ጥሎበት አምሽቶ ቤት መግባት አይወድም፤ከአቅሙ በላይ የሆነ አስገዳጅ ነገር ካልገጠመው በስተቀር፡፡ድሮ
የአንደኛ ደረጃ ተማሪ እያለ በትምህርትቤታቸው መግቢያ በር ላይ ተሰቅሎ የነበረው ‹‹ማርፈድ የስንፍና ምልክት ነው!››የሚል ማስታወቂያ
ዛሬም አይረሳውም፡፡ሁልጊዜ ያነበው ነበር፤ነገር ግን አንዴ እንኳን አርፍዶ ያልተቀጣበት ቀን ትዝ አይለውም፡፡ስለሆነም የመጀመርያ
ክፍለ ጊዜ ተከታትሎ አያውቅም፡፡
ነገር ግን በስንፍናው አልነበረም፤ በርቀት ምክንያት እንጂ፡፡ተከራይቶ እንዳይኖር ለቤት ክራይና ለምግብ
የሚከፍልለት ወገን ዘመድ አልነበረውም፡፡ስለሆነም ሁል ጊዜ ጧት ጧት 20 ኪሎ ሚትሮች ርቀት አቋርጦ በመጓዝ ነበር የሚማረው፤እንደ
አበበ ቢቄላ በባዶ እግሩ፡፡ከለሊቱ አስራ እንድ ሰዓት ተነስቶ በዚያ ጥርሶቹን ያገጠጠ ድንጋያማ መንገድ ወደ ትምህርት ቤት ሲጣደፍ
የእግሮቹ ጥፍሮች እንዳለ በእንቅፋት ተነቃቅሏል፡፡
ላቀው፣በጣም ረዠምና ቀጭን ስለነበረ የክፍል ጓደኞቹ ‹ቀጭኔ› እያሉ ነበር የሚጠሩት፡፡ነገር ግን በትምህርቱ
ጎበዝ ነበር፤ የክፍሉ አንድ ተማሪ ብቻ ነበር የሚበልጠው፡፡‹‹ማርፈድ የስንፍና ምልክት ነው!››የሚሉት ፈሊጥ ውድቅ መሆኑን የተረጋገጠው
በላቀው ነበር፡፡ዛሬ ያች ማስታወቂያ አብራው አድጋ አዲሰ አበባ ድረስ ተከተለችውና ንሮውን ‹‹ማምሸት የስንፍና ምልክት ነው››በሚል
አባባል ንዲመራ አድርጋዋለች፡፡
አዲስ አበባ የከተመው በስራ ምክንያት ነው፤ በአንድ ትልቅ የሚባል የመንግሰት መስራቤት የተቀጠረው
ልክ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቆ እንደወጣ ነበር፡፡በዚሁ መስራቤት ለአስር ዓመታት በቅንነት አግልግሏል፤‹‹አገሬ ምን አደረገችልን ሳይሆን
ለሃገሬ ምን ሰራሁ? ማለት አለብን››የሚለው አባባል ከአፉ አይለይም…ክክፍል ባለደረቦቹ ጋር ሲወያይና በትላልቅ ስብሰባዎች
የመገኘት ዕድል ሲያጋጥመው፡፡ነገር ግን አድማጭ አላገኘም፡፡ይባስ ብሎ እሱ መናገር ሲጀምር አለቆቹና አንድ አንድ በለደረቦቹ የሚናገረውን
ፈሬ ሐሳብ ሳያዳምጡና ሳይረዱ ይስቃሉ፡፡‹‹ላቀው እኮ ወንፊት ነው፤የሚያውቀውና የተሰማውን ወደኋላ ሳይል እነደ ሰካራም ይዘረግፋል፡፡ልክ
እንደ ሕፃን ልጅ ያየውንና የሰማውን ይናገራል፤ምንም ሳይጨምርና ሳይቀንስ…‹እንደ ወረደ!›፡፡ምስጢርና ምስጢረኞችን አጥብቆ ይፀየፋል፡፡››እያሉ የሚያሙት
ብዙ ናቸው፡፡
