Tuesday, February 4, 2014

ሰላም ባስ የህዝብ መመላለሻ አክስዮን ማሕበር የተጓዦች ሰላም እያሳጣ ነው




የትግራይ ልማት ማሕበር(ማ.ል.ት) ስያሜው እንደሚያመለክተው ትግራይን ለማልማት ታልሞ በትግራይ ተወላጆች መልካም ፍቀድ የተቋቋመ ማሕበር ነው፤ በእያንዳንዳቸው የትግራይ ተወላጆች በፈቃደኝነት የተመሰረተ ወርሃዊ መዋጮ፡፡ድሮም ዘንድሮም ማ.ል.ትን በገንዘቡ ወይም በእውቀቱ የማይረዳ ጤነኛ የሆነ የትግራይ ተወላጅ የለም ማለት ይቻላል፤በሃገር ውስጥም ከሃገር ውጭም፡፡

ሰላም ባስ የህዝብ መመላለሻ አክስዮን ማሕበር(ያኔ አክስዮን ማሕበር ሳይሆን ‹‹ሰላም ባስ›› ነበር የሚባለው) ታድያ በ1987 ዓ.ም ነበር በወቅቱ የነበረው የመጓጓዣ እጥረት ለመቅረፍ ታስቦ በማ.ል.ት አማካኝነት የተቋቋመው፡፡አክስዮን ማሕበሩ በ13.7 ሚልዮን ብር መነሻ ካፒታልና 25 አይቬኮ አውቶብሶችን ይዞ ነበር ስራውን በይፋ የጀመረው፡፡አውቶብሶቹ እያንዳንዳቸው 51 የመቀመጫ ወንበር ያላቸው ናቸው፤አሁንም ያኔም፡፡

እርግጥ ማሕበሩ እንደሌሎቹ በማ.ል.ት የተቋቋሙ ህዝባዊ ድርጅቶች ሁሉ የመጓጓዣ እጥረቱን ከመቀነሱ ባሻገር ህዝብን በትጋትና በጥራት በማገልገሉ ረገድ ትልቅ ድርሻ ተጫውተዋል፡፡በሙቸቱንና የተጓዦች ድህንነት በመጠበቅም ቢሆን ከዛሬዎቹ መንግስታዊ የህዝብ መመላለሻ አውቶብሶች ጋር ሲነፃፀር ተመራጭ ነው፡፡በፍጥነትም የሰላም ባስ አውቶብሶችን የሚፎካከር ያለ አይመስለኝም፤ ሰላም ባሶች ጥዋት ከአዲስ አበባ ተነስተው በአንድ ቀን መቐለ ገብተው ያድራሉ፡፡



ይሁን እንጂ ዛሬ ያ አክስዮን ማሕበር የማ.ል.ት አይደለም፤የአክስዮኑን ባለድርሻ አካላትም በግልፅ አይታወቁም፡፡ምስጢር ነው፡፡ምናልባትም የህ.ወ.ሓ.ት ከፍተኛ ባለስልጣናት የግል ንብረታቸው አድርገውት ሊሆን ይችላል፡፡ልክ እንደ ት.እ.ም.ት ማለት ነው፤ ት.እ.ም.ት ንብረትነቱ የትግራይ ህዝብ ነው ሲባል ነበረ፡፡አሁን ነገርየው ታሪክ ከሆነ ብዙ ቆይቷል፡፡የሰላም ባስ የህዝብ ንብረትነትም እንደዛው ታሪክ ሆኗል፡፡ለዛም ይመስላል የትግራይ ህዝብን እንደ ክቡር ደምበኛ ሳይሆን እንደ አሮጌ የግሉ እቃ እያንገላታው የሚገኘው፡፡ልክ ህ.ወ.ሓ.ት የትግራይ ህዝብን እንደ የግል ንብረቱን ቆጥሮ እንደፈለገው እንደሚያደርገው ማለት ነው፡፡

ሰላም ባስ የህዝብ መመላለሻ አክስዮን ማሕበር የትግራይ ህዝብን እየበደለ ያለው በአገልግሎት አሰጣጡ መበላሸትና ከሌሎች የህዝብ መመላለሻ አውቶብሶች ጋር ሲነፃፀር ክፍያውን በእጥፍ በመጨመር ነው፡፡ለምሳሌ፡ የአውቶብስ ተራ አንደኛ ደረጃ አውቶብሶች 250 ብር የሚያስከፍሉ ሲሆን ሰላም ባስ ግን 460 ብር ያስከፍላሉ፡፡በተጨማሪም በሰላም ባስ ለመጓዝ ከአንድ ሳምንት ቀድሞ መክፈል የግድ ይላል፡፡ዛሬ ወደ ትግራይ ለመጓዝ የሚፈልግ ተጓዥ የሰላም ባስ ትኬት ለማግኘት የዛሬ ሳምንት መቁረጥ ይኖርበታል፡፡አውቶብስ ተራ ግን ዛሬ ትኬት ቆርጦ ነገ ጥዋት መሄድ ይቻላል፡፡

