በአጭሩ፣እኔ የምፅፈው ሰው ስለሆንኩ
ነው፡፡ሰው በመሆኔ ብቻ ሐሳቤን በነፃነት የመግለፅ ሰብአዊ ፍላጎት አለኝ፡፡ ፖለቲካ፣ ሃይማኖት፣ ባህል፣ ብሔር ወዘተረፈ ኋላ የሚከተሉ ማህበራዊ ዳራዎች ናቸው፡፡ማንም ለማስደሰት ወይም ለማበሳጨት አይደለም የምፅፈው፡፡
ለእንጀራ፣ ለሹመት፣ለአጉል ሙገሳም ፅፌ አላውቅም፣ ለወደፊቱም እቅድ የለኝም፡፡ብፈልግም ይቻላል ብዬ አላምንም፡፡
ማንኛውም ሰው የሆነ ድምፅ ስምቶ፣
የሆነ ፅሑፍ አንብቦ ወይንም የሆነ ምልክት አይቶ የሚደሰተውም ሆነ የሚበሳጨው ከአእምሮው በሚመነጨው ሁካታና ጭኾት እንዲሁም ሽብር
ነው፡፡
የእነዚህ ነገሮች ትርጉም ሊኖርም ላይኖሩም የሚችለው ጭንቅላቱ ከመቃኘትና አለመቃኘት የሚመነጭ ብቻ ነው፡፡በጭንቅላቱ የተቃኘው
ትርጉም መጥፎ ከሆነ መጥፎ ነው ብሎ ነው የሚያምነው፤ ትርጉሙ ጥሩ ከሆነ ደሞ ጥሩ ነው ብሎ ያምናል፡፡ምስሎቹ፣ ድምፆቹ፣ቃላቱ እንዲሁም
ቅርፃ ቅፆቹ ግን በራሳቸው ትርጉም የላቸውም፡፡ትርጉም የሚሰጣቸውም ሆነ የሚነፍጋቸው ጭንቅላትህ ነው፡፡ ጭንቅላትህ ትርጉም የሚሰጣቸው
ደሞ ከተገራባቸው ሁኔታዎች አንፃር ነው፡፡
ለምሳሌ ‹‹የለም›› የሚለው ቃል እንውሰድና ትርጉሙን ከሁኔታዎች አንፃር እንየው፡፡የለም ማለት
ጥሬ ቃሉ ብቻ ወስደን ብንተረጉመው የአንድ ነገር አለመኖርን ያመለክታል፡፡ አንድ ሰው‹‹ባንዴራችን አረንጓዴ፣ብጫ፣ ቀይ በመሆኑ
የኦርቶዶክስ እምነት ብቻ ያንፀባርቃል›› ሲል፣ ሌላው ‹‹የለም እነዚህ ቀለሞች በክርስትኖች አልተፈጠሩም፤ ነበሩ ለወደፊቱም ይኖራሉ፡፡የኦርቶዶክሶች እምነት የሚያንፀባርቅ
ቢሆን ኑሮ ባንኛውም የኦርቶዶክስ ቤተክርስትያንም እነርሱ በሚበዙባቸው ሃገሮች የሚገኙት ባንዴራዎች አረንጓዴ፣ብጫና ቀይ ይሆኑ ነበር፡፡
ግን አይደሉም፡፡ የራሽያ ባንዴራ ብጫና አረንጓዴ ቀለም የለውም›› ሊል ይችላል፡፡አሁን ‹‹የለም›› ሲል አይደለም፣
ተሳስተሃል ማለቱን ነው፡፡
እስኪ በሌላ ሁኔታ ደሞ እንየው፡፡ ሰው ነህና ትበላለህ፣ትጠጣለህ፡፡ ከዛም መተንፈስ ተፈጥራዊ
ስጦታህ ስለሆነ ሽንት ቤት ሄደህ መፀዳዳት ያስፈልገሃል፡፡ሽንት ቤቱ ተዘግቶ አገኘኸው፡፡ኳ..ኳኳኳ…ኳኳኳ እርገህ ታንኳኳና ‹‹ሰው
አለ?›› ብለህ ትጠይቃለህ፣ ‹‹የለም›› የሚል መልስ አዳምጠሃል፡፡ያኔ በሩን ከፍተህ አትገባም፡፡ ትጠብቃለህ ወይም አማራጭ ካለ
ሌላ ሽንት ቤት ፍለጋ ትሔዳለህ፡፡ ምክንያቱም ‹‹የለም›› ማለት ‹‹አለ›› መሆኑን ስለሚገባህ ነው፡፡በልምድ የምታውቀው ግን የለምና
አለ ተቃራኒዎች መሆናቸውን ነው፡፡
ሌላ ምሳሌ ልንገርህ፤‹‹እናንተ ሸክም የከበዳችሁ ወገኖች ሆይ፣ ወደእኔ ኑ›› የሚለው ጥቅስ
ወይም አረፍተ ነገር ለክርስትያኖች ምንጩ መፅሐፍ ቅዱስ እንደሆነ ብቻ ነው የሚገባቸው፡፡ለእኔ ግን በመፅሐፍ ቅዱስ ስለመቀመጡ ትርጉም
አይሰጠኝም፡፡ ይበልጥ ትርጉም የሰጠኝና ለብቻየ ከትከት ብዬ እንድስቅ ያደረገኝ በአንዱ ዩኒቨርሲቲ በሚገኘው ሽንት ቤት በር ላይ
ተፅፎ ሰነበው ነው፡፡ጥቅሱ ያሽንት ቤት የፃፈው ባይሆንም ለእኔ ግን በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሳነበውና በሽንት ቤቱ በርላይ ተፅፎ
