Thursday, February 13, 2014

‹‹ግማሽ አካሌን ከከፈልኩባት ድርጅት ከሞት በስተቀር የሚለየኝ የለም!››



…የትግል ስሙ አርዐዶም ይባላል፡፡የምንጊዜም ምኞቱ ተምሮ አስተማሪ መሆን ነበር፤አልሆነለትም፡፡በ1972 ዓ.ም 11ኛ ክፍል እንደደረሰ ትምህርቱን አቋርጦ ከህወሓት ጋር ለመቀላቀል ወቅቱ እንዳስገደደው ነው የሚናገረው፡፡ታጋይ የመሆን ፍላጎት ኖሮት ባያውቅም ዕጣ ፈንታው ግን ከዛው እንዲያመልጥ አልፈቀደችለትም፡፡የትናንቱ ታጋይ፣የዛሬው የ60 ዓመት አዛውንቱ አርዓዶም እንደሚከተለው ነበር ከታሪኩ ቀንጭቦ ያጫወተኝ፡፡

‹‹…አብሮ አደጎቼ በአብዛኛው በደርግ ወታደሮች ተገፈው ተወሰዱ፤ለውትድርና፡፡የተቀሩት ኢህአፓ ናችሁ፣ምንትስ ናችሁ ተብለው ታሰሩ፤ተገድለው በየመንገዱ ተጣሉ፡፡የእኔ ዕድልም ከዝያ አያመልጥም ነበር፡፡ጓደኞቼ ኢህአፓ እንደሆን ብዙ ጊዜ ሊያሳምኑኝ መኩሮው አልተሳካላቸውም፡፡ደርግ በግዴታ ማስታጠቅ ሲጀምር ግን ተምሮ አስተማሪ የመሆን ህልሜ እንደ ጉም በኖ ሲጠፋ ታየኝ›› አለኝ፤ወደ ሩቅ አሻግሮ እያየ፡፡እርሱ ወደ ሚያየው አቅጣጫ ተመለከትኩ፤ ብዙ ነገሮች ስለተደረደሩ ዓይኖቹ ምኑ ላይ እንዳነጣጠሩ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ነጭ ፀጉር የተቀላቀለበት ሪዙን በግራ እጁ ወደ ታች ሳብ ሳብ እያደረገ ትንሽ አሰበና በረዥሙ ተንፍሶ ቀጠለ…


‹‹…አየህ፣ አማራጭ ስታጣ፣ ወደድክም ጠላህም እፊትህ ካሉት ኢ-አማራጮች አንዱን መምረጥ አለብህ፡፡እኔ ከትምክህተኞቹ ኢህአፓዎችና ከነብሰ በላው ደርግ ጋር ሆኜ መታገል አልፈለግኩም፡፡በመሆኑም ከህወሓት ጋር ለመታገል ወስኜ ወደ በረሃ ወጣሁ››
ብዙ ወጣቶች የኢህአፓ አድናቂዎች ብቻ ሳይሆን ተከታዮችም ጭምር ነበሩ፡፡ብዙዎች ደግሞ ‹‹አብዮት ጠባቂዎች›› የሚባሉ የደርግ ወታደሮች ነበሩ፤የቅርብ ቤተሰቦቻችን ጭምር፡፡አንተ ግን ህወሓት ለመሆን መረጥክ፤ ለምን? ብየ ጠየቅኩት፡፡

‹‹…የኢህአፓዎች አካሄድ በጀብድ የተሞላ እና የትም የማያደርስ ነበር፡፡በሽዎች የሚቆጠሩ ጓዶቻቸው በገፍ ተገድለው ሜዳ ላይ ተጥለው እያለ ‹‹ኢህአፓ ያቸንፋል!›› የሚሉ ፅሑፎች ይበትኑ ነበር፡፡ሳስበው በማቸነፍና በመቸነፍ ያለው ልዩነት የገባቸው አልመስልህ አሉኝ፡፡እንዴ! ጓዶቻቸው በየቀኑ እንደ ቅጠል እየረገፉ በምን ተአምር ነው ማቸነፍ የሚችሉት? አካሄዳቸው ግልፅ ነበር፤ወደ ውድቀት የሚወስድ ግልፅና ቀጥተኛ መንገድ ነበር የሚከተሉት፡፡››