እሱም ቢሆን ይህን አቋሙን አይክድም፡፡አንድ ቀን ስለ ምስጢርና ምስጢረኞች የነገር መቼም አልረሳውም፡፡
‹‹ምስጢር››አለ ላቀው ዓይኖቹን ወደ ሩቅ ልኮ ፂሙን እያፍተለተለ‹‹ የእውነትና ግልፅነት ምቀኛ ናት፤ፀረ ፍቅርና ሰላም፣ የተንኮል፣የብልጣ
ብልጥነት፣የግለኝነት፣የክፋትና የሴራ ምሽግ ነች፡፡ምስጢር የገሃነም ተምሳሌት ናት፤ እውነት በእግረ ሙቅ ታስራ በማይቅህም እሳት
እየተቀቀለች እንድትኖር የተፈረደባት እስርቤት፡፡ዳኞቹ ምስጢረኞች ናቸው፤ ለጉቦ የሚፈርዱ ፍርደ ገምድሎች፡፡ህሊናቸው የታወረ፣ስጋቸው
እንዳሻት የምታሽክራቸው ተንቀሳቃሽ በድኖች፡፡››ትኩር ብሎ ሲመለከተኝ ዓይኖቼ ተርገበገቡ፤የዓየኖቹ ጨረሮች እንደ ኤክስ ሬይ መላአካላቴን
ገልበው ውስጠ ምስጢሬን የሚያብጠረጥሩ ይመስላሉ፡፡
ዓይኖቼን ከእይታው እያሸሸሁ ‹‹ምስጢር የታማኝነት መግለጫ ሊሆን አይችልም እያልከኝ ነው?››ስል ጠየቅኩት፡፡
‹‹በጭራሽ!››አለኝ ፈርጠም ብሎ ራሱን ግራና ቀኝ እያወዛወዘ‹‹ሰዎች ምስጢር የሚጠብቁት ስለሚፈሩ ብቻ ነው፡፡እንድም የቆሸሸ ማንነታቸውን
ለመደበቅ አልያም የምስጢረኞች ጥብቅ ማስጠንቀቅያ ሽባ ስላደረጋቸው፡፡የፖለቲካ መሪዎች፣ሃይማኖታዊ ድርጅቶችና ምስጢራዊ ማህበረሰቦች
ንሯቸው በተንኮልና በምስጢሮች የተሸበበ ነው፡፡ቀጣይነታቸውን የሚፈታተን ምስጢር የሚያውቅ መንኛውም ሰው…ምስጢር ያደርጉታል፡፡ምስጢር
ለመጠበቅ የእውነት ትንሳኤ አልባ ሞት የግድ ነው፡፡እውነት እንደ እየሱስ ክርስቶስ መቃብሯን ፈንቅላ ብድግ ያለች ጊዜ ምስጢር እንደ
ጉም ትበንና ምስጢረኞች እንደ አዳምና ሄዋን ራቆታቸውን ጫካ ለጫካ ይሽሎከሎካሉ፡፡ከምድረ ገነት ወደ ምድረ ፍዳ ይባረራሉ፤ዳግም
ለይመለሱ!››እንዲህ ብሎ ለመሄድ እየተነሳ ‹‹በአጠቃላይ›› አለና ‹‹ምስጢር ብርጋሃን ትሸሻለች ፣ጨለማን ትሻለች፤እውነት ግን
እንደ ዓብዪ ፆም ፀሐይ ጥርት ባለ ሰማይ ሞቃና ደምቃ ለመታየት ትኳትናለች፡፡›› ብሎ ቻው ሳይለኝ እብስ፡፡
የቅርብ ጓደኞቹ ‹‹ላቀው፣ የምትለው ሁሉ እውነት ነው፤ነገር ግን ይህ ድርጅት በፖለቲከኞች የሚመራ
በመሆኑ ሰሚ አታገኝም፡፡እንደውም ጥርስ ውስጥ እንድትገባ እያደረገህ መሆኑን አውቀህ እንደ ወገኖችህ ለመሆን ሞክር፤ ‹በሮም ውስጥ
ስትኖር ሮማውያንን ምሰል›የሚባለው አባባል ብታምንም ባታምንም ለመኖር ስትል ብቻ ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅብሃል፡፡ከማንኛውም የስልጠና
