Wednesday, September 10, 2014
‹‹ወይ ዘንድሮ…ወይ ዘንድሮ…ወይ ዝንድሮ…››አለ ያለው እፍሬም ታምሩ
ዓምና እንደዛሬው ማታ ስለ አብርሃ ደስታ እየፃፍኩ ነበር፡፡ ዓረና ትግራይ በጳጉሜ ሁለትና ሶስት 2005 ዓ.ም ባካሄደው
ሶስተኛው ድርጅታዊ ጉባኤ አብርሃ ደስታን የድርጅቱ ማእከላዊ ኮሚቴና የስራ አስፈፃሚ አባል አድርጎ መርጦት ነበር፡፡
ያንኑ ክስተት ተንተርሼ ነበር ‹‹አብርሃ ደስታ በከፍተኛ ሹመት ወደ አዲሱ ዓመት›› በማለት የፖለቲካ
ፓርቲ አባል መሆኑን የተቃወምኩት፡፡አብርሃ ደስታ የማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባል እንዲሆን አልፈልግም ነበር፡፡ከዩኒቨርሲቲ
አስተማሪነቱ ጎን ለጎን የሃገራችን ባህላዊ፣ማህበራዊ፣ ኢኮነሚያዊና ፖለቲካዊ ህፀፆችን በጥናት እያስደገፈ የሚተች ታላቅና
ገለልተኛ ምሁር እንዲሆን ነበር ምኞቴ፡፡
እንደ እኔ ምኞት
ቢሆን አብርሃ እንደነ ሶቅራጠርስ፣ዲዮጋን፣ ናኦም ቾምስኪ ወዘተ. የአደባባይ ምሁርና ተቺ (public discourse and
social critic) እንዲሆን ነበር፡፡ አልሆነም፡፡ ይልቁንስ የዓረና ከፍተኛ አመራር በመሆን ከሃገራችን ፖለቲከኞች አንዱ ለመሆን
መረጠ፡፡አሁን ግን በማእከላዊ እስር ቤት እየማቀቀ ይገኛል፡፡በእርግጥ በሰባሰበቡ እስር ቤት እየማቀቁ ያሉ ኢትዮጵያውያን
ወጣቶች ብዙ ናቸው፡፡የአብርሃ ደስታን ያህል ግን የተቸሁት የለም፡፡በመሆኑም አሁን ያለው ሁኔታ በእጅጉ ስሜቴን ነክቶታል፡፡
ተጨማሪ መረጃ ለማሰባሰብና
የሰበሰብናቸው መረጃዎች ለማስተርጎም ተጨማሪ 28 ቀናት ይሰጠን እየተባለ የሰቀቀን ቀናቱን በየወሩ በ28 ቀናት እየተራዘሙ ይገኛሉ፡፡ይገርማል፣
የኢትዮጵያ አብዮቶች መቼ ይሆን ወላፈናቸው ዜጎችን መለብለቡን አቁሞ በድህነት፣ኋላ ቅርነት፣ በሙስና፣ በመልካም አስተዳደር
እጦት፣በአጠቃላይ በፀረ ዲሞክራሲያዊ አሰራሮች ላይ መዝመት የሚጀምረው?መቼ ይሆን የሃገራችን ፖለቲካ ነፍሰገዳይ ኮረንቲ መሆኑን
አብቅቶ ጨለማና ድህነትን የሚያጠፋ ሃይል የሚሆነው?
ሳስበው የሃገራችን ፈርጀ
ብዙ ችግሮች ምንጭ ፖለቲካችን ሳይሆን አይቀርም፡፡‹‹ቁጥር አንድ ጠላታችን ድህነት ነው›› እንላለን እንጂ የድህነታችን ምንጭ
የሆነው ፖለቲካችን ግን አውቀንም ይሁን ሳናውቅ መፍትሔ ስናስብለትም ሆነ ስንፈልለት አይታይም፡፡የፖለቲካችን እንካስ ላንትያ
መነሻና መድረሻው ተለይቶ እስካልታወቀ ድረስ መሔድ መመለሳችን፣ መውደቅ መነሳታችን መቋረጫ የሌለው ዥዋዥዌ መሆኑን የሚያበቃ
አይመስልም፡፡
ለማንኛውም የአጥፍቶ
መጥፋቱ የጥላቻ ፖለቲካችን አብቅቶ ምክንያታዊነትና የህዝቡ ሉዓላዊነት የሚነግሱበት ዘመን ያድርግልን፡፡
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment