Tuesday, April 2, 2013

የመጽሐፍ ሻጩ ሙግት





…ማንበብ እወዳለሁ።ከምንም ነገር በላይ ያዝናናኛል፤ነፍሴ ነው።በተለይ የማነበው ነገር ይዘት ከራሴ የህይወት ፍልስፍና ከተገጣጠመ አምብቤ ለመጨረስ የማደርገው ትግል ልዩ ነው።ያኔ የሚኖረኝ ትጋትና ትዕግስት ያስገርመኛል።ምነው በሁሉም ስራዎቼም እንደዚህ ያለ ጉጉትና ጥልቅ ተመስጦ በኖረኝ የሚል ምኞት ይፈጥርብኛል።

በዚህ የተነሳ ለመፅሐፍ  መግዣ የማወጣው ወጪ አያስጨንቀኝም።በጣም የተወራለት ወይም ደስ ያለኝ መጽሐፍ ካገኘሁ ቢወደድም ከመግዛት ወደ ኋላ አልልም።ሳላቅማማ እገዛዋለሁ።በቂ ጊዜ ካገኘሁ እሰዮ ነው ተረጋግቼ አነበዋለሁ።ካልሆነ ግን የእንቅልፍ ሰዓቴም ጭምር እየቀጣሁ እጨርሰዋለሁ።አንዳንዴም ለሌላ ጊዜ ይቀመጣል።ምክንያቱም የገዛሁት መጽሐፍ ሳላነበው እንደማልቀር ከልምድ ተምሬለሁና ነው።

ስለሆነም በአዲስ አበባ ጎደናዎች የእግር ጉዞ ሳደርግ ዓይኖቼ የሚንከራተቱት ከመልከ መልካሞቹ ወጣት ሴቶች ይልቅ በየአስፓልቱ ዳር የተዘረጉት መጻሕፍት ላይ ነው።አንዳንዴ ወጣትነቴ ጥሎኝ የሸሸ መስሎ ይሰማኛል።ነገር ግን ድሮውም ለሴቶች ያን ያህል አልነበርኩም።ማለት ካንቺ ወድያ ዓለም ለምኔ ብሎ እንደመነነው በዛብህና ለሮዛ ሲል ህይወቱን አሳልፎ እንደሰጠው የታይታኒኩ ተዋናይ ዓይነት ስሜት ንሮኝ አያውቅም።

እናም የሰፈረኝ የመጻሕፍት ፍቅር እንደ ለማዳ እንስሳ እየነዳ ወደ አንዱ መጻሕፍት ሻጭ ወስዶ እንደ ሐወልት ገተረኝ።ወጣት ነው፤ በሃያዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኝ ይመስለኛል።ሁል ጊዜ አንድ ዓይነት ነው፤አንድ ዓይነት ልብስ፣አንድ ዓይነት ጫማ፣በጫት የተወጠቀ አንድ ዓይነት ጉንጭ።ልጁ እንደነገረኝ ከሆነ አባቱም ዕደሜ ልካቸው መጽሐፍ ሻጭ ነበሩ ።ብዙ ጊዜ ስለምመላለስ ከልጁ ጋር ተላምደናል።አንብቤ እንደ መልስለት በቀን አንድ ብር ሒሳብ ያከራየኛል።በጣም የምፈልገው መጽሐፍ ሲነረውም እገዛዋለሁ፤በተመጣጣኝ ዋጋ።የዛሬ አመጣጤም አንድም ለመግዛት አልያም ለመከራየት ነበር።ነገር ግን ሳናስበው ቅልጥ ባለ ሙግት ውስጥ ገባን።

እንደ ልማዴ እስኪ ዛሬ ደግሞ አንድ ጥሩ ነው የምትለው መፅሐፍ መርጠህ ስጠኝ አልኩት።
«ይህ መፅሐፍ አንብበኋል?» አለኝ።ራሴን ግራና ቀኝ በማወዛወዝ አለማንበቤን ነበርኩት።
«አንብበው አሪፍ መፅሐፍ ነው።» አለኝ።አንተስ አንብበኋል? ብየ ጠየቅኩት።
«እኔ እኮ መሸጥ እንጂ ማንበብ አልወድም።አባቴ ጎበዝ አንባቢም ሻጭም ስለነበር አንብብ እያለ ይወተውተኝ ነበር።ነገር ግን በማንበብ ሳይሆን በመሸጥ ብቻ ነበር ንሯችን ሲዶጉም የነሮው።»

እና ካባትህ አንተ እንደምትሻል እየነገርከኝ ነው? 