ዕድሎች እነደ እንክርዳድ እየለዩ የሚያስቀሩህ ለምን ይመስልሃል? ካንተ እኩል የተቀጠሩት ባለደረቦችህ አሁን የት ናቸው?ብያንስ በንዱ
የስራ ክፍል ስራስኪያጆች ሁነው ተሽሟል፤የኦፊሰርነት መዓርግ የተሰጣቸውም ብዙ ናቸው፡፡›› እያሉ ሊመክሩት ቢሞክሩም አይቀበላቸውም፤‹‹እውነቱን
ተናግሮ በመሸብኝ ባደር ይሻለኛል፡፡ንፁህ ህሊና ምቹ ትራስ መሆኗን አታውቁም?››በማለት ይሞግታቿል፡፡
‹‹እኔ
ማዝነው ከስልጠናዎች መቅረቴና ስልጣን ባለማግኘቴ አይደለም፡፡የስራ ባለደረቦቼ እኔን ቀድመው የስልጠና ዕድል በማግኘታቸው ደስተኛ
ነኝ፤ድርጅታችን እንዲያድግ በእውቀታቸው ይረዳሉና፡፡በለስልጣኖች መሆናቸውም አያስከፋኝም፤ስልጣናቸው ድርጅታችን ለመለወጥ የሚያውሉት
እስከሆነ ድረስ፡፡እንደ መሰላል ለወገኖቼ መወጣጫ መሆኔን ኩራትና ብርታት ይሰማኛል፤ካለኔና መሰሎቼ እርዳታ በስተቀር አሁን የደረሱበት
ደረጃ አይደርሱም ነበርና፡፡ሳይማር ላስተማረን ወገችን ብድር መክፈል አለብን፡፡እኛ በሰላም ወጥተን የምንገባው እኮ በመቶ ሺዎች
የሚቆጠሩ ወገኖች ደማቸው እንደ ጅረት ፈሷል፣አጥንታቸው ተከስክሷል፣መተክያ የለላት ህይወታቸውን ከፍሏል፡፡ታድያ እኔ የወገኖቼ የመወጣጫ
መሰላል፣የመሸጋገርያ ድሊ ሁኜ ባገለግል ምኑን ይደንቃል?››እያለ ሊያስረዳቸው ሲሞክር አንድ ባንድ ውልቅ ይላሉ፡፡
ላቀው
የመፅሐፍ ቅድሱ እዮብ አይደለም፤ትዕግስቱ ተሟጦ አልቋል፡፡ተስፋ መቁረጥ የጀመረው ያ ስመ ገናናና አንጋፋ ድርጅት ጭንቅላታቸው እንደ
ራስ ቅላቸው መላጣ በሆኑ ፖለቲከኞች እየታመሰ ‹‹አድሮ ቃርያ›› ሁኖ በመቅረቱ ነበር፡፡እነዚያ ብቻዋ እንደ በቀለች ሸምበቆ ላይ
ደርሰው አንገታቸውን በማጠፍ ራሳቸው መሬት ሊነካ ትንሽ የቀረው የድሮ ባለደረቦቹ ከወንምበር ማሞቅና ማጨብጨብ በስተቀር ለድርጅቱ
ምንም አልፈየዱም፡፡ብዙ በለውለታ ሰራተኞች በገፍ ተባሯል፡፡የገቢው ብቸኛ ምንጭ የሆኑ ደመበኞቹ በአገልግሎት ማርካት ከተሳነው ዓመታት
ተቆጥሯል፡፡የሚያውቁት ሁሉ ከድርጅቱ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለማማከር ወደ ርሱ በመሄድ ሮሮ ያሰማሉ፤አንዳንዶቹም የችግሮቹ እናንተ
ናችሁ በማለት ጣታቸውን የቀስሩበታል፡፡እነዚህ ነገሮች ናቸው በቁጭት እርር ድብን እንዲል የሚያደርጉት፡፡
ሳይታወቀው
ለሰዎች ያነበረው ርህራሄና ቅን አሳቢነቱ በጭፍን ጥላቻና በቀል እየተበረዘ መጣ፡፡የስራ ሰዓት አያከብርም፤አራት ሰዓት ቢሮ ይገባል፣