‹‹…ደርግ ያኔ ማንም ሊገፋው የማይችል ተራራ ነበር፡፡ይሁን እንጂ ደርግ ከመሆን ይልቅ ሞት ነበር እምመርጠው፡፡ምክንያቱም ደርግ ብሆን ንሮ የአጎቴ ቤት ማቃጠል ነበረብኝ፤ያኔ የህወሓት ምልሻ ነበረና፡፡እርሱን መግደል ቀላለ ሊሆን ይችላል፤እርሱን ገድሎ፣ከብቶችና ፍየሎቹን ወስዶ ቤቱን ማቃጠል ግን የማይታሰብ ነበር፡፡የእርሱን ባላደርግም የሌሎች ወገኖቼ እንደዝያ ማድረግ ይኖርብኝ ነበር፡፡በሃይል ተገፈው የተወሰዱት ጓደኞቼ እንደዛው አድርገዋልና፡፡››

‹‹…ደርግ አብዮት ጠባቂ ብሎ ባስታጠቃቸው ወገኖቻችን እየተመራ የገበሬውን ሃብትና ንብረት መዝረፍ፣የተቀረውም በእሳት ማጋየት ሲጀመር ደሜ መፍላት ጀመረ፡፡በመሰረቱ ሰው መግደል መጥፎ ነው፤ በአንድ ሰው አማካኝነት ቤትና ንብረት አውድሞ ቤተሰብ ሙሉ ለሞትና ለስደት መዳረግ ግን ምን ሊባል እንደሚችል አላውቅም፡፡አብዛኞቹ የኋላ ኋላ ፀፀቱ ሰላም ስላሳጣቸው ከነመሳርያቸው ከህወሓት ጋር ተቀላቅሏል፡፡በደርግ ተገድደው የወገኖቻቸው ስቃይ ማብዛታቸው፣ለስደትና ለሞት መዳረጋቸው ግን በቀላሉ የሚረሱት አልነበረም፡፡በአጭሩ እነርሱ የደረጉትን ማድረግ አልፈለግኩም፡፡››

‹‹…በመሆኑም ከህወሓት ጋር በመሆን ደርግን ለመፋለም ወደ ትግራይ በረሃዎች ወጣሁ፡፡አየህ፣ ደርግ ከመጠን በላይ ቆሻሻ ስለነበር ለወታደሮቹ ለሶፍት ከሚገባው ክብር በላይ አያከብራቸውም ነበር፡፡ሶፍት የቆሸሸ አፍህንና ቂጥህን ለመጥረግ ብቻ ነው አይደለም የምትጠቀምበት?ደርግም ከተፅዳዳ በኋላ ቂጡን የሚጠርገው በወታደሮቹን ነበር፤ቅዘኑን አፅድቶባቸው ወደ ቆሻሻ መጠራቀምያ ይወረውራቸው ነበር፡፡እዚ ጋ ተራ ወታደሮቹን ትተን ጀነራል ሚካኤል ዓንዶምን ለምሳሌ ማንሳት እንችላለን፡፡የራሱ ቆሻሻ እርሳቸው ላይ አብሶ ነበር የወረወራቸው፡፡››

ከህወሓት ጋር ተሰልፈህ ለስንት ዓመታት ነበር የተታገልከው?ያኔ የነበረው ድርጅታዊ ስነስርዓት ከዛሬዋ ህወሓት ጋር ስታነፃፅረው ምን ይመስላል? አከታትየ ጠየቅኩት፡፡

