይህ መብት የሚፈቅደው አንቀፅ(39)
አምርረው ሲኮንኑ መታዘብ የተለመደ ነው፡፡ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ወደዱም ጠሉም በአንድነት ስም ተረግጠው መኖር
አለባቸው ማለት ነው፡፡ከማስገደድ ግን በመፈቃቀድ አብሮ መኖር አይሻልም? ስምምነት ከሌለ ማንኛውም ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ነፃነታቸው ለማስከበር የሚስቆማቸው ሃይል ይኖራል ብሎ ማመን ሞኝነት ነው፡፡ሰማያዊ ፓርቲ ድግሞ አንቀፅ 39ን የሚሽር የግሌ ህገ መንግስት አለኝ እያልን ነው፡፡ሰማያዊ
ፓርቲ የስልጣን ባለቤት ከሆነ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሉዓላዊነት ብሎ ነገር አይኖርም፡፡በህዝቦች ሉዓለላዊነት ስም ይደፈጠጣል፡፡
እናም ሰማያዊ ፓርቲ ከፌዴራላዊ የመንግሥት አወቃቀር ይልቅ አሀዳዊ የመንግሥት አወቃቀር፣ከቡድን መብት ይልቅ የግለሰብ መብቶች፣ከብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሉዓላዊነት ይልቅ የሕዝቦች ሉዓላዊነት እንዲሁም መሬት ከመንግስት ባለቤትነት ይልቅ የግለሰቦች እንዲሆን የሚያደርግ ህገመንግስት አርቅቋል፡፡ከመሬት
ባለቤትነት በስተቀር ግን ሌሎቹ ለዘመናት ተመኩረው ያልተሳኩ ናቸው፡፡ስለሆነም ወደ ኋላ መመለሱ አስፈላጊ አይመስለኝም፡፡

Well Said Asfaw Gedefu!!! Impressive Writing! I really appreciated it!
ReplyDelete