አስር ሰዓት ይወጣል፡፡አንዳንዴም ጭራሽ በስራው አይገኝም፡፡በፌስቡክና ሌሎች ማህበራዊ ድረገፆች ብሶቱን መተንፈስ ጀምሯል፤ ብያንስ
በቀን ሶስት ጊዜ ዘረኝነትና ፅንፈኛ የሆኑ የፖለቲካ ፅሑፍ ያሰራጫል፡፡እንዲያ ሲያደርግ ደስ ይለዋል፤ይነፍስለታል፡፡‹‹በቅንነት
መናገር እንደሞኝነት ከተወሰደ የልብን በልበ ወለድ ፅሑፎችን መተንፈስ ሌላው መፍትሔ ነው›› በሚል አዲስ አባባል ራሱን እየመራ
ይገኛል፡፡
ገና ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ነበር፤ሁሌም ወደ ቤቱ የሚገባበት ጊዜ ነው፡፡በሰፈራቸው መብራት ስላልነበረ
ግን የአላፊ አግዳሚው ቁጥር በጣም ስለቀነሰ ከለሊቱ ስድሰት ሰዓት አስመሰሎታል፡፡መብራት ሲጠፋና አከባቢው ጭር ሲል ስሜቱ ይረበሻል፤በሬድዮ
ጣብያዎች፣በጋዜጦችና መፂሔቶች የሚሰራጩ የማጅራት መቺዎች አሰቃቂ ድብደባዎችና ግድያዎች ርብትብት ድርገውታል፡፡ራሱን በተኩላዎች
እንደ ተከበበች በግ ይቆጥራል፡፡ አሁንም አሁንም አንገቱን ወደ ኋላ እያዞረ ይመለከታል፤ የተንሸዋረሩ ዓይኖቹን ገራና ቀኝ እየገላመጠ
የእርምጃ ፍጥነቱን በመጨመር ወደ ቤቱ ይንደፋደፋል፡፡ፍርሃት አመሉ
ከሆነ ብዙ ጊዜው ቢሆንም እንደ ዛሬ ግን ተጫጭኖት አያውቅም፡፡መላ አካሉ ፈርሐት ይወረዋል፤ቀዝቃዛ ላብ በጀርባው ይንቆረቆራል፡፡ትርታ
ልቡ ድው ድው ሲል የባሰውን ይቅበጠበጣል፤ትንፋሹ ይቆራረጣል፡፡አካሄዱ ሰርቆ ለማምለጥ የሚሞክር ሌባ ያስመስልበታል፡፡
ድንገት ‹ቁም!›የሚል ጎርነን ያለድምፅ ሰማና በድን
ሆነ፡፡መላ አካላቱ ይበልጥ ተንዘፈዘፈ፡፡ሽንቱን መቆጣጠር ተስኖታል፤ያ ሲያንቆረቁረው ያመሸው ድራፍት በሁለት እግሮቹ ቦይ ሰርቶ
እንደ ጎርፍ ይወርዳል፡፡ያ በፌስ ቡክ ሰለፃፈቻው ዘረኛ የስድብ ቃላት የተሰጠው የማስፈራርያ መልእክት ትዝ አለው፡፡‹‹ማንነትክን
ደረሼበታለሁ ማታ እንገናኝ!›› ነበር የሚለው መልዕክቱ፡፡ከአሁን በፊትም ብዙ የፅሑፍ ማስፈራርያዎች ደርሰውት ያውቃሉ፡፡‹‹ቀይ
መስመር እየዘለልክ ነው፤ብትተው ይሻልሃል፡፡ከልሆነ ግን ከማሕበራዊ ድረ ገፆች ሳይሆን ከምደረ ገፅም ጭምር እሰውርሃለሁ… ፡፡››ሚሉና
ሌሎች ዛቻዎች፡፡ነገር ግን ይጠነቀቃል እንጂ እንደ ዛሬው ፍርሃት ተሰምቶት አያውቀም፡፡
በፌስቡክና በሌሎች ማህበራዊ ደረ ገፆች የሚፅፋቸው ነገሮች አንዱን ብሔር ጥላሸት ይቀባሉ፤የገሃንም
ተምሳሌት በማድረግ ያትታሉ፡፡በዛች ብሔር የሚኖሩ ወገኖች በሙሉ ካሐዲዎች፣የባንዳ ዝርያዎች፣ተምረው የማይገባቸው፣በተንኮልና ሰይጣናዊ