‹‹…ህዳር 16 ቀን 1972 ዓ.ም ነበር ለመታገል ቆርጬ ወደ በረሃ የወጣሁት፡፡ያ ያደረኩበት ምክንያትም ቅድም እንዳልኩህ ደርግ እንደለመደው ብዙ ገበሬዎችና የገበሬ ልጆችን በጅምላ ጨፈጨፈ፤ቤቶችን አቃጠለ፣ የተለያዩ የሰብል ክምሮችን አቃጥሎ አመድ አደረጋቸው፡፡ያተግባሩ እብድ አደረገኝ፡፡ለማንም ሳልናገር እንደ እብድ እመር ብየ ጠፋሁ፡፡ለግማሽ ቀን በእግሬ ከተጓዝኩ በኋላ ከህወሓት ጋር ለመቀላቀል የሚጓዙ ወጣቶችን በማስተባበር ወደ ማሰልጠኛ ከሚያደርሱ ብፆት(ጓዶች) ጋር ተገናኘሁ፡፡ከዛ እማ ምን ልበልህ፣ በቃ ታጋይ ሆንኩ፡፡አካሌ ብጎድልም ደርግ ተደምስሶ በክብር እስከሸኝ ድረስ ታጋይ ነበርኩ፡፡››

‹‹…ያኔ የኔ የነበረው የእርሰ ብርስ መተሳሰብ፣አንተ ቆይ እኔ ቀድሜ ልሰዋ፣ ያኔ የነበረን ድርጅታዊ ስነስርዓትና ወታደራዊ ‹ድስፕሊን› ከዛሬው ጋር በማንኛውም መልኩ ሊወዳደር አይእልም፡፡የያኔው ብፃይነት(ጓደኝነት) እኮ በልበ ወለድ ተፅፎ የሚታነበውና በፊልም ቀርቦልህ የምትመለከተው እንጂ በግሃዱ ዓለም የከሰታል ብለህ ምትገምተው አልነበረም፡፡ለብፆትህ(ጓዶችህ) ህይወትህ ለማስቀደም ወደ ኋላ ካላልክ ምንህን ትሳሳባቸዋለህ? ከጎንህ ተሰልፎ የሚዋጋው ጓደኛህ በመስዋእት ከምታጣ ይልቅ እራስህ ብትሞት ነበር የምትመርጠው፡፡››

‹‹…ብፆት በጅግንነት አልፏል፤ እኛ አካላችን ቢጎድልም ዛሬም በህይወት አለን፡፡ሌሎች ጓደኞቻችን ደግሞ ትላልቅ ባለስጣናት ሆኗል፡፡ጥቂቶቹ የታገሉለት ዓላማ ግቡን እንዲመታ ሌት ተቀን በመሰራት ላይ ናቸው፡፡ብዙዎች ግን የትናንቱን ዓላማ እርግፍ አድርገው ረስተውታል፤ይልቅ የዛኛው ተቃራኒ ሆኖው ህዝቡን መጨቆን ጀምሯል፡፡እነዚህ ራስወዳድ ግብዞች መስዋእት የተፀየፈቻቸው ጥንብ አንሳዎች ናቸው፡፡ዝሮ ዝሮ ግን የውሻ አሟሟት ነው የሚሞቱት፡፡ህዝብ ማዕበል ነው፤ማዕበሉ ሲነሳ ጠራርጎ ድራሻቸውን ያጠፋቸዋል፡፡››

ከዚህ አባባልህ የምረዳው ከተወሰኑ የህወሓት ባለስልጣናት ጋር ቅሬታ እንዳለህ ነው፡፡በጣም የተጎሳቆለ ንሮ በመምራት ላይ እንዳለህና ህወሓት ግን እንዳንተ አካላቸውን ላጡ የድሮ ታጋዮች ምንም ዓይነት እርዳ እንደማታደርግላችሁ ነው የማውቀው፤እናንተም አትጠይቁም፡፡በህወሓት ተስፋ ቆርጣችኋል ልበል?

‹‹…መቸም ቢሆን በህወሓት ተስፋ አልቆርጥም፡፡ብዙ፣ እጅግ በጣም ብዙ ተስፋ አስቆራጭ ችግራችን በእልህ አልፈን አሁን እንዴት ተስፋ እንቆርጣለን? ምን ተስፋ የሚያስቆርጥ ፈተና ቢገጥመን ነው ዛሬ ተስፋ የምንቆርጠው?የሌሎቹ ጓደኞቼ በእርግጠኝነት ለመናገር ይከብደኛል፡፡ለእኔ ግን፣ ህወሓት ከልቤ የምትወጣው ስሞት ብቻ ነው፡፡እስኪ ትኩር ብለህ ተመልከተኝ፤አንድ ዓይኔን፣አንድ እጄንና አንድ እግሬን ያት አሉ?ለትግራይ ህዝብ ነፃነትና እኩልነት መስዋእት ሆኗል፡፡ህወሓት ግማሽ አካሌን ከፍየባታለሁ፤ግማሽ አካሌ ደግሞ ህይወቴን ለማቆየት ከእኔ ጋር ነች፡፡ታድያ የትኛዋን ግማሽ ተስፋ ልቁረጥባት?የትኛው አካሌ ከየትኛው ላስቀድም? አልችልም፤ ብፍፁም አልችልም!››