በጣም የሚያሳዝነውና የድርጅቱ አፓርታይዳዊ አሰራር ቅልብጭ አድርጎ የሚያሳየው ጉዳይ ደሞ ወደ ሃዋሳ፣ሃረር፣ድሬዳዋ ወዘተ ለመጓዝ ፈልጎ ሰላም ባስን የሚጠይቅ ሁሉ ‹‹የለም›› የማይባል መሆኑን ነው፤ደዛ እማ እንደውም ተለምነህ ነው፡፡የህ ነገር አፅንኦት ሰጥቼ ነበር በደንብ ያጣራሁት፡፡ከትግራይ ውጪ ወደ ሌሎች መደራሻዎች የሰላም ባስ አገልግሎት በየቀኑ ማግኘት ይቻላል፡፡የትግራይ ህዝብን ይህ ያህል የሚጨክኑበት ለም ይሆን?ምን አጠፋ?ሰላም ባስ ወደ ትግራይ ላለመሄድ የሚያንገራግሩት ለምን ድን ነው?በእጥፍ ከፍለህም በስንት ደጅ ጥናት(ሳምንት ጠብቀህ)፣በስንት ልምናና ልምምጥ እኮነው አገልግሎት የምታገኘው፡፡አዘንኩ፣ በጣም አዘንኩ፡፡
 
የህን የሚያደርገው ደግሞ ሆን ብሎ የሌለና አላስፈላጊ እጥረት በመፍጠር ክፍያው በእጥፍ ለመጨመርና ተጓዦችን ለማዳለት ነው፡፡አንዱ ዛሬ ቆርጦ ነገ ወደ መቐለ ሊጓዝ ይችላል፤ሌላው ግን የግድ ሳምንት መጠበቅ ይኖርበታል፡፡በአንድ ዓይነት ክፍያ ወይም ለትኬት ቆራጮች ጉቦ በመክፈል አገልግሎቱ በፈለግከው ጊዜ ማግኘት ይቻላል፡፡ለዚሁ እማኝ የሚሆነን ደግሞ ልክ እንደ አውቶብስ ተራ ሁሉ ቀደም ብሎ ትኬት ቆርጦም ቢሆን የመጀመርያ ወንበሮች ማግኘት ዘበት መሆኑን ነው፡፡

ከዚህ የባሰም አለ፡፡የባለፈው ሳምንት፣ ሳምንት አንድ ቤተሰብ ወደ ትግራይ ለመሸኘት መስቀል አደባባይ ወደ ሚገኘው የሰላም ባስ ቢሮ ህጄ ነበር፡፡እናም በሳምንቱ ጥዋት 10፡30 ላይ መስቀል አደባባይ ተገኘሁ፡፡ተጓዦች እቃዎቻቸውን እያስመዘኑ ማስጫን ጀመሩ፡፡ትንሽ ቆይቶ ግን የአውቶብሱ የእቃ ማስቀመጫ ኪስ ሞላ ተባለ፡፡ከኋላ የተሰለፈው የነበሩ ሶስት ተጓዦች እቃችሁም የምንጭንበት ቦታ የለም ተባሉ፡፡

‹‹ታድያ እኛ እንዴት እንሁን?›› ተጓዦቹ ተጨናንቀው ይጠይቃሉ፡፡
የአስተባባሪዎቹ መልስ‹‹አናውቅም!›› የሚል ሆነ፡፡
‹‹እንዴት አታውቁም? 460 ብር አስከፍሎ አናውቅም ማለት ምን ማለት ነው?›› ክርክሩ ጦፈ፡፡

ታድያላችሁ፣ ሶስቱ ተጓዦች ከአስተባባሪዎቹ ጋር በመጨቃጨቅ ላይ እያሉ የአውቶብሱ ሹፌር ካልነዳሁት ብሎ እሪ ማለት ጀመረ፡፡ተሳፋሪው እንዳለ ልያረጋጋው ቢሞክርም አሻፈረኝ ብሎ ጥሏቸው እብስ!ከሶስቱ ተጓዦች መሃል ሴትዋ በምሬት አለቀሰች፤ተደናፈቀች፡፡ወንዶቹ ከአስተባባሪዎቹ ጋር ለመደባደብ አንገት ለአንገት መተናነቅ ጀመሩ፡፡ተጓዦቹን ለመሸኘት የመጡ ቤተሰቦች ‹‹ተው ጋላ!›› ብለው ገላገሉዋቸው፡፡

በማሃል አንድ ሸምገል ያሉ ሰውየ ወደ አስተባባሪዎቹ ጠጋ ብለው ‹‹የሰራችሁት ስራ ተገቢ አይደለም፡፡ሆኖም ግን አሁን የሚያስፈልገው መደባደብ ሳይሆን መፍትሔ ማፈላለግ ነው፡፡በመሆኑም ተጓዦቹን ከስራቸው እንዳይስተጓጎሉ በሌላ አውቶብስ አሳፍራችሁ ላኩዋቸው፡፡እቃቸው ግን እዚሁ ይቆይ፤ኋላ ላኩላቸው፡፡›› በማለት አስታረቁዋቸው እላችኋለሁ፡፡
 