ስሶች የተለከፉ፣መልከ ጥፉ ምግባረ ክፉ፣ውሸታሞች፣ለማኞች፣እከካሞች፣ስደተኞች፣ሙሰኞች፣ባዕዳዊ ገዢዎች መሆናቸውን ይፅፋል፡፡በአከባቢያቸው
ከድንጋይ በቀር ሌላ ነገር እንደማይገኝ በማስረገጥ ያትታል፡፡ስለሆነም በሌሎች ኢትዮጵያውን ትክሻ ተንጠልጥለው የሚኖሩ ጥገኞች ናቸው
እያለ ይለፍፋል፡፡የገዠው ፓርቲ አገዛዝ ከናዚዝምና አፓረታይድ ጋር የከፋ አምባገነን ነው እያለ ይደሰኩራል፡፡
እሱ በተወለደበት ብሔር ግን እንከን አይገኝም፡፡አከባቢው ማርና ወተት የፈስበታል፡፡ሁሌም ጥጋብ ነው፤ከረምትና
በጋ ሳይለይ፡፡ሁሉም መልከ ቀና፣አመለ ሸጋ፣ታታሪ ሰራተኞች፣የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች፣የተማሩ የተመራመሩ ሊህቃን ናቸው፡፡በአጠቃላይ
የኢትዮጵያ ድህነት፣ኋላ ቀርነትና ድንቁርና እርሱ የተወለደበት ብሔር እንደማይወክል አስመስሎ ይፅፋል፡፡የኔ ናት የሚላት ብሔር እከክ
አያሳክካትም፣ቋቁቻ አይታይባትም፡፡ምድረ ገነት ስለሆነች ኗሪዎቿ አይሰደዱም፤እነዚያ አሜሪካና አውሮፓ እየኖሩ ራሳቸውን የአራት ኪሎ
ቤተመንግስት ህጋዊ ነገስታት አድርገው የሚያስቡት ጌቶቹ በፖለቲካ መክንያት እንጂ እንጀራ ፍለጋ አልተሰደዱም፡፡እንጀራ ቢጠፋም እነዚያ
የባንዳ ብሔር ኗሪዎች ስለዘረፉት ነው እንጂ እጥረት ስላለ አይደለም፡፡በርሱ ብሔር መጥፎ ብሎ ነገር አይታሰብም፤በጭራሽ!!!
ይህ ሁሉ ሲያደርግ እውነተኛ ስሙ ተጠቅሞ አያውቅም፡፡ድሮ ኢትዮጵያን እንደ ሻማ አቅልጠው እንደ ብረት
ቀጥቅጠው የገዙ ነገስታት ስም ይጠቀማል፤ የኢንተርኔት ካፌዎች እያቀያየረ በማሕበራዊ ድረ ገፆች ጥላቻና በቀል ይዘራል፡፡እስካሁን
ድረስ በሶስት የፌስ ቡክ አንጋፋ ዘመቻዎች ላይ በግንባር ቀደምነት ተሰልፎ ተሳትፏል፡-‹‹ድምፃችን ይከበር!››፣‹‹በቃ!›› እና
‹‹ድምፃችን ይሰማ!››፡፡በዚህ የጀግንነት ተግባሩ በውጭ ሃገራት የሚኖሩ ፅንፈኛ ፖለቲከኞች በሺዎች የሚቆጠር ዶላር አሳቅፈውታል፤የመንግስት
ድህንነቶች የሚደርሱበት ከሆነም ወደ አሜሪካ እንደሚያሻግሩት ቃል ገብተውለታል፡፡ ነገር ግን እስካሁን ድረስ ማንነቱን አልተነቃበትም
ነበር፡፡
ዛሬ ግን ጉዱ ሳይፈላ አልቀረም፡፡ሁለት ማንነታቸው የማይታወቅ ኮፍያ ያለው ጥቁር ሹራብ ከጥቁር መነፅር
ጋር ያደረጉ ሰዎች ግራና ቀኝ እያላጉ ገሃነም ወደ ሚምስል በድቅድቅ ጨለማ የተወረረ ስፍራ ወሰዱትና‹‹ይህን ሁሉ የበሬ ወለደ ውንጀላ