ሳነበው ልዩነቱ ሰማይና ምድር ነው፡፡ለምን ብትል በጭንቅላቴ የተቀረፀው ሽንት ቤት እውነትም ሸክም የከበዳቸውን ተቀብሎ እረፍት
እንደሚሰጣቸው ስላሳመንኩት ነው፡፡በልቶ ጠጥቶ ሽንት ቤት ባሰኘኝ ጊዜ የሚሰማኝ ሸክም ወደር የለውም፡፡
አየህልኝ ወገኔ? እኛ የፈጠርናቸው ነገሮች እኛ እንደፈለግነው ወይም እንደተቃኘነው ነው የምነተረጉማቸው፡፡የቻይንኛ
ቋንቋ ፊደሎች ላንተ የተበተነ ሳር መስለው ሊታዩህ ይችላሉ፡፡የማታውቃቸው ፊደሎች፣ቅርፃ ቅርፆች፣ድምፆች፣ምስሎች
እንዳለም ለንተ ስሜት አይሰጡም፡፡ስሜት እንዲሰጡህ ተደርገህ ስላልተገራህ፡፡አዲስ ቋንቋ፣ ባህል፣ ሃይማኖት፣ ርእዮተ ዓለም፣ቴክኖሎጂ፣
ቀመር ወዘተ የምትማረው ታድያ ስሜት እንዲሰጡህ አእምሮህ መቃኘት ስላለበት ነው፡፡
ለዚህም ነው ማንም ለማስደሰትም ሆነ ለማበሳጨት ብዬ የማልፅፈው፡፡የምፅፈው ሐሳቤን ለመግለፅ
ብቻ ነው ያልኩበት ምክንያትም እነዚህና መሰል ቅኝቶች የተለያየ ትርጉም እንዳላቸው ስለማውቅ ነው፡፡በመሰረቱ ግን አንድ ሰው የሚደሰተውም
ሆነ የሚበሳጨው በአስተሳሰቡ ብቻ እንጂ በሌላ ምክንያት አይደለም፡፡በዛፍ ላይ ተንጠልጥሎ የሚኖር ሰው ዛፉ በተንቀሳቀሰ ቁጥር መረበሹ
አይቀሬ ነው፡፡ደስታውም ሆነ ብስጭቱ የሚቀኘው በአየር ፀባዩ ይሆናል፡፡ንፋሱ ሲበረታ ብስጭቱም ይበረታል፣ ንፋሱ ሲረግብ ደሞ ረገብ
ይላል፡፡ዝሮ ዝሮ ግን ኑሮውና ስሜቱ ሁሌም በጊዝያዊ ብስጭትና ደስታ መካከል ዥዋ ዥዌ እያለ ነው የሚኖረው፡፡
መድሐኒቱ ደሞ ከተንጠላጠለበት ዛፍ ወርዶ ርሱን ችሎ መቆም ብቻ ነው፡፡ራሱን ችሎ ለመቆም የበቃ
ሰው ግራም ነፈሰ ቀኝ አይገደውም፡፡ምክንያቱም መሰረቱ ዛፍ ወይም ሌላ ነገር አይደለምና፡፡የሚበሳጨውም ሆነ የሚደሰትበት ምክንያት
አለው፡፡ምክንያቶቹ ደሞ ከውስጣዊ ማንነቱ እንጂ ውጫዊ ከሆኑ ነገሮች አይመነጩም፡፡አህዮች ሲያናፉም ሆነ ሲራገጡ አይቶ አይበሳጭም፡፡አሳሞቹ
ብዙ ሲበሉ አይቶም አይበሳጭም፡፡በጎቹ ዝም ስላሉም አይበሳጭም፡፡ምክንያቱም አህዮቹ ቢያናፉም ባያናፉም፣ ቢራገጡም ባይራገጡም፤ አሳሞቹ
ቢበሉም ባይበሉም፣ በጎቹ ባዓዕ ቢሉም ባይሉም ጉዳዩ አይደለም፡፡
ሁለመናው የተቃኘው የእኔ ብሎ በተቀበላቸው፣ከሰብአዊ ምርሆቹና እሴቶቹ ጋራ ቁርኝት ባላቸው
ነገሮች ብቻ ነው፡፡እነ እንትና ምንም ይሁኑ ምን፣ ከይትም ይምጡ፣ ወዴትም ይህዱ ስሜት አይሰጡትም፡፡
ለማጠቃለል ያህል፣ አንድ ፅሑፍ ከፍም አለ ዝቅ፣ አጠረም ረዘመ፣ስሜትህ ቢነካውም ባይነካውም
ትርጉሙ ከውስጥህ ፈለገው እንጂ ከፃሐፊው ጋር አታገናኘው፡፡ዘፈንም ሆነ ባዶ ጭሆት በሰማህ ቁጥር አትረበሽ፣ አትበሳጭ፡፡ዘፈነም
ጨሆ፣ ፃፈም አነበበ፣ መጣም ሄደ አንተን እያሰበ አይደለም የሚያከናውናቸው፡፡ስሜቱ ፈንቅሎት ነው፡፡አንተ በልተህ ጠጥተህ ፍኛህ
ሲወጠር ወደ ሽንት ቤት አንደምትሮጠው ሁሉ ሌላውም አንብቦና አስቦ ዝም ማለት ሲያቅተው እንደአቅምቴ መፃፍ ይሞክራል፤ ስሜቱን ለመግለፅና
ለመተንፈስ፡፡አንተ
ትርጉም ካላበጀህላቸው ትርጉም የላቸውምና፡፡
No comments:
Post a Comment