Wednesday, September 3, 2014

ጨለማውን ለምን ፈራሁት?

'

 በህልሜ ይሁን በእውኔ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ብቻ አንድ ይሆናል ብየ ያልጠበቅኩት ነገር ተከስተዋል፡፡ያለሁበት ስፍራ ድቅ ድቅ ጨለማ ነው፤ ዓይንህን እስኪጠነቁሉህ ድረስ በማታይበት፡፡በመጀመርያው አከባቢ ሌሊት መስሎኝ ነበር፤በደመናና ጉም የታጀበ የክረምት ጨለማ፡፡ የጊዜው ርዝመት ሳስበውና ሰሰላስለው ግን ሌሊት አለመሆኑን እርግጠኛ ሁኛለሁ፡፡የሌሊት ርዝመት ከ12 ሰዓት አልፎ ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል የረዘመው እስከ መቼ ነው? በፍፁም ሊሆን አይችልም፡፡የእኔ እድሜስ ከመቼው ግማሽ ክፍለ ዘመን ሞላው?

ከአጠገቤ ማንም የለም፡፡ወይም ይኑር አይኑር ማየት አልቻልኩም፡፡ በጣም አሳስቦኛል፡፡የቀበሮና የጅብ ጭሆት ከሩቅ ይሰማኛል፡፡የሆኑ ሰዎች ላምባዲና አብርተው ወድያ ወዲህ ሲሉ ይታዩኛል፡፡ በእርግጥ ሰዎቹን መለየት አልችልም፤ ምናልባትም ከቅርብ ርቀት አስፓልት ሊኖር ይችላል፡፡ውልብ ውልብ የሚልብኝ ብርሃንም የመኪኖች የፊት መብራት ሊሆን ይችላል፡፡የጅቦቹ ጭሆት ወደ እኔ እየቀረበ ነው፡፡ከሩቅ ይታዩኝ ነበሩ መብራቶችም እየተጠጉኝ ያሉ ይመስለኛል፡፡እኔን ለማጥፋት ወይንስ እኔን ለማዳን? ግን ጨለማው ዛሬ ደርሶ ለምን አስፈራኝ? ወዳጅ ከምቀኛ ለይቼ እንዳላውቅ ስለጋረደኝ ይሆን?

እኔን የሚፈልጉ ሰዎች ይሆኑ እንዴ?ለምን ይፈልጉኛል? ፈርቻለሁ ልበል? አዎ! ፈርቻለሁ፤ ፍርሃቱ ግን ይለያል፤ህፃን እያለሁ ብቻ ነበር ይህን ዓይነቱ የፍርሃት ስሜት የተሰማኝ፡፡‹‹ደርግ የተባለ ጭራቅ መጥቶ ይበላችኋል›› ተብለን የመንደራችን ኗሪዎች እንዳለ በአንድ ዋሻ ውስጥ ተደብቀን እያለ የተሰማኝ ፍርሐት ነው አሁን እየተሰማኝ ያለው፡፡ግን ደርግ ከተደመሰሰ 23 ዓመታት አልፈዋል፡፡አካሌ ውርጭ ላይ እንዳደረ ሰው ይርገፈገፋል፡፡ለብ ያለ ላብ ጀርባየን ሰንጥቆ ቁልቁል እየወረደ ነው፡፡ እጆቼም ላብ በላብ ሆኗል፡፡
በአሁኑ ወቅት ለምን በዚህ ስፍራ ተገኘሁ?በህይወት አለሁ፣ ወይስ ሙቻለሁ? በህይወት ከሌለሁ ችግር የለውም፡፡ ግሃንም ውስጥ ነኝ ማለት ነው፤የድያብሎስ ጭፍሮች እያፈላለጉኝ ይሆናል፡፡በህይወት ካለሁ ግን በእርግጠኝነት አደጋ ውስጥ ነኝ፡፡በህይወት እያሉ በዲያብሎስ ጭፍሮች ከመሰቃየት መሞት ይሻላል፡፡  