እንድትፅፍ ያዘዘህ ማን እንደሆነ ሳትደብቅ ተናግረህ፣ ለወደፊት ምንም ነገር ላለመፈፀም ቃል ካልገባህ ዛሬ የመጨረሻህ ልትሆን ትችላለች!››አለው
ያ ቅድም ቀልቡን የገፈፈው አውሬ መሳይ ሰውየ፡፡
‹‹የ…የምትለው አልገባኝም…እ…እኔ …›› አላስጨረሰውም፡፡ በያዘው ዱላ ወገቡ ላይ ሙሉ በሙሉ አሳረፈበት፤ህመሙ
አጥንቱ ድረስ ዘልቆ ስለተሰማው መጮህ አልቻልም፡፡‹‹እውነቱን መናገር ይሻልሃል አንተ ፓሮት! አለዚያ… ››አለ የያዘው ዱላ እፊቱ
ላይ እያወዛወዘ፡፡‹‹እ…እኔ ምንም ጥፋት አልሰራሁም…ሰ…ላ…ማዊ ዜጋ…›› አሁንም ሳያስጨርሰው ከቅድሙ በእጥፍ በሚበልጥ ጉልበት
ጀርባው ላይ ዠለጠው፡፡መቆም አልቻለም፤ወለሉ ላይ ተንበርክኮ የተመታበት አካሉ አያሽ ፊት ለፊቱ
ወደ ተገተረው መልአከ ሞት በተማፅኖ ይመለከታል፡፡‹‹የፈለግከው ማድረግ ትችላለህ፣ እኔ ግን ንፁህ ዜጋ ነኝ!›› አለ ድምፁን ፈርጠም
ለማድረግ እየሞከረ፡፡ነገር ግን ውስጡ በታላቅ ፍርሐት ይናጣል፤ በልቡ‹‹ወይኔ እንደፈከርከው አገኘህኝ ማለት ነው?›› አለ ፡፡
ሰውየው
የታጠፈ ወረቀት ከኪሱ አወጣና ላምባዲና ወደፊቱን ደቅኖ‹‹ይህ ፅሑፍ አንተ ያፃፍከው አይደለም?››በማለት አምባረቀበት፡፡በብርሃኑ ጨረር ዓይኖቹን እያጥበረበረ
‹‹እኔ እንደዚህ ዓይነት ነገር መፃፍ ቀርቶ አስቤም አላውቅም››በማለት የክሕደት ቃሉን ገፋበት፡፡ሰውየው መማታቱን ይቆይልኝ ያለ
ይመስላል፡፡እንደገና እጁን ወደኪሱ ላከና የመካከለኛ አልበም ስፋት ያለው ሙሉ ፎቶ አውጥቶ ‹‹ይህስ አንተ አይደለምህም?›› በማለት በምፀት ጠየቀው፡፡ምንም አልመለሰም፡፡የራሱ
ፎቶ ነበር፤በአንድ የኢንተርነት ካፌ ውስጥ ሁለት እጆቹን በኮምፒተር ኪቦርድ ላይ አድርጎ እየፃፈ መሆኑን ያሳያል፡፡ጊዜው እና ኢንተርነት
ካፌው አስታወሰው፡፡‹‹አለቀልኝ በቃ! አሁንማ በቪዲዮ የተደገፈ ማስረጃ ሳይኖራቸው አይቀርም›› እያለ ውስጥ ውስጡን ይብሰለሰል
ገባ፡፡
‹‹ላንተ
እኮ ነው? ይህ ፎቶ ያንተ
አይደለም?››በማለት ሲጮህበት
መብረቅ እንደመታው ደርቆ ዝም አለ፡፡ከአሁን በኋላ አጉል ድፍረት የትም እንደማያደርሰው ስለተረዳ አንዲት ቃል መተንፈስ አልደፈረም፡፡‹‹በል
እንጂ ተናገር›› በማለት ለሶስተኛ ጊዜ በዱላ ነረተው፡፡አሁን የስቃይ ድምፅ ከማሰማት በስተቀር ምንም አላለም፡፡ይሁን እንጂ አልቻለም፤
‹‹በፈጠረህ!ያጠፋሁት ጥፋት፣የፈፀምኩት ወንጀል ካለ ወደ ህግ ውሰደኝ እንጂ አታሰቃየኝ…››እያለ መቀባጠር ሲጀምር ሰውየው ቀበል