«አይ እንደዛ ለማለት ፈልጌ ሳይሆን።አባቴ አንብቦ ምን አገኘ ነው እምልህ።በእርግጥ በገንዘብ አያያዝ አልደርስበትም፤እሱ ያገኛት ሁሉ ይዞ ወደ ቤት ነበር የሚገባው።ነገር ግን ከጥቂት አሮጌ መፅሐፎች በቀር ያወረሰኝ ነገር የለም።» አለኝ።
አንተስ ለልጅህ ወይም ልጆችህ ምን ለማውረስ ተዘጋጅተሃል? የኔ ጥየቄ ነበር።በመፅሐፍ ሽያጭ ከምያገኘው ገቢ ከጫት መግዣ ተርፎት ምንያህል ማጠራቀም እንደሚችል በአእምሮየ እያሰላሰልኩ።

«ከዚች ያርከበ ሱቅ ተለቅ የለ የመፃሕፍት መሸጫ መደብር እማወርሳቸው ይመስለኛል።ያም ሆነ ይህ ግን አንብቡ እያልኩ አላስቸግራቸውም።»

ለምን? የሚል ጥያቄ አስከተልኩለት።የተለየ ምስጢር ይነገረኛል ብየ ሳይሆን ወሬውን ለማስቀጠል ያህል።

«ምክንያቱም ማንበብ እንድታስብ ይገፋፋል።አስበው ብዙ መፅሐፍ ባነበብክ ቁጥር ብዙ ታስባለህ።ብዙ ማሰብም ጭንቀት ያመጣል።ብዙ መጨነቅ ጀመርክ ማለት ችግር ውስጥ ላይ ነህ ማለት ነው፤ አንድ ቀን ልትነቅል ትችላለህ።በአሁኑ ዘመን ብዙ አሳሳቢ ነገሮች አሉ።እንኳንስ ከልክ በላይ አንብበህ ሳተነብም ልታብድ ትችላለህ።»

ግን ደሞ «ጥሩ ፃሐፊ ለመሆን ጥሩ አንባቢ መሆን የግድ ነው» ይባላል።ለምሳሌ አንተ የምትሸጣቸው መፅሕፍት በሙሉ መስረታቸው ከደራስያን እንጂ ከመፃሕፍት ሻጮች አይደለም።ደራስያኑ ባይፅፉ ንሮ በዚች ክዮስክ ውስጥ አንድ መፅሐፍ አናገኝም፤እኔም አላውቅህም ነበር።«ማንበብ እንድታስብ ይገፋፋል» የሚለው አባባልህ አኔም እጋራዋለሁ።ነገር ግን «ብዙ ማሰብ ጭንቀት ያስከትላል፤ጭንቀት ደግሞ ሊያሳብድ ይችላል» ካልከው አባባል ጋር አልስማማም።ማሰብ ለሰው ልጅ መሰረታዊ ነገር ነው።ልክ እንደ መለያው ልትቆጥረው ትችላለህ፤የማሰብ ችሎታ ባይነሮው ንሮ ሰው አይባልም ነበር።ደግሞ ለጭንቀትም ሆነ ለዐብደት የሚያደርስ ክፋት የለውም።ማሰብ የአእምሮ«ጂምናስቲክ» ነው፤ሌላው አካላችን በስፖርት እንደሚዝናናውና እንደሚጠነክረው ሁሉ አእምሯችንም በማሰብ የዝናናል፤የጎለብታልም። በማለት ላሳምነው ሞክሬ ነበር፤ልጁ ግን በቀላሉ እጅ የሚሰጥ አልነበረም።አንድ መጽሐፍ ገዢ ከስተናገደ በኋላ ክርከሩን ቀጠለ።

«ወዳጄ፣ መፅሐፍ የሚያነቡም ሆነ ብሎም የሚፅፉ ሰዎች ለኛ ለሻጮች፣ለአሳታሚዎችና ሌሎች አንባቢዎች አስበው እንደይመስለህ።እንሱም ልክ እንደኔ በሱስ ስለተለከፉ ነው።አንዴ አዲስ ነገር ለመሞከር ሲሉ ማንበብ ጀመሩ፤ከዛም በዛው ገፉበትና ሱስ ሆነባቸው።እናም ሱሳቸውን ለማስታገስ ሲሉ ያነባሉ፤ምርቃናውን እንዲሽርላቸውም ባገኙት ወረቀት ላይ መሞነጫጨር ይጀምራሉ።ከዛም ሳያስቡት ወደ ደራሲነት ዓለም ይገባሉ ማለት ነው።ልክ የሽጋራ ሱሰኛ አጭሶ መርካት ሲያቅተው ሐሽሽ ማጨስ እንደሚጀምረው ሁሉ።»