እነዚህ ሰዎች ወደ እኔ የሚመጡት? እዚህ ጋር መሆኔን ማን ነገራቸው? ኮቴያቸው በደምብ ይሰማኛል…ያ ህፃን እያለሁ…ከወላጆቼ ጋር ዋሻ ውስጥ ተደብቀን ሳለን ይሰማኝ ነበረው …የወታደሮች ኮቴ! አያቴ ትዝ አለችኝ…የወታደሮቹ ኮቴ ከተደበቅንበት ዋሻ ላይ ይሰማን ነበር፡፡ ቢሆንም ግን ድምፅ እስካላሰማን ድረስ ወታደሮቹ ሊያገኙን አይችሉም ነበር፤ከላይ ሲታይ ዋሻ መኖሩን ስለማያስታውቅ፡፡የአከባቢው ተወላጅ ካልሆነ በስተቀር ማንም ፈልጎ ሊያገኘው አይችልም፡፡ቢሆንም ግን ድምፅ እንዳላሰማ አፌን ጥርቅም አድርጋ ይዛኝ ነበር…አያቴ፡፡ምን አለ አሁንም በህይወት በኖረችልኝ? አጠገቤ ሆና ‹‹አይዞ ማንም አያገኘንም›› እያለች እንደታበረታታኝ፡፡ለጥቄዎቼ ሁሉም ሳይታክታት ትመልስልኝ ነበር፡፡ለምንድ ነው ቤታችን ትተን እዚሁ የተደበቅነው አደዋየ? ሽፍቶች እንዳይገድሉን ነው ልጄ፡፡በገዛ ቤታችን ለምን ይገድሉና፣ ምን አጠፋን? ምንም አላጠፋንም፤ ሽፍቶች ስለሆኑ ብቻ ሰው ይገድላሉ፣ቤት ያቃጥላሉ፣በግ፣ከብትና ፍየል ያርዳሉ፡፡የተረፉትም ይዘው ይሄዳሉ፡፡

ልጆች እያለን ከጓደኞቼ ጋር ለሁለት ተቧድነን ሽፍታ ሽፍታ እንጫወት ነበር፡፡ቡድኖቹን የሚመሩት በዕድሜ ተለቅ ተለቅ ያሉ ልጆች ሲሆኑ አሸናፊው ቡድን የተሸናፊው ቡድን አባለት እንዳለ ገድሎ፣ቤት አቃጥሎ፣አንዳች የቤት እንስሳ ሳያስቀር ይዞ ይሄዳል፡፡ሆኖም ግን ተሸናፊው ቡድን በተራው አሸናፊ ይሆንና የባላንጣው ቡድን አባላትን ይገድላል፣ቤት ያቃጥላል…የቤት እንስሳት ያርዳል…ይዘርፋል፡፡ጨዋታው የምናካሄደው የወዳደቁ እንጨቶች፣ፍልጥና ዱላ እንደ ጠብመንጃ ተጠቅመን ነበር፡፡

አብዛኛው ጊዜ እኩል ነበር የምነሸናነፈው፡፡አንዳንዴ ግን ከሁላችን የሚበልጠው ጉልቤ ሁሌም ካላሸነፍኩ እያለ ስለሚረብሽ በመሃል እንጣላ ነበር፡፡የምር ተደባድበን፣ ተላቅሰን የምንለያይበት ጊዜ ነበር፡፡በነጋታው ግን ትናንት የሆነውን እንዳለ ረስተን ጨዋታችንን እንቀጥላለን፡፡ኋላ ላይ ግን እንደ አያቴ አባባል የምር ሽፍቶች መጡብን፡፡ሁለቱም ሽፍትች እኛን ለመታደግ እንደመጡ ነበር የሚነግሩን፡፡የአንደኛው የሽፍትች ቡድን አባላት ሲገድሉም ሆነ ሲዘርፉ አይታዩም፡፡የማይታዘዙ የአከባቢው ምሁራንና ባላባቶችን አፍነው በመውሰድ መጨረሻው እንደማይታወቅ ጉድጓድ ዋጥ አርድርገዋቸው ቀርተዋል፡፡የሌላኛው ሽፍታ አባላት መስለው በመምጣትም ሴቶች አስገድደው ይደፍሩ፣ ቤት ያቃጥሉ፣ የቤት እንስሳት ይዘርፉ፣ ክምሮች ያቃጥሉ እንደነበርም ይወራል፡፡ይህን ሁሉ ግን በሽክሹክታ እንጂ በግልፅ አይወራም፡፡በግልፅ ሲያወራ የተገኘ ሰው እንደ ጅብ ሌሊት መጥተው አፍነው ይወስዱታል፡፡ከዛ በኋላ የት እንደ ገቡ አይታወቅም…የሚጠይቅም አይኖርም…ጆርጅ ኦርዌል እንዳለው እንዲተኑ ይደረጋል፡፡

