Sunday, September 14, 2014

በጋምቤላ ክልል የሚገኙ የትግራይና የወሎ ተወላጆች ማረፍያ ያጣች ወፍ ሁኗል




ግፉ ለዘመናት ሲንከባለል የመጣ ነው፡፡ በ1977 ዓ.ም ትግራይና ወሎ በድርቅ ተመትተው የሚላስ የሚቀመስ ጠፋ፡፡ መቐለና ደሴ ይቆጣጠር የበረው አምባገነናዊው የደርግ መንግስት ከዓለም አቀፍ ለጋሾች ያገኘው እርዳታ በአብዛኛው ለጦር መግዣ ብያደርገውም የተወሰነውን በከተሞቹ ለተሰበሰበው ህዝብ ያከፋፍል ነበር፡፡ ይህ ተግባር በጠኔ ለሚሰቃየው ህዝብ መልካም ዜና ነበር፡፡ በመሆኑም ከተለያዩ የገጠራማው አከባቢዎች የተመመው ህዝብ ከተሞቹን ማጥለቅለቅ ጀመረ፡፡

የደርግ መንግስት ግን የሚበላ መስጠቱን ትቶ እንደ ደሮ እያነቀ ወደ ጋምቤላ ጫካዎች ይወረውራቸው ገባ፡፡ጋምቤላ ክልል ለም ቢሆንም በጣም ሙቀታማ ስለሆነና በጫካዎቹ የሰፈረው ህዝብ ህክምና ሰለማያገኝ በወባና ተዛማጅ በሽታዎች ረገፈ፡፡አይቶትም ሆነ ሰምቶት በማያውቀው አከባቢ በግዳጅ የሰፈረው ህዝብ አከባቢውን ለመላመድ ብዙ መስዋእትነት ከፍሏል፡፡እንደገና ጎጆ መቀለስና ኑሮውን ማስተካከል ነበረበት፡፡

ያ ሁሉ ችግር አሳልፎ ለዛሬ የበቃ፡፡ሆኖም ግን ከ26 ዓመታት በኋላ ‹‹በእድ ነህና አከባቢያችንን ለቀህ ሂድ›› እየተባለ ይገኛል፡፡‹‹ፈሪሖምያ ናብ ኦም ይድይቡ እሞ ነብሪ ይፅንሖም›› ነው ነገሩ…‹‹ፍርቶ ዛፍላይ ቢወጣ በዛፉ ላይ ነብር ጠበቀው›› እንደ ማለት ነው፡፡የትግራይና የወሎ ህዝብ ተፈጥሮ ጨክናበት፣ የሚላስና የሚቀመስ አጥቶ በርሃብ እንዳይሞት ፈርቶ ነበር ደርግ ወደ ሚቆጣጠራቸው ከተሞች የገባው፡፡ ደርግ ሆየ እንደ ጫጩት እያፈነ ወደ ጋምቤላ ጫካዎች ጣላቸው፡፡ዛሬ ደሞ የጋምቤላ ተወላጆች ‹‹አከባቢያችን ለቃችሁ ካልወጣችሁ ሞት ይገባቹኋል›› ብለው በነፍጥና በገጀራ እየገደሏቸው ይገኛሉ፡፡

መገዳደሉ ከተጀመረ ቆይቷል፡፡የአከባቢው ተወላጆች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሰፋሪዎቹን(የትግራይና የወሎ ተወላጆች) መግደል ስራየ ብለው ከተያያዙት ብዙ ዓመታት ተቆጠሯል፡፡ለአከባቢው ባለስልጣናት አቤት ብለው ሰሜ ጀሮ እንዳላገኙ ነው የሚናገሩት፡፡ትእግስታቸው ተሟጥጦ ያለቀው ሰፋሪዎችም አልፎ አልፎ ደም መመለስ መጀመራቸው ይነገራል፡፡ይህን መሳይ ድርጊቶች ሲፈፀሙ የአከባቢው ታጣቂዎች፣ ፖሊሶችና ባለስልጣናት ‹‹እናንተ ወፍ ዘራሾች ደሞ በሃገራችን ሰፍራችሁ መግደል አማራችሁ?›› እያሉ ፋዳቸውን ያበዙባቸዋል፡፡

የአሁኑ ግጭት የተነሳው ግን መዠንግሮቹ ባለፈው ሳምንት(ሮብ ማታ) እንዲት እርጉዝ ሴት ቤት ዘግተው በማቃጠላቸው መሆኑን ይነገራል፡፡ይህንን ግፍ ይዘው ለአከባቢው ሐላፊዎች አብየት ለማለት የሄዱት ሰፋሪዎች ‹‹በጥባጦቹ እናንተው ናችሁ›› ተብለው ሲታሰሩ ነበር ቁጣቸው የገነፈለው፡፡ የእንቁጣጣሽ በዓል ለእነሱ በዓል አልነበረም…ቅልጥ ያለ ጦርነት እንጂ፡፡ከ10 በላይ ቀበሌዎች የተሰባሰቡ ህፃናት፣ሴቶችና ሽማግሌዎች ቴፒ ከሰፈሩ ብዙ ቀናት አስቆጥሯል፡፡ቴፒ በሚገኙ አብያተ ክርስትያናት፣ትምህርት ቤቶች እንዲሁም በአየር ማረፍያው ሜዳ ላይ ሆጭ ብለው ይገኛሉ፡፡ምግብ የለም መጠለያ የለም!

ትናንት ማታ ፌደራል ፖሊስና መከላከያ ወደ አከባቢው በመድረሳቸው ከቀያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ወደየመጡበት መመለስ ጀምረው ነበር፡፡ጦርነቱ እንደገና በማገርሸቱ ግን ወደ ቴፒ ተመልሷል፡፡በቅርቡ አንድ ትራፊክ ፖሊስና የፍርድ ቤት ሐላፊ ተገድሏል፡፡ገዳዮቹ የክልሉ መንግስት ያስታጠቃቸው ፖሊሶች እንደሆኑ ነው የሚነገረው፡፡

በስልክ ያነጋገርኳቸው የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ አስተማሪዎች የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ለእረፍት ወደየ አከባቢያቸው ባይበተኑ ኑሮ ግርግሩ ይባባስ እንደነበር ገልፀውልኛል፡፡ሆኖም ግን የመገናኛ ብዙሃን ሽፋን ማግኘት ይችል ነበር ባይ ናቸው፡፡


ከቴፒ አየር ሜዳ ደውየ ያነጋገርኳቸው ወገኖች የመከላከያ ሰራዊት አባላት‹‹አይዟችሁ፣ አሁን ይረጋጋል፣ወደየቤታችሁ ትመለሳላችሁ›› እያሉ ሊያረጋጉን ቢሞክሩም ቁጥራቸው በጣም አናሳ በመሆኑ ግጭቱ ሊያረጋጉት እንዳልቻሉ ነግረውኛል፡፡በተለይ የክልሉ ፕረዚዳንትና የፌደራል ፖሊስ ሐላፊዎች ወደ አከባቢው መጥተው የነበረ ቢሆንም ለችግሩ መፍትሔ ሳያበጁለት መመለሳቸው እንዳበሳጫቸው ነው የገለፁልኝ፡፡

No comments:

Post a Comment