እኔ በበኩሌ በሁኔታው በጣም፣እጅግ በጣም ነበር ያዘንኩት፡፡በቀጥታ ቤት እንደገባሁም የሰላም ባስ ድረ ገፅ ከፍቼ የድርጅቱ እሴቶችን(VALUES) ወደ ማንበብ ነበር ያመራሁት፡፡የድርጅቱ እሴቶች እንደሚከተለው ተከሸነው ተፅፈዋል፡
  • የደንበኞችን ፍላጎት ለሟሟላት ቁርጠኛ አቋም እንዳላቸው(Dedication to Customer Satisfaction)
  • በጣም የላቀ ጥራት ያለው አገልግሎት ለማቅረብ መሰጠት( Commitment to Service Excellence)
  • መልካም አስተዳደር(Good Governance)
እንግዲህ ይታያችሁ፤ የተፃፈው እሴትና በተግባር የሚታው እንግልት የሰማይና የምድር ያህል ሲራራቁ፡፡‹‹አራምባና ቆቦ››ይላል ያሃገሬ ሰው፡፡ደምበኞች የሚፈልጉት አገልግሎት በፈለጉት ጊዜ፣በተመጣጣኝ ዋጋ ካለ ምንም ደጅ መጥናትና እንግልት ካላገኙ የድርጅቱ ቁርጠኝነት ምኑ ላይ ነው?እጅግ የላቀ ጥራት ያለው አገልግሎት ለማቅረብ መሰጠቱስ የትኛው ነው?መልካም አስተዳደር ማለትስ እጥፍ የከፈሉ ደምበኞችን ሜዳ ላይ ጥሎ መጥፋት ነው እንዴ?

ልብ በሉልኝ፣ የሽፈሩን ሹፌሩን አምባገነንነት ያስደመመኝ መስቀል አደባባይ ላይ ሶስት ተጓዦችን ትቶ በመሄዱ ብቻ አይደለም፡፡ደሴ ደርሰው ለምሳ እንዳረፉም ሌላ አንዲት ተሳፋሪ እዛው ትቶዋት የሄደዋል፡፡እንደሰማሁት ከሆነ ተሳፋሪዎች ‹‹ተው እንጠብቃት ብለው ቢለምኑትም›› ፍቃደኛ አልሆነም፡፡እናም ያ ያኔ የሸኘሁት ቤተሰብ ጥሎብኝ እንደይ ሄድ ስለሰጋሁ አሁንም አሁንም ስደውል ነበር የዋልኩት፡፡

ሰላም ባሶች ይህን ያህል አምባገነን እንዲሆኑና በህዝቡ ላይ እንዳሻቸው እንዲፈኝጩ ያደረጋቸው ሌላው ምክንያት ደግሞ እንደ እስካይ ባስ የመሳሰሉ ሌሎች አማራጭ አውቶብሶች ወደ ትግራይ እንዳይ ሄዱ በመከልከላቸው ነው፡፡ስካይ ባሶች ወደ ጎንደር፣በሃር ዳር፣ጅማ፣ሃወሳ፣ሃረር፣ ድሬዳዋ ወዘተ ተጓዦችን ያመላልሳሉ፡፡ወደ ትግራይ ግን ድርሽ እንዳይሉ መተዘዛቸውን ነው የነገሩኝ፡፡የትግራይ ህዝብ ያ ሁሉ መስዋእት የከፈለው በሃገሩ እንደ ሁለተኛ ዜጋ ተቆጥሮ ከመጠን በላይ ስለተጨቆነ፣ታግሎ ነፃነቱን ከመቀዳጀት ውጪ ሌላ አማራጭ ስላጣ ነበር፡፡ሆኖም ግን ዛሬም የታገለለትን ያህል አማራጮች ማግኘት አልቻለም፡፡

ይህ ደግሞ ‹‹በት.እ.ም.ት ምክንያት ሌሎች ባለሃብቶች በትግራይ ውስጥ የመዋእለ ንዋይ አፍስሰው እንዳይሰሩና ፈቃድ ማጣታቸውንና እዛው የነበሩም ክልሉን ጥለው ወደ መሃል አገር እንዲመጡ እየተገደዱ ነው›› እንደሚባለው ሁሉ የትግራይ ህዝብ ከህ.ወ.ሓ.ት በስተቀር ሌላ አማራጭ ድርጅቶች እንዳያማትር መነፈጉን፣ የህ.ወ.ሓ.ት ድርጅቶች እንዳሻቸው እንዲነግዱበትና እንዲያንገላቱት መደረጉን የሚያሳይ ነው፡፡በመሆኑም የህ.ወ.ሓ.ት መሪዎች የትግራይ ህዝብ በእነርሱ ተስፋ ቆርጦ ወደ ተቃውሞ እንዲያመራ እየገፋፉት መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡










No comments:

Post a Comment