እውነትና ውሸት፣ ብርሃንና ጨለማ በዚህ መልኩ ነበር የተደበላለቁት፡፡ እነርሱ እውነት ነው ያሉት ውሸት በቃ እውነት ነው፡፡ማንም አይደለም ማለት አይችልም፡፡ በጠራራ ፀሐይ ጨልሞብናል ካሉ ‹‹ፃሐይዋ ስትጠልቅ?›› ብሎ መጠየቅ ያስቀጣል፡፡ይኸው አሁንም አንኔን ጨልሞብኛል…በአከባቢየ ከሚሰማኝ የጅብና የቀበሮ ጭኾትና ውልብ ውልብ የሚሉት መብራቶች በስተቀር ምንም ነበር አይታየኝም፡፡ወዴት መሸሽ እችላለሁ…የት ልሸሸግ? ለምንስ እሸሻለሁ…እሸሸጋለሁ? ምን አለ አሁን ጭለማው እንደ ጥቁር ልብስ ግፍፍ ብሎ ቢጠፋ? አሳዳጆቼ በግንባሬ ላይ መትረየስ ደግነው ቢታዩኝስ? አይጣል እኮ ነው! የትናንቶቹ የእኔ አለኝታዎች እኔን ሊገድሉ? አድርገውታል እኮ፣ አያደርጉትም አይባልም፡፡

የአውሬዎቹ ድምፅና የወታደሮቹ ኮቴ አጠገቤ ደርሰዋል፡፡ ማናቸው ቀድመው ይደርሱብኝ ይሆን? ወይንስ ገጭ ገጭ የሚለው ድምፅ የአውሬዎቹ ጥርሶች ናቸው? እናንተ የምታዩኝ፣ እኔ እማላያችሁ፣ ሽሽቼ እማላመልጣችሁ አሳዳጆቼ ሆይ ዞሮ ዞሮ የትም አልሄድባችሁም፤ ብትተውኝ ምን አለበት?ከአውሬዎች መንጋ መሃል ትተውኝ ሄደው ይሆን እንዴ? በቃ፣ አላወቅኩም እንጂ ለካ የአውሬዎች እራት ለመሆን ተፈርዶብኛል፡፡ ወደ እኔ የሚመጡ መስለው ይታዩኝ የነበሩ መብራቶች አሁን አይታዩኝም፡፡ ድቅ ድቅ ጨለማ ውጦኛል፡፡ መንቀሳቀስ አቃተኝሳ… ታስሬያለሁ እንዴ? አዎ፣ ታስሬያለሁ፡፡እዚሁ የጅቦች እራት መሆኔን ነው… ጅብ በልቶታል ተብሎ ይወራብኛል፡፡ ማንም ተጠያቂ አይኖርም፤ እንዲህ ነው መትነን ማለት…አልበርኩም የለሁም!

የኸው ጅቦቹ እያሸተቱኝ ነው…ኧኧኧኧዓዓዓዓዓዕዕዕ…ህእ…እ…

  




No comments:

Post a Comment