አድርጎ የምፀት ሳቅ እየሳቀ‹‹ህግ ብሎ ነገር የለም በማለት ሽንጥህን ገትረህ ስትከራከር አልነበረም እንዴ? ስለየትኛው ህግ ነው አሁን የምታወራው ባክህ?በናዚዝምና አፓርታይድ ስርዓቶች ህግ የለም በማለት የፃፍከውን
ረሳሀውና ነው?ወይስ እንዚያ ቃል
የገቡልህ አለቆችህ መጥተው ነፃ እስኪያወጡህ ድረስ ጊዜ ለመግዛት ነው?››በማለት በጥያቄዎች መዓት ያጣድፈው ገባ፡፡አሁን ፌስ ቡክ ላይ አይደለም
ያለው፡፡የብልግና፣የዘረኝነትና የጥላቻ ቃላት በመፃፍ መልስ መሰጠት፣የተመቸው<<like>>፣በጣም ያስደሰተው
<<share>>፣እጅግ እስቀያሚ የሆነውን ደግሞ <<delete>> ማድረግ አይችልም፡፡በነዚህ
ቃላት የዱላን አፀፋ መመለስ አይችልም፡፡
ሰውየው‹‹አየህ
እኔ ቃሌን አላጥፍም፤‹ያሉት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ›አይደለም የሚባለው?›› አለና ከጓደኛው ጩቤ ተቀብሎ አፍልቡ ላይ ሲሰካበት እንደ በሬ ‹‹ዓዕ››
ብሎ ሲጮህና ከእንቅልፉ ሲባንን አንድ ሆነ፡፡በህልሙ ይሁን በውኑ እርግጠኛ መሆን አልቻለም፡፡ዓይኖቹን ጨፍኖ እጆቹን ወደ ግድግዳው
ሰዶ ዳበስ ዳበስ በማድረግ የማብርያ ማጥፍያው ሶኬ ተጭኖ መብራህቱን አበራው፡፡የተኛበት አንሶላና የሌሊት ልብሱ በሽንት ተጨማልቋል፡፡ራሱን
ተዘበ፤‹‹ወይኔ ላቀው!ይህ ነው የኔ ወንድነት?ያሁሉ
ፉከራና የአርበኞች ሽለላ ሽንት በሽንት?በእውኔ
የዘራሁት ጭፍን ጥላቻና ዘረኛ መርዝ በሕልሜ ማጨድ ጀምሬለሁ ማለት ነው?ይገርማል!››
ከትከት
ብሎ ሳቀ፡፡የመሕበራዊ ድረገፆች አርበኝነት እስከዚህ ደረስ ብቻ መሆኑን ሲረዳ ራሱን ናቀ፤እነዚያ በአሜሪካና አውሮፓ አህጉሮች ተወሽቀው
የጥላቻ ፖለቲካ የሚያራምዱት አለቆቹም ታዘባቸው፡፡‹‹ለካ በዚህ መክንያት ንሯል የትግል ሜዳቸው በምዕራባውያን አውራጎደናዎች ያደረጉት?ለዚህ ነበር በኔ እግጅ እሳት ለመጨበጥ ወደ ኋላ የማይሉት፡፡አዎ
አነሱና ልጆቻቸው በተንደላቀቀ ንሮ ዓለማቸውን እየቀጩ በኛ በድሆች እጅ የእባብ አንገት ለማነቅ ይወተውታሉ፡፡ፖለቲካኛን ማመን ቀብሮ
ነው፡፡ለነገሩ ፌስቡክ በተፃፈው ፅሑፍ በህልሙ ከግድያ ሙከራ ለትንሽ ያመለጥኩት እኔ ብቻ አይደለሁም፡፡ አበበ ገላውም ለኤፍ.ቢ.አይ
የድረሱልኝ ጭሆቱን አሰምቷል፤እሱስ የመኝታ ክፍሉን ሳያበላሽ ይቀራል?››እያለ በመብሰልሰል ላይ እያለ እንደገና እንቅልፉ የዞት ጭልጥ አለ፤ወደ ሌላ ቅዠት፡፡
የካቲት
16, 2005 ዓ.ም
No comments:
Post a Comment