‹‹…አሁን እንደምታየኝ አንድ ዓይና አልነበርኩም፤አን እንደምትመለከትን አንድ እግርና እንድ እጅ ብቻ የዤ አልነበረም የተወለድኩት፤አሁን እንደምትመለከተኝ መራራ ንሮ ተረማምዳበት የኮሰመነ ጎስቋላ ሽማግሌ አልነበረኩም፡፡ባንተ እድሜ እያለሁ ቀኝ ዓይኔ የዒላማ ማነጣጠርያ ተመለክቸባት ስንት ጠላት ጥየባታለሁ፡፡ባንተ ዕድሚ ብዙ ዳገት ወጥቻለሁ፣ወርጃለሁ፣ወንዝ ተሻግሬለሁ፡፡በንተ ዕድሚ ቀኝ አጄን ብሬን አንጠልጥየባታለሁ፡፡አሁን እርጅና ቢጫጫንብኝም ዳሩ ወኔዬ ዛሬም እንዳተው ወጣት ነው፤እምቢ በል ይለኛል!››

‹‹…ገማሽ አካሌን ከከፈልኩባት ድርጅት ለአፍታም ቢሆን መለየት አልችልም፡፡ህወሓት እኮ ግማሽ አካሌ ነች፡፡የእኔ ግማሽ አካል ብቻ ግን አይደለም የከፈልንባት፤መላው የትግራይ ህዝብ ግማሽ አካሉን ከፍሎባታል፡፡ስለዚህ፣ ያለን አማራጭ የታመመው፣የቆሰለው፣ የበሰበሰው ግማሽ አካላችንን ከተቻለ ታክሞ እንዲድን አለ በተባለው ህክምና ወስደን ማሳከም፣ ካልተቻለም በቀዶ ጥገና ቆርጠን ማስወገድ ብቻ ነው፡፡ከዚህ ውጪ ያለው አማራጭ ግን የቆሰለው አካላችን ወደ ጋንግሪንነት ይቀየርና በቁማችን በስብሰን እንሞታልን!››

አርዐዶምን ከዚህ በላይ መጠየቅ ሊሆንልኝ አልቻለም፤እርሱ ጥያቄዎቼን ለመመለስ ዝግጁ ነበር፡፡እኔ ግን አልቻልኩም፤መጠን የለሽ    ፅናቱ የመጠየቅ ፍላጎቴን ውሃ ቸልሶበታል፡፡ለመልካም ትብብሩና ቀናነቱን አምስግኜው ተለያየን፡፡

እንድ እግሩንና አንድ እጁን ሰው ሰራሽ ተገጥሞለታል፡፡እንድያም ሆኖ ግን፣ ከኣንዲት የድሮ ብፂቱ ጋር ትዳር መስርቶ አንዲት ሴትና ሁለት ወንድ ልጆችን ወልዶ ለማሳደግ ችሏል፡፡ ንሯቸው ከእጅ ወደ አፍ ነው፡፡ይሁን እንጂ አንድ ነገር ደስተኛ እንዲሆን አድርጎታል፤የመጀመርያዋ ልጁን ህልም መምህርት መሆን ነበር፤ያ እርሱ በልጅነቱ ተመኝቶት ሳይሳካለት የቀረው፡፡አሁን፣የመጀመርያ ልጁ የዩኒቨርሲቲ መምህርት ስትሆን ሁለቱም ግን ገና በመማር ላይ ይገኛሉ፡፡


የታጋይ ፅናቱ እስከ ህልፈተ ሞቱ!!!

No comments:

Post a Comment