በሾርኔ ሱሰኛ ነህ እያለኝ መሆኑን ገብቶኛል፤ሆኖም ግን እንዲነቃብኝ እድል አልሰጠሁትም።ግን እኮ ማሕበረሰባችን በጣም ያደንቃቸዋል፤ያከብራቸዋልም።እንደሱሶኞች ተቆጥረው አያውቁም፤እንደ አዋቂዎች እንጂ።የማሐበረሰባችን ምስጢሮች ሳይቀር አፍረጥርጠው ስለሚፅፉ ለእውነት፣ለእኩልነትና ለፍት በብዕራቸው የሚዋጉ አርበኞች እንደሆኑ ነው የሚታወቀው።አይደለም እንዴ?

«ትክክል ነህ።ነገር ግን አብዛኛው ጊዜ ተዋቂነትም ሆነ ክብር የሚያገኙት በህይወት እያሉ ሳይሆን ከሞቱ በኋላ ነው።እንደውም ብዙዎቹ ለሰላማዊ ንሮ አልታደሉም።እነሱ በብዕሮቻቸው ይሞግታሉ ባለንጦቻቸው ደግሞ ከተቻለ ዝም እንዲሉ ይመክሯቸዋል።በምክር ካልተመለሱ አንድም በማዋከብ አገራቸውን ለቀው እንዲሰደዱ የገፋፏቸዋልቸ፣አልያም ያለፍርድ እስር ቤት ውስጥ ተቸንክረው እንዲማቅቁ ያደርጋሉ።እንዚህ ሁሉ አማራጮች ሞክረው ካልሆነም አንገታቸውን በመጠምዘዝ እስከወድያኛው እንዲያሸልቡ ያደርጋሉ።መቸስ የአቤ ጉበኛና የበዓሉ ግርማ ታሪክ አታውቅም የሚል እምነት የለኝም።ይህን ስልህ ግን የደራስያን አድናቂ አይደለሁም እያልኩህ አይደለም።በአጠቃላይ እውነተኛ የጥበብ ሰዎችን ከምንም በላይ አድንቃለሁ፤አከብራለሁ።በተለይም ትእግስታቸውና ስስት አልባ ህይወታቸው።አየህ እነሱ በህይወት እያሉ በአስርና አስራምስት ብር ታትሞ ለገበያ የወጣው ምርጥ መፅሐፍ ሁን በመቶዎች እየተቸበቸበ ይገኛል።»

የበዓሉ ግርማና የአቤ ጉበኛ ስም ሲያነሳ አንጀቴ በሐዘን ተላወሰ።ሃገር በጅቦች ጭቆና በነበረችበት ዘመን ሁለቱም ለእውነት የቆሙ ምርጥ የኢትዮጵያ አርበኞች ነበሩ።ታድያ አርበኝነታቸው መሳርያ ብእር ወረቀት ብቻ ነበር፤ማንንም አላቆሰሉም፣አልገደሉምም።ቢሆንም ግን ሁለቱም ገዳያቸው ሳይታወቅ በወጡበት ቀሩ።
አዎ፣ ገዢዎች አሰራራቸው የፈለገው ያህል ቢረቀም ምንጊዜ ከህዝብ እይታ የተሰወረ አይደለም።ወንጀለኞቹ የተቀበረ ሚስጥር ነው ብለው የሚያስቡት ሁል ለህዝቡ ንፋስ ያብጠለጠለው የመንደር ወሬ ነው።የስንቶቹን ዓይኖች አጥፍተውና የስንቶቹን ጀሮ ዘግተው ይዘልቁት ይሆን?

ከልጁ ጋር መከራከሩን ትቼ ወደ ቤቴ ጉዞ ጀመርኩ።በፖለቲከኞችና በጥበብ ሰዎች መካከል ያለው የሰማይና የመድር ልዩነት እያሰላሰልኩ።የጥበብ ሰዎች ብርሃን ናቸው፤ፖለቲከኞች ግን(ሁሉም ለማለት ባልደፍርም) በአብዛኛው ጨለማ ናቸው።ብርቱ ጥበበኛ በለበት ሁሉ ብርሃን አለ።ብርሃን ካለም ጨለማ አይኖርም።ህይወት እንደ ወተት ነጭ ነች፤ፖለቲከኞች ቡና በመጨመር ያጠቁሯታል።

  

                         እለተ እሁድ መጋቢት 22፣2005 ዓ.ም







No comments:

Post a Comment